Home › Forums › Semonegna Stories › ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ › የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ከ919 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተገለፀ
የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ
ከ919 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለፀ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ባልደረሰባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት መርሀ ግብርን (National Electrification Program) በመተግበር በስፋት እየሠራ ይገኛል።
መርሀ ግብሩ እስካሁን ብዛት ያላቸው የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፤ በቀጣይም ፍትሃዊ ተደራሽነትን ባማከለ መልኩ ሰፊ ሥራዎች እንደሚያከናውን ተገልጷል።
የሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ሁሴን መሀመድ እንደገለፁት፥ ፅ/ቤቱ ከተመሠረተበት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል ባልደረሰባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ኃይል የማዳረስ ሥራ ሲሠራ መቆየቱንና ከ2010 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም መባቻ ድረስ ከ63 ሺህ 900 በላይ አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ኃይል በማዳረስ የደንበኞች ቁጥር ለመጨመር ቁልፍ ሚና ያለው ይህ መርሀ ግብር፥ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ6 ሺህ 759 በላይ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን ኃላፊው ገልፀዋል። ከ1998 ዓ.ም በፊት ተጠቃሚ የነበሩት የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን ብዛት ሲታይ ግን ከ667 የማያላፉ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ኃላፊው አክለውም፥ ፕሮግራሙ በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት በአዲስና በመልሶ ግንባታ 405 የገጠር ከተሞችና መንደሮች በማገናኘት ከ32 ሺህ በላይ ደንበኞችን ኃይል ለማዳረስ አቅዶ፤ 325 የሚሆኑት የገጠር ከተሞችና መንደሮች በማገናኘት 25 ሺህ 232 አዳዲስ ደንበኞች የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ለዚህም ከመንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ 919 ሚሊዮን 277 ሺህ 349 ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ለዕቃ አቅርቦት ግዥ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የኃይል ማሠራጫ ዕቃዎች በተለይ የትራንስፎርመር እና የኮንዳክተር እጥረት በዋናነት የመርሀ ግብሩ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ተጠቅሷል።
በመጨረሻም በያዝነው በጀት ዓመት ፕሮግራሙ 450 የገጠር ከተሞችና መንደሮች በማገናኘት 54 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እየሠራ መሆኑን አቶ ሁሴን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመላው ሀገሪቱ ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማሳደግ በ”ብርሃን ለሁሉ” (Lighting to All) መርሀ ግብር እ.ኤ.አ በ2025 ከዋናው የኃይል ግሪድ 65 በመቶ እና ከግሪድ ውጪ በተለያዩ የኃይል አማራጮች 35 በመቶ የሚሆነውን ሕብረተስብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስትራቴጂ ቀይሶ በመንቀሳቀስ መሆኑ ይታወቃል።
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዜና ሳንወጣ፥ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ከ2.8 ቢሊዮን ኪሎ ዋትስ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነት መቀነስ መቻሉን አስታውቋል። ተቋሙ እንዳለው በ2012 በጀት ዓመት ቴክኒካልና ቴክኒካል ያልሆነ የኃይል ብክነትን ለመከላከል ባደረገው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ 2,823,055,758.11 ኪሎ ዋትስ የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነት ወይም በገንዘብ 1,113,863,407.24 ብር ከብክነት ማዳን ችሏል።
ተቋሙ የኃይል ብክነቱን መቀነስ የቻለው የኤሌክትሪክ ስርቆትን በመከላከል፣ በትክክል የማይሠሩ፣ የተቃጠሉ፤ የቆሙ ቆጣሪዎች በወቅቱ እንዲቀየሩ በማድረግ፣ የታሪፍ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውን ደንበኞች የታሪፍ ለውጥ በማድረግ፣ ቢል የማይወጣላቸው ደንበኞችን ወደ ሲስተም እንደገቡ በማድረግ፣ ያልተፈቀደ የኃይል ጭነት በመቆጣጠር፣ ከቆጣሪው ልኬት ውጪ የተገጠመ አውቶማቲክ ፊዩዝን (automatic fuse) በመቀየር፣ የዝቅተኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ደንበኞች የተገኘ የማባዣ ስህተት በማስተካከል፣ የገቢ ደረሰኝ የሌላቸው እንዲኖራቸው በማድረግ እና የመሳሰሉ ቴክኒካል ያልሆነ የኃይል ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት ነው።
ተቋሙ ቴክኒካል የኃይል ብክነትን ለመቀነስም የ2000 Common Meter Reading Instrument (CMRI) በተስተካከለው software design መጫን፣ የደንበኞች ቆጣሪ ቅያሪ ሥራ፣ የ383 የደንበኞችን መረጃ ወደ አዱሱ ሲሰተም (SAP) ማዛወርና የመሳሰሉ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን በ2013 በጀት ዓመትም ሊከሰቱ የሚችሉ ቴክኒካልና ቴክኒካል ያልሆኑ የኃይል ብክነቶችን ለመቀነስ ሰፊ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሰቀሰ በይገኛል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት