እናት ባንክ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ዕውቅና አገኘ

Home Forums Semonegna Stories ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ እናት ባንክ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ዕውቅና አገኘ

#13721
Anonymous
Inactive

እናት ባንክ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ዕውቅና አገኘ

አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– እናት ባንክ አክስዮን ማኅበር በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ዕውቅና አገኘ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ለእናት ባንክ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችለውን የዕውቅና ምስክር ወረቀት (certificate) በሰጠበት ወቅት ዋና ዳሬክተሩ ኢንጅነር ኡሌሮ ኡፒየው እንዳሉት፥ ባለስልጣኑ በምርት ገበያው ክፍያ የሚፈጽሙ ተቋማትን አፈጻጸማቸውን የመቆጣጠርና ዕውቅና የመስጠት ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው በመሆኑ እናት ባንክ ከምርት ገበያው ጋር የሚያደርገው የኤሌክትሮኒክስ የመረጃ ልውውጥ አስተማማኝ መሆኑ በመረጋገጡ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችል የዕውቅና ምስክር ወረቀት ሊያገኝ ችሏል። በዚህም ባለስልጣኑ ከባንኩ ጋር ለመሥራት የሚያስችለውን የሥራ ውል ስምምነት መፈራረሙን ተናግረዋል።

እናት ባንክ አክስዮን ማኅበር ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የተሰጠውን የዕውቅና ሰርተፍኬት በተረከበበት ወቅት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወንደወሰን ተሾመ እንዳሉት፥ የባንኩን የቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ለመሳተፍና የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ዕውቅና ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

እናት ባንክ በፌስቡክ ገጹ ላይ ያሰፈረው መግለጫ እንዲህ ይነበባል፦

እንኳን ደስ አለን…
እናት ባንክ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ኢ.ሲ.ኤክስ) የክፍያ ፈፃሚ ባንክ በመሆን የክፍያ ሥርዓቱን መጀመር የሚስችለውን የዕውቅና ሰርተፊኬት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ተቀበለ። በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምትገበያዩ ደንበኞቻችን በዚሁ አጋጣሚ አገልግሎቱን ማግኘት እንደምትችሉ ስናሳውቅ ደስታ ይሰማናል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሥራውን ሲጀምር ዕውቅና ተሰጥቷቸው በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ክፍያ ሲፈጸምባቸው የነበሩ ባንኮች ሁለት ብቻ የነበሩ ሲሆን፥ በሂደት ቁጥራቸው 15 መድረሱን አስታውሰው፥ እናት ባንክ ሲጨመር በድምሩ 16 መድረሳቸውን ተናግረዋል።

በገበያ ሥርዓቱ ውስጥ የክፍያ መፈጸሚያ ባንኮች ዋና ዋና ተግባራትና ኃላፊነቶች የምርት ገበያው አባላትና ደንበኞች በባንኮቹ ውስጥ ገንዘብ የሚሰባሰብበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ የምርት ገበያው የክፍያ መፈጸሚያ ተቋም በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ከግብይት በኋላ ገንዘብ ማዘዋወርና ስለ ወቅታዊ ደንበኞችና የአባላት የባንክ ሂሳብ ከባለስልጣኑ ጋር መረጃ መለዋወጥ መሆኑ ተገልጿል።

ከግል ባንኮች በርካታ ባለአክሲዮኖችን በመያዝ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው እናት ባንክ፥ በ2011 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 231.4 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ፣ የተጣራ ትርፉም 202 ሚሊዮን ብር መሆኑን አስታውቆ ነበር። ባንኩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች 45 ቅርንጫፎችን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ ይህንን የቅርንጫፍ ቁጥር በ2012 ሒሳብ ዓመት ወደ 70 ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን አምና ኅዳር ወር 2012 ዓ.ም. አስታውቆ ነበር።

ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

እናት ባንክ