ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

Home Forums Semonegna Stories ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

#15637
Semonegna
Keymaster

ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የመደበኛ እና የተከታታይ ትምህርት መርሀ ግብር የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎቹን ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመርቋል። የክብር እንግዳና አስመራቂ በመሆን በቪዲዮ ኮንፍረንስ መልዕክታቸዉን ለተመራቂዎች ያስተላለፉት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤ ክፍሌ፥ ተመራቂዎች ሀገራቸዉን ከድህነትና ኋላ-ቀርነት ለማላቀቅ በያዙት ሙያ ጠንክረዉ በመሥራት የበኩላቸዉን እንዲወጡ ጥሪያቸዉን በማስተላለፍ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸዉን ለተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸዉ አስተላልፈዋል ።

ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ጋር ተያይዞ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በተቀመጠዉ አቅጣጫ መሠረት፥  በበይነ-መረብ (online) አማካኝነት በማስተማር የድኅረ-ምረቃ ትምህርታቸዉን ሲከታተሉ ከነበሩ ከ45 ተማሪዎች ዉስጥ 38 ተመራቂዎች በኤሌክትሪካል ፓወር ኢንጂነሪንግ (electric power engineering)፣ በሕብረተሰብ ጤና ሳይንስ (public health)፣ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን (business administration)፣ በአካዉንቲንግ እና ፋይናንስ( accounting and finance) በዩኒቨርሲቲዉ ሴኔት ሌጅስሌሽን መሠረት የድኅረ ምረቃ  መስፈርቱን ስላሟሉ መመረቃቸዉን የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ በይፋ በማስታወቅ፤ ተመራቂዎች በተማሩበት መስክ የሰዎች ልጆችን ክብር ጠብቀዉ ሀገራቸዉን በቅንነት እንዲያገለግሉ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል ።

ፕሬዝዳንቱ አክለዉም ተመራቂዎች ወደ ብልጽግና ሀገሪቱን ለሚያሸጋግሩት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ለልዩ ልዩ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ በማስተላለፍ በራሳቸዉ እና በዩኒቨርሲቲዉ ማሕበረሰብ ስም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸዉን ለተመራቂዎች እና ለቤተሰቦቻቸዉ አስተላልፈዋል ።

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናዉ ካዉዛ፣፥ የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ እና የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት እና የዩኒቨርሲቲዉ የማኔጅመንትና የሴኔት አባላት የምረቃዉን ሥነ-ሥርዓት መታደማቸዉም ተመልክቷል።

በዕለቱ ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል ተሾመ ሊሬ በሰጠው አስተያየት፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በሀገሪቱ መከፋፈልን የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በመተው፥ በአንድነት ለእድገት መሰለፍ እንደሚባ አመልክቶ በሰለጠነበት ሙያ ሀገሩን ለማገልገል እንደሚጥርም ተናግሯል።

በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማሳካት በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል ያለው ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን (business administration) ሙያ የተመረቀው መስቀሉ ዳራ ነው። በሰለጠነበት ሙያ ራሱን፣ ብሎም ቤተሰቡንና ሀገሩን በመገልገል የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

ከተማሪዎች ምርቃት ዜና ሳንወጣ፥ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች እና የዲግሪ መርሀ-ግብሮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች በዚሁ ዕለት (ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም) በበይነ-መረብ (virtual) አስመርቋል። በዕለቱ በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelor)፣ በሁለተኛ ዲግሪ (master) እና በሦስተኛ ዲግሪ (doctorate) እና ስፔሻሊቲ ዲግሪ (specialty degree) ትምህርታቸውን ተከታትለው ያሰመረቃቸው ተማሪዎች ቁጠር በአጠቃላይ 4,290 እንደሆነ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ፕ/ር ክንደያ ገብረሕይወት ያገኘንው መረጃ ያመለክታል። በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ናቸው።

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ