Home › Forums › Semonegna Stories › ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ › የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ራሱን የቻለ ስያሜና አርማ ሥራ ላይ አዋለ
ሲቢኢ ኑር (CBE Noor) ― የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ራሱን የቻለ ስያሜና አርማ ሥራ ላይ አዋለ
አዲስ አበባ (CBE) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ‘ሲቢኢ ኑር’ (CBE Noor) የተሠኘ ስያሜና አርማ ሥራ ላይ ማዋሉን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም በተዘጋጀ የማስተዋወቂያ መርሀ-ግብር ላይ ይፋ አድርገዋል።
ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በተጠናከረ መልኩ ለሕብረተሰቡ ለማዳረስ እየተገበረ ካለው መጠነ ሰፊ የማሻሻያ ተግባራት ጋር ተያይዞ አዲሱ ስያሜና አርማ ሥራ ላይ መዋሉን አቶ አቤ ሳኖ በመርሀ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።
አዲሱን ስያሜ እና አርማ በማዘጋጀት ሂደት በርካታ አማራጮች የቀረቡ መሆኑን አቶ አቤ አስታውሰው፥ ‘ኑር’ የሚለው አረብኛ ቃል ‘የብርሀን ፍንጣቂ’ የሚለውን ትርጓሜ የያዘ ሲሆን በአማርኛ መኖር የሚለውን መልካም ተስፋን የሚያመለክት በመሆኑ ለአገልግሎቱ ፈላጊዎች ተስፋን የሚሰጥ እንዲሁም ባንኩ ያለውን ራዕይ አመላካች ቃል ስለሆነ የባንኩ የሸሪዓ አማካሪዎችና የባንኩ ከፍተኛ የሥራ አመራር አስተያየት ሰጥተውበት ስያሜው መመረጡን ገልፀዋል።
ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ አቤ፥ በእምነታቸው ምክንያት ወለድ ለማይፈልጉ ደንበኞች አገልግሎቱን እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ባንኩ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን አክለው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. በ2011 ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱን ተከትሎ እ.ኤ.አ. ከህዳር 2013 ጀምሮ በተመረጡ 23 ቅርንጫፎች በተለየ መስኮት አገልግሎቱ መሰጠት መጀመሩን በንግግራቸው ያስታወሱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት፥ በአሁኑ ጊዜ በ1574 በላይ ቅርንጫፎች በመስኮት ደረጃ እንዲሁም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ ለመስጠት በተከፈቱ ከ53 በላይ ቅርንጫፎች አማካኝነት አገልግሎቱ በመሰጠት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
ባንኩ የሸሪዓ መርህን የሚከተሉ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን ለሕብረተሰቡ በማድረስ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ አቤ እ.ኤ.አ. ግንቦት 2020 መጨረሻ ድረስ በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 30.3 ቢሊዮን ብር መድረስ መቻሉን አመላክተዋል።
አቶ አቤ በገለፃቸው፥ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን የሚጠቀሙ ደንበኞች ብዛትን 2.7 ሚሊዮን መድረሱንና ባንኩ በተለያዩ የሥራ መስኮች ለተሰማሩ ደንበኞች 3 ቢሊዮን ብር የፋይናንስ አገልግሎት ማቅረቡን አስረድተዋል።
አቶ አቤ ባንኩ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት፣ ዕውቅናና አመኔታን ያተረፉ፣ በዘርፉ በቂ የትምህርት ዝግጅት፣ ጥልቅ ዕውቀትና የካበተ ልምድ ያላቸው አምስት አባላት ያሉት የሸሪዓ መማክርት ኮሚቴ እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ ሰይሟልም ነው ያሉት።
የሸሪዓ አማካሪዎችን መሰየሙ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን የሸሪዓ እሴትን በጠበቀ መልኩ ለመስጠት እንዳስቻለው የገለፁት አቶ አቤ የሸሪዓ መርህ መከበሩን የሚያረጋግጡ የውስጥ ቁጥጥር አሠራሮችን የመተግበር፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሂሳብ መዝገብ የመለየት እና መመሪያዎችን የማርቀቅ ተግባርም ማከናወኑን አክለው ገልፀዋል።
አቶ አቤ በንግግራቸው መጨረሻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ የተሻለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የማቅረብ ትልቅ አላማ እንዳለው እና በቀጣይ የቁጠባ እና የፋይናንስ አማራጮቹን በማስፋት፣ አዳዲስ አሠራሮችን በመተግበር እና ይበልጥ ዘመናዊ በማድረግ የባንክ አገልግሎቱን ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል አመቺና ተስማሚ በሆነ መልኩ ለማቅረብን ያለውን ቁርጠኝነት ገልፀው፥ ደንበኞችና መላው ሕብረተሰብ የወቅቱ የጤና ስጋት ከሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እራስንና ቤተሰብን በመጠበቅ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሆነዉ ሲቢኢ ኑር (CBE Noor) ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሸሪዓ መርህን በመከተል በሚሰጠው ‘ሲቢኢ ኑር’ (CBE Noor) በተሰኘው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት፦
-
- ከወለድ ነፃ የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት
- ለበይክ የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት (ለሀጅ እና ኡምራ ተጓዦች)
- ዘካ የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት (ዘካ ለሚያወጡ)
- የፋይናንስ አገልግሎት
- የዓለም አቀፍ ንግድ ድጋፍ
- የዳያስፖራ የቤት መግዣ/መሥሪያ ብድር እና
- ሌሎችንም አገልግሎቶች
ከ50 በላይ በሆኑ አገልግሎቱን ብቻ ለመሥጠት በተከፈቱ ቅርንጫፎች እና ከ1574 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎች በተለየ መስኮት ይሰጣል፡፡
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ