Home › Forums › Semonegna Stories › ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት › አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ10,900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ10,900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
አዲስ አበባ/ ጎንደር (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና መርሃግብሮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 18፣ 2012 ቀን አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት በተገኙበት 5,642 ተማሪዎችን በቨርቹዋል አስመርቋል። ፕሬዝዳንቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) ምክንያት ምርቃቱን በተንጣለለ አዳራሽ ማከናወን ባይቻልም ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታችሁን በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ተመራቂዎች ቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት፣ ለሕዝብ እና ለሀገር ለውጥ ለማምጣት የሚተጉበት መሆኑን አመላክተው ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲከላከሉና ጥንቃቄ እንዳያጓድሉ እንዲሁም ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 2,270 የሚሆኑት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት (in-class and face-to-face education) ከመቋረጡ በፊት ጥናታቸውን ያቀረቡ ሲሆን 3,372 ተማሪዎች ደግሞ በትምህርት ዓመቱ መጨረሻ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።
ተመራቂዎቹ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትና ወደሀገራችን መግባት በፊት በገፅ-ለገፅ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች፣ እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት ከተቋረጠ በኃላ በኦንላይን (online) ያስተማራቸው የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ናቸው።
የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በዩኒቨርሲቲው 6 ኪሎ ግቢ ራስ መኮንን አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ በማስተላለፍ ተመራቂ ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው በሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መመቻቸቱ ተገልጿል።
ቀደም ብሎ ከሁለት ሳምንታት በፊት (ሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የሳይንስ አምባ መሰብሰቢያ አዳራሽ 5,315 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ቀደም ብለው ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለመመረቅ እየተጠባበቁ የነበሩ እንዲሁም ኤክስተርንሽፕ እና ፕሮጀክት ላይ የነበሩ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችና በኦንላይን ትምህርታቸውን የተከታተሉ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ይገኙበታል። ተመራቂዎቹ በየቤታቸው ሆነው የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በአማራ ቴሌቪዥን እንዲሳተፉ መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ገልፀዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተመራቂ ተማሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ እያለ የአገራችንና ሕዝባችንን ኑሮ የሚያሻሽሉ፣ ለወገን ፍቅር የሚሰጡ፣ ከድህነት የሚያላቅቁና ወደ ብልፅግና የሚያሻግሩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ