Home › Forums › Semonegna Stories › ከመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ ሰሞነኛ ዜናዎችና መግለጫዎች › ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሠጠ መግለጫ
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሠጠው መግለጫ
የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ ያልከፈለው ዋጋ የለም፡፡
የኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጽናትም ሲል ከመክፈል የሚሰስተው ዋጋ የለም፡፡ በመሆኑም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ መላው የክልሉ ሕዝብ በሀገር ሕልውና እና በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ላይ ያለው አቋም የጊዜ እና የሁኔታዎች መፈራረቅን ተከትሎ የማይለዋወጥ ጽኑ ሀቅ ስለመሆኑ በታሪክና በዜጎች ህሊና እንዳይፋቅ ሆኖ የተከተበ እውነታ ነው፡፡
ስለሆነም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልላችን ውስጥ የሚተለሙም ሆነ የሚፈጸሙ ማንኛውም ዓይነት ተግባራት ከዚህ ብሔራዊ መዳረሻ አንጻር የሚቃኙ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ማንኛውም ዓይነት ተቋማዊ መዋቅሮች የሚደራጁበትም አልፋ እና ኦሜጋዊ አመክንዮ ይኸው ነው፡፡
ከሰሞኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዋና አጀንዳ ከሆኑት ብሔራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውና በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን መልሶ የማደራጀት ተግባር ዋነኛ እና ብቸኛ ምክንያትም ዓላማው የኢትዮጵያን ሕልውናን የበለጠ የማበርታት የጋራ ግብን ያነገበ፣ በተሟላ ሀገራዊ ጥናት ላይ የተመሠረተ፣ የሕዝቦችን አንድነትንና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተተለመ እንዲሁም የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን እውን ለማድረግ በሁሉም ክልሎች ታምኖበት የተገባበት ወሳኝ ተግባር ነው።
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በክልሉ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የአማራ ክልልን ሕዝብ ሠላም እና ጸጥታን ለማስከበር በቅንነትና በቆራጥነት አገልግሏል፡፡
ከክልል አቀፍ ውለታው ባሻገር በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ ተጋርጦ የነበረን ከፍተኛ አደጋ ለመቀልበስ ሲል ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በመሆን በኢትዮጵያዊነት የላቀ ሥነ-ልቦናዊ ከፍታ ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት ከፍሎ ኢትዮጵያና አትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣን አደጋ በታማኝነት አምክኗል፡፡ ይህ አኩሪ ገድልና ውለታ ሁልጊዜም በታሪክና በትውልድ ልቦና ውስጥ እየተዘከረና ጽንቶ የሚኖር ታላቅ ተግባር ነው፡፡
ይህን መሰሉን ብሔራዊ ውለታ የበለጠ ለማጎልበትና ለማስፋት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አማራ ክልል ጨምሮ በሁሉም ክልላዊ መንግሥታት ውስጥ የሚገኙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን ያሰባሰበ በጥናት ላይ የተመሠረተ መልሶ የማደራጀት ሥራ በሁሉም ክልሎች በየደረጃው ካለው የፀጥታ አመራር፣ የመንግሥት አመራር፣ የልዩ ኃይል አመራርና አባላት፣ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት የተደረገበትና እየተደረገበት ያለ በሂደት ላይ የሚገኝ የጋራ ሀገራዊ ተግባር ነው።
ይህ የልዩ ኃይል ፖሊስ አደረጃጀቶችን መልሶ የማደረጃት ወይም የሪፎርም ሥራ በሁሉም የፌደራልና ክልላዊ መንግሥታት መሪዎች የጋራ ስምምነትና እንደ አንድ ሀገር አንድ ጠንካራ የፌደራልና የክልል የፀጥታ መዋቅር እንዲኖረን ታስቦ የተለያዩ አማራጮች ለልዩ ኃይል አባላቶቻችን ያቀረበ እና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በኩር ያደረገ ሀገር አቀፍ ታሪካዊ ተግባር ነው፡፡ ተግባሩም ለሁሉም ክልል የልዩ ኃይል አደረጃጀቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራልና የክልል መደበኛ ፖሊስ፣ የፌደራልና የክልል የማረሚያ ቤቶችን ፖሊስ አባል እንዲሆኑ አማራጮች ያቀረበ ብሔራዊ ተግባር ነው።
በቅርቡ በመንግሥት የተጀመረው የልዩ ኃይል ፖሊሶች የሪፎርም ተግባር እውነታዉ ከላይ በተቀመጡት አማራጮች ለሁሉም ክልሎች የልዩ ኃይል አባላት እንደየፍላጎታቸው በቀረቡት አማራጮች እንዲካተቱ ታሳቢ ያደረገ የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላትን የማጠናከር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኝ ብሔራዊ ተግባር ነው።
ይሁን እንጂ እውነታዉ ይሄ ሆኖ ሳለ አንዳንድ አካላት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን አየር ላይ እንዲበተን እየተደረገ ነው የሚል ከእውነት የራቀ ፍፁም በተሳሳተ መንገድ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የአማራን ሕዝብ ውስጣዊ ሰላምና አንድነት የሚያደፈርስ፣ የልዩ ኃይሉን አንድነት የሚረብሽ፣ ባልተገባ መንገድ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ። ድርጊቱም ሕዝባችንና የልዩ ኃይል አባሎቻችንን በተጨባጭ እየረበሸ ይገኛል።
ስለሆነም መላው የልዩ ኃይል አባላትና መላው የክልሉ ሕዝብ እንዲገነዘቡት የምንፈልገው መንግሥት ይህንን የመልሶ ማደራጀት ሥራ የሚከውነው የልዩ ኃይላችንን የሰው ኃይል ለበለጠ ፋይዳ ላለው ተልዕኮ መልሶ የማደራጀትና ብቁ የማድረግ ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ የማዘጋጀት ተግባር እንጅ በመልሶ ማደራጀቱ ሂደት ምንም ዓይነት የሚበተንም ኃይል የሌለ መሆኑን ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል።
ስለሆነም መላው የአማራ ሕዝብ በአንዳንድ አፍራሽ የሚዲያ ቡድኖች በሚነዛው አሉቧልታ ሳይታለልና ሳይደናገር እንደ አንድ ሕዝብ ያለውን ታሪኩን እና ሥነ ልቦናውን በሚመጥነው የኢትዮጵያዊነት ላዕላዊ ማእቀፍ ጥላ ስር በመሰባሰብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የማጽናት ሂደትን እንዲደግፍ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
የተከበራችሁ የክልላችን ሕዝቦች፥ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ መብትና ጥቅም የሚጋፋ የትኛውንም ዓይነት ውሳኔ ተግባራዊ እንደማያደርግ ሕዝባችን ሊያውቀው ይገባል።
የተከበራችሁ የክልላችን የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት እንዲሁም መላው ሕዝባችን፥ ለራሳቸው ጥቅምና ፖለቲካዊ ዓላማ ሲሉ ክልላችንን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ከሚሠሩ አካላት ራሳችሁን በመጠበቅ የክልላችን የፀጥታ ኃይል ብቁ ዘቦች ሁናችሁ ሰላምና ፀጥታን በማስጠበቅ ሥራችሁ እንድትተጉ እያሳሰብን የተጀመረውን ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ሥራ መላው ሕዝባችንንና ልዩ ኃይላችንን በማወያየት እና በመተማመን የሚፈፀም በመሆኑ በየካምፓችሁ ወይም በየተመደባችሁበት የሥራ ቦታ ተረጋግታችሁ በትግስት እንድትጠብቁ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
መጋቢት 29/2015 ዓም
ባሕር ዳር፥ ኢትዮጵያ
ምንጭ፦ የክልሉ ሕዝብ ግንኙነት