-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ግዙፉ የመኪና አምራች የሆነው የጀርመኑ ኩባንያ ቮልስዋገን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ፈረመ። ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበባ አበባየሁ እና ከሰሃራ በታች የኩባንያው የአፍሪካ ቀጣና ሥራ አስፈጻሚ ቶማስ ሻፈር ተፈራርመዋል። በስምምነቱ መሠረትም ኩባንያው የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ መክፈት፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎችን ማቅረብ፣ የስልጠና ማዕከል መክፈት እና ተጓዳኝ ሥራዎችን ይሠራል።
በስምምነቱ ላይ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዋልተር ስታይንማየር እና የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ተገኝተዋል።
ቮልስዋገን ኩባንያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያን የማስፋፊያ ማዕከሉ አድርጎ ሲመርጥ፣ ከኩባንያው ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈረም ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ኢትዮጵያ ሦስተኛዋ አገር (ከጋና እና ናይጄሪያ ቀጥሎ) ሆናለች።
◌ VIDEO: የጀርመኑ ግዙፍ የመኪና አምራች ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ ኢንቨስትመንት ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ ነው
ኩባንያው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመሥራት መስማማቱ በቀጥታ የእሴት ሰንሰለት የተቀናጀ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ክላስተር ለመፍጠር ወሳኝ ምዕራፍ ይከፍታል ነው የተባለው።
ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት መንግሥት አገሪቷን ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ነው።
”በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው መስክ ልዩ ክላስተር እንዲመሠረት መንግሥት ያለሰለሰ ጥረት ያደርጋል” ያሉት ኮሚሽነሩ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ቮልስዋገንን ጨምሮ ፍላጎት ካላቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ‘ዝግጁ ነው’ ብለዋል።
◌ VIDEO: German companies including Volkswagen and Siemens embarking to invest in Ethiopia
የኩባንያው የአፍሪካ ቀጣና ሥራ አስፈጻሚ ቶማስ ሻፈር በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ለአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው እድገት ትኩረት መስጠቱ ‘የሚደነቅ ነው’ ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቶማስ ሻፈር ‘ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ላይ ያለች እና በሕዝብ ብዛትም ከ አህሪካ አገራት በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠች በመሆኗ፥ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ለመስፋፋት በምናደርገው ጥረት ኢትዮጵያን ሁነኛ ተመራጭ አገር አድርገናታል፤ በተጨማሪም ቮልስዋገን ኩባንያ ሀገሪቱ ያላትን የስትራቴጂ ጥቅም ከግምት በማስገባት በ አውቶሞቲቭ ዘርፍ ከፍትኛ እድገት እንድታስመዘግብ ይተጋል’ ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የጀርመን የቢዝነስ ልኡካን ቡድን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሥራ ሃላፊዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ በሚሰማሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
ሲመንስ የተሰኘው በግዙግነቱ ከአውሮፓ ኩባንያዎች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የጀርመን የቴክኖሎጂ ኩባንያ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ሲሠራቸው ከነበሩ የቴክሎጂ ዘርፍ ሥራዎች በተጨማሪ በተጠናከረ መልኩ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል።
◌ NEWS: German automaker Volkswagen develops automotive industry in Ethiopia
የጀርመን የቴክኖሎጂ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ማኅበርም ቢሮውን አዲስ አበባ በመክፈት ወደ ሥራ ለመግባት ፍቃደኛ መሆኑን አሳውቋል። ማኅበሩ ጀርመን ውስጥ ያሉ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ማኅበር እንደመሆኑ ድርጅቶቹ በመስኩ ለመሰማራት የሚያስችላቸውን ሁኔታ ለማመቻቸት መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ይታመናል።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በጊዜያዊነት በነፃ ቢሮ በመስጠት ጭምር ማንኛውንም እገዛ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም ተገልጿል።
የልኡካን ቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ድርጅቶች ከምንዛሬ እጥረት፣ በደላላ ምክንንያት ምርቶቻቸው ተጠቃሚው ጋር በተጋነነ ዋጋ መድረስ የመሳሰሉ ችግሮች እንደገጠሟቸው ተናግረዋል።የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ለመጀመር ሥራዎች እየተሰሩ በመሆኑ ወደ ሥራ ሲገባ ችግሩ እንደሚቀረፍ ተናግረዋል።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– አዲስ አበባን ከኤርትራዋ ምጽዋ ጋር ለሚያገናኘው የባቡር መስመር ፕሮጀክት ጥናት ወጪ ለመሸፈን የጣሊያን መንግስት መስማማቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
በጣሊያን ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጣሊያን አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ ጋር ተወያይተዋል። መሪዎቹ ከውይይቱ በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ጣልያን አዲስ አበባን ከምፅዋ ለሚያገናኘው የባቡር መስመር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ጥናት ወጪ ለመሸፈን ተስማምታለች።
ከጥናቱም በኋላ በሚገኘው ውጤት በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት ጁሴፔ ኮንቴ እንደገለጹላቸውና ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ምስጋናውን እንደሚያቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ እንደ ስሟ እንድትሆንና ነዋሪዎች ወጥተው ሲገቡ የሚዝናኑበትን ቦታ ከመፈለግ አንጻር በአዲስ አበባ በሚገኙ ኤምባሲዎች የተወሰነ ቦታቸውን ለህዝብ መዝናኛ ፓርክ እንዲያውሉ ጥያቄ ቀርቧል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የጣልያን መንግስትም ለዚህ ቅን ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።
◌ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከጣሊያን አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ የሰጡት የጋራ መግለጫ
የኢትዮጵያ መንግስት የብሔራዊ ቤተ መንግስቱን ግማሽ የህዝብ መዝናኛ ፓርክ ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጠቅሰዋል። በአዲስ አበባ ለተቸገሩ ወገኖች ምግብ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ጣልያን በመዲናዋ የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ፍላጎት እንዳላትም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣልያን ቆይታቸው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በልማትና በሰላም ውይይቶች እንዳደረጉና ከአቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ ጋር ያደረጉት ሁለገብ ምክክርም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማሳደግ ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ተናግረዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ሰላም፣ ልማትና አንድነት እንዲረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጣሊያን መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ዶ/ር አብይ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያና በጣልያን መካከል የተደረገው ውይይት ፍሬያማ እንዲሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚካሄዱ የሁለትዮሽ ውይይቶች አገራቱ በሰላም፣ በልማትና በቱሪዝም ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል። አገራቱ ለጋራ እድገትና ሰላም በጋራ እንሥራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በአጠቃላይ ከልዑካን ቡድኑ ጋር በጣልያን የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበረ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት። “እንደ ወንድም አገርና እንደ ጠንካራ ወዳጅ ከምናያት ከጣልያን የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
◌ የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ምርቱን ለመጨመር እና የኤክስፖርት መጠኑን ለማሳደግ እየሠራ ነው
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጄሴፔ ኮንቴ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ታሪካዊ የሚባል ግንኙነት እንዳላቸውና በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራና በትብብር ለመሥራት መግባባታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች የጣሊያን መንግስት የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጣልያን ጉብኝት ያደረጉት የጣሊያኑ አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ በ2011 ዓ.ም መጀመሪያ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባረደጉበት ወቅት ባቀረቡላቸው ግብዣ መሠረት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣሊያን ቆይታቸው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ፣ ከዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳሬክተር ዴቪድ ቤዝሊ፣ ከተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆዜ ግራዚያኖ ዳ ሲልቫና ከግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ ፕሬዝዳንት ጊልበርት ሆዉንግቦ ጋር ተወያይተዋል።
በሌላ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተጓዘው የልዑካን ቡድን በሮም ከጣሊያን ባለሃብቶች ጋር ውይይት አካሂዷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ አምባሳደር ፍጹም አረጋ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበበ አበባየሁን ያካተተው የልዑካን ቡድን ለባለሃብቶቹ ሃገሪቱ ስላላት የተለያዩ የኢንቨሰትመንት ዘርፎችና አማራጮች ማብራሪያ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
◌ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ወደውጭ ሀገራት መላክ ጀምረዋል
ካርቪኮ ግሩፕ በአሁኑ ሰዓት በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ23 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታውን እያጠናቀቀ ሲሆን፥ በጣሊያንና በቬትናም በሚገኙ ፋብሪካዎች የሠራተኛ ስልጠና በማድረግ ዝግጅቱን ለመጀመር በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
በውይይቱ የተገኙት ሌሎች ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በመድኃኒት፣ በግንባታ፣ በግብርና ማቀነባበርያ እና አልባሳት ዘርፍ በስፋት ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ተብሏል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው የልዑካን ቡድን ከጣልያን ቆይታው በኋላ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከተማ በሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Search Results for 'አበበ አበባየሁ'
Viewing 2 results - 1 through 2 (of 2 total)
Viewing 2 results - 1 through 2 (of 2 total)