በግማሽ ቢሊዮን ብር የተገነባው ኃይሌ ሪዞርት አዳማ ተመረቀ

Home Forums Semonegna Stories ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ በግማሽ ቢሊዮን ብር የተገነባው ኃይሌ ሪዞርት አዳማ ተመረቀ

#15721
Semonegna
Keymaster

በግማሽ ቢሊዮን ብር የተገነባው ኃይሌ ሪዞርት አዳማ ተመረቀ
ተቃጥለው የነበሩ የሻሸመኔ እና ዝዋይ የኃይሌ ሪዞርቶችና ሆቴሎች ወደሥራ እንደሚመለሱም ተገለጸ

አዳማ (አዲስ ዘመን) – በአዳማ ከተማ በ500 ሚሊዮን ብር በሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ “ኃይሌ ሪዞርቶች እና ሆቴሎች” (Haile Resorts & Hotels) ኢንቨስትመንት የተገነባው ዘመናዊው ኃይሌ ሪዞርት አዳማ ተመረቀ።

ነሐሴ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የሆቴሉ ባለቤት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እንደገለጸው፥ አዲሱ ኃይሌ ሪዞርት አዳማ በአጠቃላይ 300 ለሚሆኑ ዜጎችና የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር ከፍተኛ ጥረት ባለው አገልግሎት ሕብረተሰቡን ለማገልገል የቆመ ነው ብሏል።

ለሀገር ጎብኚዎች በምቹ የቦታ አቀማመጡና ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ ሆቴሉን ተመራጭ እንደሚያደርገው የጠቆመው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ፥ ሪዞርቱ 106 የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች፣ ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁ የመመገቢያ አዳራሾች እንዲሁም ባሮችና ሌሎች ደረጃቸውን የጠበቁ የስብሰባ አዳራሾች እንዳሉትም ገልጿል።

“ኃይሌ ሪዞርቶች እና ሆቴሎች” ድርጅት ፈተናዎች ቢገጥሙትም በምሥራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ ለመሆን ተጨማሪ ሪዞርቶችን ለመክፈት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን የጠቆመው ሻለቃ ኃይሌ፥ በቅርቡም በአዲስ አበባ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በኮንሶ፣ በደብረ ብርሃን፣ በጎርጎራ እና በተቀሩት የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ሆቴሎችና ሪዞርቶችን ከፍቶ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሠራ መሆኑንም ተናግሯል።

በቅርቡ የቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸው የሻሸመኔ እና ዝዋይ የኃይሌ ሪዞርቶችና ሆቴሎች በቅርቡ ወደ ቀደመ ሥራቸው እንደሚመለሱም አትሌት ኃይሌ ተናግሯል። መንግሥት ለሪዞርቶቹ ከለላ ከመስጠት አልፎ ሥራ በማስጀመር ሂደቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲደርግም ጠይቋል።

ሪዞርቶችና ሆቴሎች ለአንድ ሀገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የላቀ ድርሻ እንዳላቸው የጠቀሰው ሻለቃ ኃይሌ፥ በእነዚህ መሠረተ ልማቶች ላይ አሉታዊ ክፍተት ሲያጋጥም መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ችግሩን ካልፈታው ኢንቨስትመንቱ ሊጎዳ እንደሚችል ጠቁሟል። ውድመት የደረሰባቸው ሁለቱ ሪዞርቶችና ሆቴሎችም የሕዝብ ገንዘብ በመሆናቸው በአስቸኳይ ወደሥራ እንደሚመለሱ አመላክቷል።

እንደሻለቃ አትሌት ኃይሌ፥ ገለፃ በተለይ ኃይሌ ሪዞርት ዝዋይ በፍጥነት ወደሥራ እንዲመለስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ በእነዚህ ሪዞርቶች እና ሆቴሎች ውስጥ ሲሠሩ የነበሩና በአሁኑ ወቅት ከሥራ ውጪ የሆኑ ሠራተኞችን ወደሥራ ለመመለስ ከመንግሥት እገዛ ይጠበቃልም ብሏል። የሆቴሎቹን መከፈት እውን ለማድረግ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋርም እየሠራ መሆኑን ተናግሯል።

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

ኃይሌ ሪዞርት አዳማ