የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራዎችን በአዲስ ኃይል ወደቀድሞ ፍጥነት ለመመለስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

Home Forums Semonegna Stories የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራዎችን በአዲስ ኃይል ወደቀድሞ ፍጥነት ለመመለስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #9081
    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፈረንሳዩ ጂ ኢ ሪኒዌብልስ አካል ከሆነ ጂ ኢ ኃይድሮ ፍራንስ ጋር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማፋጠን የሚያስችል የ61 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርሟል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራዎችን በአዲስ ኃይል ወደቀድሞ ፍጥነት ለመመለስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ በዶ/ር ኢንጂነር አብርሃም በላይ የተመራ የልዑካን ቡድን የግድቡን የሲቪልና የብረታብረት ሥራዎች ጎብኝቷል።

    የግንባታው አማካሪዎች ትራክትቤል ኢንጂነሪንግና ኤልክ ኤሌክትሮ ኮንሰልት ተወካዮች እንደገለፁት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ለታዩት ችግሮች ቴክኒካዊ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ቀደም ሲል የተጀመሩና የተከናወኑ ከብረታብረት ጋር የተያያዙ ሥራዎች ከ90 በመቶ በላይ ፍተሻ ተደርጎ ችግሮቹን ለማረም የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውም ተገልጿል።

    ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ እንደተናገሩት የግድቡ የግንባታ ሥራዎች መነቃቃት እየታየባቸው ነው። በመሆኑም የተለያዩ ሂደቶችን ማለፍ የማይጠይቁ የግንባታ ሥራዎች በፍጥነት እንዲከናወኑ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኢ/ር አብርሃም በላይ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ለማረምና ጉድለቱን ለማካካስ ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የግድቡን ግንባታ ለማፋጠን ቀደም ሲል ከብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በንዑስ ተቋራጭነት ለመሥራት ውል የነበራቸው ተቋራጮች መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከጂ ኢ ኃይድሮ ፍራንስ ጋር ውል ተፈራርሟል።

    የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስምምነቱን ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በተቋሙ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ነው ጂ ኢ ሃይድሮ ፍራንስ ከተባለው ተቋራጭ ጋር ተፈራርሟል። ጂኢ ሃይድሮ ፍራንስ በቅድሚያ እንዲያመነጩ ታስበው ዲዛይን የተደረጉትን ሁለት ተረባይኖችን ጨምሮ አምስት ኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ኮሚሌክስ ከተባለ ድርጅት ጋር በጥምረት ለማምረት፣ ለመግጠምና ለመፈተሽ የ53 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተፈርሟል።

    ጂ ኢ ሃይድሮ ፍራንስ ቀደም ሲል ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ተርባይን ጄኔሬተሮችን ለማቅረብ ብቻ የንዑስ ተቋራጭነት ስምምነት እንደነበረው ዶ/ር አብርሃም ገልጸዋል። አዲሱ ስምምነት ደግሞ የማምረት፣ የተጓደሉ አቅርቦቶችን የማሟላት፣ የተከላና የፍተሻ ሥራዎችን ያከተተ ነው ተብሏል።

    በተመሳሳይ ተቋሙ ሲኖ ሃይድሮ ከተባለው የቻይና ኩባንያ ጋር የብረታ ብረት ሥራዎች ጋር በተያያዘ ስምምነት ለመፈራረም ድርድሮች መጠናቀቃቸውም ተገልጿል። ኩባንያው የኃይል ማመንጫ የውሃ ማስተላፊያ ቱቦዎችን፣ የመቆጣሪያ እና የጎርፍ ማስተንፈሻ በሮችን የመገንባትና የማስተካከል ሥራ እንደሚያከናውን ተጠቁሟል። ሲኖ ሃይድሮ የሚሠራው ሥራ የሲቪል ሥራዎች በማፋጠን ከአጠቃላይ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ሁለቱ አስቀድመው ኃይል እንዲያመነጩ ያግዛል ተብሏል።

    ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ኤፍቢሲ እና ሮይተርስ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.