የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስገነባቸው ቤቶች አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ገለጸ

Home Forums Semonegna Stories ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስገነባቸው ቤቶች አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ገለጸ

#15304
Semonegna
Keymaster

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስገነባቸው ቤቶች አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን)፦ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ አምስት ሳይቶች የሚያካሂደው የቤቶች ግንባታ አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።

የኮርፖሬሽኑ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክብሮም ገብረመድኅን በተለይ ለአዲስ ዘመን ዕለታዊ ጋዜጣ እንዳስታወቁት፥ የቤቶቹ ግንባታ በአቧሬ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ አካባቢ፣ በመካኒሳ፣ ብሪቲሽ ካውንስልና ቦሌ ላይ እየተካሄደ ነው፤ ህንፃዎቹም እስከ 10 ፎቅ የሚደርሱና ለቅይጥ አገልግሎት (ለንግድ እና ለመኖሪያ) በሚል እየተገነቡ ያሉ ናቸው።

ግንባታዎቹ እንደየቦታው ስፋት የተለያዩ ዓይነቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ መንታ /twin/ ተደርገው የሚገነቡም እንዳሉ ጠቁመዋል። የመካኒሳው፣ የጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ አካባቢውና የብሪቲሽ ካውንስሉ ፕሮጀክቶች ባለሁለት መንታ ግዙፍ ህንፃዎች መሆናቸውን አስታውቀው፥ የቦሌው አንድ ግዙፍ ህንፃ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ የግንኙነት ኃላፊው ገለጻ፥ አንዳንዶቹ ህንፃዎች ባለሰባት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ባለ 10 ወለሎች ሲሆኑ፥ እየተገነቡ ያሉት በከተማ አስተዳደሩ የየአካባቢው ፕላን መሠረት ነው። በአጠቃላይ ግን የንግድ ተቋማቱ ብዛት በካሬ ሆኖ ወደፊት የሚለይ ሲሆን፥ የተቀሩት ግን ለቀቅ ባለ /luxurious/ በሆነ መልኩ ወደ አንድ ሺ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቤቶች እየተገነቡ ነው።

በግንባታው ላይ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተደጋጋሚ ጉብኝት በማድረግ ክትትል እንደሚደረግ ጠቅሰው፥ የተቋሙ ማኔጅመንት ካውንስል /የስራ አመራር ኮሚቴው/፣ እንዲሁም የተቋሙ ቦርድ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የፓርላማው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴም ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረው፥ ሠራተኛው፣ ተቋራጮቹ፣ መሀንዲሶቹ እንዲሁ ሁሉም በጋራ በመረዳዳት መንፈስ እየተሠራ በመሆኑ አፈጻጸሙ ስኬታማ መሆን መቻሉን ተናግረዋል። የፓርላማ አባላት ፕሮጀክቶቹን እንደጎበኙትና በአፈጻጸሙም አድናቆቱ እንዳላቸው መግለጻቸውንም የግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል።

“በቀጣይ ደግሞ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩ ይጠበቃል” ያሉት የግንኙነት ኃላፊው፥ የአሁኖቹ ፕሮጀክቶች ልምድ የሚቀሰምባቸው፣ አቅም እና ካፒታል የሚሰባሰብባቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ኮርፖሬሽኑ ማኅበራዊ ኃላፊነቱንም እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለንግዱ ማኅበረሰብ 50 በመቶ የኪራይ ቅናሽ ማድረጉን አስታውሰዋል። ባለፉት አራት ወራት በኮቪድ-19 ምክንያት በየወሩ ከኪራይ መሰብሰብ የሚገባውን 60 ሚሊየን ብር ከተከራዮች አለመሰብሰቡን ተናግረዋል።

የግንኙነት ኃላፊው በዚህ ፈተና ውስጥ እንዴት ከማኅበረሰቡ ጎን መቆም አለብኝ ብሎ በማሰብ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው በአዲስ አበባና በድሬዳዋ የሚገኙ 18,153 የመኖሪያና የድርጅት ቤቶች ተከራይ ደንበኞች የኮቪድ-19 የኮረና ቫይረስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የፈጠረባቸውን ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ በመረዳት ኪራይ የመቀነስ ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውሰዋል። በኪራይ ዋጋ ቅነሳም በየወሩ ከአጠቃላይ ገቢው 50 በመቶውን እያጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ በወር ከሚያገኘው 120 ሚሊየን ብር ገቢ እየሰበሰበ ያለው 60 ሚሊየን ብር ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ከገባ አንስቶ ባሉት አራት ወራት ኮርፖሬሽኑ ማግኘት ከነበረበት 480 ሚሊየን ብር የሰብሰበው ግማሹን ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል። ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ብሔራዊ ንቅናቄ ሲቋቋም ድጋፍ ካደረጉት የመጀመሪያ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፥ በወቅቱም 10 ሚሊየን ብር መስጠቱንም ጠቅሰዋል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባና በድሬዳዋ 18,153 ቤቶች እንዳሉት ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከእነዚህ መካከል ወደ 6ሺ 500 አካባቢ የንግድና የድርጅት ሲሆኑ፥ የተቀሩት ደግሞ የመኖሪያ ቤቶች ናቸው። ኮርፖሬሽኑ በደንብ ቁጥር 398/2009 የተለያዩ ተግባርና ኃላፊነቶች ተሰጥተዉት በራሱ ገቢ እንዲተዳደር የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን Federal Housing Corporation