ጥቁር ገበያ ላይ የአንድ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ90 ብር በላይ ደርሷል

Home Forums Semonegna Stories ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ ጥቁር ገበያ ላይ የአንድ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ90 ብር በላይ ደርሷል

#50485
Semonegna
Keymaster

ጥቁር ገበያ ላይ የአንድ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ90 ብር በላይ ደርሷል

አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቁር ገበያ ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ90 ብር በላይ መድረሱን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ዋና የዶላር ምንጭ የሆነውን ሕገ ወጥ የሃዋላ እንቅስቃሴ ነው ያለው ብሄራዊ ባንክ ዝውውሩ የሚከናወንባቸውን የሒሳብ ቁጥሮችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ባላገሩ ቴሌቭዥን ዘግቧል።

ከብር አንፃር የዶላር ዋጋ ዕለት ከዕለት እየጨመረ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ መደበኛ ባልሆነው የሃዋላ ምንዛሬ (ጥቁር ገበያ) ባለፉት ጥቂት ቀናት ዶላር ከፍተኛ ጭማሬ ማሳየቱን የባላገሩ ዘጋቢ ባደረገው ቅኝት ተረድቷል።

ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ አንድ ዶላር ጥቁር ገበያ ላይ ከ85 እስከ 87 ብር ድረስ በመመንዘር ላይ እንደሚገኝ እና በተለያዩ ሁኔታዎች ይህ ዋጋ እስከ 92 ብር ድረስ ከፍ እንደሚል ባላገሩ ቴሌቪዥን ብሔራዊ ቴያትር አካባቢ ከሚገኙት የጥቁር ገበያ መንዛሪዎች መረዳት ችሏል፡፡

በመደበኛው የምንዛሬ ገበያ አንድ ዶላር በ53 ብር አከባቢ እየተመነዘረ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድረ ገጽ ያሳያል። በአሁኑ ጊዜ በጥቁር ገበያ እና መደበኛ ገበያው መካከል ያለው ልዩነት ከ26 ብር በላይ ሆኗል።

የዶላር ዋጋ መጨመሩ በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው ዋጋ ንረት ላይ የራሱን የሆነ ጫና የሚያሳድር መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ዶ/ር አጥላው ዓለሙ ያነሳሉ፡፡ የውጭ ምንዛሬ ጥቁር ገበያ ላይ በዚህ ያህል መናር የሀገሪቱ ወጪ እና ገቢ ንግድ አለመመጣጠን መሠረታዊ ምክንያት መሆኑን ዶ/ር አጥላው ገልጸዋል፡፡

ሀገሪቱ በቂ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ባለመቻሏ ነጋዴው ማኅበረሰብ በቂ ዶላር በባንክ ቤቶች በኩል ማግኘት አለመቻሉን ዶ/ር አጥላው አንስተዋል፡፡ በዚህም ምርት ከውጭ የሚያስገቡ ነጋዴዎች የጥቁር ገበያውን እንደ ዋና የውጭ ምንዛሬ ምንጭነት እየተጠቀሙበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱን እንዳሳደገው አብራርተዋል፡፡

የጥቁር ገበያውን ለመቆጣጠር በዋናነት የባንኮችን የዶላር ክምችት ማሳደግ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ያነሱ ሲሆን፤ ለዚህም ምርትን በማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፍቃዱ ድጋፌ ከሰሞኑ ሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል ዳግም ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በተለይም ጥቁር ገበያ ላይ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

ሩሲያ እና ዩክሬን የገቡበትን ጦርነት ተከትሎ የዓለም ምርት ዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት መጨመሩንና ይህን ተከትሎ በጥቁር ገበያ የምንዛሬ ዋጋ እድገት ማሳየቱን ምክትል ገዥው አብራርተዋል፡፡

በዓለም ገበያ ላይ የዩሮ ዋጋ እየቀነሰ መምጣቱን ያነሱት አቶ ፍቃዱ፥ በተቃራኒው የአሜሪካ ዶላር ፍላጎቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ዋና የዶላር ምንጭ የሆነውን ሕገ ወጥ የሃዋላ መሆኑን ያነሱት አቶ ፍቃዱ፥ ባንኩ የዚህ እንቅስቃሴ ማካሄጃ የሒሳብ ቁጥሮችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፤ በቅርቡም በዚህ እንቅስቃሴ ላይ ሲሳተፉ በተገኙ የሒሳብ ቁጥሮች ላይ እርምጀ እንደሚወሰድ ጨምረው አንስተዋል፡፡

በመደበኛ የዶላር ምንዛሬ ገበያውም ላይም ቢሆን ባለፉት ስድስት ወራት በአንድ ዶላር የምንዛሬ ዋጋ ላይ የ2 ብር ከ60 ሳንቲም ጭማሪ እንደተደረገበት ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ምንጭ፦ ባላገሩ ቴሌቭዥን