Home › Forums › Semonegna Stories › ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና እና ኪነ-ሕንፃ ዘርፍ ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ
Tagged: ኢብራሂም ዑስማን, ኪነ-ሕንፃ, የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ, የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ, ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ
- This topic has 3 replies, 2 voices, and was last updated 5 years, 9 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
February 23, 2019 at 7:56 pm #9855SemonegnaKeymaster
ድሬዳዋ (ሰሞነኛ)– ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ያስተማራቸውንና ያሰለጠናቸውን የሕክምና ኮሌጅ ዕጩ ዶክተር ምሩቃንን እና የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል ዕጬ ምሩቃንን በዛሬው እለት የካቱት 16 ቀን 2011 ዓ.ም በደማቅ ሥነስርዓት አስመረቀ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኪነ-ሕንጻ በመደበኛ የትምህርት መርሃግብር ለ5 ዓመታት አስተምሮ ካስመረቃቸው 36 የኪነ-ሕንጻ ተማሪዎች መካከል 12ቱ ሴቶች ናቸው። ከኪነ-ሕንጻ ተመራቂዎች በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው የሕክምና ኮሌጅ ለ3ተኛ ጊዜ በሕክምና ዘርፍ ያስተማራቸውን 17 ተማሪዎችንም በሕክምና ዶክተር አስመርቋል።
◌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ማሰገንቢያ የሚውል አስር ሚሊዮን ብር ለገሰ
የገጠሩን ህብረተሰብ ጤና በመጠበቅ ምርታማነትን ለማሳደግና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሉ ክፍተቶችን ለማረም ምሩቃን ተግተው መስራት እንዳለባቸው በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን አሳስበዋል። ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ለተመራቂዎቹ ዲግሪና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የተዘጋጀውን ልዩ ሽልማትና ዋንጫ አበርክተዋል።
ከንቲባው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ተመራቂዎች የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥና በቁርጠኝነት በመስራት በሀገሪቱ የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስ ተግተው ሊሠሩ ይገባል በማለት ተናግረዋል። በተለይ ተመራቂ ሐኪሞች የገጠሩን ህብረተሰብ ጤና በአስተማማኝ መንገድ በመጠበቅ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ለማድረግ ታች ህብረተሰቡ ድረስ ወርደው መስራት እንደለባቸው አሳስበዋል።
ከንቲባው አክለውም፥ “የኪነ-ሕንፃ ተመራቂዎች የሀገራችን ቀደም የኪነ-ሕንፃ ጥበብን ከዘመናዊው ጥበብና ዕውቀት ጋር በማዋሃድ በሀገሪቱ እየተስፋፋ ያለውን የዘርፉን ዕድገት ማስቀጠል አለባቸው” ብለዋል።
ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለለፉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ያሬድ ማሞ በበኩላቸው ሁለቱም ሙያዎች ለሀገሪቱ የዕድገት ጉዞ መሳካትና ለማህበረሰቡ መለወጥ የጎላ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል።
◌ በኦሮሚያ ክልል አቦካዶ አምራች ገበሬዎች የተሻሻሉ ዘሮችን በመጠቀም ምርታቸውን ማሳደግ ችለዋል
የሕክምና ባለሙያዎች ሰብዓዊ ርህራሄና ታታሪነትን ተላብሰው በሕክምና ዘርፍ ልዩ አሻራ ማስቀመጥ እንዳለባቸው በመጠቆም፥ “የሕክምና ባለሙያዎች በቸልተኝነት ሳቢያ የታመሙ ሰዎች በእጃቸው እንዳይጠፉ ምንግዜም ተጠንቀቁ” በማለት አሳስበዋል። በተጨማሪም፥ “የኪነ-ሕንፃ ተመራቂዎች በሀገሪቱ ዕድገት ላይ ትልቅ ሚና መጫወት ይገባቸዋል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዘርዓይ መስፍን በበኩላቸው በምረቃው ላይ ተገኝተው በከፍተኛ ማዕረግ ለተመረቁት ተማሪዎች ሽልማት ሰጥተዋል። የኪነ-ሕንፃ ተመራቂዎች እስከ መጨረሻ በመማርና እውቀትን በማካፈል ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ግዳጅና ብሩህ ተስፋ ለማሳካት ትኩረት ሰጥትው መንቀሳቀስ እንደለባቸው አሳስበዋል።
ከተመራቂ ሐኪሞች መካከል 3 ነጥብ 8 ውጤት በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው ዶ/ር አቤል ወልደጊዮርጊስ በየትኛውም የሀገሪቱ የገጠር ዳርቻ በመጓዝ ወገኖቹን ለመርዳት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። “ይህም በሕክምናው መስክ የተቸገሩትን ወገኖችን የመርዳት የልጅነት ህልሜ እውን ለማድረግ ያግዘኛል” ብሏል።
በኪነ-ሕንፃ ዘርፍ 3 ነጥብ 5 ውጤት በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ወጣት ትርሲት ታምራት በሀገሪቱ እየጎለበተ ባለው የኪነ-ህንፃ ዘርፍ ሙያዊ እውቀቷን በመጠቀም አንዳች አሻራ ለማስቀመጥ መዘጋጀቷን ተናግራለች።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
March 12, 2019 at 2:48 am #10192SemonegnaKeymasterበድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ እና በሞናኮ ኢንስቲትዩት (Institut de Paléontologie Humaine, Fondation Prince Albert Ier de Monaco) መካከል በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ።
—–ስምምነቱን የድሬዳዋ ከንቲባና የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢብራሂም ኡስማን እና የኢንስቲትዩቱ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሄነሪ ዲ ሉምሌይ (Henry de Lumley) ፈርመዋል ።
ስምምነቱ ለዩኒቨርስቲው መምህራንና ተማሪዎች የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድልና አጫጭር ስልጠናዎችን የሚያስገኝ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ስምምነቱ የምርምር ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት ዕድል የሚፈጥር ሲሆን በዋናነት በጂኦሎጂና በቅድመ ታሪክ ጥናት ላይ ያተኮረ እንደሚሆን በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል ።
ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን የስምምነቱ መፈረም በድሬዳዋና በአካባቢው ቅድመ ታሪክ ላይ ጥናትና ምርምር ለማድረግ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ዩኒቨርሲቲውን በሰው ሀይል ለማጠናከር ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ሲሉ በፊርማ ስነስርአቱ ወቅት ተናግረዋል።
ምንጭ፦ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት
March 12, 2019 at 5:59 am #10195SemonegnaKeymasterየድሬዳዋ ከንቲባ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ
—–የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ዑስማን ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ለከተማ አስተዳደሩ ያቀረቡት ጥያቄ በምክር ቤቱ ተቀባይነት አገኘ።
የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ) አባል የሆኑት አቶ ኢብራሂም ለሦስት ዓመታት ከመንፈቅ በከንቲባነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ በሚደረጉ ሠልፎች ተቃውሞ ይቀርብባቸው ነበር።
ምክር ቤቱ በምትካቸው አቶ መሐዲ ዲሬን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ በማድረግ ሹሟል።
ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ
April 7, 2019 at 12:05 am #10510AnonymousInactiveየጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት ትኩረት መስጠቱን አስታወቀ
—–የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደቱን ለማስቀጠልና መልካም ስነ-ምግባር የተላበሰ ምሁር ላማፍራት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
በተለያየ አጋጣሚ ሰላምን ሊያውክ የሚችል የስነ-ምግባር ችግር በታየባቸው ተማሪዎች ላይም አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን ጨምሮ ገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክትር ኡጁሉ ኡኮክ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት መደበኛውን የመማር ማስተማር ሒደት ሰላማዊ ለማድረግ ሁሉንም ያሳተፈ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
በግቢው የሚካሔደው የትምህርት አሰጣጥ ውጤታማ እንዲሆንም የማሪዎችን ስነምግባር ከመከታተል ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በቅርቡም በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ተግባር የተፈጸመ በማስመሰል ተማሪዎችን ለሁከት ለማነሰሳት ሲሰሩ የተደረሰባቸው 30 ተማሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።።
“ከነዚህ ውስጥም 13ቱ የስንብት፣ 10 ተማሪዎች ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ከዩኒቨርሲቲው የታገዱ ሲሆን ሰባት ተማሪዎች ላይ ደግሞ የመጨረሻ የጹሁፍ ማስጠንቀቂያ እርምጃ ተወሰዷል” ብለዋል።
ዩኒቨርሲተው እርምጃውን ለመውሰድ የተገደደው የተቋሙን ስርዓትና ደህንነት ለማከበር መሆኑን ተናግረዋል።
ተማሪዎች የተወሰደባቸው እርምጃ ተገቢ አደለም በሚል ቅሬታ ማቅረባቸውንና ጉዳያቸውም በቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ እንደገና እየታየላቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
“በቀጣይም የዩኒቨርሲቲውን ህግና ደንብ የሚጥስ ተማሪ ከተገኘ ተመሳሳይ እርምጃ የመውሰዱ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል” ብለዋል።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በ2006 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን ይዞታው ያልታጠረ በመሆኑ ለጸጥታ ችግር የተጋለጠ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ይገልጻሉ።
ምንጭ፦ ኢዜአ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.