Home › Forums › Semonegna Stories › ኢትዮጵያዊው ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴ እያስገነቡ ያሉት የምግብ ዘይት ፋብሪካ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 9, 2018 at 8:27 am #7984SemonegnaKeymaster
ቡሬ ከተማ ውስጥ በአቶ በላይነህ ክንዴ የተቋቋመው የፊቤላ ኢንዳስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስር እየተገነባው ያለው የምግብ ዘይት ፋብሪካ ሥራ ሲጀምር በሀገራችን የሚስተዋለዉን የምግብ ዘይት እጥረት በ60 በመቶ ይቀንሳል።
አዲስ አበባ – በሀገራችን በህብረተሰቡ የመሰረታዊ እቃዎች የዕለት ፍጆታ ላይ የአቅርቦት እጥረት ይስተዋላል። የምግብ ዘይት አቅርቦት እጥረት በመኖሩ መንግስት ለህብረተሰቡ በየወሩ በኮታ ልክ ያከፋፍላል። ይሁንና ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቅሬታ ያነሳሉ። በአማራ ክልል በወር ከ23 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት አቅርቦት ያስፈልገዋል። ክልሉ እያሰራጨ ያለው ግን 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት እንደሆነ ከአማራ ክልል ንግድ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በቡሬ ከተማ በላይነህ ክንዴ በተሰኙ ባለሀብት ፊቤላ ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሚል ስያሜ የምግብ ዘይትና ሌሎች ምርቶች ማምረቻ ፋብሪካ እየተገነባ ይገኛል። ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦለት ግንባታው የተጀመረው ፋብሪካ የምግብ ዘይት፣ ፕላስቲክ፣ ሳሙና እና የተቀነባበረ ሰሊጥ ያመርታል።
የፊቤላ ኢንደስትሪያል ኃ/የተ/የግል ማህበር አስተዳደር እና ፋይናንስ ኃላፊ አቶ ጎጃም ዓለሙ እንደተናገሩት በ2006 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ወደ ግንባታ ገብቷል። የህንጻ እና መሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ተጠናቋል። ነገር ግን የዘይት ፋብሪካው የማሽን ተከላ ዘግይቷል። ለዚህም በዋነኝነት እንደምክንያት የሚጠቀሰው ሀገሪቱ ያጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እንደሆነ ከዚህ በፊት Mutesi የተሰኘ በአፍሪካ የንግድና ቢዝነስ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ሚዲያ ዘግቦ ነብር። አሁን ላይ ግን ማሽኑን ለመትከል ዝግጅቱ ተጠናቋል አቶ ጎጃም እንደገለጹት። በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ምርት ይገባል ነዉ ያሉት። የፊቤላ ኢንደስትሪ የምግብ ዘይት ማምረት ሥራ ሲጀምር ከ1 ሚሊዮን ሊትር በላይ በቀን የማምረት አቅም ይኖረዋል። በዚህም የአማራ ክልል የዘይት አቅርቦት እጥረትን ከመፍታት አልፎ ከክልሉ ውጭ ላሉ አካባቢዎች ማድረስ ይችላል።
“የዘይት ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር በሀገራችን ያለውን የፋብሪካ ቁጥር ያሳድጋል። በሀገር ደረጃ የሚስተዋለዉን የምግብ ዘይት እጥረት ችግር እስከ 60 በመቶ ይቀንሳል። በየዓመቱ ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቅባት እህሎችን በግብዓትነት ስለሚጠቀም ለአርሶ አደሩ የገበያ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ያደርጋል” በማለት አቶ ጎጃም ተናግረዋል። ወደ ውጭ ምርቶችን በመላክ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛልም ብለዋል።
የመብራት እና የውሀ አቅርቦት ችግር የምርት ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር እና ጊዜ የማይሰጥ እንቅፋት፥ ምናልባትም ፋብሪካው ሊያጋጥሙት ከሚችሉት ተግዳሮቶች ዋነኛው መሆኑን ጠቁመዉ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
◌ Ethiopian millionaire Belayneh Kinde and others awarded for investing in pulses, oilseeds & spices
የቡሬ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ፣ ኢንደስትሪ እና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይገርማል ሙሉሰዉ በበኩላቸዉ ፊቤላ ኢንደስትሪያል ኃ/የተ/የግል ማኅበር በሀገር ደረጃ የሚስተዋለዉን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግር ይቀንሳል ብለዋል። ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከማስገኘቱ በላይ ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር በስፋት እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
የህንጻ እና የመሠረተ ልማት ግንባታዉ ከ95 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ጠቅሰዉ የመብራት እና ውሀ አቅርቦት ችግር ካልገጠመው በተያዘው በጀት ዓመት ፋብሪካው ሥራ ይጀምራል። ይሁን እንጂ የመብራት እና የውሀ ችግሩ ስር የሰደደ እና ከከተማ አስተዳደሩ አቅም በላይ በመሆኑ የፌዴራል መንግስት ትኩረት እንደሚያሻዉ አቶ ይገርማል ነግረውናል።
ፋብሪካው እስከ 1500 ለሚሆኑ ሰዎች በቋሚነት እና በጊዚያዊነት የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅትን ዋቢ በማድረግ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ዘግቧል።
አቶ በላይነህ ክንዴ ማን ናቸው?
- የተወለዱት በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ሰቀላ ወረዳ (ቡሬ አጠገብ) ነው፤
- የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ስላልመጣላቸው ሁርሳ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ገብተው ወታደራዊ ስልጠና ተከታትለዋል፤
- ነገር ግን በውትድርና ሕይወት ብዙም አልገፉም፤ የደርግ መንግስት ወድቆ የኢህአዴግ መንግስት ስልጣን ሲይዝ የውትድርና ሥራን ትተው እጅግ አናሳ በሆነ ገቢ የቀን ሥራ ላይ ተሰማሩ፤
- በቀን ሥራ ገፍትው ጥቂት ገንዘብ እንዳጠራቀሙ የማር እና የቅቤ ንግድ ጀመሩ፤
- በማር እና ቅቤ ንግድ ለአስር ዓመታት ሠርተው ንግዳቸውን በማሳደግ “በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ” የሚል ድርጅት መሠረቱ፤
- ይህንን የአስመጪና ላኪነት ሥራ ከጊዜ ወደጊዜ በካፒታል፣ በሥራ ዘርፍ እና ሠራተኞችን በመቅጠር፣… በአጠቃላይ በሁሉም አቅጣጫዎች በማሳደግ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ጥቂት ሚሊየነሮች ተርታ ሊሰለፉ ችለዋል (ይህንንም በዓለም ታዋቂው የቢዝነስ መጽሔት ፎርቤስ/Forbes በ2009 ዓ.ም ዘገባው አንስቷቸው ነበር)፤
- በአሁኑ ወቅት የአቶ በላይነህ ክንዴ አጠቃላይ ሀብት ከሶስት ቢሊየን ብር (ከ111 ሚሊየን ዶላር) በላይ ሲሆን የተሰማሩበት የንግድና ምርት ዘርፍም አስመጪና ላኪነት፣ ትራንስፖት፣ የግንባታ ምርቶች፣ እርሻ እና ፋይናንስ ሲሆኑ ሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ግዙፍ አክሲዮን ማኅበራት፥ ለምሳሌ ያህል ጎልደን ባስ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ አዳማ ራስ ሆቴል፣ ፀሐይ ኢንዱስትሪያል ፣ ኳሊቲ ብረታ ብረት ማምረቻ አክሲዮን ማኅበራት ውስጥ ሁነኛ ድርሻ አላቸው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና Mutesi
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.