Home › Forums › Semonegna Stories › ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት › ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 5117 ተማሪዎች አስመረቀ
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 5117 ተማሪዎች አስመረቀ
ባሕር ዳር (ሰሞነኛ)– ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን መመረቅ የነበረባቸው እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት መቋረጡን ተከትሎ የዘገዩ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ 4203፣ በሁለተኛ ዲግሪ 759፣ በሦስተኛ ዲግሪ 10፣ በስፔሻሊቲ 40፣ በፒጂዲቲ ቅድመ ምረቃ (post graduate diploma in teaching/PGDT) 105፤ በአጠቃላይ 1623 ሴት፣ 3494 ወንድ ተማሪዎችን፥ በድምሩ 5117 ተማሪዎችን ጥር 29 ቀን 2013 ዓ.ም. የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በክብር እንግድነት በተገኙበት አስመርቋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፥ “የዘንድሮ ተማራቂዎችን እንደተማሪ በርካታ መሰናክሎችን አልፈው ለዛሬው ቀን በመብቃታቸው ‘ከመወርቅ’ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግሮች በመከራ ጊዜ እንደ ወርቅ ነጥራችሁ በመውጣታችሁና ለዚህ ታሪካዊ ቀን እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል። ዶ/ር ፍሬው አክለወም፥ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆንና በሀገራችን ካሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ግምባር ቀደም እንዲሆን ላገዙት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በከተማዋ ውስጥ ላሉ የወጣት አደረጃጀቶችና ለሌሎች አጋር ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ተመራቂዎች ዓለምን እየፈተነ ባለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ውስብስብ ችግሮችን አልፈው መመረቅ መቻላቸው ታሪካዊ ተመራቂዎች መሆናቸውን አውስተው፤ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገርና ቤተሰብ የጣለባቸውን አደራ በአግባቡ እንዲወጡ፣ በሰለጠኑበት የትምህርት መስክ ጠንክረው በመሥራት ሀገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው፥ ተመራቂ ተማሪዎች ‘ሀገሬ ምን አደረገችልኝ?’ ሳይሆን ‘ለሀገሬ ምን አደረኩላት?’ ብሎ ራስን መጠየቅ እና በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ጥልቅ ዕውቀት ተጠቅመው በኮሮናቫይረስ ወረርሽ የቀዘቀዘውን ኢኮኖሚ እንዲሻሻል በማገዝ በሀገር ግንባታ ላይ የበኩላችውን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለባሕር ዳር ከተማ ብሎም ለክልሉ እንደ ዓይን ብሌን የሚታይ ግዙፍ የዕውቀት ማዕከል መሆኑንም ተናግረዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ በመመረቂያ ፕሮጀክቶች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የምስክር ወረቀት እና የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሁም በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የወርቅ ዋንጫ ተሸልመዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ክብርት ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ፣ የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨረሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ ፣ የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋም ድርጅት (አመልድ) ዋና ዳይሬክተር እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ባማረው እና በተዋበው የዩኒቨርሲቲው ስታዲየም በፖሊስ ማርሽ ባንድ በቀረበ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መዝሙር እና በሙሉ ዓለም የባህል የሙዚቃ ባንድ በቀረቡ የተለያዩ ባህላዊ ውዝዋዜዎች እና ዘመናዊ ሙዚቃዎች በመታጀብ ደምቆ ውሏል።
ምንጭ፦ ዩኒቨርሲቲው