Home › Forums › Semonegna Stories › ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት › ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
ዲላ/አርባ ምንጭ (ኢዜአ/አ.ም.ዩ) – ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1,043 ተማሪዎችን ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫላ ዋታ እንደገለጹት ከተመራቂዎቹ መካከል 283 በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው። ቀሪዎቹ በምስክር ወረቀት የተመረቁ መሆኑን አስረድተዋል።
ተመራቂዎቹ ትምህርታቸውን በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሲከታተሉ እንደቆዩ አመልክተው፥ በተለይ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት የክፍል ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከልን ጨምሮ በተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ዶ/ር ጫላ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ኡዴሳ ክዮላ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ በቀጣይ በሚሰማሩበተ የሥራ መስክ ሀገርና ሕዝብ የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና ታታሪነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቱን የተከታተለው ቅዱስ ይገረሙ በሰጠው አስተያየት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በሰለጠነበት በ“ሶፍትዌር ዲዛይን” ዘርፍ በመሰማራት እራሱንና ሀገሩን ለመጥቀም እንደሚሠራ ተናግሯል።
በሁለተኛ ዲግሪ ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ የተመረቀው ዋቆ ጥላሁን በበኩሉ በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀት በመጠቀም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንደሚጥር ገልጿል።
የሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች የሚያስተምራቸው ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉት በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።
ከተማሪዎች ምርቃት ጋር በተያያዘ፥ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለ33ኛ ጊዜ አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በመደበኛ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,326 ተማሪዎች ቅዳሜ ነሐሴ 30/2012 ዓ/ም በተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው በስድስት የተለያዩ ካምፓሶች በ76 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ99 የ2ኛ ዲግሪ እና በ21 የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች በአጠቃላይ ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሀግብሮች በማስተማር ላይ ይገኛል። ተቋሙ ባለፉት 33 ዓመታት በልዩ ልዩ የምህንድስና፣ የሕክምናና የጤና፣ የግብርና፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ የማኅበራዊ እንዲሁም የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ዘርፎች 56,958 ምሩቃንን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ጉልህ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አክለውም በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛው አጋማሽ ላይ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሁሉም ደረጃዎች በመማሪያ ክፍል ሆኖ የመማር ማስተማር ሂደት የተቋረጠ ቢሆንም፥ ዩኒቨርሲቲዎች ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጥናትና ምርምር ሥራቸውን ሲሠሩ የቆዩ ተማሪዎች አስፈላጊውን የምረቃ መስፈርት በማጠናቀቅ ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ዓመታት በተከፈቱ የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች ላይ የማጠናከር ሥራ የሚሠራ ሲሆን፥ ዩኒቨርሲቲው በ2013 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ኛ ዲግሪ የሚያስመርቅ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደተናገሩት፥ የመማር ግቡ ከግለሰብ ህይወት እስከ ሀገር ድረስ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ምቹና ተስማሚ አኗኗርን ለመፍጠር የለውጥና የዕድገት ጎዳናን መከተል ነው። በመሆኑም የዕለቱ ተመራቂዎች ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ እንድትደርስ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲሉ አሳስበዋል። በተጨማሪም ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል። ሀገሪቱ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እየተሻገረች የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን ፈተናዎቹን በብቃት መክተን ወደ መልካም ዕድል መቀየር ይጠበቅብናል ብለዋል።
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እና የሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር በለጠ ይልማ የእጩ ምሩቃን መግለጫ በመስጠት አስመርቀዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በክብር እንግድነት፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ (አ.ም.ዩ)