የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተረከቡ

Home Forums Semonegna Stories ሰሞነኛ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮችና ክለቦችን የተመለከቱ ዜናዎች የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተረከቡ

#13455
Semonegna
Keymaster

የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተረከቡ

አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አስረከበ።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በርካታ ደጋፊዎችን በመያዝና የአዲስ አበባ ከተማ ተወካዮች በመሆን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ እየሳተፉ ለሚገኙት ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታውን ያስረከቡት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሁለቱ ክለቦች ከወራት በፊት የስታድየም እና ሁለገብ የስፖርት ማዕከል መገንቢያ የሚሆኑ የመሬት ይዞታዎችን እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር።

የሁለቱ ክለቦች የቦርድ የሥራ አመራሮች፣ የደጋፊ ማኅበር ተወካዮች፣ የክለቦቹ ደጋፊዎች እና የከተማ  የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በከንቲባው ጽሕፈት ቤት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ምክትል ከንቲባው ባደረጉት አጠር ያለ ንግግር ሁለቱን ክለቦች መደገፍ እና የከተማዋን አብዛኛውን ወጣቶች ፍላጎት መደገፍ ተገቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል። ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ እንደገለጹት፥ ሁለቱ ክለቦች የከተማዋ አምባሳደር ከመሆናቸውም ባለፈ በስፖርታዊ ጨዋነት እና በከተማዋ ሁለንተናዊ ሰላምን በማረጋገጥ፣ ወንድማማችነትን በመስበክ የበኩላቸው ሚና እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ሁለቱ ክለቦች በከተማዋ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጎለብት እና ወጣቱ ጊዜውን አልባሌ ስፍራ በመዋል ወይም አልባሌ ሥራ በመሥራት እንዳያሳልፍና እንዲቆጠብ ለሚያርጉት አዎንታዊ ተግባር የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ኢንጂነር ታከለ ተናግረዋል።

‘የከተማው አስተዳደር ከሁለቱ ክለቦች ጋር መሥራት ግዴታው ነው፤ የስታድየም ማስፋፊያ የመሬት ይዞታውን ከመስጠት ባሻገርም ክለቦቹ ለሚያከናውኗቸው ግንባታዎች በመዋዕለ አቅም ለመደገፍም አስተዳደሩ ዝግጁ ነው። ለክለቦቹ ከመሬት ይዞታው በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ስር ከሚገኙ የወጣት ማዕከላት መካከል ሁለት የወጣት ማዕከላትን ለሁለቱ ክለቦች በመስጠት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለቦች እንዲያስተዳድሯቸው በስጦታ ለመስጠት ዕቅድ አለው” ብለዋል ኢንጂነር ታከለ።

የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አመራሮችም በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ ለስታዲየም መገንቢያ የቦታ ይዞታ መረጋገጫ ከመስጠት ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረጉ በደጋፊዎቻቸው እና በእግር ኳስ ክለቦቹ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች