ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 419 ተማሪዎችን አስመረቀ

Home Forums Semonegna Stories ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 419 ተማሪዎችን አስመረቀ

#15349
Anonymous
Inactive

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 419 ተማሪዎችን አስመረቀ

ደሴ (ኢዜአ/ወ.ዩ.) – ወሎ ዩኒቨርሲቲ (ወ.ዩ.) በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በሁለተኛ ዲግሪ (Masters program) ያሰለጠናቸውን 350 ወንድ 69 ሴት በድምሩ 419 ተማሪዎችን ነሐሴ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ተማሪዎቹ ባሉበት ቦታ በኦንላይን (online) አስመረቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በምረቃው ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተናገሩት ተቋሙ በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ቢያስመርቁም ዘንድሮ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። በወቅታዊ የወረርሽኝ ምክንያት የመማር ማስተማሩ ሥራ ቢቋረጥም አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ተማሪዎችን በማስተማር የጀመሩትን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ መደረጉን አስታውቀዋል።

ተማሪዎች በመደበኛ፣ በማታ እና ሳምንታዊ መረሃ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን አመልክተው ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመረቁት መካከል 69 ሴቶች እንደሚገኙበት ዶ/ር አባተ ገልጸዋል።

ዶ/ር አባተ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ዓለም በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በተናወጠበት እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተከሄደበት ዓመት መመረቃቸው ታሪካዊና ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል። አያይዘውም፥ ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ዕቅዱን በአዲስ መልክ በማዋቀር ሀገር-በቀል እውቀቶችን ከምርምር ጋር በማቀናጀት ለውጥ በሚያስመዘግብ መልኩ ለመሥራት የተዘጋጀ በመሆኑ፥ ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በሚሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምረው አዳዲስ ምርምሮችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር የመሥራት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።

ተመራቂዎች በትምህርት ቆታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር ቀይረው ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከሉም የድርሻቸውን እንዲወጡ ዶ/ር አባተ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ነሐሴ 2 ቀን ያስመረቃቸው ተማሪዎች 12ኛ ዙር ሲሆኑ፥ በሕግ፣ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ፣ ማኅበራዊ ሳይንስ፣ የተፈጥሮ ቀመር፣ ቢዝነስ እና ምህንድስና የሰለጠኑ ናቸው።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ምሩቃን በቆይታቸው በቀሰሙት እውቀት በታማኝነት እኩል ሕብረተሰቡን ሊያገለግሉ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ የአንድነትና የሰላም እሴት ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍም በእውቀት ላይ የተመሠረተ እገዛ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አቶ አበበ አመልክተዋል።

ከተመራቂዎች መካከል መላኩ በላይ በሰጠው አስተያየት ምንም እንኳ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) በትምህርቱ ዘርፍ ጫና ቢያሳድርም፥ በቴክኖሎጂ ታግዘው በዕለቱ ለመመረቅ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በተማረበት ሕክምና እና ጤና ሳይንስም ሕብረተሰቡን በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ጠቁሞ፥ “በተለይ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የድርሻዬን እወጣለሁ” በማለት አክሏል።

ሌላዋ የፕሮጀክት አመራር (project management) ተመራቂ ገነት ኪሮስ በበኩሏ፥ በሙያዋ ሕዝቡን በማገልገል የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ተናግራለች። ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን የሚያስጨንቅበት ቢሆንም በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ታግዛ ለዚህ በመብቃቷ መደሰቷን ገልጻለች።

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ወሎ ዩኒቨርሲቲ (ወ.ዩ.)

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አስመረቀ