-
Search Results
-
ባህር ዳር (አብመድ)፦ ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ሹመታቸው የጸደቀላቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለምክር ቤት አባላትና ለሕዝቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንደ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንትነት ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ንግግር ያደረጉት አቶ ተመስገን በመልዕክታቸው የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ለግጭት ምክንያት ሳይሆኑ በሕግ እንዲመለሱ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢኮኖሚ ዕድገቱም ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ለኢንቨስትመንት ዕድገትም አትኩሮት እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል።
አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስከትለውም “የሕግ የበላይነትን ማስፈንም ለነገ የምንለው ጉዳይ አይሆንም” ብለዋል ለአማራ ክልል ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት።
ለመሆኑ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ ማን ናቸው?
አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ብቸና ወረዳ ወይራ ቀበሌ ነው የተወለዱት። ከታችኛው የመንግሥት መዋቅር እስከ ፌዴራል ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎችም አገልግለዋል።
በትምህርት ደረጃ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ ቀያቸው በጎተራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፤ የመለስተኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በብቸና በሚገኘው የበላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቁት። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከማይክሮሊንክ ኮሌጅ በሶፍትዌር ዘርፍ እና የሁለተኛ ዲግሪቸያውን ደግሞ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ (University of Greenwich) በለውጥ አመራርና አስተዳደር ተከታትለዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ በ አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና በፌደራል መንግስት ደረጃ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።
በአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የፀጥታ እና ቴክኖሎጂ አማካሪ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ሠርተዋል።
ፌደራል መንግስት ደረጃ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (Information Network Security Agency) ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮ-ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በመሆንም አገልግለዋል።
አቶ ተመስገን የሀገር መከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ፣ የኤሌክትሮኒክስ እና የቴክኒካል መረጃ መምሪያ ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል። በመከላከያ ሠራዊት ውስጥም እስከ ሻለቃነት ማዕረግ ደርሰዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ መሥራች ከመሆን ባለፈ በዚሁ መሥሪያ ቤት ከመምሪያ ኃላፊነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነትም አገልግለዋል። እስከ ዛሬ ድረስ ደግሞ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ምንጭ፦ የአማራ መገናኛ ብዙሀን ድርጅት (አብመድ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አጣዬ፣ ማጀቴ እና ካራቆሬ በሚባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች እንደተናገሩት፥ ጥቃቱን እያደረሱ ያሉት ኃይሎች በሚገባ ዝግጅት ያደረጉ፣ በቁጥር ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ከ አካባቢዎች የሕግ አስከባሪ ፖሊሶች ቁጥር ጋር ሲነጻጸሩ እጅጉን የበዙ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ደብረ ብርሃን (ሰሞነኛ)– በወገኖቻችን ላይ በታጠቁ ኃይሎች እየደረሰ ያለውን ጥፋት የፌዴራል እና የክልሉ መንግስት በአስቸኳይ ሊያስቆሙ ይገባል፤ ሲሉ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ።
በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች በአጣዬ፣ በካራቆሪ፣ በማጀቴና አካባቢው በሚኖሩ ሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያና ሰቆቃ መንግስት በአፋጣኝ ሊያስቆም ይገባዋል በማለት ድምፃቸውን በሰላማዊ ሰልፍ በመግለፅ ላይ ናቸው።
አጣዬ፣ ማጀቴ እና ካራቆሬ በሚባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች እንደተናገሩት፥ ጥቃቱን እያደረሱ ያሉት ኃይሎች በሚገባ ዝግጅት ያደረጉ፣ በቁጥር ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ከ አካባቢዎች የሕግ አስከባሪ ፖሊሶች ቁጥር ጋር ሲነጻጸሩ እጅጉን የበዙ እንደሆኑ ተናግረዋል።
በታጠቁ ኃይሎች የመቁስል አደጋ የደረሰባቸው መገኖቻችን ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ የተዘጉ መንገዶችን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጣልቃ ገብቶ እንዲያስከፍትም ጠይቀዋል።
ሰልፉ እስካሁን በሰላማዊ አግባብ ተካሄዶ የተጠናቀቀ ሲሆን በአጣዬ ከተማ በህብረተሰቡ ላይ ጥቃት እያደረሰ የሚገኘው ኦነግ መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን እምቢያለ ገልጸው ችግሩ ከዞኑ አቅም በላይ በመሆኑ መከላከያ ሠራዊት ገብቶ አካባቢውን እንዲያረጋጋ ድጋፍ የተጠየቀ ቢሆንም በወቅቱና በፍጥነት ባለመግባቱና ከገባም በኋላ እርምጃ እንድወስድ አልታዘዝኩም በማለቱ ችግሩ እየተባባሰ መሄዱን ተናግረዋል።
በአጣዬ ከተማ የኦነግ (የኦሮሞ ነጻ አዉጪ ግንባር) የታጠቀ ኃይል ባደረሰው ጥቃት በሰው ህይወት እና ንብረት እንድሁም በሀይማኖት ተቋማት ላይ ውድመት መድረሱን ኃላፊው ገልጸዋል።
ጥቃቱን እየፈጸመ ያለው ኃይል በተለየ መንገድ ስልጠና የወሰደ በመሆኑ ይህን አካል መደምስ ካልታቻለ የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር አስቸጋሪ በመሆኑ የክልሉና የፌዴራል መንግስትን የተቀናጀ መፍትሄ መስጠት አለባቸው ብለዋል።
ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በሚያዋስኑ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ሰላማዊ ግኑኙነት መኖሩን ጠቁመው፥ በከሚሴ ልዩ ዞን ዙሪያ የተፈጠረውን ክስተት ለመፍታት በየደረጃው የሚገኘው የመንግስት አካል የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።
የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት (አብመድ) ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እንደዘገበው፥ ወደ አጣየ፣ካራቆሬ እና ማጀቴ መከላከያ ገብቷል፤ ሁኔታውም ከሌሎች ቀናት ይልቅ በአንጻራዊ መሉ እሁድ (መጋቢት 29 ቀን፥ 2011 ዓ.ም.) እየተረጋጋ መምጣቱን፤ ተጨማሪ ፀጥታ አስከባሪ ኃይልም እየገባ መሆኑን የአማራ ክልል የሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አለበል አማረ አስረድተዋል።
የፀጥታ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም ከቅዳሜ እና ከእሁድ ረፋዱ (መጋቢት 28–29 ቀን፥ 2011 ዓ.ም.) የተሻለ መሆኑን የተናገሩት ኮሎኔል አለበል፥ ተደራጅቶ ሕዝብን ሰላም እያሳጣ ያለውን ቡድን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የተቀናጀ ሥራ እንደሚከናወንም አረጋግጠዋል።
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ፋግታ ለኮማ ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ የ14 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት (አብመድ) እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የዞኑ ፖሊስ መምሪያን በመጥቀስ ዘግበዋል።
የመምሪያው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ባለሙያ ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ ስዩም በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ይህ የመኪና አደጋ የደረሰው ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም፣ ከጠዋቱ 3፡00 አካባቢ ሲሆን፥ ቦታው ደግሞ በወረዳው “ሉሊስታ” በተባለ ቀበሌ ነው። ከዳንግላ ወደ ኮሶበር እየሔደ የነበረ 16 ሰው የመጫን አቅም ያለው የህዝብ ማመላለሻ መኪና (የሰሌዳ ቁጥሩ፦ 3-20705-አማ) እና ወደ ባህር ዳር አቅጣጫ እየሄደ ከነበረ የመከላከያ ሠራዊት ከባድ የጭነት መኪና (የሰሌዳ ቁጥሩ፦ መከ-01335) ክፉኛ በመጋጨታቸው የ1 ሰዎች ሕይወት የቀጠፈው አደጋ ሊደርስ ችሏል።
ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ በገለጻቸው “የህዝብ ማመላለሻ መኪናው ከዳንግላ ወደ ኮሶበር በመጓዝ ላይ ሳለ በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ ባህር ዳር ይመጣ ከነበረው ከባድ የጭነት መኪና ጋር በመጋጨታቸው አደጋው ሊከሰት ችሏል” ሲሉ፥ በተከሰተው አደጋ 14 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች 12 ሰዎች በጽኑ ቆስለዋል በማለት አክለው ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ አደጋው በደረሰበት ወቅት 15 ሰው ብቻ መጫን የነበረበት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው 25 ሰዎችን ጭኖ እንደነበር ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ አያይዘው ገልጸዋል።
በፋግታ ለኮማ ወረዳ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ሳጅን መልካሙ ልየው ለአብመድ ሕይወታቸው ስላለፈው ሰዎች ሲያብራሩ፥ በአደጋው ሹፌሩን እና ረዳቱን ጨምሮ የ14 ሰዎች ሕይወት አልፏል ብለዋል።
የቆሰሉት ሰዎች በዳንግላና እንጅባራ ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ በአዲስ ቅዳም ጤና ጣቢያ ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተልከዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የስምንት መንገዶች ግንባታ ሥራ የኮንትራቶችን ከተለያዩ ተቋራጮች ጋር ተፈራረመ
ከሟቾች መካከል ከሕጻን ልጃቸው ጋር ሕይወታቸው ያለፈው አንዲት እናት እንደሚገኙበት ያስታወቁት ኢንስፔክተሩ፣ የ13ቱ ሟቾች አስክሬን ወደቤተሰቦቻቸው የተላከ ሲሆን ለቀሪው የአንዲት ሴት አስከሬን ቤተሰቦቿን የማፈላለግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ ስዩም ጠቁመዋል።
ዋና ኢንስፔክተሩ እንዳስታወቁት በአሁኑ ወቅት የአደጋው መንስዔ እየተጣራ መሆኑን አመልክተው፣ የከባድ መኪናው አሽከርካሪ አደጋው ከደረሰ በኋላ በመሰወሩ በቁጥጥር ስር ለማዋል በፖሊስ በኩል ክትትል እየተደረገ ሲሆን፤ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድርስ አልተያዘም። በየቀኑ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ አሽከርካሪዎች የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ህጉን አክብረው ሊያሽከረክሩ እንደሚገባም ኢንስፔክተሩ አሳስበዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት ሀምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም የሀገሪቱ ትራንስፖርት ባለስልጣን ባወጣው በ2010 ዓ.ም የበጀት ዓመት ብቻ 5,118 ሰዎች በተሽከርካሪ አደጋ ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ ይህም ከ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 13.7 በመቶ እንደጨመረ ያስረዳል። የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ባወጣው በዚሁ መግለጫ ላይ በ2010 ዓ.ም የበጀት ዓመት በተሽከርካሪ አደጋ 7,754 ሰዎች ላይ የከባድ፣ 7,775 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሷል። በዚሁ የበጀት ዓመት የደረሰው የመኪና አደጋ (የተሽከርካሪ አደጋ) በቁጥር 41,000 ሲሆን ይህም በ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከደረሰው የተሽከርካሪ አደጋ ጋር ሲነጻጸር በመቶ እድገት አሳይቷል። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት በተሽከርካሪ ብዛት ዝቅተኛ ከሚባሉ ሀገራት ብትመደብም በተሽከርካሪ ምክንያት በሰው ላይ በሚደርስ አደጋ ግን አውራ ቦታ ከያዙት ሀገራት ውስጥ ትመደባለች።
ምንጮች፦ Xinhua፣ አብመድ እና ኢዜአ