Home › Forums › Semonegna Stories › አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን አስታወቀ
Tagged: አርባ ምንጭ, አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ, ዳምጠው ዳርዛ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 17, 2018 at 11:52 am #8126SemonegnaKeymaster
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ተዘጋጅቷል፤ የትምህርት ዘመኑን የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፤ በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ማዕከላትን ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ነው።
አርባ ምንጭ (ኢዜአ/AMU)– አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ፕሬዚዳንቱ ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ተወያይቷል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ነባርና አዲስ ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰለጥናል። ከነዚህም ከ6ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች አዲስ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገቡ በማኅበራዊ ሕይወታቸው ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ጉዳዮች ላይ የክህሎት ትምህርት እንደሚሰጥም አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ጥቅምት 11 እና 13 ቀናት የነባር ተማሪዎች ቅበላ የሚያከናውን ሲሆን፣ ጥቅምት 15 ና 16 ቀናት 2011 ዓ.ም ደግሞ አዲስ ገቢዎችን እንደሚቀበል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
ተማሪዎቹ ከአቀባበል ጀምሮ በመማር ማስተማር ሂደት ችግሮች እንዳያጋጥማቸው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ያስረዱት ዶክተር ዳምጠው፣ ከግቢ ውጭ ችግር እንዳያጋጥማቸው የከተማው ነዋሪዎች ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
◌ ተመሳሳይ ዜና፦ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በትምህርት ጥራትና ለኅብረተሰቡ ንጹህ ውሃ ለማቅረብ እየሠራ ነው
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፖለቲካ፣ ኃይማኖትና ከትምሀርት ጋር ግንኙነት በሌላቸው ጉዳዮች የጸዳ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ የሰላም ፎረም አባል አቶ ገረሱ በየነ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ተግባሩን ለማከናወን እንዲያስችለው የሰላም ፎረም እንዲያቋቁም አሳስበዋል።
ሌላኛው የሀይማኖት አባት መጋቢ ካሳዬ በየነ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው አካባቢ እየተስፋፉ የመጡትን የሺሻ፣ የጫትና የመጠጥ ቤቶች ጉዳይ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ኤዞ ኤማቆ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከውሃና ከኤሌክትሪክ መቆራረጥ ጋር የሚያጋጥሙትን ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚታዩ ሕገ ወጥ የሺሻ፣ የመጠጥና ጭፈራ ቤቶችን በመቆጣጠርና በመከታተል እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
በውይይቱ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ የከተማው የሰላም ኮሚቴ አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2011 በጀት ዓመት በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ገልጸዋል። ዳይሬክቶሬቱ ማዕከላቱን በቅርበት እንዲከታተል ኃላፊነት የተሠጠው ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመት የቢሮ መጠሪያውን ወደ ‹‹ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት›› እንደሚቀይርም አስታውቋል።
የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህለ እንደገለፁት በፌዴራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 48(6) መሠረት ሴት የመንግስት ሠራተኞች ከወሊድ በኋላ ወደ ሥራ ገበታቸው ሲመለሱ በሚሠሩበት ተቋም ውስጥ ህጻን ልጆቻቸውን በቅርበት እየተንከባከቡና እየተከታተሉ መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ለማገዝ የህፃናት ማቆያ ማቋቋም አስፈላጊ ነው። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 36(1) መሠረት ህጻናት ከወላጆቻቸው ማግኘት የሚገባቸውን ተገቢውን እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።
የህፃናት ማቆያዎቹ መቋቋም ዓላማዎች ከሆኑት ውስጥ እናቶቻቸው በሥራ ምክንያት በአቅራቢያቸው ባለመኖራቸው ምክንያት በህፃናት ጤንነትና ደህንነት ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ፣ በመንግስት ተቋማት ውስጥ የተሰማሩ እናት ሠራተኞች በህጻን ልጆቻቸው ምክንያት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈጥሩትን ክፍተቶች መሙላት፣ በሴት ሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን መቀነስ እና ውጤታማነታቸውን ማሳደግ ጥቂቶቹ ናቸው።
የህፃናት ማዋያዎቹ ከመደበኛው የሥራ መግቢያ ሰዓት እስከ ሥራ መውጫ ሰዓት ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የመኝታ፣ የማረፊያ፣ የመጫወቻ፣ የምግብ ማብሰያ፣ የመመገቢያ አቅርቦትና አገልግሎት እንዲሁም የእንክብካቤ፣ የቅርብ ክትትል እና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎቶችን አካቷል።
እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ አገልግሎቱን ለማግኘት ወላጆች የማንነት መግለጫ መታወቂያ ማቅረብ የሚኖርባቸው ሲሆን የህፃናቱን ምግብ በተመለከተ ከማቆያ ማዕከሉ ጋር በሚደረግ ስምምነት ወላጆች አዘጋጅተው ማቅረብ አልያም ተመጣጣኝ ክፍያ ፈጽመው የማዕከሉን አቅርቦት መጠቀም ይችላሉ። የማዕከሉን የውስጥ ግብዓት ከማሟላት ጀምሮ ተንከባካቢ ሞግዚት የመቅጠሩ ተግባር የዩኒቨርሲቲው ይሆናል።
ወ/ሪት ሠናይት እንደገለጹት በህፃናት ደህንነት ላይ የወጡትን ህግጋት መሠረት በማድረግ በህፃናት ጤንነት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ኬሚካሎች፣ ብናኞች፣ ድምፅ ያላቸው የማምረቻ ቦታዎችና መሠል ጎጂ ነገሮች የራቀ የህፃናት ማቆያ ለመገንባት ዩኒቨርሲቲው የቦታ መረጣ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። የህፃናት ማቆያ ማዕከላቱ ህንፃዎች የመኝታ፣ የመጫወቻና የንፅህና መጠበቂያ ክፍሎችን የሚያካትቱ ይሆናል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.