Home › Forums › Semonegna Stories › የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርመራ በጋራ ለማከናወን ተስማሙ
Tagged: SPHMMC, አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን, ወንድማገኝ ገዛኸኝ, የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል, የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 5 years, 11 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
December 7, 2018 at 6:23 pm #8859SemonegnaKeymaster
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ የደረሱበት ስምምነት በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የፎረንሲክ ምርመራ ተከትሎ በህክምናና በሕግ ጉዳዮች ላይ መረጃን በወቅቱ ለማግኘት የሚያስችል ፈጣን አሠራር ለመዘርጋት ያለመ ነው።
አዲስ አበባ (ኢዜአ)– የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ህክምና ኮሌጅ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር የፎረንሲክ ምርመራን በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ኅዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የፎረንሲክ ምርመራ ተከትሎ በህክምናና በሕግ ጉዳዮች ላይ መረጃን በወቅቱ ለማግኘት የሚያስችል ፈጣን አሠራር ለመዘርጋት ያለመ ነው ተብሏል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ዋና ፕሮቮስት ዶ/ር ወንድማገኝ ገዛኸኝ ስምምነቱ በተፈረመበት ጊዜ እንደገለጹት፥ ከምረዛና ከአደጋዎች ጋር የተያያዙ የሞት መንስዔዎችና የጤና ጉዳቶች በመለየት ለሕግ አካላት መረጃን በወቅቱ በማቅረብ ረገድ በአገሪቱ ውስጥ ክፍተቶች አሉ። በዚህም ሆስፒታሉ በቅርቡ በጀመረው አጠቃላይ የፎረንሲክ ምርመራ ማዕከል ለሕግ አካላትም ሆነ ለመረጃ የሚጠቅሙ መንስዔዎችን የማጣራት ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ይህንን የፎረንሲክ ምርመራ በማጠናከር የወንጀል ምርመራን በፍጥነት በመለየት ከፌዴራል ፖሊስ በመተባበር ለመሥራት የሚያስችለውን ቅንጅታዊ አሠራር ማጎልበት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህን ሰነድ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል ዶ/ር ወንድማገኝ።
በስምምነቱ መሠረትም የአስክሬን ምርመራን ጨምሮ፣ የአስገድዶ መደፈር ጥቃት፣ የእድሜ ምርመራና የመኪና አደጋ በስምምነቱ የተካተቱ እንደሆኑ ተጠቁሟል። በዋናነትም ለፖሊስና ለሕግ ባለሙያዎች የፎረንሲክ ህክምናና ፎረንሲክ ሳይንስ ከተግባር ትምህርት ጋር ስልጠና የመስጠት ሥራ በሆስፒታሉ የሚከናወን እንደሆነና ምርመራውን የሚያግዙ መሣሪያዎችን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ሁኔታም በስምምነቱ ተካቷል።
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ተኮላ አይፎክሩ በበኩላቸው ወንጀልን መርምሮ ተጠያቂውን አካል ለፍርድ በማቅረብ ረገድ የፎረንሲክ ምርመራን ዘመናዊና ፈጣን በሆነ መልኩ ማከናወን አስፈላጊ ነው። ”ይህም ደግሞ በአገሪቱ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥና የዜጎችን ሰላም ለማስፈን ሚናው የጎላ ከመሆኑም ባሻገር ዜጎች በፍትህ አካላት ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ ይረዳል” ብለዋል።
ወንጀሎች በተፈጸሙባቸው አካባቢዎች ከሁለቱም ተቋማት የተውጣጣ የሙያተኞች ቡድን በስፍራው በመገኘት የማጣራት ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት የሚያስችል አሠራር መስምምነቱ መካተቱን ጀኔራል ተኮላ ጠቅሰዋል። ሌላው አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች ውስጥም ብሔራዊ የፎረንሲክ ተቋማትን ለመመስረት የሚያስችል አሠራር የሚዘረጋ እንደሆነና የጋራ የሆነ የስልጠናና የምርምር ፕሮግራሞች የሚካሄድ ይሆናልም ሲሉ አክለዋል።
በአሁኑ ወቅት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፎረንሲክ ማዕከል በቀን ከ25 እስከ 30 የሚሆኑ ምርመራዎችን እንደሚያከናውን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
February 24, 2019 at 4:38 pm #9872AnonymousInactiveበመዲናዋ በሞተር ብስክሌት በመታገዝ የቅሚያ ወንጀል ከፈፀሙ ግለሰቦች መካከል ግማሽ ያህሉ ተይዘዋል – አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
—–በአዲስ አበባ በሞተር ብስክሌት በመታገዝ የቅሚያ ወንጀል ከፈፀሙ ግለሰቦች መካከል ግማሽ ያህሉ መያዛቸውን የመዲናዋ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የኢንዶክትሬሽንና ህዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ 61 በሞተር ሳይክል የተደገፈ ቅሚያ በከተማዋ መፈጸሙን ገልጸዋል።
ኮማንደሩ ወንጀሉ የተፈፀመው በከተማዋ በሚገኙ 8 ክፍለ ከተሞች መሆኑንም ተናግረዋል።
ከፍተኛ የቅሚያ ወንጀል የተፈፀመበት የቦሌ ክፍለ ከተማ 21 በሞተር ሳይክል የተደገፉ ወንጀሎች የተፈፀመበት ሲሆን፥ ዝቅተኛ የቅሚያ ወንጀል የተፈፀመው በልደታ ክፍለ ከተማ መሆኑን ገልጸዋል።
በአቃቂ ቃሊቲና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ምንም አይነት በሞተር ብስክሌት የተደገፈ ቅሚያ አለመፈጸሙን ገልጸዋል።
ኮማንደሩ ወንጀል ፈፃሚዎቹ በራሳቸውና በተከራዩት የሞተር ብስክሌት የቅሚያ ወንጀሉን እየፈፀሙ መሆኑን ገልጸዋል።
ወንጀሉን ፈጽመው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እንደተያዘና ቀሪ የወንጀል ፈጻሚዎች ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.