Home › Forums › Semonegna Stories › ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ › ወልቂጤ ከተማ ውስጥ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው ባሮክ ሆቴል ተመርቆ ሥራ ጀመረ
ወልቂጤ ከተማ ውስጥ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው ባሮክ ሆቴል ተመርቆ ሥራ ጀመረ
የዞኑ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳዳር አስታውቋል።
ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – በወልቂጤ ከተማ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ባሮክ ሆቴል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የጉራጌ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ዘግቧል። ባሮክ ሆቴል ባዘጋጀው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች ተገኘተዋል።
በሆቴሉ ምረቃዉ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ለአንድ ከተማ እድገትና ለዉጥ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ሚና የጎላ መሆኑን በማስገንዘብ እንደተናገሩት፥ የዞኑ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ከመቼዉም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ አጽንኦት ተሰጥቶ እየተሠራ ነዉ።
በተለይም ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የኢንቨስትመንት ልማት ሥራዎችን ለማሳደግ እንደ ክፍተት የሚስተዋሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በተደረገዉ እንቅስቃሴ አሁን ላይ ባለሀብቶች በዞኑ ኢንቨስት እያደረጉ ይገኛል።
ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሂደቶችም መኖራቸዉንም አቶ መሀመድ ጠቁመዉ፥ በቀጣይ በዘላቂነት የዞኑ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ከባለሀብቶች ጋር እየተሠራ ያለዉን ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመግለጽ፤ ባለሀብቶች በዞኑ ባሉ የልማት አማራጮች እንዲሰማሩ አስፈላጊዉን ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ገብረመስቀል፥ በበኩላቸዉ ከዚህ ቀደም በከተማዉ ኢንቨስት ለማድረግ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ባለሀብቶች በማበረታታት ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሠራ ነዉ ብለዋል።
ከተማዉን ለማልማት የሚመጡ ባለሀብቶች አስፈላጊዉን ድጋፍ በማድረግ ከዞኑ መንግሥት ጋር በመሆን እየተሠራ መሆኑም በመጠቆም፤ በአሁኑ ሰዓት በሆቴል ዘርፍ የተሰማራዉን ባርክ ሆቴል አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ለሌሎች ባለሀብቶች የሚያበረታታ መሆኑም አቶ እንዳለ ጠቅሰዋል።
ሌሎች በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር በተገቢው መንገድ ተቀብሎ እንደሚያስተናግዳቸው በመግለጽ፥ “ኑ! ተደጋግፈን አብረን እንልማ” የሚል ጥሪ አሰተላልፈዋል።
የባሮክ ሆቴል ባለቤት አቶ አሰፋ በቀለ በበኩላቸው ሆቴሉ ተጠናቆ አገልግሎት መሰጠት በመጀመሩ ደሰተኛ መሆናቸዉም አስረድተዋል። ሆቴሉ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 50 ሚሊየን ብር እንደሚፈጅም ተናግረዉ በሆቴሉም ከ50 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርም አስረድተዋል ።
ባሮክ ሆቴል 39 አልጋዎችና አንድ የስብሰባ አዳራሽ ያካተተ መሆኑን የገለጹት የሆቴሉ ባለቤት አቶ አሰፋ፥ በአካባቢያቸዉ በማልማታቸዉ ደስተኛ መሆናቸዉ እንዲሁም ለተደረገላቸዉ ድጋፍ የከተማ አስተዳደሩና የዞኑ መንግሥት አመስግነዋል።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ