Home › Forums › Semonegna Stories › አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለተወሰነ ጊዜ ተዘጋ
Tagged: ለሚ ጉታ, አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
January 21, 2019 at 2:18 pm #9322SemonegnaKeymaster
አዳማ (ሰሞነኛ)– አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየተስተጓገለ ያለውን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ለማስተካከል ለጊዜው የመማር ማስተማሩ ሂደት ተቋርጦ ተማሪዎች ወደ የቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መወሰኑን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ለሚ ጉታ (ዶ/ር) ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ካቋረጡ 31 ቀናት ሆናቸዋል።
ይህንኑ ቀናት ሁሉ ባክኖ የመጀመሪያውን መንፈቀ ዓመት የመማር-ማስተማር ዕቅዱን ማሳካት ስለማይቻል እንደ አዲስ ትምህርቱን የካቲት 25 ቀን እንዲጀመር በሴኔቱ ተወስኗል።
የባከነውን የትምህርት ክፍለጊዜ እንደ አዲስ አስተካክሎ ለመጀመርና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማረጋገጥ ለጊዜው ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መወሰኑን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። ተማሪዎቹ ከአንድ ወር በላይ ትምህርታቸውን ያቋረጡት አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የገባልን ቃል አልፈፀመም በሚል ሰበብ እንደነበር አስታውሰዋል።
የተማሪዎቹ ጥያቄ የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል እንደሚመቻችላቸው እንዲሁም የሥራ ዕድል ትስስር ከኢንዱስትሪዎች ጋር እንደሚፈጠርላቸው ቃል ተገብቶልን ነበር የሚል ነው። በተጨማሪም ላፕቶፕ ኮምፒዩተር እንደሚሰጣቸው የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት የነበሩት የውጭ ዜጋ ቃል ገብቶልናል የሚል ጥያቄ እንደሚያነሱም ዶክተር ለሚ አመልክተዋል።
◌ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ካጠናቀቀ በኋላ ተማሪዎችን መቀበሉ አስታወቀ
መንግስት ሁኔታዎችን አይቶና ገምግሞ የሀገሪቷን አቅም መሠረት ያደረገ መፍትሔ እንደሚፈልግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፣ የቦርድና የዩኒቨርስቲው አመራሮች ባሉበት በተካሄደው ውይይት ቢገልፅም ተማሪዎቹ ለመቀበል ሳይፈልጉ ቀርተዋል።
በዚህም ምክንያት ከአንድ ወር በላይ የመማር-ማስተማር ሂደቱን በማስተጓጎል አንዳንድ ተማሪዎች ከግቢ ወጥተው ለተለያዩ ሱሶችና አልባሌ ተግባራት እየተጋለጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
“በተቋሙ ውስጥ የምግብ፣ የመኝታና ተጓዳኝ አገልግሎት እያገኙና የሀገር ሀብት እየባከነ እንደፈለጉ መሆን ስለማይቻል ለጊዜው የመማር-ማስተማር ሂደት በማቋርጥ ተማሪዎች ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ወስነናል” ብለዋል።
አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከጥር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተማሪዎች ቅጥር ጊቢውን ለቀው እንዲወጡና ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ጠቅሰው የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸው ከነሱ የተለዩበትን ዓላማ ብቻ ከዳር እንዲያደርሱ የማድረግና የመምከር ቤተሰባዊ ኃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
በሴኔቱ ውሳኔ ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመለሱትና በአዲስ መልክ ተመዝግበው ትምህርታቸውን የሚጀምሩበት የካቲት 25 እና 26 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሆነ ያስታወሱት ዶ/ር ለሚ “ነገር ግን የባከነውን የትምህርት ክፍለጊዜ ለማካካስ በማሰብ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መልሰን ለመጥራት ርብርብ እያደረግን እንገኛለን” ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው እየተስተጓጓለ ያለውን የመማር-ማስተማር ሂደት ለማስተካከል የወሰደው እርምጃ አግባብ መሆኑን የገለጸው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሮንክስና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል የአምስተኛ ዓመት ተማሪና የተማሪዎች ተወካይ ፍፁም ቱጁባ ነው።
በ2007 ዓ.ም. በወቅቱ ተቋሙ ሲመሩ በነበረው የውጭ ዜጋ በአፍ ደረጃ የላፕቶፕ ኮምፒዩተሮችን ጨምሮ የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ እንደሚሰጣቸው የተገባውን ቃል አሁን ካልተፈፀመልን አንማርም ብሎ ትምህርት ማቋረጥ ትክክል እንዳልሆነ ጠቅሷል። አሁን ላይ ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው ራሳቸውን እንዲያዩና እንዲፈትሹ የሚያደርግ የእርምት እርምጃ በመሆኑ እንደሚደግፈው ተናግሯል። “በተቋሙ ሰላማዊ የመማር-ማስተማር ሂደት እንዲረጋገጥ የተማሪ ቤተሰቦች ጭምር የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው” ብሏል። ተማሪዎችም ቢሆኑ ከፖለቲካ ግፊትና አስተሳሰብ ወጥተው የመማር ግዴታቸውን እየተወጡ የወጡለትን ዓላማ ሳይጎዱ መብታቸውን መጠየቅ እንደሚገባቸውም ተማሪ ፍፁም መልዕክቱን አስተላልፏል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.