Home › Forums › Semonegna Stories › ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ › በኢትዮጵያ አዲስ የ200 ብር ኖት ይፋ ተደረገ፤ ነባሮቹ የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ኖቶችም ተቀይረዋል
በኢትዮጵያ አዲስ የ200 ብር ኖት ይፋ ተደረገ፤ ነባሮቹ የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ኖቶችም ተቀይረዋል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ዓይነቶች (የገንዘብ ኖቶች) ሙሉ ለሙሉ መለውጧን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ። በተጨማሪም አዲስ የ200 ብር ኖት መቅረቡንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። እንዲሁም የ5 ብር ገንዘብ ኖት ባለበት ቀጥሎ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሣንቲም እንደሚቀየርም ተገልጿል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፥ ነባሮቹን የገንዘብ ኖቶች በመተካት ለግብይት የሚሆን አዲስ የገንዘብ ኖት መጠቀም እንደምትጀምር መስከረም ሦስት ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ተደርጓል።
እነዚህ አዲስ የገንዘብ ኖቶች ለሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍን፣ ሙስናን እና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠርና ለመቀልበስ ይረዳሉ ብለዋል።
በአዲሶቹ የገንዘብ ኖቶች ላይ የተካተቱት ምስጢራዊ ምልክቶችና መለያዎች የገንዘብ ኖቶቹን አመሳስሎ ለማተም የሚደረጉ ሕገ ወጥ ጥረቶችንም ለማስቀረት እንደሚያግዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት (እንግሊዝኛ) እንዲህ ይነበባል፦
“Ethiopia today unveils new Birr notes for 10, 50 & 100 denominations, with introduction of a new Birr 200 note. The new notes will curb financing of illegal activities; corruption & contraband. Enhanced security features on the new notes will also cease counterfeit production.”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የገንዘብ (የብር) ኖቶች ለውጡን ተከትሎ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ዝግጅት ተደርጓል። በተለያዩ ጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያ የብር ኖቶች ክምችት መኖሩን የጠቀሱት ዶ/ር ይናገር፥ ለብር ለውጡ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል። ለዚህም ከጸጥታና የደህንነት አካላት ጋር በመነጋገር የመቆጣጠርና የማምከን ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል። በተለይ በድንበር አካባቢ የሚገኙ ባንኮችም በብር ኖቶች ለውጡ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እንዳይጋለጡ ጥብቅ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
ዶ/ር ይናገር የብር ኖቶች ቅያሬውን ለማከናወን ማንኛውም ግለሰብ የብር ኖቶቹን ራሱ በባንክ መቀየር ሲገባው፥ በሌላ ግለሰብ (በውክልና) የገንዘብ ኖት ለውጥ ማከናወን የማይችል መሆኑንም ተናግረዋል።
በ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን የብር ኖት መታተሙንና የመጠባበቂያ ክምችት እንዲኖር ተጨማሪ የብር ኖቶች እየታተሙ መሆኑን ዶ/ር ይናገር አመልክተዋል። ባለፉት ጥቂት ወራት አዳዲሶቹን የብር ኖቶች ወደ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የማጓጓዝ ሥራ መሠራቱንና አሮጌውን ገንዘብ መቀየር የሚያስችል በቂ ክምችት እንዳለ ገልጸዋል።
ካፒታል ኢትዮጵያ ሳምንታዊ ጋዜጣ በግንቦት ወር 2012 ዓም እንደዘገበው፥ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር (EBA) በነበሩት የብር ኖቶች ላይ ለውጥ እንዲደረግ መጠየቁን ገልጾ ነበር። ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ በብር ኖቶች መበላሸት ምክንያት ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ ከባንክ አገልግሎት ውጪ እንደሆነ በመጥቀስ፥ የሚታየውን የብር ኖቶች ከገበያ/ ከአገልግሎት ውጪ መሆን ችግር ለመቅረፍ የብር ኖቶችን መቀየር አስፈላጊነት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ (NBE) አስገንዝቦ ነበር።
ሌሎች ዜናዎች፦
- የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስገነባቸው ቤቶች አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ገለጸ
- ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ በ3 ቢሊዮን ብር ለሚያስገነባው ገርጂ የመኖሪያ መንደር ከተቋራጮች ጋር ስምምነት ተፈራረመ
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበረራ ትኬትን በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ዘዴ አማካኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ስምምነት አደረገ
- በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቱሪስት ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ሄሎ ታክሲ በተባለ ድርጅት አማካኝነት በይፋ ተመርቀው ሥራ ጀመሩ
- ግማሽ ቢሊዮን ብር የተገነባው ኃይሌ ሪዞርት አዳማ ተመረቀ፤ ተቃጥለው የነበሩ የሻሸመኔ እና ዝዋይ የኃይሌ ሪዞርቶችና ሆቴሎች ወደሥራ እንደሚመለሱም ተገለጸ