Home › Forums › Semonegna Stories › አንበሳ የከተማ አውቶቡስ በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማቋረጡ ተገልጋዮች ለችግር ተዳርገዋል
- This topic has 3 replies, 2 voices, and was last updated 5 years, 10 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
November 2, 2018 at 5:33 pm #8375SemonegnaKeymaster
አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አሠራሩን በማሻሻል ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራርን መሰረት ያደረገ አገልግሎት በመስጠት ፋንታ አንዳንድ የአገልግሎት መስመሮቹን መዝጋቱ ተገቢ አለመሆኑን ተገልጋዮች ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ በረጅም ዘመን አገልግሎቱ የሚታወቀው አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በተወሰኑ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማቋረጡ ለትራንስፖርት እጥረት መጋለጣቸውን ተገልጋዮች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሪፖርተር በኮልፌ ቀራንዮ፣ ቀጨኔ፣ ሚኪሊላንድና መሰል አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች እንዳሉት አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በእነዚህ አካባቢዎች ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት በማቋረጡ ለችግር ተዳርገዋል።
የቀጨኔ አካባቢ ነዋሪዋ ወ/ሮ ባዩሽ ለማ ከሰፈራቸው እስከ መርካቶ በሁለት ብር የምታደርሳቸው ስምንት ቁጥር አውቶቡስ አገልግሎት በማቋረጧ ለተጨማሪ ወጪና እንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
በሚኪሊላንድ የጋራ መኖሪያ ቤት የሚኖሩት መምህር በላቸው አንዳርጌም ከሚኖሩበት አካባቢ ተነስተው ወደ መርካቶ እና ፒያሳ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አውቶቡሶች አገልግሎት በማቋረጣቸው ህብረተሰቡ ለችግር መዳረጉን ገልጸዋል።
መምህር በላቸው እንዳሉት አገልግሎቱ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚሰጠው የተመጣጠነ አገልግሎት በተጨማሪ ለተማሪዎችና መንግስት ሠራተኞችም የጎላ አስተዋጽዖ አለው።
አንበሳ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አሠራሩን በማሻሻል ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራርን መሰረት ያደረገ አገልግሎት በመስጠት ፋንታ የአገልግሎት መስመሮቹን መዝጋቱ ተገቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል።
በአስኮ የአዲስ ሰፈር ነዋሪው ወጣት ሳሙኤል መንገሻ በአካባቢው በተለይ ጠዋትና ማታ ህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገረ መሆኑን ገልጾ ከአስኮ አዲስ ሰፈር አገልግሎት ለመስጠት የተመደበችው አውቶቡስ ስራ ማቆሟ ችግሩን እንደሚያባብሰው ተናግሯል።
ከስድስት ኪሎ በሩፋዔል አስኮ እንዲሁም ከስድስት ኪሎ በሜክሲኮ ቄራ ይመላለሱ የነበሩትን አውቶብሶች ለማግኘት መቸገሩን የተናገረው ደግሞ ተማሪ ያለው ደምሴ ነው። ይህም በተለይ የማታ ትምህርት ለመከታተተል የትራንስፖርት እጥረቱን እንዳባባሰው ነው የተናገረው።
በአንበሳ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የብዙሃን ትራንስፖርት ዋና ሥራ ሂደት ተጠባባቂ ሃላፊ አቶ መላኩ ካሳዬ የነዋሪዎቹ ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑን አምነዋል።
ይሁን እንጂ ችግሩ የተፈጠረው የአገልግሎት መስመሮች በመታጠፋቸው ሳይሆን በርካታ አውቶብሶች በእርጅና ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው መሆኑን አብራርተዋል።
ችግሩን ለመፍታ ድርጅቱ ሰባት መቶ አውቶብሶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው ከመጪው ሰኞ ጀምሮ አዳዲስ አውቶብሶችን እንደሚረከብም ገልጸዋል። አሁን ያሉትን አውቶብሶች በአግባቡ በመጠቀም ችግሩን ለማቃለል ጥረት እደሚደረግም ነው ኃላፊው የተናሩት።
አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በአሁኑ ወቅት 444 አውቶብሶችን በየቀኑ እያሰማራ ቢሆንም ከ20 በላይ የሚሆኑት አውቶቢሶች በብልሽትና በቴክኒክ ጉድለት ሳቢያ በየቀኑ በአግባቡ አገልግሎት እንደማይሰጡ አስታውቀዋል።
በ1935 ዓ.ም በአራት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት የጀመረው አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት በ1967 ዓ.ም ወደ መንግስት ይዞታነት ተሸጋግሮ እስካሁን ድረስ ቆይቷል። በተለያዩ የሥራ መስኮችም ከሰባት ሺህ አምስት መቶ በላይ ሠራተኞች አሉት።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
February 8, 2019 at 6:10 am #9574AnonymousInactiveበአዲስ አበባ እያጋጠመ ባለው የትራንስፖርት እጥረት መቸገራቸውን ነዋሪዎች ገለጹ
—–በአዲስ አበባ እያጋጠመ ባለው የትራንስፖርት እጥረት ሳቢያ በዕለት ተእለት እንቅስቃሴቸው ላይ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ተናገሩ።
የአዲሰ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን በበኩሉ ችግሩ የተከሰተው የትራንስፖርት ተጠቃሚው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ አየጨመረ በመሆኑ ለማቃለል እየሰራሁ ነው ብሏል።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት መንግስት የትራንስፖርት ችግሩን ለማቃለል በተለያዩ ጊዜያት የተማሪዎች ሰርቪስና ሌሎችንም ተሽከርካሪዎች ሲያስገባና ለተጠቃሚዎች አገልግሎት ሲሰጥ ይስተዋላል።
ይሁንና ችግሩ ሊፈታ እንዳልቻለና ተማሪዎች አሁንም ድረስ ከሰራተኛው ጋር እየተጋፉ ትራንስፖርትን ለመጠቀም እየተገደዱ መሆናቸውንም ነው የሚገልጹት።
የትራንስፖርት ተጠቃሚ ወጣት ፍሬወይኒ መኮንን እብደተናገረችው”ትራንስፖርቱና ህዝቡ ተመጣጣኝ አይደለም ህዝቡ በየወቅቱ እየጨመረ ነው የመጣው በአሁኑ ወቅት በጠዋት ብትወጪ ስልፉ ዞሮ ነው የምታይው በጣም ረጅም ነው ትራንስፖርቱ በቂ ነው ለማት በጣም አስቸጋሪ ነው፤ የስራ ስዓት ይረፍዳል።”
የታክሲ ተራ አስከባሪ ወጣት ይውዳኖስ አለሙ በአስተያየቱ”ያሉት ኮድ 1 ታክሲዎች በቂ ናቸው ብዬ አላምንም ተጨማሪ የተሻለ ለህብረተሰቡ አገልግሎት ቢቀርብ” ጥሩ ነው ብሏል፡፡
የአዲሰ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ዘለቀ እንድገለጹት ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ አዲሰ አበባ የሚመጣው ህዝብቁጥር ከነዋሪው ጋር ተደምሮ ከፍተኛ በመሆኑ ጫናው እየጨመረ መጥቷል።
ችግሩን ለቃለል በዚህ በጀት ዓመት 137 አዳዲስ አወቶብሶች በግዥ ገብተው ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት ባለባቸው አከባቢዎች ይሰማራሉ ብለዋል።
ህብረተሰቡ አማራጭ ትራንስፖረቶችን አብዘቶ የመጠቀም ልማድ ብዙም እንዳልሆነ የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ በቀጣይ አመራጮችን በመጠቀም ችግሩ እንዲቃለል የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
February 17, 2019 at 7:31 pm #9761AnonymousInactive100 የአሊያንስ ትራንስፖርት አውቶቢሶች ከስራ ታገዱ
—–
አንድ መቶ ያህል የአሊያንስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ንብረት የሆኑ የከተማ አውቶቡሶች ከስራ ታገዱ፡፡ አውቶቡሶቹ የታገዱት በባንክ የብድር አከፋፈል ስርዓት ላይ በተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነም ታውቋል፡፡ባለፈው ረቡዕ ከሰዓት በኋላ የአሊያንስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢና አባላት በጌትፋም ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አክሲዮን ማህበሩ በገባው ውል መሰረት ብድሩን በየወሩ ለመክፈል በአገሪቱ ላይ የተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ አውቶቡሶቹ የሚያስፈልጋቸውን የመለዋወጫ እቃ ከውጭ ለማስመጣት በነበረ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ተያያዥ ችግሮች እንቅፋት በመሆናቸው በውል መሰረት መክፈል አለመቻላቸውንና በዚህም ምክንያት አበዳሪያቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቶዎቹ አውቶቡሶች ስምሪት ላይ እንዳይውል ከጥር 28 ጀምሮ እግድ ማውጣቱን ተናግረዋል፡፡
ከ2500 በላይ ባለ አክሲዮኖች እና ከ600 በላይ ሰራተኞች ያሉት አሊያንስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር፤ በ2005 ዓ.ም 25 ያህል አውቶቡሶችን በመግዛት የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለፁት የቦርድ ሰብሳቢው ዶ/ር አዲል አብደላ፣ መንግሥት በ2008 ዓ.ም 500 ያህል የከተማ አውቶቡሶች በግል አንቀሳቃሾች ወደ አዲስ አበባ ገብተው በአዲስ አበባና በዙሪያው ላሉ ከተሞች አገልግሎት እንዲሰጡ የቀረጥ ነፃና የብድር አቅርቦት ባመቻቸበት ወቅት 300 ያህል አውቶቡሶች እንዲገዙ ከመንግስት ፈቃድ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበራቸው አቅም ከ100 አውቶቡሶች በላይ ማስመጣት ባለመቻሉ መቶዎቹን ብቻ በብድር ገዝተው ወደስራ እንዲሰማሩ መደረጉን ገልፀው ባንኩ የ6 ወር የእፎይታ ጊዜ ቢሰጣቸውም አውቶቡሶቹ ወደ አገር ገብተው ከማለቃቸው በፊት የእፎይታ ጊዜው እንዳለቀና አውቶቡሶቹ በቅጡ ስራ ሳይጀምሩ ባንኩ ብድር ክፈሉ በማለቱ ከሌሎች በጀቶችም ከሌላም እያመጡ መክፈል መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
“መቶዎቹ አውቶቡሶች የመንግስት ፕሮጀክቶችና ራሱ መንግስት ታሪፍ ያወጣላቸው እንጂ በንግድ ታሪፍ የሚሰሩ አይደሉም” ያሉት የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ አባላት በአሁን ጊዜ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ለባንኩ ደብዳቤ በመፃፍ፣ ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ በማቋቋምና ራሳቸውም ከባንኩ ጋር በመወያየት ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ምንጭ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ
February 26, 2019 at 8:45 pm #9922AnonymousInactiveየመርካቶ አውቶቡስ ተርሚናል ግንባታ 46 በመቶ ደርሷል
—–የመርካቶ አውቶቡስ ተርሚናል ግንባታ 46 በመቶ መድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጽህፈት ቤቱ የእግረኛና ብዙሃን ትራንስፖርት አስተዳደር ኃላፊ አቶ ናትናኤል ጫላ እንዳሉት በመርካቶ የተሳፋሪዎችን ምቾት ጠብቆ በርካታ አገልግሎቶችን በአንዴ መስጠት የሚያስችል ዘመናዊ ተርሚናል በ200 ሚሊዮን ብር እየተገነባ ነው።
ግንባታውን በ2011 በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑንና አፈጻጸሙ 46 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።
20 አውቶቡሶችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግደው ተርሚናሉ የራሳቸው መግቢያና መውጫ ያላቸው ሁለት ወለሎች፣ የአስተዳደር ቢሮዎች፣ የአውቶቡስ መጠበቂያ ቦታ፣ የትኬት መሸጫ፣ የተሳፋሪ መጫኛና ማራገፊያ ስፍራዎችን ያካተተ ነው።
ከ50-80 ሺህ የመርካቶ ገበያተኛችን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል ታስቦ የሚገነባው ተርሚናሉ በ4 ሺህ 125 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን በሠዓት ለ6 ሺህ የብዙሃን ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች አገልግሎት ይሰጣል።
ከተማ አስተዳደሩ አሮጌ ተርሚናሎችን ዓለም በደረሰበት ደረጃ ማሻሻል፣ የማስተናገድ አቅማቸውን ማሳደግና ማልማት ስራ በመከወን ላይ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ የመርካቶ ተርሚናል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠው ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም እንደነበረ አውስተዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.