የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለቀረቡላቸው አማራጮች ፈንታ በከተማው ውስጥ ሁከት በመፍጠራቸው ከባህር ዳር እንዲወጡ ተጠየቀ

Home Forums Semonegna Stories የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለቀረቡላቸው አማራጮች ፈንታ በከተማው ውስጥ ሁከት በመፍጠራቸው ከባህር ዳር እንዲወጡ ተጠየቀ

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • Author
    Posts
  • #9228
    Semonegna
    Keymaster

    ባህር ዳር (ኢዜአ)–ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በመውጣት በባህር ዳር ከተማ የተጠለሉ የአማራ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ለቀረቡላቸው አማራጮች ከመስማማት ይልቅ የጸጥታ ችግር እየፈጠሩ በመሆኑ ከተማውን ለቀው እንዲወጡ የከተማው ከንቲባ አሳሰቡ።

    የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተማሪዎች የከተማው ህዝብ ባደረገላቸው ድጋፍና እንክብካቤ ከታህሳስ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

    የከተማው ህዝብና ወጣቶች የመኝታ ፍራሽ፣ የምግብ አቅርቦትና አልባሳትን በመደገፍ ያልተቆጠበ ወገናዊ ድጋፍ ቢያደርግም ከጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ጀምሮ ከተጠለሉበት በመውጣት የከተማውን ጸጥታ እያወኩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    “በዛሬው ዕለትም ተመሳሳይ ሁከት በመፍጠር የቱሪዝም ከተማ የሆነችውንና በሰላማዊነቷ የምትታወቀውን የባህር ዳር ከተማ ሲረብሹና ጉዳት ሲያደርሱ ውለዋል” በማለት ጥር 7 ቀን ተናግረዋል።

    “ድንጋይ በመወርወር ጉዳት ማድረስ፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎችና ሌሎች የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲዘጉና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲስተጓጎልም አድርገዋል” ብለዋል።

    ችግሩ በመባባሱ የከተማው ሰላም እየታወከ በነዋሪዎችና በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት መቀጠል ስለሌለበት ከተማውን ለቀው ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረው የከተማው ወጣቶች ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር ላደረጉት የማረጋጋት ጥረትም ምስጋና አቅርበዋል።

    የከተማ አስተዳደሩ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘውዱ ዘለቀ በበኩላቸው “ተማሪዎቹ ከከተማው አልፈው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ፣ ፖሊና ሰላም ካምፓሶች በመግባት ረብሻ እንዲፈጠር አድርገዋል” ብለዋል።

    ከባህር ዳር ከተማ የሚወጣም ሆነ የሚገባ ስምንት በመኪና የተጫነ እህል በማራገፍ፣ ተሽከርካሪዎችን በመስበር፣ ቤቶችን በመደብደብ ከተማረ ሰው የማይጠበቅ ተግባር መፈጸማቸውንም አመልክተዋል።

    ተማሪዎቹ ጩቤ፣ የጭስ ቦንብ፣ የአደጋ መከላከያ ሄልሜትና ዱላ ጭምር በመያዝ አደጋ መፍጠራቸውን ጠቅሰው፤ የፀጥታ መዋቅሩ ከከተማው ሰላም ፈላጊ ወጣቶች ጋር በመተባበር ያለምንም ሰብዓዊ ጉዳት እንዲረጋጋ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን አስረድተዋል።

    “አሁን ላይ ለከተማዋ የሰላም መደፍረስ ምክንያት በመሆናቸው ከህዝቡ ጋር በመሆን የክልሉ መንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ ለመሸኘት ሥራ እየተሠራ ነው” ብለዋል።

    ተማሪዎችን ለማግባባትና መፍትሄ ለመስጠት በከፍተኛ አመራሩ ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም የቀረበላቸውን አማራጭ ባለመቀበል መግባባት ላይ መድረስ አለመቻሉን የገለፁት ደግሞ የክልሉ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ ናቸው።

    ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰው መደበኛ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ አለበለዚያ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም ባለመስማማት ጥር 7 ቀን በኃይል በመጠቀም በአካባቢው የከፋ ችግር ለመፍጠር መሞከራቸውን ጠቁመዋል።

    በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል በተፈጠረ ግጭት የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ችግራቸው እስኪፈታ በጊዜያዊነት በባህር ዳር ከተማ መጠለላቸው ይታወሳል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች


    #10356
    Anonymous
    Inactive

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን ከማስቀጠል ረገድ፡
    —–

    የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በምርምር የታገዘ ስራ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

    በዩኒቨርሲቲው የገዳና ባህል ጥናት ተቋም /Institute of Culture and Gada Study/ በ30/06/2011ዓ.ም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከተጋበዙ ምሁራን ፣ አባገዳዎች፣የዩኒቨርሲቲው አመራር እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ የተውጣጡ አካላት በተገኙበት ማዕከሉ በይፋ ተመርቋል::

    በፕሮግራሙ ላይ ጥናታዊ ጸሑፍ ቀርቧል፣ የባህል ስዕል፣ የምግብና የፎቶ አውደ ርኢይ ጉብኝት ተካሄዷል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.