Home › Forums › Semonegna Stories › የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን አስመልክቶ የአቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና የጠ/ሚ አብይ አህመድ መልዕክት › አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ተያዙ፤ ኦነግ ሸኔ ከተባለው ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው።
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ተያዙ፤ ኦነግ ሸኔ ከተባለው ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ዋነኛ የተባሉ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሐምሌ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. አስታውቋል። ሦስተኛው ተጠርጣሪ ደግሞ እየተፈተለገ ነው ብሏል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክብርት አዳነች አቤቤ ሐምሌ 3 ቀን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አንደኛው ተጠርጣሪ ጥላሁን ያኒ የተባለ ሃጫሉ የተገደለበት ገላን የተባለዉ የአዲስ አበባ አካባቢ ነዋሪ እንደሆነ አስታዉቀዋል። በግድያው ተባባሪ የተባለዉ ሁለተኛ ተጠርጣሪ አብዲ ዓለማየሁም በቁጥጥር ስር መዋሉን ክብርት አዳነች ተናግረዋል።
ዋነኛ የተባለው ተጠርጣሪ ጥላሁን ያኒ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል መሣሪያውን የተኮሰው እሱ መሆኑን እና ተልዕኮውንም ከኦነግ ሸኔ መቀበሉን ማመኑ ተገልጿል። ጥላሁን ያኒ ለፖሊስ በሰጠው የእምነት ቃል ድርጊቱን የፈፀመው “ኦነግ ሸኔ” ከተባለው ክንፍ በተሰጠው ተልኮ መሆኑን መግለፁን፤ ተልኮውን የሰጡት ግለሰቦችም ሁለት መሆናቸውን አምኖ መቀበሉን ክብርት አዳነች አስረድተዋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ክብርት ሕግ አዳነች አቤቤ አያይዘው እንደገለጹትም ከበደ ገመቹ የተባለ ሦስተኛ ተጠርጣሪ እስካሁን በቁጥጥር ስር እንዳልዋለ እና በፖሊስ እየተፈለገ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኦነግ ሸኔ እያለ የሚጠራቸውና ራሱን “የኦሮሞ ነፃነት ጦር” ብለው በሎ የሚጠራው (ከዋናው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተከፍሎ ጫካ የቀረው) ቡድን ሀገር ወስጥ በተደጓጋሚ ጥቃት እያደረሰ ለንጹሃን ዜጎች ሞት፤ መቁሰል እና ለንብረት መጥፋት ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል። ለምሳሌ የካቲት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል የቡራዩ ከተማ ፖሊስ አዛዥን የገደለውና የካቲት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በአምቦ ከተማ ውስጥ ለድጋፍ ሰላማዊ ሠልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ ቦምብ በመወርወር የአካል ጉዳት ያደረሰው ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን መሆኑን የኦሮሚያ ክልል አስታውቆ ነበር።
በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም. ደግሞ የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ሠራተኛ የነበሩት አቶ አብዱላሂ ሳጆር ከአሶሳ ወደ ነቀምት ለሥራ ጉዳይ በመሄድ ላይ እያሉ ዛሬ በታጣቂዎች መገደላቸውን፤ ጥቃቱንም የፈጸመው ትጥቅ ያልፈታው ኦነግ ሸኔ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት አስታውቆ ነበር።
በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ ዞኖች በመንቀሳቀስ የሰላማዊ ሰዎችን ኖሮ እና እንቅስቃሴ የሚያውከውን የኦነግ ሸኔ ቡድን ድርጊት በማውገዝ የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብና ምስራቅ ወለጋ እንዲሁም ቡሎ በደሌ የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎች ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓም የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደው ነበር። በሰላማዊ ሰልፉም ላይ ነዋሪዎቹ ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን እንደማይወክላቸው፣ ይልቁንም የሕዝቡን ሰላም እያደፈረሰ መሆኑን ገልጸው ነበር።