Search Results for 'ብርሃኑ ፀጋዬ'

Home Forums Search Search Results for 'ብርሃኑ ፀጋዬ'

Viewing 1 results (of 1 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴዎች ዙሪያና በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠረጥረዉ በቁጥጥር ስር እየዋሉ የሚገኙ አካላትን በተመለከተ ሚያዚያ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኃላ በጽሕፈት ቤታቸው ለመገናኛ ብዙኀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

    በመንግስት ተቋማት እና ፕሮጀክቶች ላይ የተፈጸመ ከባድ የሙስና ወንጀልን በተመለከተ በተለይም የመንግስት ግዥ ንብረት አስተዳደርና ማስወገድ አገልግሎት፣ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንና በመድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲ በሦስቱም ተቋማት በበርካታ ሚሊየን የሚቆጠር የመንግስትና የሕዝብ ሀብት የመዘበሩ ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተደራጀዉ የምርመራ ቡድን በቂ ማሰረጃና መረጃ በመሰብሰብ 59 በወንጀሉ የተጠረጠሩ የቀድሞ የሥራ ኃላፊዎችና ግብረ-አበሮች በቁጥጥር ሥር በማዋል ዐቃቤ ሕግ ክስ ለመመሥረት ተጨማሪ የምርመራ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

    በተደራጀ መልኩ በሙስና ወንጀል እጃቸው አለበት ተብሎ ከተጠረጠሩት መካከልም የቀድሞ የመንግስት ግዥ ንብረት አስተዳደርና ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግስቱ ከበደ፣ የመንግስት ግዥ ንብረት አስተዳደርና ማስወገድ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተሮች፣ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ አትክልት ተካ፣ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ፣ የመድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲ (PFSA) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ኃይለስላሴ ቢሆን፣ የመድሃኒት ፈንድ ኤጀንሲ ም/ዋ/ዳይሬክተር እና ሌሎች የነዚህ ተቋማት መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች በተጨማሪም በጥቅም የተሳሰሩ ሌሎች ግበረ-አበሮቻቸው እንደሚገኙ በመግለጫዉ ይፋ ተደርጓል።

    በተያያዘም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሀኑ ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፥ ተቋሙ የሕግና የፍትህ ምህዳሩን ለማስፋትና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የቆመላቸው ዋና ዋና ዓላማዎች ማለትም ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማክበርና ማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የወንጀል ሕግን ማስከበርና የፌዴራል መንግስቱን እና የሕዝብን የፍትሀ ብሄር ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ተቋማዊ ለውጦችን ማከናወኑን ተናግረዋል።

    በመደበኛ ሥራዎች ላይም ሰፋፊ ለዉጦች ማምጣት ጀምረናል ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ፥ በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎችና አተገባበር በማጥናትና የባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ለማሻሻል የሕጎቹን አተገባበር የሚገመግም ጥናትና በጥናቶቹ ግኝት ተከታታይ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኮች በማካሄድ ከተገኘው ግብዓት በመነሳት ረቂቅ ሕግ የማዘጋጀትና በረቂቅ ሕጎችም ላይ ግብዓት የማሰባሰብ ተግባር መከናወኑን አዉስተዉ አጠቃላይ የተሠሩ የሕግ ማሻሻያዎችን አፈፃፀምን በመግለጫቸዉ አንስተዋል።

    በተጨማሪም በልዩ ሁኔታ ምርመራና ክስ እየተደረገባቸው ያሉ ጉዳዩችን በተመለከተ የሰብዓዊ መብት ጥስት ወንጀል ፈጽመዋል በሚል 42 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዉለዉ የወንጀል ምርመራ ሲጣራባቸው የነበረ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ በ10 የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት እንዲሁም በ9 የማረሚያ ቤት አመራሮች ላይ ክስ ተመሥርቶ በክርክር ሂደት ላይ ያለ ሲሆን፣ በ21 የደኅንነት አባላት ምርመራ ተከፍቶ ምስክር እየተሰማ እንደሚገኝ ተገልጿል።

    በተያያዘ መልኩም በተለያዩ ቦታዎች ከተፈጠሩ ሁከትና ብጥብጦች ጋር ተያይዞ በተከናወነ የምርመራ ሥራዎች በወንጀል ተግባራት የተሳተፉ አካላትን ለይቶ ለሕግ በማቅረብ በኩል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ለአብነትም በሐዋሳ ከተማ ከተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ፣ ሱማሌ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈጸመ ወንጀል፣ በኦሮሚያ ክልል ቡራዩና በአዲስ አበባ በተለያዩ በክፍለ ከተሞች ተነሰቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

    በመጨረሻም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ አካባቢዎች ዓለማቀፍ ግንኙነት ያላቸዉና የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በዝግጅት ላይ የነበሩ አካላትን ሊያደርሱት የነበሩትን ጉዳት በመቆጣጠርና ቁጥጥር ስር ለማዋል ከብሔራዊ የመረጃ ደኅንነት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንና የምርመራው ሂደት እንደተጠናቀቀ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ካሉ በኋላ ሰላም የሁላችንም ሀብት በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከመንግስት ጎን በመቆም በጋራ ሊሠራ ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

    ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ


Viewing 1 results (of 1 total)