Home › Forums › Semonegna Stories › የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻሉን አሳወቀ
Tagged: ዲላ ዩኒቨርሲቲ, ዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 10, 2018 at 6:12 pm #7998SemonegnaKeymaster
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎቶቹን ከማስፋት ባለፈ ለባለሙያዎች በየጊዜው በሚሰጣቸው ሥልጠናዎች ታካሚዎችን በትህትናና እንክብካቤ ለማስተናገድ የሥነልቦና ዝግጁነት እንዲኖራቸው አድርጓል።
ዲላ (ኢዜአ) – የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ተገልጋዮች የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች እንደ ግብዓት በመጠቀም የማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ገለጸ።
የሆስፒታሉ የአስተዳደርና ቢዝነስ ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ እንግዳ ኢዮብ እንደገለጹት ሆስፒታሉ ከተገልጋዮች ጋር በሚያዘጋጃቸው መድረኮች የሚነሱ ቅሬታዎችንና ሀሳቦችን እንደ ግብዓት እየተጠቀመባቸው ነው።
በዚህም ሆስፒታሉ በቅርቡ በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ የገዛቸውን ዘመናዊ የራጅና የላብራቶሪ መሣሪያዎች ተገልጋዮች ወደ ግልና ሌሎች የመንግሥት ህክምና ተቋማት መሄዳቸውን ከማስቀረታቸውም በላይ ታካሚዎችን ከእንግልትና ከተጨማሪ ወጪ አድኗቸዋል። ሆስፒታሉ አሁን የሚሰጣቸውን የምርመራ ዓይነቶች ከ30 ወደ 80 መድረሳቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በሆስፒታሉ የአጥንት ቀዶ ጥገና፣ የውስጥ ደዌ ህክምና ፣ መድኃኒት የተለማመደ የሳምባ ነቀርሳ በሽታ (Tuberculosis) ህክምና መስጠት ተጀምሯል ብለዋል። ብቃት ያላቸው ስፔሻሊስት ሐኪሞችንና ሌሎች ባለሙያዎችን በመቅጠርም አገልግሎቱን ለማሟላት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የመድኃኒትና የህክምና ግብዓቶች አቅርቦት ከመንግሥት የመድኃኒት አቅራቢ ተቋማት ጋር ውል በመግባት እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፤ በአገር ደረጃ ባለው የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ሳቢያ ፍላጎቱን ለማሟላት እንዳልተቻለ አቶ እንግዳ አመልክተዋል።
የዲላ ከተማ ነዋሪዎች መድኃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ በአቅራቢያው እንዲያገኝ ከከፈተው መድኃኒት መደብር በተጨማሪ ሌሎች መደብሮችን ለመክፈት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
የሆስፒታሉ ባለሙያዎች በህክምና ሥነ ምግባር የተሟላ አገልግሎት ለታካሚዎች እንዲሰጡ ሥልጠና፣ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ገልጸዋል።
የሆስፒታሉ ፅዳት አጠባበቅን የሰው ኃይል ከማሟላት ጀምሮ የመፀዳጃ ቤቶች እድሳትና አዳዲስ ግንባታዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በሆስፒታሉ ተኝተው የቀዶ ህክምና ክትትል እያደረጉ ከሚገኙ ታካሚዎች መካካል የዲላ ከተማ ነዋሪው ወጣት ሲሳይ ጂግሶ ሆስፒታሉ ከዚህ በፊት ይስተዋሉበት የነበሩት ችግሮችን በማቃለል አገልግሎት አሰጣጡን እየተሻሻለ መጥቷል ብሏል። በዚህም ታካሚዎችን በአግባቡ ያለማስተናገድና በቂ ምርመራ ያለማድረግን የመሰሉ ጉድለቶቹ እየታረሙ መጥተዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ከአቻ ሆስፒታሎች እኩል ለመራመድ የመድኃኒት አቅርቦትን ጨምሮ አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል እንደሚገባውም አስረድቷል።
ከቡሌ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ምንታምር ዘውዱ በበኩላቸው ከዚህ በፊት እህታቸውን ለማስታመም በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል አይቻለሁ ብለዋል።
ከሲዳማ ዞን አለታ ጩኮ ወረዳ አቶ አዲሱ ቡኩላ በበኩላቸው ልጃቸው ሞተር ቢስክሌት በማሽከርከር ላይ እንዳለ ባጋጠመው የአጥንት ስብራት ስላጋጠመው ወደ ሆስፒታሉ ሊያሳክሙት መምጣታቸውን ይናገራሉ። በቂ የህክምና ክትትል እየተደረገለት መሆኑንም ይገልጻሉ።
ከዚህ በፊት በአካባቢያቸው ተመሳሳይ አደጋ የደረሰባቸው ግለሰቦች ለህክምና ወደ ሀዋሳና ወላይታ ሶዶ ሆስፒታሎች ይሄዱ እንደነበር አውስተው፣ በዚህም ለመጉላላትና ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጉ እንደነበር ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ የቀዶ ጥገናና ተኝቶ ህክምና ክፍል ምክትል አስተባባሪ ነርስ እስራኤል ብርሃኑ ሆስፒታሉ ህክምና በጀመረባቸው አዳዲስ አገልግሎቶች የታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ አገልግሎቶቹን ከማስፋት ባለፈ ለባለሙያዎች በየጊዜው በሚሰጣቸው ሥልጠናዎች ታካሚዎችን በትህትናና እንክብካቤ ለማስተናገድ የሥነልቦና ዝግጁነት እንዲኖራቸው አድርጓል ሲሉም ተናግረዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ከጌዲዮ፣ ከምሥራቅ ጉጂ፣ ከምዕራብ ጉጂና ከቦረና ዞኖች እንዲሁም ከሲዳማ ዞንለሚመጡ ታካሚዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.