Home › Forums › Semonegna Stories › ከመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ ሰሞነኛ ዜናዎችና መግለጫዎች › በአዲስ አበባ 25 ሺህ 491 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች በዕጣ ተላለፉ
በአዲስ አበባ 25 ሺህ 491 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች በዕጣ ተላለፉ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ14ኛ ዙር የ20/80 እና የ3ኛ ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ሐምሌ 1 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ተካሂዷል። በዚህም በድምሩ 25 ሺህ 491 የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ዕድለኞች ተለይተዋል።
በዕለቱ የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ አዲስ የመረጃ መያዣ እና ዕጣ ማውጫ የቴክኖሎጂ ሥርዓት በጥቅም ላይ መዋሉ ተገልጿል። ይህንን ተከትሎም የቤት ተጠቃሚዎች በአዲሱ ሲስተም በቀጥታ የወጣውን የአሸናፊዎችን ሙሉ መረጃ በ‘ኦንላይን’ ማረጋገጥ እንደሚችሉም ተገልጿል።
በማዘጋጃ ቤት አዳራሽ በተካሄደው የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች፣ ቤት ፈላጊዎች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለቤት ፈላጊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት በማስተላለፍ የዕጣ አወጣጥ መርሐ ግብሩን አስጀምረዋል።
በብዙ ፈተናዎች መካከል ውስጥ ሆነንም ቢሆን ግንባታቸው የተጓተቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ በቅተናል ነው ያሉት ከንቲባዋ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ “የከተማ አስተዳደራችን የከተማዋን የቤት ችግር ለመፋታት የተለያዩ የቤት ልማት አዳዲስ አማራጮችን በመዘርጋት የጀመረውን ርብርብ አጠናክሮ ይቀጥላል።” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልገዋል።
በተጨማሪም ከንቲባዋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ለረጅም ዓመታት በትዕግስት ገንዘባችሁን እየቆጠባችሁ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን በጉጉት የተጠባበቃችሁ የቤት ባለእድለኞች በሙሉ፤ እንኳን ደስ አላችሁ! የከተማ አስተዳደሩ የተረከበውን በርካታ ውስብስብ ችግሮች የነበሩባቸው ቤቶች እንዲሁም በተረከብነው ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ እዳ ተስፋ ባለመቁረጥ ይልቁንም በቁጭትና እልህ ሌት ተቀን በመረባረብ ከ21 ቢሊየን ብር በላይ በጀት በመጠቀም ለዛሬ ውጤት በመብቃታችን መላውን የከተማ በተለይም የቤቶች ልማትና የቤቶች ኮርፖሬሽን አመራሮችና ሰራተኞች፤ ኮንትራክተሮች፤የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፤ እና ሌሎች ለዚህ ስራ ስኬታማነት ሚናችሁን የተወጣችሁ በሙሉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ! የከተማዋን የቤት ችግር ለመፍታት የተለያዩ የቤት ልማት አዳዲስ አማራጮችን በመዘርጋት የጀመረውን ስራ አጠናክረን የምንቀጥል ሲሆን የከተማችን ነዋሪዎች እንደ ሁልጊውም ከጎናችን በመሆን ጉዞ ከጫፍ እንድናደርስ ጥሪዬን ማስተላለፍ እወዳለሁ!”
የከተማ አስተዳደሩ ለቤቶቹ መሠረታዊ ግንባታ የሚሆን ወደ 21 ቢሊዮን ብር በማውጣት ሥራውን ሲያከናውን መቆየቱንና ለበርካቶችም የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አክለዋል።
በዕጣው የተካተቱት በ1997 እና በ2005 ዓ.ም ተመዝግበው እስከ የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በአማካይ ለ60 ወራት የቆጠቡ የ20/80 እና 40 በመቶ እና ከዚያ በላይ የቆጠቡ የ40/60 ቤት ፈላጊዎች ናቸው ተብሏል።
በዚሁ መሠረት በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 27 ሺህ 195 እና በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 52 ሺህ 599 በአጠቃላይ 79 ሺህ 794 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ ሆነው በዕጣ እንዲካተቱ ተደርጓል ነው የተባለው።
በዕለቱ ዕለት ዕጣ የወጣባቸው ቤቶች የሚገኙባቸው ሳይቶችም በ40/60 መርሃ ግብር የተገነቡ ቤቶች አያት 2፣ ቦሌ በሻሌ እና ቡልቡላ ሎት 2 እንዲሁም በ20/80 መርሃ ግብር የተገነቡ ቤቶች በረከት፣ ቦሌ አራብሳ (ሳይት 3፣5፣6)፣ ወታደር፣ የካ ጣፎ፣ ጀሞ ጋራ፣ ጎሮ ሥላሴ፣ ፉሪ ሃና እና ፋኑኤል መሆናቸው ተገልጿል።
ሐምሌ 1 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የተላለፉ የጋራ መኖርያ ቤቶችን የተመለከቱ መረጃዎች፡-
- አሁናዊ የአንድ ካሬ የቤት ማስተላለፊያ ዋጋ፦ የሥራ አመራር ቦርዱ ታህሳስ 5 ቀን 2014 ዓ.ም በወሰነው መሠረት አሁን በሥራ ላይ ያለው አሁናዊ የአንድ ካሬ ማስተላለፊያ ዋጋ፡-
-
- 20/80 ቤት ልማት ፕሮግራም 7,997.17 ብር
- 40/60 ቤት ልማት ፕሮግራም 11,162.97 ብር ነው።
- ለዕጣ የቀረቡ ቤቶች የሚገኙባቸው ሳይቶች፣ የቤት ዓይነትና ብዛት በተመለከተ
- የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም — አያት 2፤ ቦሌ በሻሌ፤ ቡልቡላ ሎት 2 ሲሆኑ
- የ20/80 ቤት ልማት ፕሮግራም — በረከት፣ ቦሌ አራብሳ (ሳይት 3፣ 5፣ 6)፣ ወታደር፣ የካ ጣፎ፣ ጀሞ ጋራ፣ ጎሮ ስላሴ፣ ፉሪ ሃና እና ፋኑኤል
- በቤት ዓይነትና ብዛት ሲታይ
- በ20/80 የቤቱ ብዛት ስቱዲዮ ፡-3318 ባለአንድ መኝታ ፡- 7171 ባለሁለት መኝታ፤- 8159 በድምሩ 18648 ናቸው።
- በ40/60 ባለአንድ መኝታ፤- 1870 ባለሁለት መኝታ 4220 እና ባለሶስት መኝታ 753 በአጠቃላይ በድምሩ 25491 ቤቶች ናቸው።
- በዚህ ዙር ለዕጣ የቀረቡ ቤቶች የግንባታ አፈጻጸም ሁኔታ በጋራ መኖሪያና ንግድ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ በወጣ መመሪያ ቁጥር 3/2011 በሥራ አመራር ቦርድ በማስወሰን
- የ20/80 ከ96% በላይ፣ በ40/60 ከ87% በላይ የግንባታ አፈጻጸም ያላቸው ቤቶች ለዕጣ ቀርበዋል።
- የዚህ ዙር የዕጣ ተሳታፊዎች ሁኔታ (የቤት ፈላጊ ተመዝጋቢ ሁኔታ) የ20/80 ነባር ተመዝጋቢዎች (1997) በመመሪያው መሠረት ዝቅተኛውን የ60 ወራት ቁጠባ መጠን ያሟሉ ለእጣ ውድድር ብቁ የሆኑ እስከ የካቲት 21 2014 ዓ.ም ድረስ እና የ40/60 40% እና ከዚያ በላይ ቁጠባ ያላቸው እስከ የካቲት 21 2014 ዓ.ም የቆጠቡ ናቸው።
- በዕጣ ውስጥ የተካተቱት ተመዝጋቢዎችን በተመለከተ ከባንክ በተገኘው መረጃ መሠረት በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 27,195 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 52,599 በአጠቃላይ 79,794 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ ሆነው በዚህ ዙር ዕጣ እንዲካተቱ ተደርጓል። የዕጣ ተሳታፊዎች ሁኔታ ለዕጣ ከቀረቡ የቤት ዓይነቶች አኳያ በዝርዝር ሲታይ
- በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚደረጉ ማህበረሰብ ክፍሎችን በተመለከተ በመመሪያ ቁጥር 3/2011 በተገለጸው መሠረት ከ20/80 ነባር ተመዝጋቢዎች (1997) እና 40/60 ተመዝጋቢዎች ውስጥ
- መንግሥት ሠራተኞች 20 በመቶ፣
- ሴቶች 30 በመቶ፣
- አካል ጉዳተኞች 5 በመቶ እና አጠቃላይ ተመዝጋቢዎች 45 በመቶ በዕጣ የቤት ተጠቃሚዎች የሚለዩ ይሆናሉ።
- በከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክቱን ለመኖር ብቁ ለማድረግ ና ቤቶቹን ለማጠናቀቅ ከባንክ ቦንድ ብድር ብር 18.7 ቢሊዮን እና ለመሠረተ ልማት ግንባታ ከመደበኛ በጀት ብር 2.871 ቢሊዮን በድምሩ ብር 21.571 ቢሊዮን በሥራ ላይ ውሏል።
- በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 27,195 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 52,599 በአጠቃላይ 79,794 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ ሆነው በዚህ ዙር ዕጣ እንዲካተቱ ተደርጓል።
- በዚህ ዙር ከተላለፉ ቤቶች ውስጥ ከዚህ በፊት በማጣራት ሂደት የተገኙ ቤቶች ለልማት ተነሺ ሲስተናገዱበት ቆይተው የቀሩት ተካተዋል።
- የቤት ልማት ፕሮግራም ከጀመረበት አንስቶ በ17 ዓመታት ውስጥ ለህብረተሰቡ ማቅረብ የተቻለው 300 ሺህ ያህል ቤቶችን ብቻ ነው።
- የቤት ዕጣ አወጣጡ እንደ ቅደም ተከተል ሲሆን በ20/80 ፕሮግራም የ97 ተመዝጋቢዎች ቅድሚያ አግኝተዋል።
- የባለ ሦስት መኝታ ቤት በተመለከተ ፕሮግራሙ ባለፈው ዙር በቦርድ ውሳኔ በመዘጋቱ በቀጣይ በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱ ይሆናል።