-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል አለማየሁ አፅም ከሀገረ እንግሊዝ ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ ኢትዮጵያ ተጠየቀ። በተጨማሪም ለንደን ከተማ ውስጥ በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም (Victoria and Albert Museum) የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።
በኢፌዴሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድን መጋቢት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በለንደን ጉብኝት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም በለንደን የዊንዶዘር ቤተመንግስት (Windsor Castle) የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን መካነ መቃብር እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አፄ ሃይለስላሴ ይጸልዩበት የነበረውን ወንበር ጎብኝተዋል።
ዶ/ር ሂሩት ካሳው በአጼ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል አለማየሁ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን እንደመረጃ ምንጭነት በመጥቀስ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
በጉብኝቱ ወቅትም “የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ማግኘታችን ደስ ብሎናል፤ ይሁን እንጂ ከትውልድ ቦታው ተለይቶ ህይወቱ ያለፈው ልዑል አለማየሁ አፅም በትውልድ ሀገሩ እንዲያርፍ የኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ስለሆነ በክብር ወደ አገሩ እንዲመለስ” ሲሉ ዶክተር ሂሩት ጠይቀዋል።
አፅሙ ወደኢትዮጵያ ተመልሶ ከአባቱ አጼ ቴዎድሮስና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መቀላቀል እንደሚገባውና የዊንዶዘር ቤተመንግስት ለሚመለከተው አካል ጥያቄውን አቅርቦ በአፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ ልዑካን ቡድኑን በመቀበል ከቡድኑ ጋር የተወያዩት የዊንዶዘር ቤተ-መንግስት ሃላፊ ዶ/ር ማርክ ፓወል በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንነጋገርበታለን ብለዋል። ሂደቱን በተመለከተ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመከታተል እልባት እንዲያገኝ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግም ሚኒስቴሩ ተገልጿል።
በሌላ በኩል የልዑካን ቡድኑ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለንደን የሚገኘውን የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም ጎብኝቷል። በዶ/ር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድኑና በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሙዚየሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ትሪስታራም ኸንት (Tristram Hunt, PhD) ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ ወቅት በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።
እ.አ.አ በ2018 የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ለኢትዮጵያ መመለስ እንደማይችል፤ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ውሰት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚቻል መገለጹ ይታወቃል። የሙዚየሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ትሪስታራም ኸንት ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው ውሰት የሚለው ቃልም ለኢትዮጵያውያን ከባድ መሆኑን እንደተረዱት ተናግረዋል። በመሆኑም “የተቸገሩት ጉዳዩ የሕግ ጉዳይ በመሆኑና ምላሽ ለመስጠት ያለን አማራጭ ይህ ብቻ ስለሆነ ነው ” ብለዋል።
“ያለን አማራጭ ይህን ቀዳዳ በመጠቀም ሊስተካከሉ የሚችሉ አባባሎችን ተጠቅመን የሚመለሱበትን ሁኔታ መፍጠር፤ ይህን ካላደረግን ግን በሕጉ ላይ ጸንተን ወደፊት የሚሆነውን ነገር መመልከት ይኖርብናል” ሲሉም ዶ/ር ኸንት አክለዋል።
የባህል ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ቅርሶቹ የኢትዮጵያ በመሆናቸው በረጅም ጊዜ ውሰት ሳይሆን በቋሚነት ቅርሶቹ ለኢትዮጵያ መመለስ የሚችሉበት አማራጭ መፍትሄ ሙዚየሙ ሊያበጅ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በኤምባሲውና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል በአስቸኳይ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም፣ ካለው ሕግ ጋር በማይጋጭና የኢትዮጵያን ጥያቄ ሊመልስ በሚችልበት ሁኔታ በመንቀሳቀስ ጉዳዩ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት እልባት እንደሚያገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸፀዋል።
በለንደን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ባለው ሙሉ አቅምና ጊዜ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ቅርሶቹ ወደ አገራቸው እንዲገቡ እንደሚያደርጉ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻወል ገብሬ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ አድርጎ ለትውልድ ለማሸጋገር የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደዘገብው፥ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባን የወንዞችና ወንዝ ዳርቻዎች ማልማት አዲስ ፕሮጀክትን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት “በተራሮች ከፍታ ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ ሆና ለትውልድ የምትሸጋገር ውብ ከተማ ማድረግ ይገባል” ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) መሪነት በከተማ አስተዳደሩ አስተባባሪነትና በከተማዋ ነዋሪዎችና በወጣቶች ትብብር ለትውልድ የሚሸጋገር ድንቅ ከተማ መገንባታችንን እንቀጥላለንም ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ። ፕሮጀክቱ ለትውልድ የሚተላለፍ የትውልድ አሻራ ያለበትና ሁላችንም የጋራ እሴቶቻችንን የምናስተላልፍበት በመሆኑ ልንደሰት ይገባል በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል።
ፕሮጀክቱ ከተማዋ እንደስሟ እንድትኖር ወንዞችና የወንዞች ዳርቻዎች ሁሉ የቆሻሻ መናኸሪያ ሳይሆኑ የሰው ልጅ በተለይም ደግሞ ወጣቶች ቁጭ ብለው በመነጋገር ሀሳብ የሚቀያየሩበትና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች የጋራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ ከእንጦጦ ተራራ ተነስቶ ፒያሳን አካሎ እስከ ብሔራዊ ቤተመንግስት የሚዘልቅ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እስከ ብሔራዊ ቤተመንግስት ገራዥ የሚያልፍ ሆኖ እንደማሳያ የሚጀመር ነው ብለዋል።
በከተማዋ የተያዘው የልማት የወደፊት ስሌት (strategy) ሕዝቦቿ ከልማቱ ጋር የሚያድጉና የሚበለፅጉ እንዲሆኑ የሚያስችል እንጂ አንዱን የህንፃ ባለቤት በማድረግ ሌላውን ለማፈናቀል የሚሠራ አለመሆኑንም ተናግርዋል ኢንጂነር ታከለ ኡማ።
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው ከተማዋ ብዙ ታላላቅ ቅርሶች ያሏት፣ አብያተ መንግስት፣ ቤተ እምነቶችና እንደመርካቶ ያሉ የታላላቅ ገበያዎች መገኛ ናት ብለዋል። ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ምርጥ ሕዝቦች በፍቅር በአንድነት በደም ተሳስረው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗንም አስረድተዋል ኃላፊው።
ራሳችን ተንፍሰንና ተዝናንተን ቁጭ ብለን የምንወያይበት እነጂ የተጣበበ የአስተሳሰብ መንገድ እንዳይኖረን ሰፋ ያለ የስፍራ አጠቃቀምን የሚያሳዩ የቱሪስት መዳረሻዎች የሉንም ያሉት ኃላፊው፤ ፕሮጀክቱ ለልጆቻችን ልናተርፍላቸው የሚገባ የመዝናኛ፣ የመነጋገሪያና የመናፈሻ ቦታ እንዳለውም ተናግረዋል። ከዚህም ባሻገር ልጆቻችን ሌሎች ሰዎችን ጋብዘው የሚጠቀሙበት የቱሪስት መዳረሻ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
- ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ ሊሰጥ ነው
- ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛዎቹ የታሸጉ ውሃዎች የጥራት ችግር ይታይባቸዋል
- “ብሔራዊ የግብር ገቢ ንቅናቄ” በጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት በይፋ ተጀመረ
- በአዲስ አበባ “ለሁሉ” የክፍያ ማዕከላት ተገልጋዮች መጉላላት እየገጠማቸው ነው
- አንበሳ የከተማ አውቶቡስ በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማቋረጡ ተገልጋዮች ለችግር ተዳርገዋል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲው የበላይ ኃላፊ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይና ከጣልያን የባህል ማዕከላትና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው ልዩ ልዩ እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል።
በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ረዳት ዳይሬክተር መ/ር ተመስገን ዮሐንስ ሙሉ ፕሮግራሙን የመሩት ሲሆን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ካፈራቸው ምሁራን አንዱ ናቸው።
በመርሐ ግብሩ መሠረት የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በይፋ መጀመሩን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው የበላይ ኃላፊ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሲሆኑ በመግቢያ ንግግራቸው ላይ ኮሌጁ በመማር ማስተማሩ ሂደት ዛሬ ላይ ለመድረስ የነበሩትን ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለዩኒቨርሲቲ ደረጃ መድረሱ እግዚአብሔርን ካመሰገኑ በኋላ ዩኒቨርሲቲው አሁን የደረሰበትን ደረጃ እንዲደርስ ሌት ተቀን የሠሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን፣ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳት፣ የቦርድ የሥራ አመራር አባላትና የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
ከብፁዕነታቸው በመቀጠል ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር ኃይሉ ሀብቱ ናቸው።ተባባሪ ፕሮፌሰ ርኃይሉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚገኙ አምስት ኮሌጆችና ት/ቤቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ገልፀው፥ ትምህርት ቤቱ ከጥቅምት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በማስተርስ ኦፍ አርትስ (M.A.) ዲግሪ ደረጃ የድኅረ ምረቃ ትምህርት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል። ፕሮግራሙን ለማጠናቀቅ የሚወስደው ጊዜ ሁለት ዓመት መሆኑንና የአንደኛው ዓመት መርሐ ግብር ለተማሪዎች፦ (1) በኢትዮጵያ ታሪክ፣ (2) በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ (3) በብሔረሰቦች ወግና ሥርዓት ሰፊጥናትና ጥልቅ ግንዛቤ የሚሰጥ ሲሆን በሁለተኛው መርሃ ግብርም፦ (1) በትውፊታዊ ሥነ መድኃኒት/ ሥነ ፈውስ፣ (2) በትውፊታዊ ሥርዓተ ሕግ፣ (3) በኢትዮጵያ ጥናት አውራ ርዕሰ ጉዳዮች የሚያተኩሩ እንደሆኑ አብራርተዋል። የማስተማሪያ መደበኛ ቋንቋ እንግሊዝኛ ቢሆንም አገርኛ ቋንቋዎች ግዕዝን ጨምሮ እንደ አማራጭ ማስተማሪያ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ነፃነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ለአብነት ያህል በ17ኛው እና 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ እንደነ ወለተ ጴጥሮስ፣ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ማካኤልን የመሳሰሉ አባቶችና እናቶች ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ሰማዕት ሆነዋል ብለዋል።
ከዚህ በመቀጠል የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባል የሆኑት ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ ንግግር አድርገዋል። ከተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊያ ልሆኑ የትምህርት ተቅዋማትና ድርጅቶች የመጡትን እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ከልብ አመስግነዋል። በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በመቀጠልም በፕሮግራሙ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የተገኙ እንግዶች ለዩኒቨርሲቲው ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳቦችና አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን ከቅድስት በዓታ ለማርያም ቤተክርስቲያን የመጡ መምህር በዓሉን የሚገልጽ ቅኔ አቅርበዋል።
በመጨረሻም በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በብራና መጻሕፍት ዝግጅት ክፍል የሚዘጋጁትን የተለያዩ የብራና መጻሕፍት፣ ቀለምና የብራና መሣሪያዎችን በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ እንግዶች ጐብኝተዋል።
የቀድሞ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በ1935 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ካህናትንና የቤተክርስቲያን ሊቃውንትን ዘመናዊውንና የአብነት ትምህርታቸውን አስተባብረው እንዲይዙ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ እንደተጀመረ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ኮሌጁ በዚህ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፥ በመቀጠልም በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማዕረግ በማስተማር ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ዕጩዎችን ሲያበቃ ቆይቷል። የኮሌጅን ደረጃ በ1960 ዓ.ም. ካገኘ በኋላ ከሦስት ዓመት በኋላ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቲኦሎጂ ፋኩልቲ አካል ሆኖ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ዘልቋል። የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ፋኩልቲው ሲዘጋ በወቅቱ በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩት በሚፈልጉት የትምህርት መስክ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተዛውረው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ መደረጉ ይታወሳል። መንፈሳዊ ኮሌጁ ተወርሶ አራት ኪሎ ከጎኑ የሚገኘው የሳይንስ ፋኩልቲ ለራሱ የትምህርት መርሐ ግብር እንዲጠቀምበት ተደረገ። በ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ኮሌጁ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተመልሶ በነበረው ዕውቅናና ደረጃ የመማር ማስተማሩን ሒደት ሲያከናውን ቆይቷል። ኮሌጁ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ከፍተኛ የሆኑ የልማት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።
መንፈሳዊ ኮሌጁ እስከ አሁን ድረስ ከ3,500 በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን ከዚሁ በበለጠ መልኩ እንዲጠናከርና የቤተክርስቲያኒቱ የጥናትና የምርምር ተቅዋም እንዲሆን መሉ ዝግጁቱን አጠናቅቆ በመጨረሱ በአሁኑ ሰዓት በቲዮሎጂ (ስነ መለኮት) የትምህርት ዘርፍ በዶክትሬት፣ በማስተርስ ዲግሪ፤ በመደበኛ የመጀመሪያ ዲግሪ፤ በማታው ተከታታይ እና በርቀት ትምህርት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዲግሪ፤ ዲፕሎማ፤ በግእዝቋንቋ (extension) ዲግሪና ዲፕሎማ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።
ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ፈቃድ ወደ ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ እንዲያድግ ተደርጓል። በዚሁም መሠረት ከኅዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ እንዲጠራ መወሰኑ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ዩኒቨርሲቲው / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት አውስቷል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር ያለው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ-ጥበባት ማዕከል 40ኛ የጥበብ ውሎ መድረኩን ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ አካሒዷል።
በዝግጅቱ ላይ የዕውቁ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ሰው የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ተደርጓል። ሥራዎቹን እና ሕይወቱን አስመልክቶ የሙዚቃ ባለሙያ እና በቅርቡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ሆኖ የተሾመው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት የውይይት መነሻ ጥናት አቅርቦ በታዳሚዎች ውይይት ተካሂዶ ነበር።
“ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ <ባለዋሽንቱ እረኛ>(The Shepherd Flutist) በተሰኘ ታላቂ ሥራ የኢትዮጵያን መልክ በረቂቅ ሙዚቃ ያሳዩ ናቸው” በማለት አቶ ሠርፀ የገለጿቸው የሙዚቃውን ረቂቅነት በመጥቀስ ሲሆን፤ ፕሮፌሰር አሸናፊ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አውስቷል።
በሙዚቃ ላይ ከሠሯቸው ከበርካታ የምርምር ሥራዎቻቸው ውስጥ “Roots of Black Music” የተሰኘው መጽሐፋቸው በብዙ የዓለማችን የሙዚቃ አጥኚዎች የተዘነጉ (የተዘለሉ) የአፍሪካ/የምሥራቁ ዓለምን የሙዚቃ ስልትና ፍልስፍናን አጉልተው ለተቀረው ዓለም ያሳዩበት እንደሆነም አቅራቢው አብራርተዋል።
በውይይቱም ከተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዘመናት መካከል የመድመቅና መልሶ የመደብዘዝ ችግር ከምን የመነጨ እንደሆነ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፥ “ዋናው ችግር በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተቋም ፈርሷል፤ እሱን መልሶ መገንባት የቤት ሥራችን ነው” ብለዋል አቶ ሠርፀ። አክለውም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ትምህርት ሥርዓት ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከምዕራባውያን የሙዚቃ ሥርዓተ-ትምህርት ነፃ መውጣት ያለመቻሉም ሌላ ምክንያት እንደሆነ አቅራቢው ጠቅሰዋል።
ውይቱን የመሩት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ እንዳለጌታ ከበደ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ማደግ ብርቱ ጥረት ያደረጉ የጥበብ ሰዎችን ፈለግ እና ሥራዎቻቸውን ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ በሁሉም አካላት ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ አዲስ አበባ ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። አባታቸው ግራዝማች ከበደ አድነው፣ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ፋንታዬ ነከሬ ያባሉ ነበር። የሙዚቃ ፍቅርን ገና በልጅነታቸው ያሳደሩባቸው እናታቸው ቢሆኑም ታዳጊው አሸናፊ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳሉ እናታቸውን በሞት አጥተዋል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ መሠረታዊ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (አሁን ኮከበ ጽባሕ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚባለው) ካጠናቀቁ በኋላ ከሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ተመርቀዋል። ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት ኒው ዮርክ ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሮቸስተር፣ ኢስትማን የሙዚቃ ትምህርት ቤት (University of Rochester’s Eastman School of Music) በ1954 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሰ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን መሥርተዋል። የትምህርት ቤቱም የመጀመሪያው ዳይሬክተር ከመሆናቸውም ባሻገር በመሆን ሙዚቃን ከማስተማሩ ባሻገር አገልግለዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ.ወ.ክ.ማ.)፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት መርሓ-ዕውራን ትምህርት ቤት እና በመሳሰሉ የወጣቶች ማኅበራት እየተገኙ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጡ ነበር።
በድጋሚ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ተመልሰው፣ ኮነቲከት ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዌስልያን ዩኒቨርሲቲ (Wesleyan University) በ1961 ዓ.ም የማስትሬት፣ እንዲሁም በ1963 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ምዕራባዊ ባልሆኑ ሙዚቃዎች ምርምር (ethnomusicology) አግኝተዋል።
ከሙዚቃው መምህርነትና ተመራማሪነት ባሻገር ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ደራሲም ነበሩ። እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም ኮንፌሽን (Confession)፣ እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም ሩትስ ኦፍ ብላክ ሙዚክ (Roots of Black Music) የሚሉ መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲሆን፣ በሙዚቃ ላይ ያተኮሩ በርካታ ጽሁፎችን፥ በተለይም ደግሞ በአፍሪካ-አሜሪካውያን ባህልና አኗኗር ላይ ለሚያተኩረው “The Chronicler” ለተሰኘው መጽሔት ጽፈዋል።
በአሜሪካ ፕሮፌሰር አሸናፊ ኑሯቸው ፍሎሪዳ ክፍለ ሀገር በሚገኘው ፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርሲቲ (Florida State University) የሙዚቃ ኮሌጅ ውስጥ በመምህርነት የሠራ ሲሆን፣ ተቀማጭነቱን እዚያው አሜሪካ ያደረገውናታዋቂውን የኢትዮጵያ ምርምር ካውንስልን (Ethiopian Research Council) በዳይረክተርነት መርቷል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ባለቤታቸው (ወ/ሮ እሌኒ ገብረመስቀል) እና ሁለተኛ ባለቤታቸው (አሜሪካዊ) አራት ልጆችን (ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ) ልጆችን አፍርተዋል። ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የ60ኛ የልደት በዓላቸው ዕለት በመኖሪያ ቤታቸው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሞተው የተገኙ ሲሆን፤ ምናልባትም የራሳቸውን ሕይወት ሳያጠፉ እንዳልቀሩ ብዙዎች ይገምታሉ።
PHOTO: Ethiopian Academy of Sciencesአዲሱ የካቢኔ አባላት ሹመት የቀረበው የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ እንደገና ለማሻሻል የቀረበውን አዲስ ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤቱ መፅደቁን ተከትሎ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።
አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ20 አዳዲስ የካቢኔ አባላት ሹመት ውስጥ 50 በመቶ ሴቶች ሆነው እንዲያገለግሉ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የቀረበውን ሹመት ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ አፀደቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሚሾሙት 20 ካቢኔዎች ውስጥ 10 ሴቶች ሆነው በተሰጣቸው ኃላፊነት እንዲያገለግሉ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
አዲሱ የካቢኔ አባላት ሹመት የቀረበው የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ እንደገና ለማሻሻል የቀረበውን አዲስ ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤቱ መፅደቁን ተከትሎ ነው።
በዚህም መሠረት የሹመቱ ዋና መስፈርት ብቃት፣ የትምህርት ዝግጅትና ለውጥን የመምራት አቅም መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ከሚሾሙት ካቢኔዎች 50 በመቶ (በቁጥር፥ ወይም ከ20ዎቹ 10 ሴት) ካቢኔዎች መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ይህም በኢትዮጵያ ምናልባትም በአፍሪካ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም በምክር ቤቱ ተገልጿል።
በዚህ በተደረገው የካቢኔ ሹመት ለውጥ ውስጥ ከዚህ በፊት “የፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር” ተብሎ ይጠራ የነበረው ሚኒስቴር ተለውጦ አሁን “ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን” (Civil Service Commission) በሚል እንደተተካ ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ ሶስት ኮሚሽኖችም በአዲስ መልክ ተካተዋል፤ እነዚህም (1) የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን (Job Creation Commission)፣ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን (Environment, Forestry and Climate Change Commission) እና የፕላንና እድገት ኮሚሽን (Plan and Development Commission) ናቸው።
አዲስ በተዋቀረው ካቢኔ ውስጥ የተሰየሙት ባለስልጣናትና የተሰየሙበት ስልጣን ዝርዝር
- ዶ/ር ሂሩት ካሳው ― የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር
- ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ― የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
- ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ― የሰላም ሚኒስቴር
- ዶ/ር ሳሙኤል ሆርቃ ― የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር
- ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ― የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር
- አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ― ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
- አቶ አህመድ ሺዴ ― የገንዘብ ሚኒስቴር
- ዶ/ር አሚን አማን ሐጎስ ― የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር
- ወ/ሮ አዳነች አበበ ― የገቢዎች ሚኒስቴር
- ኢ/ር አይሻ መሀመድ ሙሳ ― የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር
- አቶ ኡመር ሁሴን ― የግብርና ሚኒስቴር
- ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ― የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
- ወ/ሮ የዓለምፀጋይ አስፋው — የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር
- ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ― የትራንስፖርት ሚኒስቴር
- አቶ ጃንጥራር አባይ ― የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር
- ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ ― የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
- ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ ― አምባዬ የትምህርት ሚኒስቴር
- ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ― የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
- ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ-እግዚአብሔር ― የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
- ዶ/ር ፍፁም አሰፋ ― የፕላን ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በጥቅምት ወር ዓም የጸደቀው የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ የፊልም ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በአግባቡ እንዲያሳድገው ከተፈለገ የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅለት ይገባል – በሀገሪቱ ውስጥ በፊልም ሥራ ላየ እንደተሰማሩ ባለሙያዎች ማብራሪያ።
በጌትነት ተስፋማርያም (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ ዘርፉን በአግባቡ እንዲያሳድገው ከተፈለገ የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅለት እንደሚገባ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪያዎች ማህበር የቀድሞ ፕሬዚዳንት አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ እንደገለጸው፤ የዘርፉን ችግሮች ለማቃለል የሚያስችል አ ሠራር ይኖረዋል የተባለው ፖሊሲ ባለፈው ዓመት ጸድቋል። ነገር ግን ፖሊሲው ዝርዝር ጉዳዮችን የማይዝ በመሆኑ እያንዳንዱን የዘርፉን ችግሮች ሊቀርፍ የሚችል የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅ ይገባል።
እንደ አርቲስት ደሳለኝ ገለጻ፤ የፊልም ኢንዱስትሪው ለአምስት መቶ ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል መሆኑን በጥናት ተረጋግጧል። ነገር ግን እስካሁን በአግባቡ ስላልተሠራበት ውጤቱ እምብዛም ነው። ከአጠቃላይ የአገሪቷ ገቢ ውስጥ ያለው ድርሻም ዝቅተኛ ነው። የፊልም ፖሊሲው አስፈጻሚ አካል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ካለው የሰው ኃይል፣ የፊልም ጥበብ ዕውቀት ችግር እና አደረጃጀት አኳያ ዘርፉን በሚገባው ልክ እያገዘ አይደለም። በመሆኑም የፊልም ባለሙያዎች ዋነኛውን ድርሻ በመውሰድ ለፖሊሲው ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ለማውጣት ሌት ከቀን መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
የፊልም ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ መዋ በበኩሉ፤ እንደ አንድ የፊልም ባለሙያ ፖሊሲው ሲጸድቅ በኢንዱስትሪው ያሉት ችግሮች ይቀረፋሉ ብሎ እንደጠበቀ ገልጿል። ዝርዝር ጉዳዮችን ለማስተካከል እና ወጥ አሠራር ለማምጣት የማስፈጸሚያ ሰነዱ የግድ መዘጋጀት እንዳለበት ባለሙያዎች ሊገነዘቡ እንደሚገባ ተናግሯል። የማስፈጸሚያ ሰነዱንም ለማዘጋጀት የሚያስችል ቡድን ከባለድርሻ አካላት ተውጣጥቶ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን በር በየጊዜው በማንኳኳት ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ የፊልም ሠሪዎች የዘርፍ ማኀበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢንያም አለማየሁ እንደገለጸው፤ የማስፈጸሚያ ሰነዱ ቢዘጋጅ በመጀመሪያ ኢንዱስትሪው በማደጉ ተጠቃሚ የሚሆነው ባለሙያው ነው። በመሆኑም አርቲስቶች፣ ዳይሬክተሮች እና በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦች ሳይሰለቹ ለፖሊሲው የማስፈጸሚያ ሰነዱ ዝግጅት መሥራት አለባቸው። በዘርፉ ያለውን የዕውቀት፣ የገቢ እና የአሠራር እድገት ለማስመዝገብ ማስፈጸሚያ ሰነዱ ቁልፍ ሥራ መሆኑን በመረዳት ማንኛውም ባለሙያ በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባ ገልጿል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ሰላም ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ የፊልም ሠሪዎች የዘርፍ ማኅበር በጋራ ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ፊልም ፖሊሲ ትግበራ ላይ ያተኮረ ውይይት ሰሞኑን በብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አዳራሽ ማካሄዱ ይታወሳል። በውይይቱ መጨረሻ ከ20 ያላነሱ በኪነጥበቡ ላይ ተሳትፎ ያላቸው በጎፈቃደኛ ባለሙያዎች የፊልም ፖሊሲው ማስፈጸሚያ ሰነድ ለማዘጋጀት በሚደረገው ጥረት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተመርጠዋል።
እንደ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ፥ የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ በኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. መጽደቁ ይታወሳል።
በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን የፊልም ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ሙሉ ዶሴ (ፋይል) በፒ.ዲ.ኤፍ (PDF) እዚህ ጋር ያገኙታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት