በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በይፋ ተመርቆ ሥራ ጀመረ

Home Forums Semonegna Stories በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በይፋ ተመርቆ ሥራ ጀመረ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #9147
    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲው የበላይ ኃላፊ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይና ከጣልያን የባህል ማዕከላትና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው ልዩ ልዩ እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል።

    በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ረዳት ዳይሬክተር መ/ር ተመስገን ዮሐንስ ሙሉ ፕሮግራሙን የመሩት ሲሆን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ካፈራቸው ምሁራን አንዱ ናቸው።

    በመርሐ ግብሩ መሠረት የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በይፋ መጀመሩን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው የበላይ ኃላፊ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሲሆኑ በመግቢያ ንግግራቸው ላይ ኮሌጁ በመማር ማስተማሩ ሂደት ዛሬ ላይ ለመድረስ የነበሩትን ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለዩኒቨርሲቲ ደረጃ መድረሱ እግዚአብሔርን ካመሰገኑ በኋላ ዩኒቨርሲቲው አሁን የደረሰበትን ደረጃ እንዲደርስ ሌት ተቀን የሠሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን፣ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳት፣ የቦርድ የሥራ አመራር አባላትና የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

    ከብፁዕነታቸው በመቀጠል ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር ኃይሉ ሀብቱ ናቸው።ተባባሪ ፕሮፌሰ ርኃይሉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚገኙ አምስት ኮሌጆችና ት/ቤቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ገልፀው፥ ትምህርት ቤቱ ከጥቅምት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በማስተርስ ኦፍ አርትስ (M.A.) ዲግሪ ደረጃ የድኅረ ምረቃ ትምህርት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል። ፕሮግራሙን ለማጠናቀቅ የሚወስደው ጊዜ ሁለት ዓመት መሆኑንና የአንደኛው ዓመት መርሐ ግብር ለተማሪዎች፦ (1) በኢትዮጵያ ታሪክ፣ (2) በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ (3) በብሔረሰቦች ወግና ሥርዓት ሰፊጥናትና ጥልቅ ግንዛቤ የሚሰጥ ሲሆን በሁለተኛው መርሃ ግብርም፦ (1) በትውፊታዊ ሥነ መድኃኒት/ ሥነ ፈውስ፣ (2) በትውፊታዊ ሥርዓተ ሕግ፣ (3) በኢትዮጵያ ጥናት አውራ ርዕሰ ጉዳዮች የሚያተኩሩ እንደሆኑ አብራርተዋል። የማስተማሪያ መደበኛ ቋንቋ እንግሊዝኛ ቢሆንም አገርኛ ቋንቋዎች ግዕዝን ጨምሮ እንደ አማራጭ ማስተማሪያ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

    የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ነፃነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ለአብነት ያህል በ17ኛው እና 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ እንደነ ወለተ ጴጥሮስ፣ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ማካኤልን የመሳሰሉ አባቶችና እናቶች ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ሰማዕት ሆነዋል ብለዋል።

    ከዚህ በመቀጠል የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባል የሆኑት ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ ንግግር አድርገዋል። ከተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊያ ልሆኑ የትምህርት ተቅዋማትና ድርጅቶች የመጡትን እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ከልብ አመስግነዋል። በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

    በመቀጠልም በፕሮግራሙ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የተገኙ እንግዶች ለዩኒቨርሲቲው ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳቦችና አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን ከቅድስት በዓታ ለማርያም ቤተክርስቲያን የመጡ መምህር በዓሉን የሚገልጽ ቅኔ አቅርበዋል።

    በመጨረሻም በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በብራና መጻሕፍት ዝግጅት ክፍል የሚዘጋጁትን የተለያዩ የብራና መጻሕፍት፣ ቀለምና የብራና መሣሪያዎችን በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ እንግዶች ጐብኝተዋል።

    የቀድሞ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በ1935 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ካህናትንና የቤተክርስቲያን ሊቃውንትን ዘመናዊውንና የአብነት ትምህርታቸውን አስተባብረው እንዲይዙ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ እንደተጀመረ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ኮሌጁ በዚህ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፥ በመቀጠልም በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማዕረግ በማስተማር ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ዕጩዎችን ሲያበቃ ቆይቷል። የኮሌጅን ደረጃ በ1960 ዓ.ም. ካገኘ በኋላ ከሦስት ዓመት በኋላ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቲኦሎጂ ፋኩልቲ አካል ሆኖ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ዘልቋል። የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ፋኩልቲው ሲዘጋ በወቅቱ በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩት በሚፈልጉት የትምህርት መስክ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተዛውረው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ መደረጉ ይታወሳል። መንፈሳዊ ኮሌጁ ተወርሶ አራት ኪሎ ከጎኑ የሚገኘው የሳይንስ ፋኩልቲ ለራሱ የትምህርት መርሐ ግብር እንዲጠቀምበት ተደረገ። በ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ኮሌጁ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተመልሶ በነበረው ዕውቅናና ደረጃ የመማር ማስተማሩን ሒደት ሲያከናውን ቆይቷል። ኮሌጁ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ከፍተኛ የሆኑ የልማት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።

    መንፈሳዊ ኮሌጁ እስከ አሁን ድረስ ከ3,500 በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን ከዚሁ በበለጠ መልኩ እንዲጠናከርና የቤተክርስቲያኒቱ የጥናትና የምርምር ተቅዋም እንዲሆን መሉ ዝግጁቱን አጠናቅቆ በመጨረሱ በአሁኑ ሰዓት በቲዮሎጂ (ስነ መለኮት) የትምህርት ዘርፍ በዶክትሬት፣ በማስተርስ ዲግሪ፤ በመደበኛ የመጀመሪያ ዲግሪ፤ በማታው ተከታታይ እና በርቀት ትምህርት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዲግሪ፤ ዲፕሎማ፤ በግእዝቋንቋ (extension) ዲግሪና ዲፕሎማ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።

    ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ፈቃድ ወደ ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ እንዲያድግ ተደርጓል። በዚሁም መሠረት ከኅዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ እንዲጠራ መወሰኑ ይታወሳል።

    ምንጭ፦ ዩኒቨርሲቲው / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.