እናት ባንክ እና ዳሸን ባንክ የብድር ወለድ ስረዛ/እፎይታ እና የአገልግሎት ማሻሻያ አደረጉ

Home Forums Semonegna Stories ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ እናት ባንክ እና ዳሸን ባንክ የብድር ወለድ ስረዛ/እፎይታ እና የአገልግሎት ማሻሻያ አደረጉ

#14525
Anonymous
Inactive

እናት ባንክ እና ዳሸን ባንክ የብድር ወለድ ስረዛ/እፎይታ እና የአገልግሎት ማሻሻያ አደረጉ

አዲስ አበባ (ፋና/ዋልታ) – እናት ባንክ ለተለያዩ የብድር ዘርፎች የብድር ወለድ ስረዛና የአገልግሎት ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ። ባንኩ በሰጠው መግለጫ ኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝነት በዓለምአቀፍ ደረጃ መሰራጨት ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በዓለም ማኅበረሰብ ላይ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን በማድረስ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሷል።

ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ  የንግድ እንቅስቃሴና በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት በማድረስ ላይ መሆኑን ነው የገለጸው። በመሆኑም እናት ባንክ ይህንን ጉዳይ በከፋተኛ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ተበዳሪዎቹ የብድር ወለድ ስረዛና የተለያዩ የአገልግሎት ማሻሻያዎችን ማድረጉን ነው ያሳወቀው።

የማሻሻያው ዋና ዓላማም እየተከሰተ ያለውን ችግር በጋራ ለመወጣት፣ በደንበኞች የንግድ እንቅሳቃሴ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ፣ የብድር አመላለስን የተሻለ ለማድረግና የሀገራችን ኢኮኖሚ ሚዛናዊነቱን ጠብቆ ማስኬድ በሚቻልበት አካሄድ ባንኩ የራሱን ድርሻ ለመወጣት ታሳቢ ያደረገ ነው ብሏል ።

በዚህም መሠረት የብድር ወለድና አገልግሎት ክፍያን አስመልክቶ በሆቴልና ቱሪዝም የሥራ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞች ከግንቦት እስከ ሀምሌ የብድር ወለድ እንዳይከፍሉ መሰረዙን ገልጿል።

ከዚያም ባለፈ የብደር ማራዘሚያ ላይ የሚከፈለዉ የአገልግሎት ዋጋ፣ የኦቨር ድራፍት እድሳት ላይ የሚከፈለዉ የአገልግሎት ዋጋ፣ ብድራቸውን ከሚጠበቅባቸው የመክፈያ ጊዜ ቀድመው ለሚከፋሉ ደንበኞች ይጣል የነበረው ቅጣት እንዲሁም ውዝፍ የብድር ዕዳን አዘግይቶ ሲከፈል የሚጣል ቅጣት ሙሉ ለሙሉ መነሳቱንም ነው ያብራራው።

በዓለምአቀፍ ባንኪንግ ዙሪያም እናት ባንክ የተለያዩ ማሻሻያዎች ማድረጉን ገልጾ፥ በዚህም አስመጪዎች እቃ ወደ ሀገር ለማስገባት ለከፈቱት ሌተር ኦፍ ክሬዲት (LC) አሁን በዓለም ላይ ከተፈጠረዉ ችግር አኳያ አስቀድመዉ ለማራዘሚያ የሚጠየቁት የአገልግሎት ክፍያ ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳ መደረጉን አንስቷል።

በተያያዘም ከኮቪድ-19 ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ዕቃዎች ለሚያሰመጡ አስመጪዎች ባንኩ ሃምሳ በመቶ (50%) የአገልግሎትና የኮሚሽን ክፍያ መቀነሱን ነው የገለጸው።

እናት ባንክ ማኅብራዊ ኃላፊነትን ለመወጣትና ኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ለብሔራዊ የኮቪድ-19 ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የብር 2 ሚሊዮን ብርድጋፍ ከማበርከቱም ባለፈ የባንኩ ሠራተኞችና የደንበኞች ደኅንነት ከወረርሽኙ ለመጠበቅ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆኑን ከባንኩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

በተመሳሳይ ዜና፥ ዳሸን ባንክ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እንደሚያሳድርባቸዉ በጥናት በተለዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቹ የወለድ ቅናሽ፣ የብድር እፎይታና ማራዘሚያ ጊዜ ለመስጠት ወስኗል።

የኮቪድ-19 ስርጭት በተለይ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ እያስከተለ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በመገንዘብ ቀደም ሲል በሌሎች ተጎጂ መስኮች ላይ እንዳደረገው ሁሉ በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ ደንበኞቹ እየደረሰባቸዉ ያለዉን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመጋራት መወሰኑን ለዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን (ዋልታ) በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በዚህም መሠረት በአበባና አትክልት፣ በሆቴልና ማስጎብኘት (ቱሪዝም)፣ በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራቾች፣ በፋብሪካ ምርት (manufacturing)፣ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት እና ትምህርት ተቋማት ዘርፎች ለተሰማሩና በሥራ ላይ ላሉ ደንበኞች እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር (እ.አ.አ.) ከሰኔ 1 ቀን 2020 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የወለድ ቅናሽ፣ የብድር እፎይታና ማራዘሚያ ጊዜ ሰጥቷል።

ባንኩ በአበባና አትክልት ዘርፍ ለተሰማሩ ተበዳሪዎች ቀደም ሲል በዝቅተኛ ወለድ እያበደረ የነበረ ቢሆንም፥ ዘርፉ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዞ የደረሰበትን የኢኮኖሚ ጉዳት ከግምት ዉስጥ በማስገባት ከ 1 በመቶ እስከ 2 በመቶ ተጨማሪ ቅናሽ አድርጓል።

ከፈረንጆቹ ሰኔ 1 ጀምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ደንበኞች 7 በመቶ የወለድ ምጣኔ ብቻ እንዲከፍሉ ወስኗል። በተጨማሪም ተበዳሪዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት የ6 ወር የብድር እፎይታና እስከ 5 ዓመት የሚቆይ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ ፈቅዷል።

በሆቴልና ማስጎብኘት ዘርፍ የተሰማሩ ተበዳሪዎች እ.አ.አ. ከሰኔ 1 ቀን 2020 ጀምሮ  የሚከፍሉት የወለድ ምጣኔ ወደ 7 በመቶ እንዲቀንስና ተበዳሪዎቹ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት የስድስት ወር የብድር እፎይታ ጊዜና እስከ 5 ዓመት ድረስ የሚቆይ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ እንያገኙ ለማድረግ ወስኗል።

በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራቾችም እንዲሁ እ.አ.አ. ከሰኔ 1 ቀን 2020 ጀምሮ  የወለድ ምጣኔ ቅናሹ ተጠቃሚ ሆነው ለሶስት ወራት 7 በመቶ ብቻ ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል። ከዚህም ሌላ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረትም የሦስት ወር የብድር መክፈያ ዕፎይታ ጊዜና እስከ ሦስት ዓመት ያለምንም የብድር ማራዘሚያ ክፍያ እንዲስተናገዱ መደረጉን ባንኩ በመግለጫው አትቷል ።

በፋብሪካ ምርት (manufacturing)፣ በሕዝብ ማመላለሻ አዉቶብስና በትምህርት ዘርፎች የተሰማሩ ተበዳሪዎችም ጭምር በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ከሰኔ 1 ጀምሮ ለ 6 ወር የብድር መክፈያ እፎይታ ጊዜና እስከ 3 ዓመት ድረስ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ ለመስጠት ወስኗል።

በተጨማሪ ዳሸን ባንክ ከላይ ለተጠቀሱትና በቫይረሱ ስርጭት ይበልጥ ለኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንሚዳረጉ በጥናት ለተለዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተጨማሪ የወለድ ምጣኔ ማስተካከያ እንዲደረግላቸዉም ወስኗል። ከ17.5 በመቶ እስከ 18 በመቶ ወለድ ይከፍሉ የነበሩና በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ ደንበኞች የ1.5 በመቶ ወለድ ቅናሽ ተደርጎላቸዉ 16 በመቶና 16.5 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል ብሏል። ከ14 በመቶ እስከ 17 በመቶ ወለድ ይከፍሉ የነበሩ ደግሞ የ1 በመቶ ቅናሽ ተደርጎላቸዉ ከ13 በመቶ እስከ 16 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ተወስኗል ።

ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም የብድር አገልግሎት ማሻሻያ ዉሳኔዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከታወጀበት ጊዜ በፊት በተበላሸ ብድር ዝርዝር ዉስጥ ይገኙ የነበሩ ብድሮችን እንደማይጨምርም ዳሸን ባንክ አስታውቋል።

ምኝጮች፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት/ ዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት

እናት ባንክ እና ዳሸን ባንክ የብድር ወለድ ስረዛ/እፎይታና የአገልግሎት ማሻሻያ አደረጉ