-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት የማቆም አድማ ላይ የተሰማሩ የሕክምና ተማሪዎችን በተመለከተ ያወጣው መግለጫ
በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የመጨረሻ ዓመት (intern) ተማሪዎችና ስፔሻሊቲ (resident) ተማሪዎች ላነሱዋቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሴክተሩ ባለሙያዎች እና ተማሪዎች ጋር ሲወያዩ ተማሪዎች ላነሷቸው ጥያቄዎች በሰጡት አመራር የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል።
በዚሁ መሠረት፦
- የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን በተመለከተ የሕክምና ተማሪዎች እንደ ሌሎች ተማሪዎች የወጣባቸውን ትክክለኛ ወጪ እንዲጋሩ (cost sharing) እና ከዚህ በፊት አምስት መቶ ሺህ (500,000) ብር ይፈርሙ የነበሩት እንዲቀር መደረጉ፤
- የተግባር ትምህርት አተገባበርን በተመለከተ የአዳርና ለረዥም ጊዜ በሥራ ላይ መቆየት ጋር ተያይዞ የሥርዓተ ትምህርት ፍተሻ እንዲደረግና የውሳኔ ሃሳብ እንዲቀርብ፤
- የማስተማርያ ሆስፒታሎችን ለሥራ ምቹ ማድረግንና ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ ተቋማት ባላቸው አቅም በፍጥነት እርምጃ እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን በተለያዩ አካላት መገለጫ መሰጠቱ ይታወሳል።
በተጨማሪም እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮችን በዝርዝር አጥንቶ ዘላቂ መፍትሔ ለመሰጠት አራት ግብረ ሃይል ተቋቁመው ወደ ሥራ ገብተዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ በጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎች ተስተውለዋል። ይህ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተገንዝበው ተማሪዎቹ በፍጥነት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እያልን ከሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ትምህርታቸው የማይመለሱትን ተማሪዎች ተቋማት ባላቸው የመማር ማስተማር (academic) ሕግ ቀጣይ እርምጃ እንዲወስዱ መመሪያ የተላለፈ መሆኑን እንገልጻለን።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ ተመረጡ
- መንግሥት ሆይ፥ የጤና ባለሙያውን ጥያቄ ከልብህ አድምጥና መፍትሄ ስጥ
- አለርት ሆስፒታል ውስጥ ዘመናዊ የሕፃናት ሆስፒታል እና የአደጋ ሕክምና ማዕከል ይገነባሉ
- የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጣሊያን መንግስት የላብራቶሪ መሣሪያዎችን በእርዳታ አገኘ
- የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ፕሬዝዳንት ከዩኒቨርሲቲው ኮሌጆችና አስተዳደር ሠራተኞች ጋር ያዘጋጁት የምክክር መድረክ
በምክክር በድረኩም የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሐብታሙ አበበ ዩኒቨርሲቲውን በታታሪነት፣ በታማኝነት እና በቅንነት በማገልገል ዩኒቨርሲቲውን የልሂቃን ተቋም እና የመጀመሪያ ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ ተግተው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ሆሳዕና ከተማ (ሰሞነኛ)– ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ለአራት ወራት ያህል ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትነት መረጣ ሲያካሂድ ቆይቶ፥ ለመጨረሻ ዙርም ዶ/ር ሐብታሙ አበበ፣ ዶ/ር ኑሪ ላፌቦ እና ዶ/ር አብርሃም አለማየሁ አልፈው ነበር። ከእነዚህ ሦስት ዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከልም ዶ/ር ሐብታሙ አበበ በአጠቃላይ ውጤት 69.57% በማስመዝገብ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትነት ብቁ መሆናቸውን አስመስክረው፣ የኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ለዩንቨርሲቲውና ለሚመለከታቸው ቢሮዎች በፃፈው ደብዳቤ ዶ/ር ሐብታሙ አበበን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ሆነው ተሹመዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ሐብታሙ አበበ ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ያቀረቡትን የዩኒቨርሲቲውን የእድገት ስልታዊ ዕቅድ (University’s Development Strategic Plan) በይበልጥ ለማስገንዘብ እና በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የላቀ ታታሪነት፣ ትብብር እና ስኬታማ የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ስኬቶችን ለማስመዝገብ የሚያስችላቸውን የመጀመሪያ ዙር ምክክር ከማኅበራዊ ሳይንስ፣ ንግድ እና ምጣኔ ሀብት (Business and Economics)፣ ከግብርናና ከተፈጥሮ ሀብት ኮሌጆች እና ከሕግ ትምህርት ቤት ጋር ግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምረዋል።
በምክክር በድረኩም ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲውን በታታሪነት፣ በታማኝነት እና በቅንነት በማገልገል ዩኒቨርሲቲውን የልሂቃን ተቋም እና የመጀመሪያ ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ ተግተው እንደሚሠሩ በመግለጻቸው ከተሰብሳቢ መምህራን አድናቆት ከመቸራቸውም በላይ በጋራ ራዕያቸውን ለማሳካት ተግተው አብረዋቸው እንደሚሠሩ መምህራኑ ቃል ገብተውላቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ እያደረጉት ያለውን የምክክር መድረክ ቀጥለው ግንቦት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በዩንቨርሲቲው ዱራሜ ካምፓስ፣ ግንቦት 7 ቀን በዋናው ካምፓስ ምህንድስና (Engineering)፣ ጤና እና የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ (Natural and Computational Sciences) ኮሌጆች፣ በመጨረሻም ግንቦት 8 ቀን በዩንቨርሲቲው የንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ሆስፒታል እና ከዩኒቨርስቲው የአስተዳደር ሠራተኞች ጋር እእንደሚቀጥል ታውቋል።
ዶ/ር ሐብታሙ አበበ በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም. አንድራ ፕራዴሽ (Andhra Pradesh) ግዛት (ደቡም ምስራቃዊ ህንድ) ውስጥ ከሚገኘው አንድራ ዩኒቨርሲቲ (Andhra University) የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ምንጭ፦ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ ተመረጡ
- የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንፃ ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን አስመረቀ
- ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣው የማኅበረሰብ አገልግሎቱ
- አክሱም ዩኒቨርሲቲ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምህንድስና ትምህርት ክፍል ሊከፍት ነው
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
ተከሳሽ ዓለም ታምራት ከተለያዩ ዓለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ጥሪዎችን በማስተላለፍ ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን መሠረተ ልማት ወደ ጎን በመተው ዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት ጥፋተኛ ተብላለች።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ዓለም ታምራት የተባለችው ተከሳሽ የቴሌኮም መሣሪያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት፣ ለመጠቀም እና የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራት ወደ ሕገወጥ ተግባሩ መግባቷ ተጠቁሟል። ወንጀሉ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ስሙ ገርጅ አካባቢ መፈጸሙ ታውቋል።
የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 761/2004 አንቀጽ1/ለ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሳሽ ከቀድሞው ኢፌዲሪ መገናኛ እና ኢንስፎርሜሽን ሚኒስቴር በተሰጠ ፍቃድ ብቻ ወደ ሀገር ውስጥ ለመጠቀም የሚቻሉትን የኮል ተርሚኔሽን (call termination)፣ ኮል ባክ (call back)፣ ጥሪ የመቀበል እና ጥሪ የመላክ አገልግሎት መስጠት እንደነበር ተነግሯል።
ሆኖም ግለሰቧ ከሕግ አግባብ ውጪ ኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርዶችን በውስጣቸው በማስገባት በአንድ ጊዜ ብዛት ያላቸውን እቃዎች በቅናሽ በመግዛት እና ጥሪዎችን ማስተላለፍ የሚችሉ ብዛታቸው 4 የሆኑ ጌትዌይ (gateway) የቴሌኮም መሣሪያዎችን በድብቅ በማስገባት ወንጀል ፈጽመዋል።
በድብቅ የገቡ መሣሪያዎችን ከበይነመረብ (internet) የግንኙነት አውታር ጋር በማገናኘት የሚያገኙትን ኔትወርክ (network) በማብዛት ወደ ዋየርለስ ኔትወርክ (wireless network) እንዲቀየር በማድረግ የራሳቸውን ኔትወርክ መፍጠር የሚችሉ 15 ቶፒ ሊንክ የተባሉ መሣሪያዎችን ከሌሎች አጋዥ መሣሪያዎች ጋር መጠቀማቸው በክሱ ቀርቧል።
ግለሰቧ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን ኢትዮ ቴሌኮም በዘረጋው ኔትወርክ በኩል እንዲያልፉ በማድረግ ኢትዮ ቴሌኮምን 6,379,342.19 ብር ማሳጣቷ ተጠቅሷል።
ተከሳሽ ዓለም ታምራት ከተለያዩ ዓለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ጥሪዎችን በማስተላለፍ ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን መሠረተ ልማት ወደ ጎን በመተው ዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት ጥፋተኛ ተብላለች።
ጉዳዩን ተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14 ወንጀል ችሎትም አቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በመመልከት በሚያዝያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ63 ሚሊዮን የገንዘብ መቀጮ አሳልፎባታል።
ምንጭ፡- የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ / የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ሌሎች ዜናዎች፦- በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 59 ባለስልጣናትና ባለሃብቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ
- ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከኔዘርላንድ ኤንባሲ ጋር በመተባበር ለሕግ ባለሙያዎች የትምህርት ዕድል ሰጠ
- አጣየ፣ ካራቆሬ፣ ማጀቴ እና አካባው በሚኖሩ ዜጎች ላይ የታጠቁ ኃይሎች እያደረሱት ያለው ኢ-ሰብአዊ በደል
- ሕገ-ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል ተጨማሪ 36 አዳዲስ ኬላዎች ተቋቁመዋል – የገቢዎች ሚኒስቴር
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ አሠራሩን ለማዘመን ከእንግሊዝ ሀገር አቻው ጋር ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ አሠራሩን ለማዘመን የሚያግዙ ሀሳቦች ላይ ከእንግሊዝ ቤተ መዛግብት ኃላፊዎች ጋር ምክክር አደረገ።
በምክክሩ የቤተመዛግብት እና ቤተ መፃሕፍት አያይዝን ለማዘመን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የእንግሊዙ አቻ ተቋም ልምድ ምን እንደሆነ ያወያየ ምክክር ሚያዚያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በኤጀንሲዉ የቪዲዮ ኮንፈረንስ አዳራሽ ተካሄደ። ለውይይቱ መክፈቻ የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ የኩኖአምላክ መዝገቡ ለእንግዶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ኢትዮጵያ የብዙ መዛግብቶች መገኛና ባለቤት ብትሆንም እንኳን ያላትን ሀብት ለራሷም ለዓለምም ለማበርከት የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እጥረት እንዳለባት በማንሳት ይህንን ክፍተት የእንግሊዝ ቤተ መዛግብት የቴክኖሎጂ ሽግግር እገዛ አንዲያደርግላቸዉ ጠይቀዋል።
በመቀጠል በእንግሊዝ ቤተ መዛግብት የኤሲያና የአፍሪካ የመዛግብት ስብስብ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሊዊሳ ኤሌና ሜንጎሊ (Luisa Elena Mengoni, Head of Asian and African Collections at the British Library) እንዳሉት በሁለቱ ሀገራት ዉስጥ ያሉ ተመራማሪዎች፣ ደራሲያን፣ እንዲሁም ሌሎች ፀሐፍት የእርስ በእርስ የልምድ ልዉዉጥ እንዲያደርጉ መንገዱን ማመቻቸት ለስነ-ፅሑፍ እድገት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
አቶ ክርስቲያን ጄንሰን (Kristian Jensen) የእንግሊዝ ቤተ መዛግብት ኃላፊ እንዲህ አይነት የምክክር መድረኮች ክፍተቶችን ለመለየትና መፍትሔ ለማበጀት እንደሚጠቅሙና ቀጣይነት እዲኖራቸዉ በተለይም የሥነ-ፅሑፍ ታሪኳ ከአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሀገር ቤተ መፅሐፍቷና ቤተ መዛግብቷን በማዘመን ረገድ የእንግሊዝ ቤተመዛግብት እንደሚያግዝ ተናግረዉ፥ ኃላፊዉ የማይክሮ ፊልም (የመፅሐፍት ላይ ፅሑፎችን ወደ ሶፍት ኮፒ የሚቀይር መሣሪያ) በእርዳታ መስጠቷ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር በዶ/ር ሂሩት ካሳዉ በኩል ለኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ለአቶ የኩኖአምላክ መዝገቡ ርክክብ ከተደረገ በኋላ ባህላዊ የቡና ጠጡ ሥነ-ስርዓት ተከናዉኖ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
ምንጭ፦ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ሌሎች ዜናዎች፦- የልዑል አለማየሁ አፅም ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ ተጠየቀ
- የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንፃ (አርክቴክቸር) ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን አስመረቀ
- ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በደብረ ብርሃን ከተማ ሃውልት ሊቆምላቸው ነው
- ጉዞ ዓድዋ ― ታላቁ የዓድዋ ድልን የሚገባው የታሪክ ማማ ላይ ለመስቀል የሚጥር ኢትዮጵያዊ ማኅበር
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
- ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች መሠረታዊ ችግሮች በጥናት ሊለዩ ይገባል ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ
መንግስት በሀገር ውስጥ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን በማስፋፋት ለሥራ ፈላጊ ዜጎች አስፈላጊውን ጥቅም ለማዳረስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። መሥራት ለሚችሉ ዜጎች ሁሉ በሀገር ውስጥ ላሉ የሥራ ዕድሎች ቅድሚያ በመስጠት ሠርተው የሚለወጡበትን ሁኔታዎች በማመቻቸት ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሠርቶ ለመኖር በርካታ መልካም አጋጣሚዎች አሉ። ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑ በሀገራቸው ሠርተው የተለወጡ በርካታ ወጣቶችን መጥቀስ ይቻላል።
ከዚህ ባለፈ ወደ ውጭ ሀገራት ለሥራ መሄድ የሚያስቡ ዜጎች እራሳቸውን ከአቻ ግፊትና ከሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሊጠብቁ ይገባል። ዜጎች ስለሚሄዱበት ሀገር ስላለው እውነታ ያላቸው ግንዛቤና መረጃ ውስንና የተዛባ በመሆኑ ከመሄዳቸው በፊት ስለሚሄዱበት ሀገር ባህል፣ ወግና ልማድ መረዳትና እና የዜጎችን መብት ደህንነትና ክብር ለማስጠበቅ ሲባል በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 923/2008 ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል።
ለጉዞ ከመነሳታችን በፊት ምን ማወቅ ይጠበቅብናል?
ወደ ውጭ ሀገር ሄደን ለመሥራት በምናስብበት ወቅት ጊዜ ሰጥቶ ማሰብ ይገባል። ለምን እንደምንሄድ፣ ከሄድን በኋላ የሚያጋጥሙንን መልካምና መጥፎ አጋጣሚዎች እንዴት መቋቋምና ማለፍ እንደሚገባን፣ የምንሄድበትን ሀገር ባህል፣ ወግ፣ ልማድና ስርዓት እንዴት ተላምደን መኖር እንደምንችል፣ የሠራንበትን ገንዘብ ወደ ሀገራች እንዴት መላክና መቆጠብ እንደምንችል፣ ኮንትራታችንን ጨርሰን መቼ ወደ ሀገራችን መመለስ እንዳለብን አስቀድመን ማቀድ ያስፈልጋል።
በአዋጅ ቁጥር 923/2008 መሠረት በውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ፣ 8ኛ ክፍል ያጠናቀቁ (ወደ 9ኛ ክፍል የተዛወሩ)፣ በሚሄዱበት የሥራ መስክ ስልጠና ወስደው የብቃት ማረጋገጫ ያገኙ፣ የቅድመ ጉዞ ስልጠና ወስደው ሰርተፊኬት የያዙ፣ የጤና ኢንሹራንስ የተገባላቸው፣ ሙሉ የጤና ምርምራ ያደረጉና ከወንጀል ነጻ ሊሆኑ ይገባል።
ይህን ያሟሉ ዜጎች በአስቀጣሪ ኤጀንሲ በኩል ወይም በራሳቸው አማካኝነት ሥራውን በማፈላለግ ማለትም በቀጥታ ቅጥር አስፈላጊውን የቅጥር ፎርማሊቲ በማሟላት ቪዛውን አግኝተው መሄድ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ በቀጥታ ቅጥር የሚጓዙ ሠራተኞች መደበኛ ስልጠና የወሰዱና ከቤት ሠራተኝነት ውጭ በልዩ ልዩ ሙያዎች የሰለጠኑ ሲሆን የሚሠሩትም በካምፓኒና በልዩ ልዩ አነስተኛ የቢዝነስ ተቋማት ውስጥ ነው። ከዚህ በፊት በውጭ ሀገር ሠርተው የተመለሱ ልምድ ይኖራቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ መረጃ ማቅረብ የሚችሉ ከሆነ ስልጠናውን መውሰድ ግዴታ ባይሆንም የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
ለሥራ የት ሀገር ነው መሄድ የሚቻለው?
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቤት ሠራተኝነት የሚሄድ ከሆነ ሊጓዝ የሚችለው በኤጀንሲዎች አማካኝነት ብቻ መሆኑን ሊረዳ ይገባል። የሥራ ስምሪት ማድረግ የሚችለውም አገሪቷ የሁለትዮሽ ስምምነት ወደተፈራረመችባቸው ሀገራት ብቻ ነው። የሁለትዮሽ ስምምነት የተፈፀመባቸው መዳረሻ ሀገራት ለጊዜው ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታርና ጆርዳን ሲሆኑ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚደረገው ስምምነትም በሂደት ይቀጥላል።
ስምምነት በተፈፀመባቸው ሀገሮች የደመወዝ መጠን ስንመለከት ከኳታር መንግስት 1200 ለቤት ሠራተኛና 1300 ለእንክብካቤ (care giver) የኳታር ሪያል፣ ከጆርዳን መንግስት ለጀማሪ 225 ዶላር፣ ልምድ ላላው 250 ዶላር፣ ከሳውዲ አረቢያ መንግሰት ጋር 1000 የሳውዲ ሪያል እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በሠራተኞችና በአሠሪዎች የሚሸፈኑ ወጪዎች
አንድ ሠራተኛ በሥራ ለመሰማራት አስፈላጊውን መስፈርት ካሟላና ብቁ ከሆነ በአዋጁ የተደነገጉ የቅጥርና ምልመላ መንገዶችን በመከተል አስፈላጊውን መፈጸም እና ወጪዎችን መሸፈን ይገባል።
- አሠሪው ወይንም ኤጀንሲው የሚሸፍናቸው ወጪዎች
በአሠሪው የሚሸፈኑ ወጪዎች ሠራተኛውን ወደ ተቀባይ አገር ለማድረስ፣ በተቀባይ አገር ያለችግር እንዲቆይና እንዲሠራ ለማድረግ፣ እንዲሁም በሥራ ላይ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚወጡ ወጪዎች ናቸው።
እነርሱም የተቀባይ አገር የመግቢያ ቪዛ፣ የደርሶ መልስ መጓጓዣ፣ የሥራ ፍቃድ፣ የመኖሪያ ፍቃድ፣ የሥራ ውል ማጽደቂያ ክፍያዎች፣ የመድህን ዋስትና ሽፋን እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኝ የተቀባይ አገር ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ጽህፈት ቤት የሚከፈል ከቪዛና ከሰነድ ማረጋገጥ ጋር የተያያዘ ማናቸውም ወጪዎች ናቸው።
- በሠራተኛው የሚሸፈኑ ወጪዎች
አንድ ሠራተኛ ለሥራ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በሚጓዝበት ወቅት የሚያወጣው ወጪ በአብዛኛው በህይወት ዘመኑና በማህበራዊ ህይወቱ ውስጥ የትኛውም ሰው ስለሚጠቀምባቸው የሚያወጣቸው ወጪዎች ናቸው።
እነርሱም ለልደት ሰርተፊኬት፣ ለፓስፖርት፣ ለክትባት፣ ለህክምና ምርመራ፣ ለሙያ ብቃት ማረጋገጫ፣ ከወንጀል ነፃ ማስረጃ ማረጋገጫ ወጪዎች ናቸው። እነኝህ ክፍያዎች በሙሉ አገልግሎቱን ለሰጡ ሌሎች መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት የሚከፈል እንጂ ምልመላውን ለሚያከናውነው ኤጀንሲ የሚከፈል አይደለም። ኤጀንሲው ምንም አይነት ክፍያ ከሠራተኛው ቢጠይቅ ህገወጥ ያደርገዋል።
ይሁን እንጂ ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ አስፈላጊ ሁኔታዎች ተጠናቀው ያለበቂ ምክንያት ሠራተኛው ወደ ሥራ ባይሰማራ ከቅጥሩ ጋር በተያያዘ አሠሪው ያወጣውን ወጪ ሠራተኛው እንዲከፍለው ሊጠይቅ ይችላል። በተመሳሳይ መንገድ በተራ ቁጥር 2 ላይ የተጠቀሱትን ወጪዎች ሠራተኛው አውጥቶ በራሱ ጉድለት ባልሆነ ምክንያት በሥራ ላይ ካልተሰማራ ኤጀንሲው ወይም አሠሪው የሠራተኛውን ወጪ የመተካት ግዴታ ይኖርበታል።
ለውጭ አገር ለሥራ ስምሪት የሚሰጡ ስልጠናዎችና ማሰልጠኛ ተቋማቱ
ለውጭ አገር ሥራ ስምሪት የሚሰጡ ስልጠናዎች ሶስት ሲሆኑ እነሱም በቤት አያያዝ (Household Service) በቤት ውስጥ ሥራ (Domestic Help) እና በእንክብካቤ ሥራ (Care Giving) ናቸው።
የእነዚህ ሙያዎች የስልጠና መሳሪያዎች፣ የሙያ ደረጃ፤ ሥርዓተ ትምህርት እና የብቃት ማረጋገጫ ምዘና መሳሪያዎች ሲዘጋጁ ለማንኛውም ዜጋ እንዲያገለግል ሲሆን ወንድም ሆነ ሴት በፍላጎቱ ሊሰለጥን ይችላል። ሠልጣኞች ስልጠናውን በግላቸው ሊሠሩበት፣ በአገር ውስጥ ሊቀጠሩበት እንዲሁም ወደውጭ አገር ሊሰማሩበት እንደሚችሉ ሊገነዘቡና በምልመላ ወቅትም ሊነገራቸው ይገባል። በተጨማሪም በስልጠናው የተሳተፈ ሁሉ የብቃት ምዘናውን ያልፋል ማለት አይደለም፣ የብቃት ምዘናውን ያለፈ ሁሉ ቀጣሪ ያገኛል ማለትም አይደለም። በመሆኑም በተጠቀሱት ሙያ እንዲሰለጥኑ የተደረጉ ሁሉ ወደአረብ ሀገር መሄድን እንደመብት ሊያዩት አይገባም።
ይሁን እንጂ ወደአረብ አገር መሄድ የሚፈልጉ ሰልጣኞች ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ሙያዎች ከሰለጠኑ በኋላም የብቃት ምዘና ማረጋገጫ ተፈትነው ማለፍና ሰርተፊኬት መያዝ ይኖርባቸዋል። ስልጠናው በየክልላቸውና በአቅራቢያቸው በሚገኙ በተመረጡ ማሰልጠኛ ተቋማት ይሰጣል። ስልጠናው በየክልላቸውና አቅራቢያቸው የመሰጠቱ ጠቀሜታም የሠራተኞች ምልመላ በየክልላቸው የሚካሄድ በመሆኑ፣ አስፈላጊ መረጃዎችን ለማጣራትና ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን ደህንነትና ክብር በቅርብ ለመከታተል እና ከስልጠና፣ ከምልመላ ጋር ተያይዞ ለአላስፈላጊ ወጪና የመብት ጥሰቶች እንዳይጋለጡ ያግዛል።
ስልጠናን በተመለከተም፣ የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት ትምህርቱን በነፃ የሚሰጡ ሲሆን ማንኛውም ሰልጣኝ በክልሉ በሚገኝ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ወይም በየዞኑና ክፍለ ከተማው ወይም ወረዳዎች በሚገኙ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤቶች በመመዝገብ ለየማሰልጠኛዎቹ በመላክ እንዲሰለጥኑ ይደረጋል።
በተጨማሪም የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት የተደራሽነትና የአቅም ውስንነት ስላለባቸው በፌደራልና በክልል በሚገኙት የቴ/ሙ/ት/ስ/ኤጀንሲ ቢሮዎች ለግል ማሰልጠኛ ተቋማት ፍቃድ በመስጠት በማሰልጠን ሥራው እንዲሳተፉ ተደርጓል። በመሆኑም የግል ማሰልጠኛ ተቋማት የስልጠና ጥራታቸው ላይ ጥንቃቄ በማድረግና አስፈላጊ የስልጠና ቁሳቁሶችን በማሟላት የትምህርቱን ጥራት እንዲጠብቁ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ፍቃድ ሰጪ አካላትም የጀመሩትን ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ በማጠናከር እገዛ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
በየክልሉ የተመረጡ የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት ዝርዝር
በመንግስት የተመረጡ 66 ማሰልጠኛ ተቋማት ሲሆኑ ስልጠናውም በሁሉም ክልል በነፃ ይሰጣል።
የማሰልጠኛ ተቋማት ዝርዝር በየክልሉ፡-
አማራ ክልል
- ባህርዳር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ወልድያ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ደሴ ወ/ሮ ስህን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ከሚሴ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ
- ደ/ብርሃን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ጎንደር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- እንጂባራ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ቡሬ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ
- ደብረታቦር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ደብረ ማርቆስ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ሠቆጣ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ
ደቡብ ክልል
- አዋሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- አርባ ምንጭ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ሶዶ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ዱራሜ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ሆሳዕና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ወራቤ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ቡታጅራ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ሀላባ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ይርጋለም ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ዲላ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
ትግራይ ክልል
- መቀሌ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ዶ/ር ተወልደ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ
- አክሱም ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ዶ/ር አርዕያ ካሳ ኮሌጅ
- ውቅሮ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- (ማይጨው) ጥላሁን ይግዛው ፖሊቴክኒክ
- አላማጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
- እንጦጦ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና (ቴ/ሙ/ት/ስልጠና) ኮሌጅ
- ጄነራል ዊንጌት ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
- ንፋስ ስልክ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
- ምሥራቅ አጠቃላይ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
- የካ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ልደታ ማኒፋክቸሪንግ ኮሌጅ
- አዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ቂርቆስ ማኒፋክቸሪንግ ኮሌጅ
- አቃቂ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር
- መለስ ዜናዊ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
ኦሮሚያ ክልል
- ሀሮማያ ቴክኒክና ሙያ
- አሰላ ቴክኒክና ሙያ
- ሻሸመኔ ቴክኒክና ሙያ
- መርቲ ፖሊ ቴክኒክ
- ቢሾፍቱ ቴክኒክና ሙያ
- ጂማ ቴክኒክና ሙያ
- መቱ ቴክኒክና ሙያ
- መቱ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ
- ነቀምት ቴክኒክና ሙያ
- ነቀምት ጤና ሳይንስ ኮሌጅ
- ባቱ ተራራ ቴክኒክና ሙያ
- ዶና ባርበር ቴክኒክና ሙያ
- ፍቼ ቴክኒክና ሙያ
- መርቲ ፖሊ ቴክኒክ
- አዳማ ፖሊ ቴክኒክ
- አብቦ ፖሊ ቴክኒክ
- ሰበታ ፖሊ ቴክኒክ
- ወሊሶ ፖሊ ቴክኒክ
- አጋሮ ፖሊ ቴክኒከ
- አደላ ፖሊ ቴክኒክ
- ቡሌ ሆራ ፖሊ ቴክኒክ
- ጨርጭር ፖሊ ቴክኒክ
- ደደር ፖሊ ቴክኒክ
- አርሲ ነገሌ ፖሊ ቴክኒክ
- ሀሰሳ ፖሊ ቴክኒክ
- ጊምቢ ፖሊ ቴክኒክ
- ወንጂ ፖሊ ቴክኒክ
ምንጭ፦ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የገቢዎች ሚኒስቴር የተጠናከረ የጉምሩክ ስርዓት እና የተጠናከረ ኬላ ፍተሻ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚያዙ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችና የተለያዩ አገራት ገንዘቦችም (የገንዘብ ኖቶችም) ጨምረዋል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ለሕገ-ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ዝውውር ስጋት ናቸው የተባሉ ቦታዎችን በመለየት ተጨማሪ 36 አዳዲስ የጉምሩክ ኬላዎች መቋቋማቸውን የኢፌዴሪ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
አዳዲስ ኬላዎችን በመክፈት እንዲሁም ቦታቸው ትክክል ያልነበሩ ነባር ኬላዎችን ወደ ትክክለኛ ቦታ በመቀየር ሕገ-ወጥ የገንዘብና የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ይርጋ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ተናግረዋል።
ችግሩን ለመከላከል በተደረው ጥናት በኬላዎች ላይ 1 ሺህ 400 የፖሊስ ኃይል እንደሚያስፈልግ በተጨማሪ ተገልጿል።
ጥናቱን ተከትሎ ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ፣ ስምሪቱ በጉምሩክ ኮሚሽን የሆነ ጥሩ ሥነ ምግባር የተላበሰ፣ ለቦታው የሚመጥን የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ፖሊስ እንዲቋቋምና ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ዳይሬክተሩ አቶ አዲሱ ይርጋ ገልጸዋል።
የተጠናከረ የጉምሩክ ስርዓት እና የተጠናከረ ኬላ ፍተሻ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚያዙ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችና ገንዘቦችም ጨምረዋል ነው የተባለው።
የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጀላል አብዲ በበኩላቸው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ የራሳቸውን ገንዘብ ለማግኘት በሚንቀሳቀሱ ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ከተለያዩ አገራት (በተለይም ከጎረቤት አገራት) ወደ አገር ውስጥ ይገባል ብለዋል።
የጦር መሣሪያዎቹን መዳረሻ ለማወቅ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም ከሁኔታ ግምገማ በመነሳት በአገር ውስጥ ጸጥታና የደህንነት ስጋት ያለ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ራሱን እና ንብረቱን ለመጠበቅ የጦር መሣሪያ ፍላጎት እንደ አንድ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የተለያየ ዓላማና ግብ ያላቸው የታጠቁ ቡድኖችም የጦር መሣሪያ መዳረሻ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል ዳይሬክተሩ።
የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑ ይታዋሳል።
ምንጭ፦ ኢቢሲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት የተሠራው ባለሞተር ማረሻ ተመረቀ
- አለርት ሆስፒታል ውስጥ ዘመናዊ የሕፃናት ሆስፒታል እና የአደጋ ሕክምና ማዕከል ይገነባሉ
- ዩኒቨርሲቲዎች በሦስት መስኮች ተደልድለው እንዲያስተምሩ የሚያስችል ጥናት እየተጠናቀቀ ነው
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
- ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች መሠረታዊ ችግሮች በጥናት ሊለዩ ይገባል ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት የተሠራው ለእርሻ አገልግሎት የሚውል ባለሞተር ማረሻ ተመረቀ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያን (ዶ/ር ኢንጂ.) ጨምሮ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የሮዳ ኢንጂነሪን ሠራተኞች በተገኙበት ተመርቋል።
ከዚህ ቀደም ከውጭ ሀገራት የአርሶ አደሩን ድካም ያቃልላሉ ተብለው የተገዙ ዘመናዊ የማረሻ መሣሪያዎች ከሀገራችን ድንጋያማ መሬት ጋር ባለመስማማታቸው የሚጠበቅባቸውን ጥቅም ሳይሰጡ በ አጭር ጊዜ ውስጥ ከጥቅም ውጭ ይውላሉ። ይህ በኢትዮፕያውያን ዲዛይን ተደርጎ የተሠራው ባለሞተር ማረሻ ግን ለሀገራችን መሬት ተስማሚ እንዲሆን ተደርጎ የተሠራ ነው።
ማረሻው ከተገጠመለት ሞተር ውጪ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሠራ በመሆኑ ለጥገና፣ ማሻሻያ ለማድረግና ተጨማሪ ጥቅሞችን ለመጨመር የተመቸ መሆኑን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በቀጣይ በዚሁ ባለሞተር ማረሻ ላይ አርሶ አደሩ ተቀምጦ የሚያርስበት፣ መሬቱን ለመጎልጎል የሚያስችል፣ ምርቱን ማረሻው ላይ ለመጫን የሚያስችሉ አዳዲስ ግልጋሎቶችን እንዲሰጥ ተደርጎ እንደሚዘምን የሮዳ ኢንጂነሪን ባለቤት አቶ አክሊሉ አባተ ተናግረዋል። ማጨድና መውቃት፣ እንዲሁም ምርት መሰብሰብ የሚችል መጎታችም በቀጣይ እንደሚሠራለት ተጠቁሟል። አርሶ አደሩ በቀላሉ ነዳጅ ማግኘት እንዲችል ከእፀዋት ተረፈ ምርት መሠራት የሚችል ባዮፊዩል (biofuel) እንዲጠቀምም ይደረጋል።
አርሶ አደሮቻንን እስከ ዛሬ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አላደርግናቸውም ያሉት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) በቀጣይ ችግሮቻቸውን የሚያቃልሉ ቴክኖሎጂዎችን ማላመድና መፍጠር ላይ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል። አክለውም፥ ባለሞተር ማረሻውን አርሶ አደሮች የመግዛት አቅም ኖሯቸው እንዲጠቀሙበት ለማድረግም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ይሠራል ነው ያሉት።
ባለሞተር ማረሻውን ከማዘመንና ጠጨማሪ አገልግሎቶችን አንዲያረክት ማሻሻያዎችን ከማድረግ በተጨማሪ ዋጋውም ከጥንድ በሬዎች መግዣ ባነሰ ዋጋ አርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ ጥረት ይደረጋል ተብሏል። ባለሞተር ማረሻው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በሮዳ ኢንጂነሪንግ ትብብር የተሠራ ነው።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- በአዲስ አበባ “ለሁሉ” የክፍያ ማዕከላት ተገልጋዮች መጉላላት እየገጠማቸው ነው
- የሴቶችን ጫና የሚያቃልሉ የተወሰኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባሉ
- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ነው
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
- ቮልስዋገን በኢትዮጵያ የመኪና መገጥጠሚያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፤ የጀርመን የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በስፋት ለመግባት እያመቻቹ ነው
የሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ከሚያዚያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል። ዶ/ር ጀማል ዩኒቨርሲቲው ውስጥ እ.ኤ.አ ከ2003 ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ቦታዎች አገልግለዋል።
ጅማ (ሰሞነኛ) – ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለፕሬዝዳንትነት ቦታ ብቃቱና ፍላጎት ያላቸዉ አመልካቾች እንዲወዳደሩ ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ባወጣዉ ግልጽ ማስታወቂያ መሠረት አመልካቾች መረጃቸዉን በማስገባት በተለያዩ ደረጃዎች ዉድድር ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል::
በምርጫ ሂደቱም ከ250 በላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የዩቨርሲቲዉ ሴኔት እና የሥራ አመራር ቦርድ መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የቃለ-መጠይቅ ፓናል በማካሄድ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩና ማጣሪያዎችን አልፈው የደረሱ 9 ዕጩዎችን በመገምገም 5 ዕጩዎችን ለዩኒቨሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ አስተላልፏል።
የዉድድሩ ሂደት የተመራዉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣዉ መስፈርት ሲሆን፤ ሂደቱን ለመምራት አምስት ሰዎችን የያዘ ኮሚቴ ተቋቁሞ በየደረጃዉ ግምገማ ሲያካሄድ ቆይቷል። ኮሚቴዉ ከቦርድ አባላት፣ ከሴኔት አባላት፣ ከተማሪ፣ ከመምህራን እና ከአስተዳደር ሠራተኞች ተወካይ የተዉጣጣ ሲሆን የዉድድር ማስታወቂያ ከማዉጣት ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ ጉባዔ የሂደቱን ዉጤት እስከ ማሳወቅ ድረስ በትጋት ሲሠራ ቆይቷል።
በዚሁ መሠረት የዩኒቨርሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ ሚያዚያ 02 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሔደው ልዩ ጉባዔ 3 ዕጩዎችን (ዶ/ር ጀማል አባፊጣ፣ ፕሮፌሰር አርጋዉ አምበሉ እና ዶ/ር ናቃቸዉ ባሹን) በዕጩነት ለሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አቅርቧል:: የሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ዶ/ር ጀማል አባፊጣን ከሚያዚያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል።
ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የዩኒቨርሲቲዉ ነባር መምህር እና ተመራማሪ ሲሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች በዩኒቨርሲቲውና ከዩኒቨርሲቲው ውጭ በሃላፊነት ያገለገሉና በአሁኑም ወቅት የማኅበረሰብ አገልግሎት ቢሮ ዳይሬክተር ሆነዉ እያገለገሉ ይገኛሉ። ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስታቲስቲክስ (BSc in Statistics)፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ (MA in Economics)፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በደቡብ ኮርያ ቻንችኦን ከተማ ከሚገኘው ካንግዎን ናሽናል ዩኒቨርሲቲ (Kangwon National University; Chuncheon, South Korea) በግብርና ግብዓቶች ምጣኔ ሀብት (Agricultural Resources Economics) አግኝተዋል።
ስለ ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ይህን ማስፈንጠርያ በመጫን ሙሉ መረጃ ማግኘት ይችላሉ።
ምንጭ፦ ጅማ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና እና ኪነ-ሕንፃ ዘርፍ ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ
- የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንፃ (አርክቴክቸር) ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን አስመረቀ
- አክሱም ዩኒቨርሲቲ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምህንድስና ትምህርት ክፍል ሊከፍት ነው
- ዩኒቨርሲቲዎች በሦስት መስኮች ተደልድለው እንዲያስተምሩ የሚያስችል ጥናት እየተጠናቀቀ ነው
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
ነቀምቴ (ሰሞነኛ) – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በኦሮሚያ ክልል፣ ምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር፣ ነቀምቴ ከተማ ውስጥ የተገነባውን የወለጋ ስታድየም መርቀው ከፈቱ። ስታዲየሙ በግንባታዉ በዓይነቱ ልዩ እና የገዳ ስርዓትን 8 ዙር ቅርፅ ይዞ የተገነባ መሆኑ ተጠቁሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ስታድየሙ በምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል ስፖርት መነቃቃት ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
”ወለጋ አገሪቱ በድርቅ በተጠቃችበት ጊዜ ሌላውን ማህበረሰብ ያስጠለለ አካባቢ ነው” ያሉት ዶ/ር አብይ፥ ”ምሥራቅ ወለጋን ማልማት ምዕራቡን የአገሪቱ ክፍል በልማትና በንግድ ማስተሳሰር ነው” ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው አንድነትና ሕዝባዊ ትብብር ካለ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል የወለጋ ስታድየም ማሳያ ነው ብለዋል። ከእኛ አልፎ ለሌላው የምትተርፍ ኦሮሚያን ለመፍጠር ከአካባቢው ልማት መነሳት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የስታድየሙ ግንባታ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተሾመ ገመዳ በ1999 ዓ.ም. የተጀመረው የወለጋ ስታድየም የመንግስትን እጅ ሳይጠብቁ ሕዝብ በራሱ ተሳትፎ ፕሮጀክት ቀርፆ ሰርቶ ማስመረቅ እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። የወለጋ ስታድየም በዝቅተኛ ዋጋ በስርዓት በመገንባቱ ልዩ የሚያደርገዉ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል።
ለስታድየሙ ግንባታ እስካሁን 196 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን በቀጣይ የወንበርና ሌሎች የማጠናቀቂያ ወጪዎችን ሲጨምር 226 ሚሊዮን ብር ወጪ ይሆንበታል ተብሎ ይገመታል። እስካሁን የህብረተሰቡ ተሳትፎ 48 ሚሊዮን ብር ለስታድየሙ ግንባታ ውሏል።
የወለጋ ስታድየም 30 ሺህ የተመልካች ወንበሮች ያሉት ስቴድየሙ 17 የስፖርት አይነቶችን ያስተናግዳል ተብሏል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ከወለጋ ስታድየም ምርቃት መልስ ነቀምቴ ከተማ በነበሩበት ጊዜ ከከተማው እና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም ወቅት ትምህርት አጠናቀው ለሚገኙ ወጣቶች መንግስት የሥራ ዕድል እንዲፈጥርላቸው የነቀምቴ ከተማና አከባቢዋ ነዋሪዎች ጠየቁ። በውይይቱ ነዋሪዎች እንዳነሱት፤ የምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል ትልቁ ችግር የሥራ አጥነት ነው።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በፌዴራል ደረጃ የመጣው ለውጥ ወደታች መውረድ እንዳለበት ገልጸዋል።
የወለጋ ህዝብ ከለውጥ አመራሩ ጎን እንደተሰለፈ የገለጹት ተሳታፊዎቹ ለውጡን የመቀልበስ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች በመካከል በመግባት ሕዝቡን ከአመራሩ ጋር ለማጣላት እንደሚሞክሩ ጠቁመዋል።
በፌደራል ደረጃ የታየው የሴቶች የአመራርነት መዋቅር በተለይ በነቀምቴ ከተማ እንዲሠራበት እና ሙስና እንዲቀንስ መንግስት ጠንክሮ እንዲሠራ ጠይቀዋል።
የነቀምቴ ከተማና አከባቢዋ የሥራ አጥነት ችግር ያነሱት ነዋሪዎቹ በተለይም የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ዝግጅት እያላቸው በከተማ ጎዳና ላይ የፈሰሱት ወጣቶች መንግስት በአፋጣኝ የሥራ ዕድል እንዲፈጥርላቸው ጠይቀዋል።
በነዋሪዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች የክልሉ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ምላሽ ሰጥተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በሦስት መስኮች ዩኒቨርሲቲዎቹን መደልደል ያስፈለገው፥ እስካሁን የትምህርት ተቋማቱ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ለማስተማር ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ ስላልነበር እንደሆነ ተነግሯል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር፣ የቲቺንግና የፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ ተብለው ለሦስት ተከፍለው እንዲሠሩ የሚያደርግ ጥናት እያለቀ መሆኑንና በጥናቱ ውጤትም ላይ በቅርቡ ውይይት እንደሚደረግ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ሂሩት ወልደማርያም (ዶ/ር) ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለጹ። ምደባው ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና በትኩረት አቅጣጫ የመደልደል ነገር በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተመልክቷል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ለምርምር የተሻለ የመሠረት ልማትና የሰው ኃይል ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ዩኒቨርሲቲ መደብ ውስጥ እንደሚገቡና በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ፕሮግራሞችንም እንደሚሰጡ አስረድተዋል። የንድፈ ሐሳብና ተግባራዊ ትምህርት አጣምረው የሚሰጡ ፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲዎች መደብ ሥር የሚገቡት ለተግባር ትምህርት የተሻለ የመሠረተ ልማት ዝግጅት ያላቸው ይሆናሉ ተብሏል። ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ሠልጣኞችን እንዲያፈሩና ለቴክኒክና ሙያ ተቋማትም የበቁ መምህራንን እንዲያወጡ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ዶክተር ሂሩት ናቸው። የተቀሩት የማስተማር ተግባር (ቲቺንግ) ላይ የሚያተኩሩ መርሀ ግርብሮች ላይ የሚያተኩሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሆነው እንደሚቀጥሉም ታውቋል።
በሦስት መስኮች ዩኒቨርሲቲዎቹን መደልደል ያስፈለገው፥ እስካሁን የትምህርት ተቋማቱ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ለማስተማር ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ ስላልነበር እንደሆነ ተነግሯል።
◌ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
“ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማሩም፣ በምርምሩም፣ በቴክኖሎጂውም፣ በግብርናውም፣ በሁሉም ዘርፎች ነው የሚያስተምሩት። ይህ ደግሞ ውጤታማ ሊሆኑ በሚችሉበት መስክ እንዳይሠሩና ሀብትም እንዲበታተን አድርጓል” ያሉት ሚኒስትሯ፥ ድልድሉም ዩኒቨርሲቲዎቹ እንዳላቸው የመሠረት ልማት ዝግጅትና ያሉበት አካባቢ ከሚሰጣቸው መልካም አጋጣሚ አንፃር እየታየ ነው ብለዋል።
እንደ ላሊበላና አክሱም ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አርኪዮሎጂ ላይ ያተኮሩ የልህቀት ማዕከላት (center of excellence) ቢሆኑ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኙ፣ በግብርና ላይ ተሞክሮና ታሪክ ያላቸው እንደ ሐሮማያ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በግብርና ውጤታማ የሆነ ባለሙያዎች ማፍራት እንደሚችሉ አስረድተዋል። “ሁሉም ላይ እንሥራ ሲሉ ግን ችግር ነው። በሁሉም ዘመናዊ ማሽኖችን፣ የምርምር ግብዓቶችን፣ ሪፈራል ሆስፒታሎችን መገንባትና ማሟላት አይቻልም፣ የአገርም ሀብት ይባክናል” ብለዋል።
ምንጭ፦ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከስዊድኑ ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ (The University of Gothenburg) ጋር በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤን የሚመለከት ትምህርት ለመስጠት የሚያስችላቸው የመግባቢያ ሰነድ ይፈርማሉ።
በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ መስክ በሀገራችን ያለውን የባለሙያ እጥረት የሚቀርፍ መነሻ ሀሳብ ከስዊድን ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ የመጡ መምህራን ለክቡራን ሚንስትሮች ገለፃ አድርገዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሀገራችን ኢትዮጵያ ከስዊድን መንግስት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑ በተለይ በኪነ-ሕንፃ ትህምርት ዘርፍ ያላቸው ልምዶች ታሪካዊና ጠናካራ ግንኙነት የተፈጠረበት መሆኑ ብዙ ይወሳል።
በመሆኑም የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስዊድን ውስጥ በትልቅነቱ ሁለተኛ ከሆነው ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ (The University of Gothenburg) ጋር በትብብር ለመክፈት ያሰበው የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ እውን እንዲሆንና የቅርስ ጥገና ተግባራዊ ትምህርት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥ ታስቦ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በኩል ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርኪዮሎጂ (archeology) ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር መንግስቱ ጎበዜ፥ የታሰበው የትምህርት መርሀግብር ለክቡራን ሚኒስትሮች (ለፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና ለወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት፥ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ) የሥልጠናውን ዓላማና ግብ የሚያግባባ ገለፃና ትውውቅ አድርገውላቸዋል።
በመቀጠልም በልዑካኑ በስዊድን ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በኩል የመጡት መምህራን ያላቸውን ዝግጁነትና ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲሁም የገጠሩ ሕዝብ ባህላዊ ሀብቱን እየተወ ወደ ከተማ ከሚኮበልል እዛው በቅርሱ ተጠቃሚ የሚሆንበት መሠረት የጣለ ልምድ መኖሩን የሚያብራራ ገለጻ በ‘Bosse Lagerqvist’ እና ‘Lars Runnquist’ የልዑኩን ቡድ ኑን በመወከል ገለፃ አደርገዋል። ተመራማሪ ፕሮፌሰሮች በነሱ በኩል ተግባራዊ ትምህርቱ ከቁሰቁስ አቅርቦት እንደሚደገፍ ጭምር በትብብር የሚሠራበት ሁኔታ ለመፍጠር በቻርትና ስዕላዊ መግለጫዎች ማብራሪያ አድርገዋል።
◌ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
ለመርሀግሩ ማጠቃለያ ክቡራን ሚኒስትሮችም በበኩላቸው በሁለቱም ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት መልካም በሚባል ደረጃ የደረሰ መሆኑን በማመስገን፥ ያቀረባችሁት ሀሳብ የሚጠቅመንና እንደኢትዮጵያ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ መስክ የሚሰጡ ትምህርቶች በንድፈ-ሀሳብ ብቻ በመሆኑ በትብብር ስለምንሠራው ብዙ ባለሙያዎችን የምናፈራበት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የትምህርት ማስተማሪያ መርሀግብሩ የሁለተኛ ዲግሪ ለመስጠት የሚያበቃ ሲሆን፥ ለዚህ የመግባቢያ ሰነድ በቅርብ ጊዜ እንደሚፈረም እንዲሁም ተግባራዊ ትምህርቱ የሚሰጥበት ቦታ አንድ ካምፓስ በላሊበላ ቅርጫፍ የሚዘጋጅበት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የዓለም የውሃ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ መጋቢት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. “ማንንም ባለመተው” (“Leaving no one behind”) በሚል መሪ ቃል ተከብሯል። የዓለም የውሃ ቀን በዓለም አቀፍ ለ27ኛ ጊዜ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን፥ በሥነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር፣ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት ተዎካዮችና የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በበዓሉ መርሀግብር ላይ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሚተገበር የሁለተኛው ዋን ዋሽ ብሔራዊ መርሃ ግብር (One WASH National Program) ይፋ መደረጉን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሁለተኛው ዋን ዋሽ ብሔራዊ መርሃ የገጠር፣ የከተማና የተቋማት ንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ንጽሕና እና የጤና ንጽሕና አጠባበቅ (water, sanitation and hygiene) የሚያካትትና በሀገር አቀፍ (ብሔራዊ) ደረጃ የሚተገበር፣ የመጠጥ ውሃ፣ሳኒቴሽንና ሃይጅንን በገጠር፣ በከተማ፣ በት/ቤቶችና በጤና ጣቢያዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የሚረዳ እንደሆነ ተገልጿል።
● SEMONEGNA on Social Media: Facebook | Twitter | Instagram | Pinterest
ይህ መርሀግብር (ፕሮግራም) በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በጤና ሚኒስቴር፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ በልማት አጋር አካላትና በህብረተሰቡ ቅንጅት የሚተገበር ነው።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ዋን ዋሽ መርሀግብር (One WASH Program) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለየት ያለ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እየተተገበረ ያለ ፕሮግራም መሆኑን ጠቁመው፥ መንግሥት፣ የልማት አጋሮችና ሕብረተሰቡ አንድ ላይ ሀብት በማሰባሰብና ወደ አንድ ቋት በማስገባት፣ አንድ ላይ በማቀድ፣ አንድ ላይ አፈጻጸሙን በመከታተልና በመገምገም፣ አንድ ላይ ሪፖርትም በማድረግ የሚፈጸም ፕሮግራም መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
የመጀመሪያው የዋን ዋሽ ፕሮግራም ባለፉት አራት ዓመታት ከስድስት ወራት ሲተገበር መቆየቱን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ሁለተኛው የዋን ዋሽ ፕሮግራም ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ትግበራ እንደሚገባና የአምስት ዓመታት ፕሮግራም መሆኑን ተናግረዋል። በመጀመሪያው ፕሮግራም 3ነጥብ6 ሚሊየን ሰዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፥ 90 በመቶ ያህል ተግባራዊ መደረጉ ነው የተገለጸው። በሚቀጥሉት ወራትም እቅዱን በመቶ በመቶ ለማካናዎን እንደሚሰራ ተጠቁሟል።
ሁተለኛው ዋሽ በመጀመሪያው የዋን ዋሽ ፕሮግራም ይተገበር ከነበረው በገጠርና በከተማ፣ በጤና ተቋማትና በት/ቤቶች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽንን ለህብረተሰቡ ከማቅረብ በተጨማሪ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚተገበረውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የመጠጥ ውሃ ፕሮግራም (Climate Resilient WASH) የተካተተበት እንደሆነ ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ተናግረዋል።
በሁለተኛው የዋን ዋሽ ፕሮግራም ከመንግሥት፣ ከልማት አጋሮች፣ ከህብረተሰቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ፣ በአነስተኛ ወለድና በረጅም ጊዜ ክፍያ የሚከፈል ብድር ከአበዳሪ ተቋማት በጠቅላላው 6.5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሀብት ተሰባስቦ ለፕሮግራሙ ማስተግበሪያ ይውላል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው።
ዓመታዊው የትምህርት ጉባዔ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት ተጠናቆ ለመንግስት ውሳኔ በሚቀርብበት፣ 5ኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር የሦስት ዓመት አፈጻጸም የሚዳሰስበት፣ ለቀጣይ ሥራ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነበር።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የሚያዘጋጀው 28ኛው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በትግራይ ብሔራዊ ክልል መቐለ ከተማ ተካሔደ። በየዓመቱ ሚካሄደው እና ከመጋቢት 12 እስከ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በቆየው 28ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በመድረኩ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ከሁሉም ክልሎችና ከተለያዩ ከተማዎች አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች የተውጣጡ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለ ድርሻ አካላት እንዲሁም የትምህርት ልማት አጋር አካላት በሀገር አቀፉ የትምህርት ጉባዔ ተሳታፊ ሆነዋል።
● SEMONEGNA on Social Media: Facebook | Twitter | Instagram | Pinterest
ዓመታዊ ጉባዔው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት ተጠናቆ ለመንግስት ውሳኔ በሚቀርብበት፣ 5ኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር የሦስት ዓመት አፈጻጸም የሚዳሰስበት፣ ለቀጣይ ሥራ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው አቅጣጫ የሚቀመጥበት ሁነኛ ጉባዔ እንደነበር የትምህርት ሚኒስቴር ዘግቧል።
በተጨማሪም በአፈፃጸም ሂደት የተገኙ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ለአብነት የትምህርት ጥራትና የትምህርት ቤቶች ደረጃ ምደባ ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት እንደተደረገባቸው ታውቋል።
የዘንድሮውን ትምህርት ጉባዔን ለየት የሚያደርገው ሀገር አቀፍ የተማሪዎች ስፓርት ጨዋታ ጋር አቀናጅቶ እንዲካሄድ መደረጉ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።
The 28th National Education conference is being held in Mekelle. Major agendas are; the new Education Road Map strategic issues, ESDP V performance evaluation and 2018 National Learning Assessment study findings and future actions to be taken in the remaining two years. pic.twitter.com/h6XTlcTWTv
— Tilaye Gete Ambaye (PhD) (@DrGete) March 22, 2019
ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የዓለም የውሃ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ተከበረ።
- በኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን አገራዊ የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅድ ይፋ ሆነ
- ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች መሠረታዊ ችግሮች በጥናት ሊለዩ ይገባል ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ
- ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
- ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ፤ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ይጀመራል
ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ልዑካን ቡድን አባላት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በሙያቸው እንዲያግዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ተክተሎ የመጡ ናቸው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲካሄድ የቆየው መንግስት ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያለውን ዝግጁነት የሚለይና ለችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ አውደ-ጥናት ተጠናቀቀ።
በአውደ ጥናቱ የመንግስት አግልግሎት አሰጣጥ፣ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያለው ዝግጁነት፣ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ክፍተት ተለይተውበታል – ሚኒስቴሩ እንደዘገበው።
የጤና አስተዳደር፣ የታክስ አሰባሰብ ስርዓት፣ የመረጃ ግንኙነት (ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን) ቴክኖሎጂ ደኅንነት፣ በባንክ አገልግሎት፣ በኢንሹራንስ አገልግሎት፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኦዲት አገልግሎት፣ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት፣ የውሃ አወጋገድ ላይ ክፍተቶች ተለይተዋል።
አሜሪካ ውስጥ ቨርጂንያ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ (Virginia International University; Fairfax, VA) መምህር በሆኑት ዶ/ር ተፈራ በየነ የተመራው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ልዑክ ክፍተቶቹን ከለዩ በኋላ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
◌ ከ7ሺህ 800 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በመላው አገሪቱ ሊቋቋሙ ነው
ባለሙያዎቹ በኢንሹራንስ፣ በህክምና ቴክኖሎጂ፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኑኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአሜሪካን ሀገር በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የፋይናንስ ዳይሬክተሮች እና ሌሎችም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ከቡድኑ ጋር ለ1 ሳምንት ክፍተቶችን እና ጉድለቶችን የመለየት ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል።
የሚመለከታቸው አካላት በየዘርፉ የሚደረጉ ማስተካከያዎችን በኃላፊነት ወስደው ወደ ተግባር የመቀየር ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። በማጠቃለያው ላይ፥ ልዑካኑ የኢትዮጵያ መንግስት ወይም የሚመለከተው መንግስታዊ ተቋም ዕድሉን ከሰጠን የሀገራችንን ችግር ለመፍታት በቂ አቅም አለን ብለዋል። ወደፊትም በማንኛውም መልኩ ሀገራቸውን ለማገዝ ቃል ገብተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታዎች ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) እና ጀማል በከር ልዑካኑ ሀገራቸውን ለመረዳት ያላቸውን ቁርጠኝነት በማድነቅ ምስጋና አቅርበዋል።
የልዑካን ቡድኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በሙያቸው እንዲያግዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ተክተሎ የመጡ ናቸው።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
- በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እስካሁን ድረስ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቧል
- ኢትዮጵያ በአሜሪካ ሁለተኛ ቆንስላ አጠቃላይ ጽህፈት ቤት በሚኒሶታ ግዛት ከፈተች
- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ መቋቋሙን ተከትሎ ወደ ተግባር ለመግባት የመዋቅርና የሕግ ማዕቀፍ ሥራን አጠናቀቀ
- ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
- ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ፤ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ይጀመራል