ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ 2891 ተማሪዎችን በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመረቀ

Home Forums Semonegna Stories ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ 2891 ተማሪዎችን በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመረቀ

#48766
Semonegna
Keymaster

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ 2891 ተማሪዎችን በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመረቀ

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በድህረ ምረቃ፣ በቅድመ ምረቃ እና ዲፕሎማ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን 2891 ተማሪዎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሐምሌ 10 ቀን፥ 2014 ዓ.ም በደማቅ ሥነ ሥርዓት አስመርቋል።

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ለዕለቱ ተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ባሰሙበት ንግግራቸው፥ ነባሩ እና አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በማታና በተከታታይ የዲፕሎማ፣ የዲግሪ እና የማስትሬት መርሐግብሮች ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀው፣ አስፈላጊውን የምረቃ መስፈርት አሟልተው በዕለቱ ለምረቃ የበቁት የ2014 ዓ.ም ተመራቂዎች 2891 መሆናቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህም ተመራቂዎች መካከል ወንድ 1409፣ ሴት ደግሞ 1482 ሲሆኑ፣ ይህም የሴት ተመራቂዎች ቁጥር ብልጫ ያለው መሆኑንና ዩኒቨርሲቲውም ለሴቶች ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ያሳያል ሲሉ ዶክተር ብርሃነመስቀል ተናግረዋል። በመጨረሻም ፕሬዝዳንቱ የዕለቱ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው አዲሱ ስያሜ፣ ተልዕኮ፣ ሎጎ እና ህብረ ዝማሬ በመመረቃቸው የተቋሙ ታሪክ አካል እንደሚያደርጋቸው አስገንዝበዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአዲስ መልክ እየተዋቀረ ያለው ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሀገሪቱን የትምህርት ችግሮች ለመቅረፍ በከፍተኛ ደረጃ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ፣ ይህንን ልዩ ተልዕኮውን ለመወጣት በሚያደርገው ጥረትም የትምህርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግለት ገልጸዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይም በትምህርታቸው ብልጫ ላሳዩ ተመራቂዎች የዋንጫ እና ሌሎች ሽልማቶች ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የሽግግር ወቅት ልዩ ልዩ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላትም የዕውቅና ምስክር ወረቀትና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

ከከፍተኛ ትምህርት ዜና ሳንወጣ፥ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጀርመን ስቱትጋርት ከተማ ውስጥከሚገኘው የሆኸንሃየም ዩኒቨርሲቲ (University of Hohenheim) ጋር የአጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ከዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝደንት እና ከዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ጋር በመሆን በጀርመን ሀገር በግብርናና በሥነ ምግብ ሳይንስ ቀዳሚ ከሆነው ከሆኸንሃየም ዩኒቨርሲቲ (University of Hohenheim) ጋር ላለፉት 8 ዓመታት ሲተገበር በነበረው የCLIFOOD ፕሮጀክት ወርክሾፕ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ ተመራማሪ በዶ/ር ስንታየሁ ይግረም አስተባባሪነት የሚመራው ይህ የCLIFOOD ፕሮጀክት በአየር ንብረት ለውጥና በምግብ ዋስትና ዙሪያ የሚሠራ ሲሆን ለ27 የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሦስትኛ ዲግሪና የድኅረ-ዶክትሬት (postdoctoral)  ትምህርት እንዲማሩና፣ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ላቦራቶሪዎች አቅም እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ሁለቱ አንጋፋ የትምህርትና ምርምር ተቋማት ግንኙነታቸውን ለማደስና በሌሎች ዘርፎችም አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ውል ተፈራርመዋል፡፡

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ