-
Search Results
-
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) ሕጋዊ ሰውነት ማጣትን በተመለከተ ውሳኔ ሰጠ። ይህንንም ተከትሎ አዲሱ ብልጽግና ፓርቲ እና ራሱን ያገለለው ህወሓት ንብረት እንዲከፋፈሉ ቦርዱ ወስኗል።
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ) – የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በሊቀመንበሩ በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ ግንባሩ መፍረሱን ለቦርዱ ያሳወቀ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሊቀመንበሩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ግንባሩ በመፍረሱ የንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ቦርዱ) ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ አቅርበዋል።
የግንባርን (የጥምረት ፓርቲን) መፍረስ የመወሰን ስልጣን የቦርዱ በመሆኑ፥ ግንባሩም ሆነ ህወሓት ግንባሩ መፍረሱን መጥቀሳቸው የማይገባ ቢሆንም ቦርዱ ሁለቱ ሊቃነመናብርት ያቀረቧቸውን የጽሁፍ ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ “ግንባሩ መፍረስ አለበት ወይ? ከፈረሰስ ውጤቱ ምን ይሆናል?” በሚል ቦርዱ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል።
በመሆኑም ቦርዱ የግንባሩ አባል ሦስት ፓርቲዎች ከግንባሩ ወጥተው አዲስ ውህድ ፓርቲ መመሥረታቸውን የብልጽግና ፓርቲን አመሠራረት ከሚያሳየው መዝገብ ተረድቷል። በመሆኑም ግንባሩ በተግባር መፍረሱን ቦርዱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። የግንባሩ መፍረስ ተከትሎ ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ ውሳኔ መስጠት እንደሚያስፈልግም ተረድቷል።
በመሆኑም የኢህአዴግ አባል ድርጅት የነበሩት ሦስቱ ፓርቲዎች (ማለትምየአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/) “ብልጽግና ፓርቲ” የሚባል አዲስ ፓርቲ መመሥረታቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህወሃት ህልውናውን ጠብቆ የቆየ ፓርቲ በመሆኑ በሕጉ መሠረት በብልጽግና እና በህወሃት መካከል የኢህአዴግን ንብረት ክፍፍል ማድረግ እንደሚገባ ቦርዱ ተገንዝቧል። በመሆኑም ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ወስኗል።
- ብልጽግና እና ህወሃት የኢህአዴግ ንብረት እና ሂሳብ የሚያጣራ አጣሪ በጋራ እንዲሰይሙ፣
- በኢህአዴግ ስም (የተመዘገበ) ያለ ማናቸውም እዳ ተጣርቶ እንዲከፈል፣
- ከእዳ ክፍያ ቀሪ የሆነ ሃብት ሦስት ሩብ ያህሉ (¾ ተኛው) ለብልጽግና ፓርቲ (የሦስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት በመሆኑ) ሩብ ያህሉ (¼ተኛ) ደግሞ ለህወሃት ድርሻ መሆኑ ታውቆ በዚያ መሠረት ክፍፍል እንዲያጠናቅቁ፣
- ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በሕጉ መሠረት በ6 ወር ውስጥ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ተወስኗል። (ውሳኔው በጽሁፍ የሚደርሳቸው ይሆናል)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባየአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ በቀጣይ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ሕዝብን ማዕከል ባደረገ እና ባሳተፈ መንገድ አጠናክሮ ለመቀጠል በቁርጠኝነት መወሰኑንም አቶ አብርሀም አለኸኝ ተናግረዋል።
ባህር ዳር (አዴፓ) – የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ለአማራ ሕዝብ ህልውና እና ለሀገር እንድነት አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገለፀ።
ፓርቲው ሲያካሂድ የቆየውን የማዕከላዊ ኮሚቴ ውይይት ማጠናቀቁን አስመልክቶ የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤቱ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሀም አለኸኝ ለሚዲያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠዋል።
አቶ አብርሀም በመግለጫቸው፥ ማዕከላዊ ኮሚቴው የለውጥ ሂደቱ ከተጀመረ እስከ አሁን ምን ጥንካሬዎች ምን ጉድለቶች ነበሩ? የሚለውን በዝርዝር መገምገሙን ገልፀው፤ የለውጥ ሂደቱ ጥንካሬዎችም ፈተናዎችን አንድ በአንድ ለመለየት ጥረት ማድረጉን ገልፀዋል።
እንደ አቶ አብርሀም ገለፃ በተለይም የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በተመለከተ ከሞላ ጎደል በተሻለ ሁኔታ መመራቱን የማዕከላዊ ኮሚቴው በግምገማው ማረጋገጡን ገልፀዋል።
በለውጥ ሂደቱ ውስጥ ደግሞ ትልቁ ፈተና እና መሰረታዊ ችግር ሁኖ የተነሳው የሰላም እጦትና የሕግ የበላይነት መከበር ላይ የነበሩ ጉድለቶች እንደነበሩ ማዕከላዊ ኮሚቴው በስፋት መገምገሙን ገልፀዋል::
አቶ አብርሀም አክለውም የሕግ የበላይነት እየተንገራገጨ ሔዶ ሔዶ በመጨረሻም መሪዎቻችንን መብላቱ በታሪክ የማይረሳ ጠባሳ ሁኖ አልፏል ብለዋል።
◌ ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከእልቂት ለማዳን ቆም ብለን በሰከነ ሁኔታ ማሰብና መራመድ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን
በክልሉ ባጋጠመው የሰላም እጦት ምክንያትም ክልሉን ለማልማት በተሟላ መነሳሳት ወደ ሥራ የገቡ ባለሀብቶችንም ለስጋት መዳረጉን ጨምረው ገልፀዋል።
ከዚህ አኳያ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ በቀጣይ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ሕዝብን ማዕከል ባደረገ እና ባሳተፈ መንገድ አጠናክሮ ለመቀጠል በቁርጠኝነት መወሰኑንም አቶ አብርሀም አውስተዋል።
ሰኔ 15 በአመራሮች ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ እና በጭካኔ የተሞላ ግድያ ለአማራ ሕዝብ ታሪክ የማይመጥን ነው ያሉት አቶ አብርሀም የተፈጠረውን ችግር ለመቀልበስ የፀጥታ ኣካላት መስዋትነትና የህዝባችን ድጋፍ ወሳኝ እንደነበር በመግለፅ ፓርቲው ለፀጥታ አካላት እና ለህዝቡ ያለውን እድናቆትና አክብሮትም ገልፃል ብለዋል።
በዚህ ሳቢያም የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት ለመሙላት ማዕከላዊ ኮሚቴው በአጀንዳነት ይዞ አመራሩን መምረጡንም አብራርተዋል።
በቀጣይም ፓርቲው የአማራ ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ እንደሚያደርግ የገለፁት አቶ አብርሀም ፓርቲው ለአማራ ሕዝብ ህልውና እና ለሀገር አንድነት ሲል መስዋትነት ለመክፈል መዘጋጀቱንም ገልፀዋል።
በተለይም የክልላችን ልማት ለማፋጠን የሥራ እድል ፈጠራ እና ወቅታዊውን የገበያ ንረት ለማረጋጋት ሰፊ ርብርብ እንደሚያደርግ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ጨምረው ገልፀዋል።
ምንጭ፦ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Topic: እንደ አንድ ዜጋ እጠይቃለሁ ― ታማኝ በየነ
እንደ አንድ ዜጋ እጠይቃለሁ ― ታማኝ በየነ
ይድረስ ለኢትዮጵያ መንግስት፤
እኔ በደረሰኝ መረጃ ከትናንት ጀምሮ በወሎ ከሚሴና በሽዋ አጣዬ በደረሰ ግጭት ንጹሃን ዜጎች እየሞቱ ነው፡፡
ለመሆኑ ሰላም የነበር አካባቢ በአንዴ ወደ ጦርነት ቀጠና እንዴት ሊለወጥ ቻለ?
የአማራ ክልል መንግስት በእካባቢው የታጠቁ ሃይሎች ሲገቡና ሲወጡ አላየም ነበር?
የኦሮሚያ ክልል መንግስትስ ከራሱ ኃይል ውጭ የታጠቀ ኃይል ሲያይ ‘ማን ነህ?’ ብሎ አይጠይቅም ወይ?
ኦዴፓ (የኦሮሞ ዲሚክራሲያዊ ፓርቲ) እና አዴፓ (የአማራ ዲሚክራሲያዊ ፓርቲ) በእርግጥ እየተነጋገራችሁ ነው የምትሠሩት? ከሆነስ የአንድ ንጹህ ዜጋ ህይወት ከማለፉ በፊት ለምን ግጭቱን ተነጋግራችሁ አትፈቱትም ነበር?
የፌደራል መንግስት እንደ እኛ ውጭ እንዳለነው እኩል ነው ግጭቱን የሰማው?
በአጠቃላይ ለተፈጠረው ቀውስ ከፌደራል መንግስቱና ከሁለቱ የክልል መንግስታት ውጭ በዚህ ጉዳይ ተጠያቂ የለም።
በአጠቃላይ በየቦታው የሚታዩት ግጭቶች ነገን አስፈሪ እያደረጉት ነው፡፡ መንግስት ሁሉንም በእኩል ዓይን አይቶ በጥፋተኛው ላይ የማያዳግም እርምጃ ካልወሰደ ወደ ፈራነው እልቂት እንደምንገባ ለመናገር ትንቢት ተናጋሪ መሆን አያስፈልግም፡፡
ገና በጠዋት ‘የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የዘር ፖለቲካ መሠረት ሲጣል አይበጀንም!’ ብዬ አደባባይ የወጣሁት የዘረ ፖለቲካ መጨረሻው ዛሬ የምናየው በእጅጉ በከፋ ሁኔታ ነገ የምንጋፈጠው መሆኑን በመረዳት ነበር።
ዛሬ የዘር ፖለቲካ በድርስ ዘዋሪ አፍላ ጎረምሳዎችም፣ እድሜ በተጫናቸው በችግሩ አምጪ አዛውንቶችም በአስፈሪ ሁኔታ እየተራገበ እሳቱ ደግሞ በየቀኑ አገር የቆመችበትን ምሶሶ እየለበለበ የዜጎችን ነፍስ እየቀጠፈ ነው።
አስገራሚው ነገር በተመሳሳይ ወቅት ያልተማርንበት የሩዋንዳ የዘር ፍጅት መታሰቢያ ለ25ኛ ጊዜ በዓለም መድረክ እየታወሰ ነው። እኛ እንደሌሎቹ ካለፈው መማሩ ቢሳነን ዛሬ እየሆነ ባለው በራሳችን ውድቀት ለመማር እንኳን ዝግጁ የሆንን አንመስልም።
እርግጥ ነው መንግስት በቅርቡ የአገራችን መሠረታዊ ችግር የምንከተለው የብሔር ፖለቲካ ነው ሲል የደረሰበትን ድምዳሜ በግልፅ ማሳወቁ የተስፋ ምልክት ሆኖ ሊታይ ይችላል።
ይህ በራሱ ግን ከዛሬው እልቂት የሚታደገን አይደለምና የፌደራል መንግስቱም ሆነ የሁለቱ ክልል መንግስታት በአፋጣኝ ይህን ሁኔታ ቀልብሰው ከዚህ በላይ ሌላ ጉዳት እንዳይደርስ እንዲከላከሉ ይህንን ሰይጣናዊ ተግባር የሚፈፅሙ አካላትንም በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ እንደ አንድ ዜጋ ለመጠየቅ እወዳለሁ።
ኢትዮጵያዊው ታማኝ በየነ (አሜሪካ)
ምንጭ፦ ECADF Ethiopian News / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ተያያዥ ዜና፦ አጣየ፣ ካራቆሬ፣ ማጀቴ እና አካባው በሚኖሩ ዜጎች ላይ የታጠቁ ኃይሎች እያደረሱት ያለው ኢ-ሰብአዊ በደል
የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ ተከትሎ የአዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የጠቅላይ ሚኒስትር የመሠረተ ልማት እና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር አምባቸው መኮንን ርዕስ መስተዳደር ሆነው ተሹመዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መልቀቂያ ጥያቄ አቀረቡ። ርዕሰ መስተዳድሩ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው ጥያቄውን ያቀረቡ ሲሆን፥ ምክር ቤቱም ጥያቄያቸውን ተቀብሏል። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)በበኩሉም የርዕሰ መስተዳድሩን ጥያቄ መቀበሉን የ አማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግበዋል።
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ለሦስተኛ ዙር በርዕሰ መስተዳድርነት ተመርጠው ሲያገለግሉ እንደነበር ይታወሳል። በአጠቃላይም ከታህሳስ ወር 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመሆን አገልግለዋል።
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “ታላቁን የአማራ ሕዝብ ለመምራት ዕድል የሰጠኝን ፓርቲዬን አመሠግናለሁ፤ በስልጣን ዘመኔ በሰጠኋቸው ውሳኔዎች ያስከፋኋችሁ ካላችሁ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ወኔና ጉልበት ሆኖኝ የኖረውን የአማራ ሕዝብ አመሠግናለሁ፤ ለአዲሱ ርዕሰ መስተዳድርም መልካም የሥራ ዘመን እመኛለሁ” ብለዋል በመሰናበቻ ንግግራቸው።
የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ ተከትሎ ምክር ቤቱ የአዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑትን ዶ/ር አምባቸው መኮንንን ርዕስ መስተዳደር አደርጎ ሾሟል። ዶ/ር አምባቸው ከአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን የመሠረተ ልማት እና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር በመሆን እያገለገሉ ነበር።
እድገታቸው ጋይንት፣ ጎንደር ውስጥ የሆነው ዶ/ር አምባቸው መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በተለያዩ የመንግስት ቦታዎች ለ28 ዓመታት ሠርተዋል።
ዶ/ር አምባቸው ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፣ ቀጥሎም ደቡብ ኮርያ ከሚገኘው ከኮርያ የልማት ኢንስቲትዩት (Korea Development Institute) በፐብሊክ ፖሊሲ የማስተርስ ዲግሪ፣ ከዚያም እንግሊዝ ሀገር ካንተርበሪ ከተማ ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬንት (University of Kent) ሌላ ማስተርስ ዲግሪ እና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የግብርና ምርምር ፕሮጀክት ተመረቀ
- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽኖች ምርምር ምን ላይ ደረሰ?
- ዓባይ ኢንዱስትሪያል የልማት አክስዮን ማኅበር ደጀን ከተማ ላይ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው
- የአርሶ አደሩን መሬት እየነጠቁና እያደኸዩ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ አይቻልም – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
- “መንግስት ዜግነታችንን የካደ ግፍ ፈጽሞብናል” ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ውስጥ ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) የአማራ ክልል የልማትና ኢንቨስትመንት ድርጅት በሆነው ጥረት ኮርፖሬት ላይ ከደረሰ የሀብት ብክነት ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልላዊ መንግስት ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ዝግአለ ገበየሁ አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ (“ተጠርጣሪዎች”) በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ባህር ዳር መወሰዳቸውን ለመገናኛ ብዙኃንና ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል። እንደ አቶ ዝግአለ ገለጻ፥ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ከፍተኛ በሆነ የሀብት ብክነት ምክንያት ጥረት ኮርፖሬትን ለኪሳራ ዳርገዋል፤ ይህም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ምክንያት እንደሆነና የተጠረጠሩበት ወንጀል የተፈፀመው በክልሉ በመሆኑ ጉዳያቸው በክልሉ ፍርድ ቤት የሚታይ ይሆናል።
የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በእስካሁኑ የመረጃና ማስረጃ ማሰባሰብ ሂደት በሁለቱ ግለሰቦች ላይ ተገቢውን ክስ ለመመሥረት የሚያስችለውን በቂ መረጃ/ማስረጃ መሰበሰቡንም አስታውቋል።
◌ አባይ የህትመትና የወረቀት ፓኬጂን ፋብሪካ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ሥራ ጀመረ
አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕድን)እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መሥራቾች ከመሆናቸው በተጨማሪ በፌደራልና በክልል መንግስታዊ ቦታውች ለረዥም ጊዜ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በጥረት ኮርፖሬት ውስጥ ደግሞ አቶ ታደሰ ካሳ በዋና ሥራ አስፈፃሚነት አቶ በረከት ስምኦን ደግሞ በቦርድ ሰብሳቢነት ለበርካታ ዓመታት መሥራታቸው ተጠቁሟል።
አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳን በቁጥጥር ስር ለመዋል ያበቃቸውና ጥረት ኮርፖሬት ላይ የተፈጸመው የሀብት ብክነት ምንድን ነው?
የጥረት ኮርፖሬት የሀብት፣ እንዲሁም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የገንዘብ ብክነት ተፈጽሞብኛል ያላቸው ዝርዝሮች፦
- የኮርፖሬቱ ንብረት የሆኑ አምስት ኩባንያዎች ከ ክስዮን መሸጥ/ግዢ ጋር በተያያዘ ለሀብት ብክነት የዳረገ ብልሹ አሠራር በኦዲት ተደርሶበታል፤
- ሌሎች ሁለት እህት ኩባንያዎች ላይ ተመሳሳይ የኦዲት ሥራ እየተሠራ ነው፤
- ተጠርጣሪዎቹ በኮርፖሬቱ ውስጥ በስልጣን ላይ እያሉ የተመሠረቱ ስድስት እህት ኩባንያዎች፥ ከመመሥረታቸው በፊት አስፈላጊውን የአዋጭነት ጥናት ሳይደረግ ለእነዚህ ኩባንያዎች መመሠረቻ/ ግዢ ወደ ሚሊዮን ብር ወጪ ወጥቷል፤
- እነዚህ ስድስት እህት ኩባንያዎች ከተመሠረቱ/ ከተገዙ በኋላ በጊዜው ወደሥራ ባለመግባታቸው ኮርፖሬቱን ለተጨማሪ ወጪ/ ኪሳራ ዳርገውታል፤
- ጥረት ኮርፖሬሽን በአጋርነት ከሚሠራቸው ኩባንያዎች ጋርም ከኮርፖሬቱ የፋይናንስ አሠራርና ሕግ ውጪ 7 ሚሊየን ብር ለሁለት ኩባንያዎች ተሰጥቷል፤
- በሦስት ግለሰቦች ለሚተዳደር አንድ የማዕድን ኩባንያ ላወጣው የእያንዳንዱ አክሲዮን ዋጋ 1,000 ብር ሲሆን፥ ጥረት ኮርፖሬት በአንጻሩ የእያንዳንዱን አክሲዮን ዋጋ በ2,200 ብር እንዲገዛ ተደርጓል። በዚህም ሦስቱ ባለሀብቶች የ4 ሚሊየን 320 ሺህ ብር ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆኑ፥ ጥረት ኮርፖሬት ግን ለኪሳራ ተዳርጓል፤
- ባለሙያን ያላካተተ የአክስዮን መግዛትና መሸጥ ሥራ በኮርፖሬቱ ውስጥ ይተገበር ነበር፤ ይህም ለሀብት ብክነት ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል፤
- ለካፒታል ዕድገት ለሀገር ውስጥ ገቢ መክፈል የነበረበትን 1 ሚሊዮን 296 ሺህ ብር ባለመክፈሉ ጥረት ኮርፖሬት ባለዕዳ አድርጎታል፤
- ለፋብሪካ ይገነባል በሚል የ17 ሚሊየን ብር ግብዓት ተገዝቶ እስካሁን ምንም ዓይነት ሥራላ በለመዋሉ ኮርፖሬቱን ለሌላ የሀብት ብክነት ዳርጎታል።
በስተመጨረሻም አቶ ዝግአለ እንዳስታወቁት የአቶ በረከት ስምኦን እና የአቶ ታደሰ ካሳ በቁጥጥር ስር መዋል መጀመሪያ እንደሆነና፥ ሌሎችም በእንዲህ ዓይነት ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ይውላሉ።
ቀድሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን)፣ በመሀል ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣ አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የተባለው የአማራ ሕዝብ ፓርቲ ያቋቋመው ጥረት ኮርፖሬት በአምራችነት ዘርፍ፣ በአገልግሎት መሰጠት ዘርፍ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ እና በ አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የአስራ ዘጠኝ ኩባንያዎች ባለቤት መሆኑን የኮርፖሬቱ ድረ ገጽ ያሳያል።
ድሬ ዳዋ (ሰሞነኛ)– የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በአንድነት ለመሥራት ቃል ገቡ። ከሰሞኑ ግጭት ውስጥ የገቡ ተማሪዎች የሀይማኖት አባቶችና ከፍተኛ የመንግስት አካላት በተገኙበት ዕርቅ አውርደዋል።
ሰሞኑን ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ባልተከሰተና በሀሰት በተሰራጨ መረጃ ምክንያት በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ዳግመኛ እንዳይከሰት ተማሪዎቹ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉና በተማሪዎች መካከል የሚፈጠሩ የግለሰብ ግጭቶችንም ወደ ቡድንና የብሄር ግጭትነት ለመቀየር የሚፈልጉ አካላትን ጥረት እንደሚያወግዙ ተናግረዋል።
ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ማዕከል ውስጥ በተካሄደው የእርቅ ዝግጅት ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት፥ ተማሪዎችን በብሄር እንዲጋጩ ሁኔታዎችን በሚፈጥሩና በሚያነሳሱ ተማሪዎችና አገልግሎት ሰጪ አካላት ላይ ዩኒቨርሲቲው ክትትል አድርጎ አስተማሪ እርምጃዎችን በመውሰድ የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር ጠይቀዋል።
ከየትኛውም ብሄር ጥሩ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ መጥፎዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉና እነዚህ ሰዎች በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ የእኩይ ተግባራቸውን ለማስፈፀም ብሄራቸውን ሽፋን በማድረግ ለመጠቀም ስለሚሞክሩ ተማሪዎች ተሳስተው የወንጀለኞች ተባባሪና የእኩይ ተግባራት ማስፈፀሚያ እንዳይሆኑ መረጃዎችንና ሁኔታዎችን ከስሜት በጸዳና በምክንያታዊነት እንዲመለከቱ የመድረኩ ተሳታፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
◌ These two Ethiopian students are working to launch their own rocket – the future Eng. Kitaw Ejigu
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባለፉት ዓመታት በአንድነት ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ እንደነበርና በመካከላቸውም አለመስማማቶች ሲፈጠሩ በራሳቸው መንገድ ተወያይተው ችግሮችን ሲፈቱ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮም ይህን አንድነታችንን በማስጠበቅ በመካከላችን ልዩነቶችን በመፍጠርና ግጭት እንዲቀሰቀስ በማነሳሳት የድብቅ ሴራቸው ማስፈፀሚያ ሊያደርጉን የሚፈልጉ አካላትን ሴራ እናከሽፋለን ብለዋል። ባለፉት ጥቂት ቀናት መለስተኛ ግጭት በመፈጠሩ ይቅርታ የተጠያየቁት ተማሪዎች አጋጣሚውን ለቀጣይ በመማሪያነት በመውስድ ችግሮችን በጋራ ለመከላከል እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።
የአማራ ክልልንና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (አዴፓ) ወክለው የተገኙት አቶ ባዘዘው ጫኔ እንደተናገሩት ችግሩ በመፈጠሩ የአማራ ክልልና የክልሉ ገዢ ፓርቲ አዴፓ ማዘኑን ገልፀው ግጭቱ ሳይሰፋና የከፋ ችግር ሳያስከትል በቁጥጥር ስር እንዲውል የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ተማሪዎች እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ አካላት ላደረጉት ጥረት ደግሞ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሰዎች በብዛት ተሰባስበው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ግጭት ሊከሰት እንደሚችል አቶ ባዘዘው አስታውሰው በግለሰቦች የሚጀመር ግጭትን ወደብሄር ማዞሩ አደገኛና ሊወገዝ የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል። በሐረማያ ዩኒቨርሲቲም ሰሞኑን በተከሰተው ግጭት በርካታ ተማሪዎች ጉዳዩን በማውገዝ ወደ ግጭት ባለመግባታቸው ቶሎ በቁጥጥር ስር እንዲውል እንዳስቻለ የተናገሩት አቶ ባዘዘው ተማሪዎች በአንድነት ተሳስቦ በፍቅር የመኖር ልማዳቸውን በማጎልበት የዩኒቨርሲቲያቸውንና የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሚያ ክልልንና የክልሉ ገዢ ፓርቲ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ኦዲፓ) ወክለው የተገኙት አቶ አብዱላዚዝ መሀመድ ባደረጉት ንግግር ተማሪዎቹ እርቅ ለማውረድ ያሳዩትን ፍላጎት አድንቀዋል። አቶ አብዱላዚዝ አያይዘውም ባለፉት ሰባት ወራት መንግስት ለዓመታት የተከማቹ የሕዝብ ጥያቄዎችን በመፍታት ላይ እንደሚገኝና በዚህም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ በመሆኑ ይህን ለውጥ የማይፈልጉ አካላት የመንግስትን የለውጥ ጉዞን ለማደናቀፍ በየቦታው ግጭቶች እንዲነሱ በማድረግ መንግስትን ግጭቶችን በመከላከል ላይ እንዲጠመድ በማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ጉዞዎችን ለማደናቀፍ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።
ስለዚህ የነገዋ ባለተስፋና የዜጎቿ መኩሪያ የሆነች ኢትዮጵያን ተረካቢ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ይህን ተረድተው ራሳቸውን ከስሜታዊነት አርቀው፣ መረጃዎችን በጥንቃቄ በመመርመር ምክንያታዊ በመሆን ግጭቶች እንዳይከሰቱ ጥረት እንዲያደርጉና ከግጭቶች በመራቅ የእኩይ ተግባር ማስፈፀሚያ ከመሆን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አቶ አብዱላዚዝ ለተማሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።
በሀገራችን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸው ወጣቶች የሚገኙበት እንደሆነ እንደሚታመን የተናገሩት የሳይንስና የከፍተኛ ትምህር ጉዳዮች ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ጌታቸው ነጋሽ በአስተሳሰባችሁ መላቃችሁንና ማኅበረሰባችን የሰጣችሁን ይህን ግምት ትክክለኛነት ለማሳየት ምክንያታዊ በመሆን ለነገሮች መፍትሄ በመስጠት ልታስመሰክሩ እንጂ እንደዘይትና ውሃ የተፈጠራችሁበት ነገር ሳይለያይ በብሄር ልትከፋፈሉና ልትጋጩ አይገባም ብለዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዝዳንት ጀማል ዩሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተማሪዎች በብሄር ከማሰብ ወጥተው አንድነት ላይ በማተኮር የዩኒቨርሲቲውን ሰላም በጋራ በማስጠበቅ በቂ ዕውቀት ጨብጠው በሀገራችን የእድገት ጉዞ ላይ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉና ራሳቸውን የጥፋት ኃይሎች ድብቅ ዓላማ አስፈፃሚ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይኖር እንቅፋት ይፈጥራሉ በማለት በተማሪዎች በቀረቡ ጥቆማዎች ላይም አስፈላጊውን ክትትል ግምገማ በማድረግ የእርምት እርምጃዎችና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራዎች እንደሚከናወኑ ዶ/ር ጀማል አረጋግጠዋል።
በእርቅ መድረኩ ላይ የተሳተፉ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም በተማሪዎች መካከል ሰላም፣ ፍቅርና ይቅር ባይነት እንዲጎለብት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።
ምንጭ፦ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ (HU FM 91.5 RADIO)
Search Results for 'አዴፓ'
Viewing 8 results - 1 through 8 (of 8 total)
Viewing 8 results - 1 through 8 (of 8 total)