Home › Forums › Semonegna Stories › አዲስ አበባ ከተማን የተመለከቱ ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች › ሸገር ፓርክ በትልቅ ሥነ-ሥርዓት ተመርቋል
ሸገር ፓርክ በትልቅ ሥነ-ሥርዓት ተመርቋል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባን ከተማ የቀይራል ተብሎ የሚጠበቀው ሸገር ፓርክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በአዲስ ዓመት ዋዜማ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ባለስልጣናት እና ጥሪ የተደረገላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም በተገኙበት ተካሂዷል።
ሸገር ፓርክ የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊነት በሚያሳይ መልኩ የተገነባ ሲሆን፥ በውስጡ የተፈጥሮ እጽዋትንም ያካተተ ነው። ፓርኩ የኢትዮጵያን ቀደምት ታሪክ በማሳየት የወደፊት ብሩህ ተስፋን የሚያሳይ የወዳጅነት ፓርክ እንደሆነ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
ግንባታው ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ሸገር ፓርክ በቻይና ግዙፉ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ “China Communications Construction Company (CCCC)” የተገነባ ነው።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፓርኩ ግንባታ አስተዋጽኦ ላደረጉ የቻይና የተለያዩ ኩባንያዎች ትልቁን የወዳጅነት ሽልማት አበርክተዋል። በግንባታው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያንም እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሸገር ፓርክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰዱ ነጥቦች፡-
- አዲስ አበባ ይህን ፓርክ ማግኘቷ ስሟንና ደረጃዋን ከፍ ያደርገዋል፤
- ይህ እና ሌሎች ፓርኮች የከተማይቱንና የሀገራችንን ገፅታ ያስውቡታል፤
- ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤
- ፓርኩ ተባብሮ መሥራት የሚያስገኘውን ውጤት ማሳያ ነው፤
- ሸገር ፓርክ ከመሃል ሀገር ሳንወጣ ሩቅ ቦታ የተጓዝን የሚያስመስለን ፓርክ ነው፤
- ከተለምዶው የተለየ ነገር ማየት አድማሳችንን ያሰፋዋል፤
- [በግሌ] ይህ ፓርክ በዚህ ፍጥነት ለምረቃ ይበቃል ብዬ አላሰብኩም ነበር፤
- በፓርኩ በሚገኘው የአበባ ማፍያ ስፍራ ከዓይናችን ጠፍተው የቆዩ አበቦችን ሳይቀር ማስተዋል ችያለሁ፤
- ውበትን መሻት ካለንበት ሀኔታ ጋር አይፃረርም፤
- አገራችንን የማስዋብ ጥረታችንን ከሌሎች የልማት ጥረቶቻችን ጋር ጎን ለጎን ካስኬድነው በአጭር ጊዜ የአገራችንን ገፅታ መቀየር እንችላለን፤
- በፕሮጀክቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል።