Home › Forums › Semonegna Stories › ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ › ብርሃን ባንክ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለጉዳት የተጋለጡ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለመደገፍ የብድር ወለድ ቅናሽ አደረገ
ብርሃን ባንክ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለጉዳት የተጋለጡ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለመደገፍ የብድር ወለድ ቅናሽ አደረገ
ብርሃን ባንክ አክሲዮን ማኅበር (አ.ማ.) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ተጽዕኖን ለማቃለል በማሰብ ከ 0.5% እስከ 4% የሚደርስ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ ከግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ ከሜይ 18 ቀን 2020) ጀምሮ ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ። ጋዜጣዊ መግለጫው እንደሚያስረዳው፥ የወለድ ቅናሽ ማስተከካያው በተለያዩ ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ኮቪድ-19 ያስከተለውን ተጽዕኖ ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሲሆን፥ ሁሉም የብድር ዘርፎች ማለትም የግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ የአገር ውስጥ፣ ንግድና አገልግሎት፣ የወጪ ንግድ፣ ሕንፃና ግንባታ፣ የግል ብድር ዘርፎች የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ተጠቃሚ ሆነዋል።
የወለድ ምጣኔ ቅናሹ በተለይም በኮቪድ-19 ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ዘርፎች ከፍተኛውን የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። በዚህም መሠረት ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላኪ ዘርፍ የ4% የወለድ ምጣኔ ቅናሽ የተደረገ ሲሆን፤ እንዲሁም ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ደግሞ የ3.5% ቅናሽ ተደርጓል። በተጨማሪም ለእነዚህ የኢኮኖሚ ዘርፎች የስድስት ወራት የፍሬ ብድር እና የወለድ ክፍያ የእፎይታ ጊዜ ከግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ ከሜይ 18 ቀን 2020) ጀምሮ እንዲደረግላቸው ባንኩ ወስኗል። በሌላም በኩል ተበዳሪዎቻችን በኮቪድ-19 ጫና ምክንያት የብድር ክፍያ ማራዘሚያ ጥያቄ ቢያቀርቡ ጥያቄያቸው እንደሁኔታው እየታየ የሚስተናገድ ይሆናል።
ብርሃን ባንክ ይህንን የወለድ ምጣኔ ቅናሽ በማድረጉ በዓመት ሊያገኝ የሚችለውን ወደ ብር 100 ሚሊዮን የሚሆን የወለድ ገቢ የሚያሳጣው መሆኑ ታውቋል። ይህም ውሳኔ ከባንኩ እድሜ እና አቅም አንፃር ሲታይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ብሔራዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ባንኩ የበኩሉን አስተዋፅኦ ከማበርከት አንፃር የሚሄድበትን ርቀት እና ቁርጠኝነት ያመለክታል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) በሀገራችን ከተከሰተ ጀምሮ ብርሃን ባንክ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ሰፊውን ማኅበረሰብ እና የባንኩን ደንበኞች ማዕከል ያደረጉ በርካታ ተግባራትና ድጋፎች ከዚህ ቀደም ማከናወኑ ይታወቃል። ከዚህም አንፃር ቀደም ሲል የ Letter of Credit ማራዚሚያ ኮሚሽን ሙሉ በሙሉ ማንሣቱን፣ የብድር ማራዘሚያ ኮሚሽንና የተጨማሪ ወለድ ማንሣቱ፤ በአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች በ35 ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች የንፅህና አገልግሎት መስጫ የውሃ ታንከሮችን ማዘጋጀቱ እና እንዲሁም ለጤና ሚኒስቴር ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ብር 3 ሚሊዮን ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።
በመጨረሻም ብርሃን ባንክ ለወደፊቱም የወረርሽኙን ተጽዕኖ ለመቅረፍ ተመሳሳይ ድጋፎችን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አስታውቋል።
ምንጭ፦ berhanbanksc.com