ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጨማሪ አቅም የሚሆነው ሲዳማ ባንክ

Home Forums Semonegna Stories ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጨማሪ አቅም የሚሆነው ሲዳማ ባንክ

#55297
Semonegna
Keymaster

ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጨማሪ አቅም የሚሆነው ሲዳማ ባንክ

ቀደም ሲል “ሲዳማ ማይክሮፋይናንስ ተቋም” በመባል የሚታወቀው የብድርና ቁጠባ ተቋም “ሲዳማ ባንክ አክሲዮን ማኅበር” ሆኖ በባንክነት ለመደራጀት በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቷል።

አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – በአንድ ሀገር የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ሚና ካላቸው ባለድርሻ አካላት መካከል የፋይናንስ ተቋማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ተቋማት በሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ ካላቸው ሚና መካከል አንዱ ለኢንቨስትመንት ተግባራት የፋይናንስ ምንጭ መሆናቸው ነው።

የብድርና ቁጠባ ተቋማትን ጨምሮ ባንኮችና የመድን (insurance) ድርጅቶች በአነስተኛም ሆነ በትልልቅ የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ኩባንያዎች የሥራ ማከናወኛ የገንዘብ ምንጮች እና የንብረት ዋስትናዎች ሆነው ይሠራሉ። ውጤታማ የኢንቨስትመንት ተግባራት አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት የሚፈልግ በመሆኑ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ዓለም ያሉ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ከእነዚህ የገንዘብ ተቋማት ተሳትፎ ውጭ የሚታሰቡ አይደሉም።

ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት በበጎ የለወጡት የብድርና ቁጠባ ተቋማት ለአነስተኛና መካከለኛ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ውጤታማነት የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አይዘነጋም። በኢትዮጵያ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት ደንበኞች ቁጥር ከባንክ ደንበኞች ቁጥር በብዙ እጥፍ የላቀ ነው። ይህም ለአብዛኛው ሕዝብ የብድር አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት እነዚህ ተቋማት እንደሆኑ አመላካች ነው። አንጋፋ የሚባሉት የብድርና ቁጠባ ተቋማት የፋይናንስ አቅማቸው ከብዙ አዳዲስ ባንኮች ጭምር የተሻለ ነው። ዛሬ በትልቅ ስምና አቅም የሚታወቁ ብዙ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች መነሻቸው እነዚህ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብድርና ቁጠባ (የማይክሮፋይናንስ) ተቋማት አስተማማኝና ፍትሐዊ በሆነ አሠራር እንዲሠሩና ሕዝባዊ ተዓማኒነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ባንክ ሆነው ለመንቀሳቀስ የሚስችላቸው ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው የሚያስችል መመሪያ ከሁለት ዓመታት በፊት ማውጣቱ ይታወሳል። የብድርና ቁጠባ ተቋማቱ ያላቸውን ግዙፍ የደንበኛና የፋይናንስ አቅም ትልልቅ በሆኑና የተሻለ ትርፍ ሊያመጡ በሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲያውሉት የተዘጋጀው ይህ መመሪያ፤ ብዙ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩና ወደ መደበኛ የባንክ ሥራ እንዲገቡ እያስቻለ ነው።

በዚሁ መመሪያ መሠረት ቀደም ሲል “ሲዳማ ማይክሮፋይናንስ ተቋም” (Sidama Microfinance In­stitution) በመባል የሚታወቀው የብድርና ቁጠባ ተቋም “ሲዳማ ባንክ አክሲዮን ማኅበር” (Sidama Bank S.C.) ሆኖ በባንክነት ለመደራጀት በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቷል። ባንኩ 1,988 ባለአክሲዮኖች ያሉት ሲሆን፥ የተፈረመ ካፒታሉ አንድ ቢሊዮን 447 ሚሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ ከ583 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ገንዘብ የተከፈለ ካፒታል ነው።

የሲዳማ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ መንበር አቶ አብርሃም ማርሻሎ ባንኩ ከብሔራዊ ባንክ የሥራ ፈቃድ ማግኘቱን ተከትሎ በባንክ ዘርፍ ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያስችሉትን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እንዳከናወነ ይናገራሉ። አቶ አብርሃም በዚህ ረገድ ስለተከናወኑ ተግባራት ሲገልፁ “የባንኩ የውስጥ አሠራር የሚመራባቸውን መመሪያዎችን የማዘጋጀት፤ በብሔራዊ ባንክ መስፈርት መሠረት ውስጣዊ አደረጃጀቶችን የማሟላት፣ ከባንክ ዘርፉ ወቅታዊ እድገት ጋር የሚጣጣምና ባንኩን ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል የኮር ባንኪንግ ሶፍትዌር ግዢ ለመፈፀምና ባንኩ የሚመራበትን የአምስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ እቅድ ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት ተግባራትን የማጠናቀቅ፣ የሠራተኞችን አቅም በስልጠና የመገንባትና ተቋሙን በብቁ ሰው ኃይል የማጠናከር፣ በመጀመሪያ ዙር የተሟላ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ 10 ቅርንጫፎችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የማዘጋጀት እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ሂሳብን ጨምሮ የመጠባበቂያና የክፍያ ሂሳቦችን የመክፈት ተግባራት ተከናውነዋል” ሲሉ ያብራራሉ።

እንደ እርሳቸው ገለፃ፥ ባንኩ ባለፈው የበጀት ዓመት 142.3 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 177 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ ከእቅድ የበላይ የሆነ አፈፃፀም አስመዝግቧል። ይህም ካለፈው ዓመት የባንኩ አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ58 በመቶ ብልጫ እንዲኖረው አድርጓል። 48 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ 83 ሚሊዮን ብር በማትረፍ በባንኩ ታሪክ የተሻለ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል። በጠቅላላው 165 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በመሰብሰብም ከቀዳሚው ዓመት አፈፃፀም የ29 በመቶ እድገት አሳይቷል።

በብድር አቅርቦት ረገድ ደግሞ ባንኩ የሰጠውን ብድር በ86.6 ሚሊዮን ብር (በ29 በመቶ) በማሳደግ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠውን ብድር 462.5 ሚሊዮን ብር ማድረስ ችሏል። “የባንኩ የተበላሽ ብድር ምጣኔ 3.6 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ ምጣኔ አንፃር ሲታይ የሲዳማ ባንክ የተበላሸ የብድር ምጣኔ ጤናማ እንደሆነ አመላካች ነው” ይላሉ።

የሲዳማ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ሐጢያ ባንኩ ማይክሮፋይናንስ ተቋም በነበረበት ጊዜ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ሲያገለግል እንደነበር አስታውሰው፤ አገልግሎቱ አዋጭና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ ማዕቀፍ መሠረት ባንኩ ይህን አገልግሎቱን እንደሚቀጥልም ይናገራሉ። ባንኩ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የባንክ አገልግሎትን በገጠርና በከተማ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ መሆኑም ይህን አገልግሎቱን የማስቀጠል አካል ነው።

እርሳቸው እንደሚሉት፥ ተቋሙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ አድርጓል። ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ የባንኩን አገልግሎት የሚጠቀሙ በእርሻ፣ በሆቴልና በሌሎችም የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች አሉ። የተቋሙ በባንክ አሠራር መደራጀት ደግሞ ይህን አገልግሎት ለማስፋትና ለማዘመን ተጨማሪ ዕድልና አቅም ይፈጥራል።

ተቋሙ ወደ ባንክ ሲሸጋገር ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን አነስተኛ መነሻ ካፒታል ለማሟላት የአክስዮን ሽያጭ ያከናወነ ሲሆን፣ የተፈረሙ አክሲዮኖች ተከፍለው እንዲጠናቀቁ በማድረግ ከመደበኛ የባንክ ሥራዎች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የባንክ ሥራዎችን ለማከናወን እየሠራ ይገኛል። “ወደ ባንክ ሥራ ስንገባ የጠንካራ የፋይናንስ አቅም ባለቤት መሆን ያስፈልጋል፤ አለበለዚያ አቅም ካላቸው ከሌሎች ባንኮች ጋር ለመወዳዳር አስቸጋሪ ይሆናል። ለትልልቅ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ብድር ማቅረብም ሆነ በፋይናንስ ገበያው ላይ ተፎካካሪ መሆን አይቻልም” ይላሉ። ይህን ለማሳካትም የተፈረሙ አክሲዮኖች እንዲከፈሉና የኮርባንኪንግ (Core Banking) ሥራን ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ አቶ ታደሰ ያስረዳሉ።

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ መፈቀዱ መልካም ዕድሎችና ፈተናዎች እንደሚኖሩት የሚገልጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፥ መልካም ዕድሎችን መጠቀም ከተቻለ ፈተናዎቹን መቀነስና ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻል ነው የተናገሩት። የባንኮቹ መግባት የሀገር ውስጥ ባንኮች ውድድሩን ለመቋቋም ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ፣ በዚህም ተገልጋዩ ሕብረተሰብ ተጠቃሚ እንደሚሆን ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ባንኮች በካፒታል አቅምም ሆነ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ በሚጠበቅባቸውና ወቅቱ በሚፈልገው ልክ እየተንቀሳቀሱ አለመሆናቸውን ተናግረው፥ እነዚህን ክፍተቶች በማስተካከል ለውድድር መዘጋጀትና ለተገልጋዩ እርካታ መሥራት እንዳለባቸው ይመክራሉ። ከዚህ አንፃር ሲዳማ ባንክ ትልቅ አቅም ያላቸውን ባለሀብቶችን እንዲሁም ዳያስፖራውን ማሳተፍን ጨምሮ ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቅሞ በባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ማቀዱን አቶ ታደሰ ገልፀዋል።

ሲዳማ ባንክ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚኖረውን አዎንታዊ አስተዋፅኦ በተመለከተም አቶ ታደሰ ሲናገሩ፥ “ገበያው አዋጭ በመሆኑ ባንኩ ለኢንቨስትመንት ሥራዎች የፋይናንስ ምንጭ የመሆን አቅም አለው። ቀደም ሲልም የባንኩን አገልግሎት የሚጠቀሙ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች አሉ። ወደፊትም ባንኩ ይህን ተግባሩን በስፋት አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።

ሲዳማ ባንክ በማይክሮፋይናንስ ደረጃ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎችን ሲያገለግልና ለግለሰቦች እንዲሁም በአነስተኛና ጥቃቅን የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ማኅበራት የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። ብዙ ግለሰቦችና ማኅበራትም በተቋሙ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ሥራቸውን አሳድገው ዛሬ ትልልቅ ኢንቨስተሮች ለመሆን በቅተዋል።

የሲዳማ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ መስፍን ቂጤሳ እንደሚናገሩት፣ ተቋሙ በግል ንግድ ላይ ለተሰማሩ በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች ባለውለታ ነው። እርሳቸውም ከባንኩ ጋር ያላቸው ደንበኝነት የቆየ መሆኑን አስታውሰው፥ “ከባንኩ የወሰድነው ብድር በጣም ጠቅሞናል፤ ትርፋማ ሆነን እንድንሠራ አግዞናል” በማለት የባንኩ የብድር አገልግሎት ለውጤታማነታቸው አጋዥ እንደሆናቸው አስረድተዋል።

“አካባቢው በቡና ምርት የታወቀ ስለሆነ ባንኩም ለቡናው ዘርፍ ትልቅ ድጋፍ እያደረገ ነው” የሚሉት አቶ መስፍን፤ ለቡና አብቃዮችና ነጋዴዎች እንዲሁም ለተደራጁ ማኅበራትም የፋይናንስ ዕድል እንደሚያመቻች ይገልፃሉ። በቀጣይም ከባንኩ ጋር ያላቸውን ደንበኝነት አጠናክረው፥ በይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተፈጠረውን መልካም ዕድል በመጠቀም ቡናን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

“ከዚህ ቀደም የነበረው የባንኮች ተደራሽነት ውስን ስለነበር ብድር ለማግኘት ችግሮች ነበሩ። ሲዳማ ባንክ ለኢንቨስትመንት ሥራዎች ብድር በማቅረብ ጥሩ ዕድል ይፈጥራል፤ ለልማት በተለይ ለኢንቨስትመንት ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝ ባንክ ነው። ጥሩ ተስፋ ያለው ባንክም ነው” በማለት አቶ መስፍን ባንኩ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ስለሚኖረው አስተዋፅዖ ይናገራሉ።

በግል የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ አየለች ዱካሞም የባንኩ ደንበኛ ናቸው። “ቀደም ሲል የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ነበርኩ” የሚሉት ወይዘሮ አየለች፥ ተቋሙ ባንክ ከሆነ በኋላ ከባንኩ ብድር መውሰዴ ሥራዬን ሰፋ አድርጌ እንድሠራ አግዞኛል። ብዙ ሰው ከሲዳማ ባንክ ብድር እየወሰደ እየሠራ ነው፤ እየተለወጠም ነው። ከባንክ ጋር መሥራት ጥቅሙ ብዙ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ። ሲዳማ ባንክ በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ትልቅ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሰው፤ ከባንኩ ብድር ወስደው ከአነስተኛ የንግድ ሥራ ተነስተው ለትልቅ ደረጃ የበቁ ሰዎችን እንደሚያውቁም ነው የጠቀሱት። ወደፊትም ከባንኩ ጋር ብዙ ሥራዎችን የመሥራት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

ሲዳማ ባንክ Sidama Bank