አድዋ (ሰሞነኛ) – አክሱም ዩኒቨርሲቲ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምህንድስና ትምህርት ክፍል ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ። በአድዋ ከተማ በ60 ሚሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘው የትምህርት ክፍሉ ህንጻ በመጪው ሰኔ ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጸሐዬ አስመላሽ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት፥ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምህንድስና ትምህርት ክፍል መክፈት ያስፈለገው የዘርፉ ኢንዱስትሪ በምርምርና ጥናት እንዲታገዝ ለማስቻል ነው።
“በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ፍላጎት እያደገ መጥቷል” ያሉት ዶ/ር ጸሐዬ፥ የትምህርት ክፍሉ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ዘርፍ በዕውቀትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመደገፍ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በአዲሱ የትምህርት ክፍል በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያገለግሉ ግብዓቶችን የሟሟላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑ አስረድተዋል።
የትምህርት ክፍሉ በተያዘው የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራውን ለመጀመር በዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በግንባታ መጓተት ምክንያት ሥራ መጀመር አለመቻሉን አመልክተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ግንባታ (ኮንስትራክሽን) ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ይትባረክ የሥራ ሂደቱ የተጓተተው በአገር አቀፍ ደረጃ ያጋጠመውን የግንባታ ዕቃዎች ግብዓት እጥረት እና ፕሮጀክቱ ያረፈበት የቦታ ጥበት መሆኑን ጠቁመዋል። ችግሮቹ በመፈታታቸው የትምህርት ክፍሉን ግንባታዎች እስከመጪው ሰኔ ወር ለማጠናቀት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ቴዎድሮስ እንዳሉት፥ የተማሪዎች መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-መጻሕፍት፣ ቤተ-ሙከራ እና ሁለት የተማሪዎች የመመገቢያ አደረሾች ግንባታ ተጠናቋል፤ ባለ አራት ወለል የያዙ ሁለት የተማሪዎች መኝታ ክፍሎችና የተማሪዎች መማሪያ ህንጻዎች ግንባታ እየተገባደደ ይገኛል።
አክሱም ዩኒቨርሲቲ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ምህንድስና ትምህርት ክፍል ለመክፈት መዘጋጀቱ ለዘርፉ ኢንዱስትሪው እድገት የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ በአድዋ ከተማ የሚገኘው የአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክለማርያም ተስፉ ናቸው።
“የምህንድስና ትምህርት ክፍሉ በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አቅራቢያ መገንባቱ ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል”ብለዋል አቶ ተክለማርያም።
በፋብሪካው ያሉትን ማሽነሪዎች እና አሰራሮችን በማየትና ችግሮችን በመለየት የተሻለ ክህሎት እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ሥራ አስክያጁ አክለው ተናግረዋል።
በአደዋ ከተማ የአብነት ቀበሌ ነዋሪ ወ/ሮ ዘመም ፍስሃ የዩኒቨርስቲው በዓድዋ ከተማ የትምህርት ክፍል መክፈቱ ሥራ ዕድል እንደሚፈጥር እና ለከተማዋ እድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖውም ገልጸዋል።
የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በትግራይ ክልል ሃያ የሚሆኑ ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ ተሰማርተው እየሠሩ መሆኑ ይታወቃል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ