በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቱሪስት ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች በይፋ ተመረቁ

Home Forums Semonegna Stories ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቱሪስት ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች በይፋ ተመረቁ

#15111
Anonymous
Inactive

በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቱሪስት ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ሄሎ ታክሲ በተባለ ድርጅት አማካኝነት በይፋ ተመርቀው ሥራ ጀመሩ

አዲስ አበባ (ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር) – ኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ የሚገጣጥማቸውና በሄሎ ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ታክሲዎች በሸራተን አዲስ ሆቴል በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው በይፋ ተመርቀዋል።

የኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሶሎሞን ሙሉጌታ፥ “ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ የቱሪዝም ሀብት ያላትና የተስፋ ምድር በመሆኗ ለቱሪስት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎችን ቀድመን ለማዘጋጀት ችለናል” ብለዋል።

የሄሎ ታክሲ መሥራችና ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሐንስ በበኩላቸው፥ “ሄሎ ታክሲ በቀጣይም ቱሪስቱን በአውሮፕላን ወደ ቱሪስት መዳረሻዎች ለማድረስና አመርቂ አገልግሎት ለመስጠት 50% ዝግጅቱን አጠናቋል” ብለዋል።

ሄሎ ታክሲ ከዚህ ቀደም 40 ታክሲዎችን አስመርቆ በይፋ ሥራ ያስጀመረ ሲሆን፥ አሁን ደግሞ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የቱሪስት ታክሲ ወደ አገልግሎት በማስገባት ሥራውን ጀምሯል። ሄሎ ታክሲ ከዚህ ቀደም በታክሲ አገልግሎት ተሰማርተው መኪኖቻቸው አሮጌ በመሆናቸው ከአገልግሎት ውጭ ለሆኑባቸው አሮጌውን መኪና በመቀበልና በአዲስ በመተካት የታክሲ ባለቤቶችን እየታደገ ያለ ድርጅት መሆኑም ተገልጿል። የተሰበሰቡ አሮጌ ታክሲዎችም ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመንጃ ፍቃድና ተግባራዊ የመኪና ጥገና መማሪያ እንዲሆኑ፤ ከዚያም ሲያልፍ የዋጋ ተመን ወጥቶላቸው ወደ ማቅለጫ ገብተውና ለውጭ ገበያ ተሽጠው ገቢ እንዲያስገኙ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስተር ክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው፥ “መንግሥት የታክሲ ሞተሮች ከቀረጥ ነጻ ሆነው ወደ ሀገራችን እንዲገቡ የወሰነው ግብር መሰብሰብ አቅቶት ሳይሆን፥ አሮጌ መኪኖችን በአዲስ ተተክተው የአየር ብክለት እንዲቀንስ፣ ሀገር ውስጥ ሲገጣጠሙም ተጨማሪ የሥራ ዕድል ስለሚፈጥሩ፣ ዜጎቻችንም በሀገራቸው ሠርተው እንዲከብሩ፣ ስርቆት የሚፀየፍ ጥሩ አገልጋይ እንድትሆኑ ነው” ብለዋል።

ሚኒስትሯ አክለውም፥ ታክሲዎችን በአዲስ እንደቀየራችሁ ሁሉ አስተሳሰባችሁንና ሕይወታችሁን በመቀየር ለቱሪስቶቻችንም ቀድሞ መረጃ በመስጠት ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ የሀገራችንን ገፅታ እንድትገነቡ አሳስባለሁ ብለዋል።

የክህሎትና የአገልግሎት አሰጣጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለታክሲ ሹፌሮች ይሰጣል ያሉት ሚኒስትሯ፥ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሕጋዊ አሠራርን መከተል እና ለረዥም ዓመታት በአሮጌ መኪና ጭስ የተበከለችውን ሀገራችንን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብራችን ችግኝ በመትከልና በማልማት ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ ብለዋል።

በመጨረሻም ክብርት ወ/ሮ ቡዜና አልኸድር የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ፥ ለታክሲ አገልግሎት ማኅበራቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሳተፉ የችግኝ ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን፥ ከሄሎ ታክሲ ድርጅት ጋርም በቱሪስት የታክሲ አገልግሎት ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

የኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ተወካይ አቶ ሸምሰዲን አብዱራህማን በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ተደራሽ የሚሆኑ ለ110 ሥራ አጥ ወጣቶች በ100% ብድር የሚሰጡ ሄሎ ታክሲዎችን፣ አስር የቱሪስት አምቡላንሶችን፣ በ59 ቋንቋዎች የማስተርጎም ሥራ የሚሠሩ ሃምሳ ማሽኖችን ለክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው አስረክበዋል።

የሄሎ ታክሲ ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሐንስ በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ተደራሽ የሚሆኑ ለ250 ሰዎች አሮጌ ታክሲያቸውን ብቻ ሰጥተው አዲስ ታክሲ እንዲረከቡ የሚያስችል ስጦታ ያቀረቡ ሲሆን፥ የታክሲ ማኅበራትም ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የምስጋና ስጦታ ለክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው አበርክተዋል።

ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

ሄሎ ታክሲ ኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ