ተረፈ-ምርትን በመጠቀም ማምረት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
—–
ቆሻሻና አነስተኛ ውሃን በመጠቀም የአሳና ዶሮ ምግብ፣ ማዳበሪያ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በቀላሉ ማምረት የሚያስችል የተቀናጀ የግብርና ዘዴ የምርምር ፕሮጀክት ተጠናቆ ወደ ስራ ሊገባ ነው፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለ3 ዓመታት ባደረገው ምርምር አርሶ አደሩ በአነስተኛ የጓሮ መሬትና ውስን የጉድጓድ ውሃ በማዘጋጀት ዘርፈ ብዙ ምርት መሰብሰብ የሚቻልበት ፕሮጀክት ተጠናቆ ለትግበራ ተዘጋጅቷል፡፡
ምርምሩ በተደረገበት በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ይምሎ ቀበሌ የተደራጁ ወጣቶችን በማሳተፍ ውጤታማ የአሳ፣ የዶሮ፣ የማዳበሪያ፣ የሙዝና የሸንኮራ አገዳ ምርቶችን በአነስተኛ መሬት ላይ ማሳካት ተችሏል፡፡
በፕሮጀክቱ ምረቃ ላይ የተገኙት የአ.ፌ.ዴ.ሪ. ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ይህን ፕሮጀክት ትልቅ የሚያደርገው ወጣቶች በአነስተኛ ወጪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊጠቀሙበት የሚችሉበት መሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ የፕሮጀክቱን የአተገባበር ሰነድ ለዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ለአቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ አስረክበዋል፡፡
ምንጭ፦ ዋልታ ሚዲያ