ምን ልታዘዝ ― በቀልዳ ቀልድ ለዛ የተዋበውና ፖለቲካዊ ሥላቅ ዘውግ ያለው ድራማ

Home Forums Semonegna Stories ምን ልታዘዝ ― በቀልዳ ቀልድ ለዛ የተዋበውና ፖለቲካዊ ሥላቅ ዘውግ ያለው ድራማ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #8398
    Semonegna
    Keymaster

    “… እኛ እንደ ባለሞያ እንደ ወጣት ለሚፈጸሙ ነገሮች ቲፎዞ ልንሆን አንችልም። እገሌን እደግፋለሁ፣ እገሌን አስቀድማለሁ ሳይሆን… የምናየው የኛ አገር ነው። ካፌው አገርን ነው የሚመስለው።…” ምን ልታዘዝ ድራማ መሪ ተዋናይ ሚካኤል ታምሬ። “… ካፌ በተፈጥሮ ብዙ ሃሳብ ማስገባትና ማስወጣት ይፈቅዳል። እናም እንዲያ ማድረግ እፈልግ ነበር።…” የትዕይንቱ ጸሐፊና ዳይሬክተር በኃይሉ ዋሴ (ዋጄ)።

    (የአሜሪካ ድምጽ) – “ሳታየር” (ስላቅ) ከተሰኘው የጥበብ ዘርፍ የሚመደብ፣ ፈጥኖም የብዙዎች የተከታታዮቹን ቀልብ ለመሳብ እና ተወዳጅነት ለማትረፍ ጭምር የታደለ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ነው – “ምን ልታዘዝ!”

    በቀልዳ ቀልድ ለዛ የተዋበው ፖለቲካዊ ሥላቅ (political satire)፣ በሥነ ጽሁፍ፥ በመድረክ አለያም በሥዕላዊ ሥራዎች አማካኝነት በማኅበረሠብ ውስጥ እየታዩ ያሉ ማኅበራዊ ህጸጾችንና ክስረቶችን ለመንቀስና ለመተቸት የሚሳል የጥበብ ዘዬ ነው። ፈታ-ዘና ብለው እንዲከተሉት የሚፈቅደው ይህ የጥበብ ዘዬ ታዲያ በአጫጭር ትዕይንቶች ይሞላ እንጅ ከኮርኳሪነቱ ጋር ቀልጠፍ ያለው ቅብብል ጭብጡን በቅጡ ከታዳሚው ከማድረስ አያገደውም።

    ዘዬው በግለሰቦች የተፈጸሙ ድርጊቶችን ብቻ ሳይሆን በቡድኖች፣ አለያም በተቋማት፣ በአስተዳደርና በመንግስት ሲደረጉ የሚስተዋሉ ነገር ግን “ያልሆኑ” ጉዳዮች ይተቻል፤ ያጣጥላል።

    በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም በፋና ቴሌቪዥን በየሳምንቱ እሁድ መተላለፍ የጀመርው ምን ልታዘዝ አስቂኝ የቴሌቪዥን ድራማ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ብዙም ጊዜ አልፈጀበተም። ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ.ም ግዮን ሆቴል በተከናወነው ስምንተኛው ለዛ የአድማጮች ምርጭ ሽልማት ላይ በምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ አሸናፊ ለመሆን ችሏል። በበኃይሉ ዋሴ (ዋጄ) እና ደመወዝ ጎሽሜ ተደርሶና ዳይሬክት ተደርጎ፣ በሁሰት ፊልም ፕሮዳክሽን ተሠርቶ የሚቀርበው ምን ልታዘዝ ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ሁለተኛ ምዕራፉን ሲጀመር በመጀመሪያው ትዕይንት ላይ ታዋቂዋን አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆን በተጋባዥ ተዋናይነት (guest star) አሳትፏት ነበር።

    ምን ልታዘዝ

    ከምን ልታዘዝ ካፌ እንዝለቅ። የትዕይንቱ ጸሃፊና ዳይሬክተር በኃይሉ ዋሴ እና መሪ ተዋናዩ ሚካኤል ታምሬ እየጠበቁን ነው።

    ደራሲው በኃይሉ ዋሴ (ዋጄ) እና መሪ ተዋናዩ ሚካኤል ታምሬ ከአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ የመጀመሪያ ክፍል እዚህ ጋር በመጫን ያዳምጡ።

    ምን ልታዘዝ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ
    ደራሲና ዳይሬክተር፦ በኃይሉ ዋሴ (ዋጄ) እና ደመወዝ ጎሽሜ
    ረዳት ዳይሬክተር፦ ምትኩ በቀለ እና ዓለማየሁ አጅበው
    ሲኒማቶግራፊና ኤዲተር፦ ታምሩ ጥሩዓለም
    ተዋንያን፦ ሚካኤል ታምሬ፣ መስፍን ኃይለየሱስ፣ ሰለሞን ሙሄ፣ መስከረም አበራ፣ ዘቢባ ግርማ፣ ሰለሞን ተስፋዬ፣ አያሌው አስረስ
    ፕሮዳክሽን ማናጀር፦ ዓለማየሁ አጅበው
    ሙዚቃ፦ ታደለ ፈለቀ
    ግራፊክስ፦ ዘአማኑኤል አበራ
    ድምጽ፦ አግኝቻለሁ ምስጋና እና ናትናኤል ጌታቸው
    ፕሮዳክሽን አስተባባሪ፦ ግሩም ሽቶ እና ደመቀ አበራ
    ፕሮዲዩሰር፦ በኃይሉ ዋሴ (ዋጄ) እና አያልነህ ተሾመ
    ሁሰት ፊልም ፕሮዳክሽን ካሜን ፊልምስ

    ምን ልታዘዝ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.