ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከ37 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ለሠራተኞቹ ያስገነባቸውን ቤቶች አስረከበ

Home Forums Semonegna Stories ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከ37 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ለሠራተኞቹ ያስገነባቸውን ቤቶች አስረከበ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #8078
    Semonegna
    Keymaster

    ዩኒቨርሲቲው ለሠራተኞቹ ያስተላለፋቸው መኖርያ ቤቶች ስቱዲዮ፣ ባለ አንድ መኝታ፣ ባለ ሁለት መኝታ እና ባለ ሦስት መኝታ ሲሆኑ ሠራተኞቹ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሠራተኝነት እስካሉ ድረስ ቤቶቹን በነጻ ይገለገሉባቸዋል።

    ነቀምቴ (ኢዜአ) – ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን መኖርያ ቤቶች ለሠራተኞቹ አስረከበ።

    የዩኒቨርሲቲው የመሠረተ ልማትና የሕንፃ ግንባታ ዳይሬክተር ዶክተር ደረጄ አደባ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የመኖርያ ቤት ለሌላቸው ሠራተኞቹ የቤት ባለቤት ለማድረግ ያስገነባቸውን 134 መኖሪያ ቤቶች ትናንት አስረክቧል። ለመኖሪያ ቤቶቹ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ገልጸዋል።

    ከዚህ በተጨማሪ በ1999 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩና በገንዘብ እጥረት ምክንያት ግንባታቸው የተቋረጡ 10 ሕንፃዎችን በመግዛት ሠራተኞቹን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን፥ ሕንጻዎቹ ሲጠናቀቁ 150 የሚሆኑ የተቋሙን ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ዶክተር ደረጄ አክለው ገልጸዋል።

    ዶክተር ደረጄ እንዳሉት መኖርያ ቤቶቹ ስቱዲዮ፣ ባለ አንድ መኝታ፣ ባለ ሁለት መኝታ እና ባለ ሦስት መኝታ ሲሆኑ ሠራተኞቹ በተቋሙ እስካሉ ድረስ ቤቶቹን በነጻ ይገለገሉባቸዋል።

    ከዩኒቨርሲቲው ሠራተኞቹ መካከል መምህር ተስፋዬ ፍቃዱ በሰጡት አስተያየት ተቋሙ በግል የኪራይ ቤት ሲንከራተቱ ይገጥማቸው ከነበረው ችግር እንደተፈታላቸው ተናግረዋል። በግል ተከራይቶ መኖር ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉት ገልጸው በአከራዩና በተከራይ መካከል ቅሬታ በተፈጠረ ቁጥር ይደርስባቸው በነበረው መጉላላት ይማረሩ እንደነበር ገልጸዋል።

    መምህር እሱባለሁ ዳባ በበኩላቸው የግል ቤት በተከራዩበት ወቅት ከውሃና መብራት ክፍያ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጭቅጭቅና ግጭት ውስጥ ይገቡ እንደነበር አስታውሰዋል።

    በተመሳሳይ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪዎች በርካታ መርሀ ግብሮችን ከፈቱ

    በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው በኩል የመኖሪያ ቤት ችግራቸው መፈታቱ የትምህርትና የምርምር ሥራቸውን ተረጋግተው ለማከናወን እንደሚያስችላቸው ጠቁመው በተቋሙ በኩል ለተደረገላቸው የመኖርያ ቤት ስጦታ መስጋናቸውን አቅርበዋል።

    መኖርያ ቤት ማግኘታቸው ከዚህ ቀደም ለግለሰብ ይከፍሉት የነበረውን የቤት ኪራይ ወጪ ከመቀነሱ ባለፈ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲተሳሰሩ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ደግሞ መምህር ኤልያስ ቱጁባ ናቸው። መምህሩ እንዳሉት ሠራተኞች አንድ አካባቢ መሆናቸው ለትራንስፖርት አገልግሎትና ለኢንቴርኔት አገልግሎት ምቹ ሁነታ ከመፍጠር አኳያ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

    ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከዚህን ቀደም ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመኖርያ ቤት ሕንፃ በማስገንባት ከ60 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞቹ ማሰረከቡ የተቋሙን መረጃ ያሳያል።

    በየካቲት ወር 1999 ዓ.ም የተቋቋመው ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት 82 በመጀመሪያ (bachelors)፣ በሁለተኛ (masters) እና በዶክትሬት ዲግሪዎች ተማሪዎችን እንደሚያስተምር የዩኒቨርሲቲው ድረ ገጽ ያስረዳል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ወለጋ ዩኒቨርሲቲ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.