Search Results for 'አማራ ክልል'

Home Forums Search Search Results for 'አማራ ክልል'

Viewing 15 results - 91 through 105 (of 120 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሴቶችን ጫና በሚያቀልሉ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ መሆኑን የሚኒስቴሩ የሴቶች፤ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ገብረሥላሴ አስታውቀዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በ7 ክልሎች ውስጥ በቴክኖሎጂ ውጤቶች ሊደገፉ የሚችሉ ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ያሉ ሥራዎችን በጥናት ለይቷል።

    ችግሮቹ የተለዩት በአፋር፤ በቤኒሻንጉል፤ በጋምቤላ፤ በደቡብ፤ በአማራ፤ በትግራይና በሶማሌ ክልል በተጠናው ጥናት መሠረት መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

    በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የምግብ ማብሰያ፤ በሬ ለምኔ ዘመናዊ ማረሻ እና የቆጮ መፋቂያ ማሽን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተገልጿል። ዘመናዊ የበቆሎ መፈልፈያና የአፋ አሊ (የአፋር ቤት) መሥሪያ በመካከለኛ ጊዜ ወደ ሥራ ለማስገባት የታቀደ ሲሆን በመስመር መዝሪያ እና ከጉድጓድ ውሃ ማውጫ መሣሪያ ደግሞ በረጅም ጊዜ ወደ ሥራ ለማስገባት በዕቅድ ተይዟል።

    የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሴቶችን ጫና በሚያቀልሉ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው። የሚኒሰቴሩ የሴቶች፤ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ገብረሥላሴ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሴቶችን የሥራ ጫና የሚያቃልሉና ምርታማ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ለስኬታማነቱ የሚመለከታቸው ሁሉ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ዳይሬክተሯ ጥሪ አቅርበዋል።

    ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የሴቶችን ጫና የሚያቃልሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች


    Semonegna
    Keymaster

    ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ መኖሪያ ቤታቸው ለፈረሱባቸው ዜጐች ተገቢዉን ድጋፍ እና ተመጣጣኝ ካሳ በአስቸኳይ እንዲያደርጉና በሠላም የመኖር መብታቸውን እንዲያስጠብቁላቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ጠይቋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ ለገጣፎ ከተማ፣ የዜጐች መኖሪያ ቤት መፍረሱ በእጅጉ እንዳሳሰበው የገለፀው የተባበሩት መንግስታት (ተመድ)፥ ጉዳዩን በትኩረት እንደሚመረምር አስታውቋል። በተባበሩት መንግስታት የመኖሪያ ቤት ምጣኔ ኃላፊዋ ለይላኒ ፋራህ (Ms. Leilani Farha) እንደገለፁት፥ በለገጣፎ 12ሺህ ቤቶች እንዲፈርሱ መወሰኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ቤት አልባ አድርጐ፣ ለእንግልት ይዳርጋል፤ ይህም ግልጽ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ብለዋል።

    ስለ ቤቶቹ መፍረስ መረጃው ለተቋማቸው መድረሱን ያረጋገጡት ለይላኒ ፈራህ፥ በቀጣይ ጉዳዩ በልዩ መርማሪዎች ተመርምሮ፣ በዚህ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ወገኖች እንዲጋለጡ ይደረጋል ብለዋል። የዜጐችን መኖሪያ ቤት በዚህ መልኩ ማፍረስ በተባበሩት መንግስታት፣ ሀገራት ቃል ኪዳን የገቡለትን የማንኛውም ዜጋ፣ መጠለያ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት በእጅጉ የሚፃረር ነው ብለዋል – ኃላፊዋ።

    በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) በለገጣፎ ዜጐች መጠለያ አልባ መደረጋቸውን በጽኑ አውግዞ፥ ቤት ለፈረሰባቸው ወገኖች፣ የፌደራል መንግስትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተገቢውን ድጋፍና ተመጣጣኝ ካሣ በአስቸኳይ እንዲያቀርብ እንዲሁም እየተካሄደ ያለው የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስና ዜጐችን የማፈናቀል ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል።

    የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በጉዳዩ ላይ ያወጣው መግለጫ የሚከተለው ነው።

    ዜጐችን ማፈናቀል በአስቸኳይ ይቁም!!

    በኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ዙሪያ ልዩ ዞን የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር በ01 እና 02 ቀበሌዎች፣ ጭላሎ፣ ወበሪ፣ ለገዳዲ ቄራ፣ ገዋሳ፣ እና በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን “ህገወጥ ግንባታዎች ናቸው፤ ለአረንጓዴ ልማት ይፈለጋሉ” በማለት ከየካቲት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በኃይል በማፍረስ ላይ ይገኛል። የከተማዋ ከንቲባ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፁትም በቀጣይም ከ12 ሺህ በላይ ቤቶችን እንደሚያፈርሱም አረጋግጠዋል። ሰመጉ ስለጉዳዩ የከተማዋን ከንቲባ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

    ሰመጉ ያነጋገራቸው ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው በርካታ ዜጐች እንዳስረዱት ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግስት ላይ እምነታቸውን ጥለው በተለያየ ወቅት በገዙት ቦታ ላይ የገነቡትን መኖሪያ ቤቶች በመገንባት እና አካባቢ በማልማት ከተማዋን ለእድገት አብቅተዋታል። በእነዚሁ ዓመታት ውስጥም የአካባቢው የመንግስት ኃላፊዎች እያወቁት የመብራት እና ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መሆናቸውን፣ ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን፤ በተለያዩ አስተዳደራዊና የልማት እንቅስቃሴ ላይ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አስረድተዋል። ይሁን እንጂ የከተማዋ አስተዳደር ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመተባበር ከነዋሪዎች ጋር በቂ ምክክር ሳያደርግ እና ሊመጣ የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ላይ ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ሳይኖረው ቤቶችን በማፍረስ ህፃናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች ሜዳ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል። በዚህም የዜጐችን ለኑሮ አመቺ በሆነ አካባቢ የመኖርን መብት፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃና ምግብ የማግኘት መብት፣ የአካል ደህንነት መብት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ መብቶች ተጥሰዋል።

    የከተማው አስተዳደር የወሰደውን የኃይል እርምጃ ይበልጥ አስከፊ እና አጠያያቂ የሚያደርገው ከመኖሪያቸው በ7 ቀናት የማስጠንቀቂያ ጊዜ በኃይል እንዲፈናቀሉ ለተደረጉ ዜጐች ምንም ዓይነት አማራጭ የመኖሪያ ስፍራም ሆነ ጊዜያዊ የመጠለያ ስፍራ ያልተዘጋጀላቸውና ሰብዓዊ እርዳታም ያልተደረገላቸው መሆኑ ነው።

    የፌዴራል መንግስትም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በዜጐች ላይ እየተፈፀመ ያለውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት፤ እየተካሄደ ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ማፍረስና ዜጐችን ማፈናቀል በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ፣ መኖሪያቸው ለፈረሱባቸው ዜጐች ተገቢዉን ድጋፍ እና ተመጣጣኝ ካሳ በአስቸኳይ እንዲያደርጉና በሠላም የመኖር መብታቸውን እንዲያስጠብቁላቸው ሰመጉ ይጠይቃል።

    ምንጮች፦ አዲስ አድማ ጋዜጣሰመጉሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ


    Semonegna
    Keymaster

    የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ በዚህ ፕሮጀክት የተሳተፉ ተመራማሪዎችን ያሉትን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ለዚህ በመብቃታቸው ምስጋና ቸረዋቸዋል።

    ደብረ ብርሃን (ሰሞነኛ)– የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ከኢፌዴሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ይምሎ ቀበሌ በተቀናጀ የአሳ፣ የዶሮ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ሲያካሂድ የቆየውን የምርምር ፕሮጀክት አጠናቆ ለዞኑ አስተዳደርና ለአካበቢው ማኅበረሰብ አስረከበ።

    በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ወቅት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህርና መሪ ተመራማሪ ዶ/ር ገዛኸኝ ደግፌ እንደተናገሩት ምርምሩ በትንሽ ቦታ አሳን፣ ዶሮንና አትክልትን አቀናጅቶ ማልማት የሚያስችል የቴክኖሎጅ ዕውቀትን በመጠቀም የአሳ፣ የዶሮና የአትክልት ልማቱን አቀናጅቶ መሥራት እንደሚቻል ነው ብለዋል። በዚህም የዶሮ ኩስን ለአሳዎች ምግብ እንዲውል እንዲሁም “vermicompost” ቆሻሻን ወደ ጠቃሚ ነገርነትና ማዳበሪያነት የሚቀይሩ ትሎችን ለዶሮዎችና ለአሳ ምግብነት እንዲውል የሚያስችል እንደሆነ አብራርተዋል።

    በምስራቅ ጎጃም ዞን ስንዴ አምራች ወረዳዎች ለገበሬዎች የቀረቡላቸው ኮምባይነሮች በምርታቸው ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ እያደረጉ ነው

    አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳደሪ እንዳሉት ይህ ለምርቃት የበቃው የምርምር ሥራ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዞኑ ከሚያከናውናቸው ምርምሮች አንዱ ሲሆን ፣ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፈጻሚነትና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ የተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ዋና አስተዳዳሪው አክለው እንዳስታወቁት ይህንን ምርምር በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለማስፋፋት ትልቅ ኃላፊነትና አደራ የተጣለባቸው መሆኑን አውስተው ለተግባራዊነቱም እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

    የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ባደረጉት ንግግር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ከሚደግፋቸው በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በሚባል ደረጃ ከ60 በላይ ምርምሮች መካከል የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አንዱና ውጤታማው በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በሚችሉ ትናንሽ ፕሮጀክቶች በመደገፍ የሀገራችንን ልማት ማረጋገጥ ይኖርብናል ብለዋል። ይህን ፕሮጀከት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች እንዲተላለፍ ማኑዋልና ስታንዳርድ ተዘጋጅቷል። የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርም በአማራ ክልል ለሚገኙ ሁሉም ዞኖች እንዲያደርስ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሰራጭ አናደርጋለን ብለዋል።

    ዶ/ር አልማዝ አፈራ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት በበኩላቸው በዚህ ፕሮጀክት የተሳተፉ ተመራማሪዎችን ያሉትን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ለዚህ በመብቃታቸው ምስጋና ቸረዋቸዋል። እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለፃ፥ በሀገራችን እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ሥራ-አጥ ወጣቶች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን እንደነዚህ ዓይነት የምርምር ሥራዎች ደግሞ ወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ በማድረግ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል። ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲም ብዙ የምርምር ውጤቶች ያሉት ሲሆን እነዚህን ምርምሮች ወደ ፕሮጀክት መቀየር የሚያስችል ተሞክሮ ስለሆነ ይህ ትልቅ ማሳያ ይሆነናል ብለዋል። በመጨረሻም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርንና የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳደርን ላደረጉት ድጋፍና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

    ምንጭ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የግብርና ምርምር ፕሮጀክት


    Anonymous
    Inactive

    የትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም (ትእምት) ለመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታል 11 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
    —–

    የትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም የበጎ አድራጎት ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ታረቀ የገንዘብ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ድጋፉ ሆስፒታሉ የተሻለና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ለማጠናከር በማሰብ ነው።

    የመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታል ለረጅም ዓመታት ከአፋር፣ አማራና ሌሎች አጎራባች ክልሎች ለሚመጡ ህሙማን ጭምር አገልግሎት መስጠቱን አስታውሰው፣ ተቋሙ ከሚሰጠው አገልግሎት እንጻር ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች ሳይሟሉለት መቆየቱን አስታውሰዋል።

    በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የህሙማን ህክምናና እንክብካቤ የሥራ ሂደት ተጠባባቂ አስተባባሪ አቶ በሪሁ መስፍን የገንዘብ ድጋፉ ሆስፒታሉ ያለበትን የህክምና መሳሪያዎች ችግር በተወሰነ ደረጃ እንደሚፈታ ተናግረዋል።

    የገንዘብ አርዳታው በሆስፒታሉ የሚገኙትን ያረጁ የህክምና መሳሪያዎች፣ የላቦራቶሪ ዕቃዎችና ኬሚካሎችን እጥረት በአጭር ጊዜ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ይብራህ አለማየሁ ናቸው።

    የመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታል በዓመት ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህሙማን አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን እስከ 5 ሺህ ነፍሰጡር እናቶችንም እንደሚያዋልድ ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

    የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

    Semonegna
    Keymaster

    ጎንደር (ሰሞነኛ)– በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እየተተገበረ ለሚገኘው የጤና መረጃ አብዮት ትልቅ የሰው ኃይል የሚፈጥር የቀጠና/ወረዳ ጤና መረጃ ሥርዓት (District Health Information System 2 – DHIS2) አካዳሚ እና የኤለክትሮኒክስ ጤና ፈጠራ ቤተሙከራ (e-health innovation lab) በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም ተመረቀ።

    በምረቃ ፕሮግራሙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባው ገበየሁ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሄልዝ ኢንፎርማቲክስ (Health Informatics) ትምህርት ክፍል የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች፣ የአቅም ግንባታ እና የሜንተርሽፕ ድጋፍ ፕሮጀክትን (Capacity Building and Mentorship Project – CBMP) ከሚተገብሩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተሳታፊ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

    VIDEO: Ethio-American Doctors Group (EADG): Building a regional healthcare system & medical tourism

    የምረቃ መርሀግብሩን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የተመረቀው አካዳሚ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች እየተተገበረ የሚገኘውን የአቅም ግንባታ እና የሜንተርሽፕ ድጋፍ ፕሮጀክት (CBMP) ለመደገፍ ታስቦ የተከፈተ መሆኑን ገልፀው፤ በተለይ በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚገኙ የጤና ተቋማት የሰው ኃይል በማሰልጠን ትልቅ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ሀገሪቱ የያዘችውን የጤና መረጃ ሥርዓት በማዘመን የልህቀት ማዕከል ለመሆን ዩኒቨርሲቲው እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ለተሳታፊዎች ለፕሮጀክቱ ቡድን አባላት እዲሁም ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ለክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ምስጋና አቅርበዋል ዶ/ር ደሳለኝ በንግግራቸው መብቂያ።

    በሀገራችን የሚታየው የጤና መረጃ አያያዝ ሥርዓት ከማሰባሰብ እስከ መረጃ መተንተን የሚታዩ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ እንደ DHIS2 ዓይነት ሥርዓቶችን መጠቀም ግድ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አበባው፥ ዩኒቨርሲቲው በትክክለኛው ሰዓት አካዳሚውን በመክፈቱ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል። ዶ/ር አበባው አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን መስጠት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው የተጀመረው ሥራ እንደሀገርም እንደ ዩኒቨርሲቲም የሚያኮራ ነው ብለዋል።

    በአሁኑ ሰዓት 90 በመቶ የሚሆኑ የጤና ተቋማት በDHIS2 ሥርዓት ሪፖርቶችን ማቅረብ መጀመራቸው ከጤና ጥበቃ ሚንስተር የመጡ ኃላፊዎች ተናግረዋል። መሆኑም ተመርቆ የተከፈተው አካዳሚ የጤና ኬላዎችን በመከታተል እና በመገምገም ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም ወረዳዎችን በመረጃ አያያዝ ሥርዓት ሞዱል የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ኃላፊዎች ተናግረዋል።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ተቀራርቦ እየሠራ የሚገኘው ሥራ ለሌሎች ተቋማትም አርአያ መሆኑን የገለፁት ተሳታፊዎች፥ የ DHIS2 አካዳሚ በዩኒቨርሲቲው መከፈቱ የዩኒቨርሲቲውን አመራሮች እና አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ የሚያኮር ሥራ መሆኑ ገልፀዋል።

    በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተያዘው የጤና መረጃ አብዮት ዙሪያ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፥ ዶ/ር ቢንያም ጫቅሉ በአቅም ግንባታ እና የሜንተርሽፕ ድጋፍ ፕሮጀክት (CBMP) እስካሁን የተሠሩ ተግባራትን እና የወደፊት አቅጣጫዎችን አቅርበዋል። በቀረበው ሀሳብ ላይ ውይይት ተደርጎ መርሀ ግብሩ ተጠናቋል።

    District Health Information System 2 (DHIS2) ምን እንደሆነ በዝርዝር ለማንበብ እዚህ ይጫኑ (እንግሊዝኛ)

    ምንጭ፦ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    DHIS2


    Anonymous
    Inactive

    ሃገራዊውን የግብር ንቅናቄ በደቡብ ክልል ለማስቀጠል በአዲስ አበባ ከተማ የሩጫ ውድድር ሊካሄድ ነው
    —–

    አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራና በትግራይ ክልሎች የተጀመረውን የግብር ንቅናቄ በማስቀጠል በአዲስ አበባ ከተማ የሩጫ ውድድር ሊያካሂድ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

    የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግላጫ እንዳስታወቁት÷ “ግብር ለሃገሬ “ በሚል መሪ ቃል የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

    ሚኒስትሯ የግብር ንቅናቄው በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት፡፡

    ሁሉም የሚሳተፍበት የእምዬን ለእምዬ በሚል መርህ የስዕልና የሙዚቃ ድግስ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድም ተናግረዋል፡፡

    ሚኒስትሯ በሀገሪቱ ግብር መክፈል ከነበረባቸው ዜጎች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሚከፍሉ ገልጸዋል፡፡

    ደረሰኝ ከመስጠትና ከመቀበል ጋር በተያያዘም እስካሁን የግንዛቤ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

    በሚኒስቴሩ በግብር ማጭበርበርና ስወራዎች ላይ በተደረገ ክትትል ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷልም ነው ያሉት።

    ሃገሪቱ ከግብር ስወራና ማጭበርበር ጋር በተያያዘ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ማጣቷንም አንስተዋል።

    ኤፍ.ቢ.ሲ

    Semonegna
    Keymaster

    የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ያዘጋጁት የዘንድሮው ውድድር ለ2ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፥ በባለፈው ዓመት የተመረጠችው ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል በተካሄደው የቁንጅና ውድድር ላይ ተሳትፋ 3ኛ ደረጃ መውጣቷም ተገልጿል።

    ደብረ ብርሃን (ሰሞነኛ)– በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ‹‹ቱሪዝም ለአካባቢ እንክብካቤና ለማኅበረሰብ አቅም መጎልበት›› በሚል መሪ ቃል ሲከበር የቆየው የቱሪዝም ሳምንት ጥር 24/2011 ዓ/ም የቁንጅና ውድድር በማካሄድ ተጠናቀቀ።

    በውድድሩም ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ያብፀጋ አይነኩሉ ከሁለተኛ ዓመት የሎጅስቲክና ሰፕላይ ቼን ማኔጅመንት (Logistics and Supply Chain Management) ትምህርት ክፍል ተመርጣለች። በሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ኤልሳቤጥ ደስታ የ3ኛ ዓመት የባዮቴክኖሎጂ (Biotechnology) እና በሦስተኛነት ደረጃ ተማሪ ትንሳኤ ፀጋዬ አንደኛ ዓመት የሳይኮሎጂ (Psychology) ትምህርት ክፍል እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።

    VIDEO: The Yellow Movement AAU: Speaking up for women and girls – empowering women (Ethiopia)

    የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ተወካይ ዶ/ር ጌትነት አሸናፊ በፕሮግራሙ መዝጊያ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ከሳምንት በፊት ጀምሮ በዩኒቨርስቲው ግቢና ውጪ ያለውን አካባቢ በማጽዳት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ ተግባራት በማከናወን የቆዩ መሆናቸውን በመግለፅ ላደረጉት በጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።

    የቱሪዝም ማኔጅመንት የትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አብርሃም ኪዳኔ እንደገለፁት የዘንድሮው ውድድር ለ2ኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፥ በባለፈው ዓመት የተመረጠችው ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል በተካሄደው የቁንጅና ውድድር ላይ ተሳትፋ 3ኛ ደረጃ በመውጣቷ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘች መሆኗን ተናግረዋል።

    በመጨረሻም ለጓሳ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ መታሰቢያነት ‹‹ቱሪዝም ለአካባቢ እንክብካቤና ለማህበረሰብ አቅም መጎልበት›› በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የቱሪዝም ሳምንት 8 /ስምንት/ ተወዳዳሪዎችን ያሳተፈው የቁንጅና ውድድር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የወጡትን አሸናፊዎችን በመምረጥና እውቅና በመስጠት በዓሉ ተጠናቋል።

    ምንጭ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል


    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማይናጋ መሰረት ላይ ለመጣል ግብር ከፋዩ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል — ወይዘሮ አዳነች አበቤ
    —–

    የኢትዮጵያን ኢኮኖሚዋ በማይናጋ መሰረት ላይ ለመገንባት ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የውዴታ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የገቢዎች ሚኒስቴር ወይዘሮ አዳነች አበቤ ገለጹ።

    የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ2011 በጀት ዓመት የግብር ህግ ተገዥነትን ለማሳደግ የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አስጀምሯል።

    “ግዴታዬን እወጣለሁ፣ መብቴን እጠይቃለሁ” በሚል መሪ ቃል በተጀመረው የንቅናቄ መድረክ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አበቤ እንደገለጹት በኩሩ ህዝቦቿ ተጋድሎ ማንነቷ ተከብሮ የኖረችው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ድሃ ከሚባሉት አገራት ተርታ ትገኛለች።

    “ይህን ስሟን ለማስቀየርና ኢኮኖሚዋ በማይናጋ መስረት ላይ እንዲገነባ ለማድረግ ግብር ከፋዩ ሕብረተሰብ በፍላጎትና በአገራዊ ፍቅር ስሜት ከሚያገኘው ገቢ ላይ ለመንግስት ግብርን መክፈል አለበት” ብለዋል።

    በአገሪቱ የተከሰተውን ለውጥ ምክንያት በማድረግ ለውጡ ጥቅማቸውን የነካባቸው አካላት ሰላም እንዲደፈርስና የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ግብረ በአግባቡ እንዳይከፈል እያደረጉ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግዋል።

    ” ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ግብር መክፈል ለራሱና ለሚወዳት አገሩ መሆኑን ተገንዝቦ ኃላፊነቱን ከመወጣት ባለፈ እንደ ጥንት አባቶች አንድነቱን አጠናክሮ መንቀሳቀስ ይኖርበታል ” ብለዋል።

    የአማራ ክልልም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የፌዴራል መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

    ሙሉ ታሪኩን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገጽ ላይ ያንብቡ

    Semonegna
    Keymaster

    ዓባይ ኢንዱስትሪያል የልማት አክስዮን ማኅበር ደጀን ከተማ ውስጥ (አማራ ክልል) የሚያስገነባው ሲሚንቶ ፋብሪካ አጠቃላይ ወጪው 8.8 ቢልዮን ብር እንደሆነና ግንባታው በ24 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ዓባይ ኢንዱስትሪያል የልማት አክስዮን ማኅበር በአማራ ክልል ደጀን ከተማ ላይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ከሁለት የውጭ ሀገር ድርጅቶች ጋር የሦስትዮሽ የሥራ ስምምነት ተፈራረመ።

    አክስዮን ማኅበሩ አክስዮን ማኅበሩ ስምምነቱን የተፈራረመው መቀመጫውን ኮፐንሃገን ከተማ (ዴንማር) ያደረገውና ዓለምአቀፍ የምህንድስና (ግሎባል ኢንጂነሪንግ) ኩባንያ ከሆነው “FLSmidth & Co. A/S” እና መቀመጫውን ያንግጆ ከተማ፣ ቻይና (Yangzhou, China) ያደረገው ሌላው ዓለምአቀፍ የምህንድስና ኩባንያ “Hengyuan Group” ጋር አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሸራተን አዲስ ሆቴል ውስጥ ነው ነው። በስምምነቱ መሠረት “FLSmidth & Co. A/S” የግንባታ መሣሪያዎችን ሲያቀርብ፣ “Hengyuan Group” ደግሞ የግንባታውን ሥራ ያከናውናል። የፋብሪካው ግንባታ አጠቃላይ ወጪውም 8.8 ቢልዮን ብር እንደሆነና ግንባታው በ24 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል።

    ቪድዮ፦ በ8.8 ቢልዮን ብር በደጀን ከተማ (አማራ ክልል) የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው።

    የዓባይ ኢንዱስትሪያል የልማት አክስዮን ማኅበር ለሚገነባው ፋብሪካ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውንም የአክስዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል ጠቁመዋል።

    በስምምነቱ ወቅት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፦ “ይሄ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለክልሉ ልማት ትልቅ አጋዥ ይሆናል የሚል እምነት አለን፤ ስለዚህ ገንቢዎቹም፣ አቅራቢዎቹም፣ ሁላችሁም ደጀን ላይ ይህንን ሲሚንቶ ፋብሪካ ለማፋጠን በምታደርጉት ጥረት የአማራ ክልል ሕዝብና መንግስት ሁልጊዜም ቢሆን ከጎናችሁ ይሆናል” በማለት የክልሉን መንግስት ደጋፍ አረጋግጠዋል።

    የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም በበኩላቸው የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ብቻ ትርጉም እንደሌለውና፣ ይልቁንም በፍጥነት ተገንብተው ወደማምረት ሥራና ለኅብረተሰቡ የሥራ ዕድል ፈጠራ መግባት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

    የሲሚንቶ ፋብሪካው ወደ ሥራ ሲገባ በቀን 5 ሺህ ቶን ክሊንከር እና በዓመት 2.25 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ እንዲያመርት፣ ለዚህም 655 ሰዎችን በቋሚነት የሚቀጥር ሲሆን፥ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ደግሞ የሠራተኞቹን ቁጥር ወደ 1,500 ለማሳደግ ታቅዶ እንደሚገነባ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

    ዓባይ ኢንዱስትሪያል የልማት አክስዮን ማኅበር በህዝብና በግል ባለሀብቶች ባለቤትነት በአክስዮን የተቋቋመ የንግድ ድርጅት ነው። ዋና መሥሪያ ቤቱም የአማራ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በሆነችው ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ነው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ዓባይ ኢንዱስትሪያል የልማት አክስዮን ማኅበር


    Anonymous
    Inactive

    የአቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ በቁጥጥር ሥር መዋል

    ሁለቱ የቀድሞ የብአዴንና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ሥር የዋሉት በጥረት ኮርፕሬት ፈፅመዋል ተብለው በተጠረጠሩበት የኃብት ብክነት ወንጀል ነው።
    ባህር ዳር —

    ሁለቱ የቀድሞ የብአዴንና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ሥር የዋሉት በጥረት ኮርፕሬት ፈፅመዋል ተብለው በተጠረጠሩበት የኃብት ብክነት ወንጀል ነው።
    አቶ ታደሰ ካሳ በጥረት ኮርፕሬት በዋና ሥራ አስፈፃሚነት አቶ በረከት ስምኦን ደግሞ የጥረት ኮርፕሬት የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ለበርካታ ዓመታት ሰርተዋል። ሁለቱ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ነው የተያዙት።
    ይህንን ተከትሎ የአማራ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ዛሬ ጠዋት ባህር ዳር ከተማ የገቡ ሲሆን በጊዜያዊ ማረፊያ ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ኮሚሽነር ዝግ አለ ገበየሁ ተናግረዋል።

    ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
    VOA Amharic

    Anonymous
    Inactive

    አቶ በረከት አቶ ታደሰ ባሕርዳር ይዳኛሉ
    የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕድን)ና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መሥራቾች አቶ በረከት ስሞዖንና አቶ ታደሰ ካሳ የታሰሩትም፣የሚዳኙትም አማራ ክልል እንደሆነ የክክሉ ባለሥልጣን አስታወቀ።የአማራ መስተዳድር የሥነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ዝግአለ ገበየሁ ለጋዜጠኞች እንደነገሩት ሁለቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የታሰሩት ጥረት የተሰኘዉን የኩባንዮች ስብስብ በማክሰራቸዉ ነዉ።ድሮ ኢሕዴን፣ በመሐሉ ብአዴን፣ በቅርብ ደግሞ አዴፓ በሚሉ ምሕፃረ-ቃላት የሚጠራዉ የአማራ ክልክል ገዢ ፓርቲ የመሠረተዉና የሚቆጣጠረዉ ድርጅት የአስራ-ሠባት አምራችን ነጋዴ ኩባንዮች ባለቤት ነዉ።

    አውዲዮውን ያዳምጡ።
    Deutsche Welle

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) የአማራ ክልል የልማትና ኢንቨስትመንት ድርጅት በሆነው ጥረት ኮርፖሬት ላይ ከደረሰ የሀብት ብክነት ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልላዊ መንግስት ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

    የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ዝግአለ ገበየሁ አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ (“ተጠርጣሪዎች”) በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ባህር ዳር መወሰዳቸውን ለመገናኛ ብዙኃንና ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል። እንደ አቶ ዝግአለ ገለጻ፥ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ከፍተኛ በሆነ የሀብት ብክነት ምክንያት ጥረት ኮርፖሬትን ለኪሳራ ዳርገዋል፤ ይህም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ምክንያት እንደሆነና የተጠረጠሩበት ወንጀል የተፈፀመው በክልሉ በመሆኑ ጉዳያቸው በክልሉ ፍርድ ቤት የሚታይ ይሆናል።

    የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በእስካሁኑ የመረጃና ማስረጃ ማሰባሰብ ሂደት በሁለቱ ግለሰቦች ላይ ተገቢውን ክስ ለመመሥረት የሚያስችለውን በቂ መረጃ/ማስረጃ መሰበሰቡንም አስታውቋል።

    አባይ የህትመትና የወረቀት ፓኬጂን ፋብሪካ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ሥራ ጀመረ

    አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕድን)እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መሥራቾች ከመሆናቸው በተጨማሪ በፌደራልና በክልል መንግስታዊ ቦታውች ለረዥም ጊዜ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በጥረት ኮርፖሬት ውስጥ ደግሞ አቶ ታደሰ ካሳ በዋና ሥራ አስፈፃሚነት አቶ በረከት ስምኦን ደግሞ በቦርድ ሰብሳቢነት ለበርካታ ዓመታት መሥራታቸው ተጠቁሟል።

    አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳን በቁጥጥር ስር ለመዋል ያበቃቸውና ጥረት ኮርፖሬት ላይ የተፈጸመው የሀብት ብክነት ምንድን ነው?

    የጥረት ኮርፖሬት የሀብት፣ እንዲሁም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የገንዘብ ብክነት ተፈጽሞብኛል ያላቸው ዝርዝሮች፦

    • የኮርፖሬቱ ንብረት የሆኑ አምስት ኩባንያዎች ከ ክስዮን መሸጥ/ግዢ ጋር በተያያዘ ለሀብት ብክነት የዳረገ ብልሹ አሠራር በኦዲት ተደርሶበታል፤
    • ሌሎች ሁለት እህት ኩባንያዎች ላይ ተመሳሳይ የኦዲት ሥራ እየተሠራ ነው፤
    • ተጠርጣሪዎቹ በኮርፖሬቱ ውስጥ በስልጣን ላይ እያሉ የተመሠረቱ ስድስት እህት ኩባንያዎች፥ ከመመሥረታቸው በፊት አስፈላጊውን የአዋጭነት ጥናት ሳይደረግ ለእነዚህ ኩባንያዎች መመሠረቻ/ ግዢ ወደ ሚሊዮን ብር ወጪ ወጥቷል፤
    • እነዚህ ስድስት እህት ኩባንያዎች ከተመሠረቱ/ ከተገዙ በኋላ በጊዜው ወደሥራ ባለመግባታቸው ኮርፖሬቱን ለተጨማሪ ወጪ/ ኪሳራ ዳርገውታል፤
    • ጥረት ኮርፖሬሽን በአጋርነት ከሚሠራቸው ኩባንያዎች ጋርም ከኮርፖሬቱ የፋይናንስ አሠራርና ሕግ ውጪ 7 ሚሊየን ብር ለሁለት ኩባንያዎች ተሰጥቷል፤
    • በሦስት ግለሰቦች ለሚተዳደር አንድ የማዕድን ኩባንያ ላወጣው የእያንዳንዱ አክሲዮን ዋጋ 1,000 ብር ሲሆን፥ ጥረት ኮርፖሬት በአንጻሩ የእያንዳንዱን አክሲዮን ዋጋ በ2,200 ብር እንዲገዛ ተደርጓል። በዚህም ሦስቱ ባለሀብቶች የ4 ሚሊየን 320 ሺህ ብር ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆኑ፥ ጥረት ኮርፖሬት ግን ለኪሳራ ተዳርጓል፤
    • ባለሙያን ያላካተተ የአክስዮን መግዛትና መሸጥ ሥራ በኮርፖሬቱ ውስጥ ይተገበር ነበር፤ ይህም ለሀብት ብክነት ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል፤
    • ለካፒታል ዕድገት ለሀገር ውስጥ ገቢ መክፈል የነበረበትን 1 ሚሊዮን 296 ሺህ ብር ባለመክፈሉ ጥረት ኮርፖሬት ባለዕዳ አድርጎታል፤
    • ለፋብሪካ ይገነባል በሚል የ17 ሚሊየን ብር ግብዓት ተገዝቶ እስካሁን ምንም ዓይነት ሥራላ በለመዋሉ ኮርፖሬቱን ለሌላ የሀብት ብክነት ዳርጎታል።

    በስተመጨረሻም አቶ ዝግአለ እንዳስታወቁት የአቶ በረከት ስምኦን እና የአቶ ታደሰ ካሳ በቁጥጥር ስር መዋል መጀመሪያ እንደሆነና፥ ሌሎችም በእንዲህ ዓይነት ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ይውላሉ።

    ቀድሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን)፣ በመሀል ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣ አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የተባለው የአማራ ሕዝብ ፓርቲ ያቋቋመው ጥረት ኮርፖሬት በአምራችነት ዘርፍ፣ በአገልግሎት መሰጠት ዘርፍ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ እና በ አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የአስራ ዘጠኝ ኩባንያዎች ባለቤት መሆኑን የኮርፖሬቱ ድረ ገጽ ያሳያል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በ2006 ዓ.ም. በሰባት የየመገናኛ ብዙሃን (ሚዲያ) እና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተቋቋመው ጉዞ ዓድዋ፥ አንድ ሺሕ አስር ኪሎሜትሮችን የሚሸፍን፣ ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ተነስቶ መዳረሻውን የዓድዋ ድል አምባ ተራሮች ጫፍ ላይ የሚያደርግ ረዥም የእግር ጉዞ ነው። ላለፉት ስድስት ዓመታት ከጥር ወር ጀምሮ የዓድዋ ድል በዓል እስከ ሚከበርበት የካቲት 23 ቀን ድረስ ከስድስት ሳምንታት ላላነሰ በየዓመቱ ሳይቋረጥ የቆየው ጉዞ ዓድዋ፥ ዘንድሮ የኢትዮጵያዊነቱ ስሜት እጅግ ጎልቶ በጉዞው ላይ የሚሳተፉት ቁጥርም ጨምሯል። በዘንድሮው ጊዞ ዓድዋ 44 ተጋዦች ከአዲስ አበባ እና 4 ተጓዦች ከሐረር በአጠቃላይ 48 ተጓዦች ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀን ከአዲስ አበባ ተነስተዋል።

    የመላው አፍሪቃውያን ድል እስከመባል የደረሰው ታላቁ የዓድዋ ድል፥ የግዝፈቱን ያህል ክብር እና መታወሻ ሥነሥርዐት ሳይኖረው እየተከታተለ ከመጣው ትውልድ ጋር የበዓሉ አከባበር ዐውድ እየወረደ ጭራሽ እየተዘነጋ እና እየደበዘዘ መሔድ ያሳሰባቸው የጉዞ ዓድዋ መሥራቾች ትውልዱ ትኩረት ሰጥቶ የድሉን መንፈስ እንዲጋራ ለማድረግ ይህንን የጉዞ ሐሳብ አመንጭተዋል።

    ◌ የጉዞ ዓድዋ ተጓዦችና የኢትዮጵያዊያን አስተያየት

    በዚህም የተነሣ ጉዞ ዓድዋ ባለፉት ስድስት ዓመታት ብቻ ከታለመው ዓላማ አንጻር ከፍተኛ የሆነ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ የዓድዋ ድል በዓል ቀድሞ ከነበረበት አከባበር የላቀ ተሳትፎ ያለው የድል በዓል እንዲሆን አስተዋጽዖ ለማድረግ ተችሏል።

    ጉዞውን ከማካሔድ በተጓዳኝ በየመንገዱ ተንቀሳቃሽ የመጻሕፍት ንባብ መሰናዶ በማካሔድ በየዓመቱ የሚጓዙ አባላትን በዓድዋ ጦርነት እና ድል ዙሪያ በቂ የሆነ ግንዛቤ እና ዕውቀት የማጋራት ዝግጅቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል። ከአንድ ወር በላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን የሚሰጠው የጉዞው የዕለት ተእለት ውሎ፣ በዓሉ ከመድረሱ አስቀድሞ በበርካታው ሕዝባችን ላይ የካቲት 23 ዕለትን በጉጉት የመጠበቅ ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል።

    ◌ የዓድዋ ድል በዓል በጎሰኞች ዓይን የዲያቆን ዳንኤል ክብረት መጣጥፍ

    ከዚህ ቀደም የድል በዓሉ በብቸኝነት ከሚከበርባቸው የአዲስ አበባ እና የዓድዋ ከተሞች በተጨማሪ ከ28 በላይየሚሆኑ የክልል ከተሞች እና በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸው የገጠር ወረዳዎች ተጓዥ ቡድኑ በየደረሰበት በሚኖሩ ደማቅ አቀባበሎች ላይ በሚሰጡ የግንዛቤ መስጫ መልዕክቶች ስለ ዓድዋ ድል ታሪክ ግንዛቤ በመሰጠቱ የበዓሉአከባበር ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛል። የጉዞ ዓድዋ ትሩፋቶች፦

    • በዓድዋ ከተማ ውስጥ በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የነበረው የዓድዋ ድል በዓል አከባበር ሥነ ሥርዐትበየዓመቱ እንዲካሔድ አስችሏል።
    • የበዓሉ አከባበር በፌደራል መንግሥት ደረጃ እንዲከበር ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል።
    • ከ120 ዓመታት በፊት መቀሌ ከተማ በሚገኘው የእንዳየሱስን ምሽግ ለማስለቀቅ ከጣሊያን ጦር ጋር ሲዋጉ ሕይወታቸው ያለፉ ጀግና ኢትዮጵያውያን አጽም የትም ተበታትኖ በመቅረቱ፥ ጉዞ ዓድዋ በአሁኑ ሰዓት የቦታው አስተዳዳሪ የሆነውን የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በማንቃት፤ የካቲት 26 ቀን 2008 ዓ. ም አጽማቸውን አሰባስቦ በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል። ከዚህም ባሻገር በዓመቱ የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ወጪ “የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን መታሰቢያ ሙዚየም” የተሰኘ ጣራ አልባ ቤተ መዘክር በእንዳየሱስ ታሪካዊ ምሽግ ላይ ተገንብቶ ለመመረቅ በቅቷል።
    • የዓድዋ ጦርነት መንስዔ የሆነው የዉጫሌ ውል የተፈረመበት “ይስማ ንጉሥ” የተባለው ታሪካዊ ቦታ ተከልሎ ጥበቃ እንዲደረግለት በማድረግ ጉዞ ዓድዋ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ከዚህም በተጨማሪ ውሉ በተፈረመበት ዕለት ሚያዝያ 25 ቀን በየዓመቱ፤ ምሁራዊ ተዋስዖ የሚደረግባቸው መድረኮች በመፍጠር፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት ባበረከተው የላቀ አስተጽዖ የአምባሰል ወረዳ የዓድዋ ድልን ለመዘከርና ቦታውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ያለመቋሚ ቤተ መዘክር በቦታው ላይ እንዲገነባ የሚያስችል የ19 ሚልዮን ብር የበጀት ድጋፍ ከአማራ ክልል መንግሥት እንዲያገኝ ጉዞ ዓድዋ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
    • ለበርካታ ዓመታት አገልግሎቱ ተዘግቶ የቆየው በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የትውልድ መንደር “አንጎለላ” የሚገኘው የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ መታሰቢያ ክሊኒክ እንዲከፈት ከፍተኛ ቅስቀሳ በማድረግ፤ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድጋፍ ክሊኒኩ ታዳጊ የጤና ጣቢያ ሆኖ በድጋሚ አገልግሎት እንዲሰጥ ጉዞ ዓድዋ አስተዋጽዖ ካደረጉ መካከል ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውቷል።
    • የዓድዋ ጀግና የሆኑት ራስ አሉላ አባ ነጋ የቀብር ቦታ በሆነው የአባ ገሪማ ገዳም ውስጥ ለሁለቱም ጾታዎች ጉብኝት ምቹ በሆነ ቦታ ላይ ሐውልት እንዲቆምላቸው ጉዞ ዓድዋ ባመቻቸው ዕድል በአንድ ባለ ሀብት ሐውልታቸው ተሠርቶ ለምረቃ በቅቷል።
    • በየዓመቱ በሚካሔዱ ጉዞዎች ከዓድዋ ድል ጋር ግንኙነት ያላቸው ቦታዋችን እና ልዩ ታሪካዊ መረጃዎችን በምስል እና በጽሑፍ በመሰብሰብ ለጥናትና ምርምር አስተዋጽዖ ማበርከት የሚችሉ የታሪክ ግብዓቶችን በማደራጀት በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በተለይም የማኅበራዊ ድረ ገጽን በመጠቀም ቅርሶችን የማስተዋወቅና የመጠበቅ ሥራዎችንበ መሥራት ላይ ይገኛል።

    የጉዞ ዓድዋ ማኅበር የዓድዋ ድል በዓል በኢትዮጵያውያን እንዲሁም በጥቁር አፍሪካውያን ዘንድ የሚገባውን ክብር እንዲያገኝ ላደረገው ጥረት፣ ከላይ ለተጠቀሱት እና በየዓመቱ በሚያደርጋቸው እጅግ አመርቂ ክንዋኔዎች ምክንያት በ2009 ዓም በቅርስና ባሕል ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ተሸላሚ ሆኗል።

    ላይ የሚሳተፉ ተጓዦች በጉዞአቸው ላይ የሚያደርጓቸውን የተለያዩ ክንዋኔዎችና የሚዘግቧቸውን ታሪክ ተኮር ዘገባዎች ለመከታተል የማኅበሩን የፌስቦክ ገጽ ይጎብኙ።

    ◌ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በደብረ ብርሃን ከተማ ሃውልት ሊቆምላቸው ነው

    ምንጭ፦ በጎ ሰው ሽልማት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ጉዞ ዓድዋ


    Semonegna
    Keymaster

    ባህር ዳር (ኢዜአ)–ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በመውጣት በባህር ዳር ከተማ የተጠለሉ የአማራ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ለቀረቡላቸው አማራጮች ከመስማማት ይልቅ የጸጥታ ችግር እየፈጠሩ በመሆኑ ከተማውን ለቀው እንዲወጡ የከተማው ከንቲባ አሳሰቡ።

    የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተማሪዎች የከተማው ህዝብ ባደረገላቸው ድጋፍና እንክብካቤ ከታህሳስ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

    የከተማው ህዝብና ወጣቶች የመኝታ ፍራሽ፣ የምግብ አቅርቦትና አልባሳትን በመደገፍ ያልተቆጠበ ወገናዊ ድጋፍ ቢያደርግም ከጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ጀምሮ ከተጠለሉበት በመውጣት የከተማውን ጸጥታ እያወኩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    “በዛሬው ዕለትም ተመሳሳይ ሁከት በመፍጠር የቱሪዝም ከተማ የሆነችውንና በሰላማዊነቷ የምትታወቀውን የባህር ዳር ከተማ ሲረብሹና ጉዳት ሲያደርሱ ውለዋል” በማለት ጥር 7 ቀን ተናግረዋል።

    “ድንጋይ በመወርወር ጉዳት ማድረስ፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎችና ሌሎች የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲዘጉና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲስተጓጎልም አድርገዋል” ብለዋል።

    ችግሩ በመባባሱ የከተማው ሰላም እየታወከ በነዋሪዎችና በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት መቀጠል ስለሌለበት ከተማውን ለቀው ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረው የከተማው ወጣቶች ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር ላደረጉት የማረጋጋት ጥረትም ምስጋና አቅርበዋል።

    የከተማ አስተዳደሩ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘውዱ ዘለቀ በበኩላቸው “ተማሪዎቹ ከከተማው አልፈው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ፣ ፖሊና ሰላም ካምፓሶች በመግባት ረብሻ እንዲፈጠር አድርገዋል” ብለዋል።

    ከባህር ዳር ከተማ የሚወጣም ሆነ የሚገባ ስምንት በመኪና የተጫነ እህል በማራገፍ፣ ተሽከርካሪዎችን በመስበር፣ ቤቶችን በመደብደብ ከተማረ ሰው የማይጠበቅ ተግባር መፈጸማቸውንም አመልክተዋል።

    ተማሪዎቹ ጩቤ፣ የጭስ ቦንብ፣ የአደጋ መከላከያ ሄልሜትና ዱላ ጭምር በመያዝ አደጋ መፍጠራቸውን ጠቅሰው፤ የፀጥታ መዋቅሩ ከከተማው ሰላም ፈላጊ ወጣቶች ጋር በመተባበር ያለምንም ሰብዓዊ ጉዳት እንዲረጋጋ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን አስረድተዋል።

    “አሁን ላይ ለከተማዋ የሰላም መደፍረስ ምክንያት በመሆናቸው ከህዝቡ ጋር በመሆን የክልሉ መንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ ለመሸኘት ሥራ እየተሠራ ነው” ብለዋል።

    ተማሪዎችን ለማግባባትና መፍትሄ ለመስጠት በከፍተኛ አመራሩ ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም የቀረበላቸውን አማራጭ ባለመቀበል መግባባት ላይ መድረስ አለመቻሉን የገለፁት ደግሞ የክልሉ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ ናቸው።

    ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰው መደበኛ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ አለበለዚያ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም ባለመስማማት ጥር 7 ቀን በኃይል በመጠቀም በአካባቢው የከፋ ችግር ለመፍጠር መሞከራቸውን ጠቁመዋል።

    በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል በተፈጠረ ግጭት የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ችግራቸው እስኪፈታ በጊዜያዊነት በባህር ዳር ከተማ መጠለላቸው ይታወሳል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች


    Semonegna
    Keymaster

    ኬር ኢትዮጵያ ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያስረከበው ይህ የምርምርና የስልጠና ማዕከል በምሥራቅ ኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማጎጎልበት ከአርሶና አርብቶ አደሮች ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥረት ተጨማሪ አቅም ይፈጥርለታል ተብሎ ይጠበቃል።

    ሐረር (ኢዜአ) – ኬር ኢትዮጵያ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ኩርፋ ጨሌ ወረዳ በ7 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጭ ያስገነባውንና የእንስሳት ምርምርና የአርሶ አደሮች ማስልጠኛ ማዕከል ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ።

    በኬር ኢትዮጵያ የምሥራቅ ሐረርጌ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቶ ሆሳዕና ኃይለማርያም በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ማዕከሉ ለእንስሳት እርባታ፣ ድለባና የዝናብ እጥረት ተቋቁመው ምርት የሚሰጡ የአዝዕርት ሰብሎች ላይ ምርምር ያካሂድበታል።

    ማዕከሉ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ አካባቢዎች የሚያከናውናቸውን የምርምር ሥራዎች እንደሚያጠናከርለትም አመልክተዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጣቢያዎች ዳይሬክተር አቶ አድምቀው ኃይሉ በበኩላቸው ማዕከሉ በምሥራቅ ኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማጎጎልበት ከአርሶና አርብቶ አደሮች ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥረት ተጨማሪ አቅም ይፈጥርለታል ብለዋል። በዚህም የሚገኙ የገበሬዎች ማሰልጠኛ ተቋማትን በመጠቀም ለአርብቶና አርሶ አደሮች በእንስሳት አመጋገብ፣ አያያዝ፣ ርባታና ድለባ ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል። የእንስሳት ጤና ተማሪዎችንና ባለሙያዎችን በመጠቀም የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

    በአማራ ክልል ለገበሬዎች እፎይታን የሰጠ የስንዴ ምርትን መሰብሰቢያ ማሽን (ኮንባይነር)

    የኩርፋጨሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አልዪ ጠለሀ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማኅበረሰብና አርሶ አደሩን በምርጥ ዘር ስርጭትና በሌሎች የማህበረሰብ አገልግሎት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

    ማዕከሉ ኩርፋ ጨሌን ጨምሮ የሦስት ወረዳዎች አርሶና አርብቶ አደሮች በምርምር የሚያገኟቸውን የእንስሳትም ሆነ የሰብል ዝርያዎችን እንዲጠቀምና የቴክኖሎጂ ተጋሪ እንዲሆን ያደርጉታል ብለዋል።

    የኩርፋ ጨሌ ወረዳ ሁላጀነታ ቀበሌ ነዋሪዋ ከፊል አርሶ አደር መፍቱሃ አብዱላሂ ዩኒቨርሲቲው ምርጥ የድንችና የሰብል ዝርያዎችን በማሰራጨት ምርታቸውን እንዳሳደገላቸው ተናግረዋል።

    “በአሁኑ ወቅት የድለባ ከብት ተሰጥቶኝ የማድለብ ሥራ ጀምሬያለሁ” ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፣በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የሰብል በሽታን ለመከላከል ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

    የዚሁ ቀበሌ ሌላዋ ነዋሪ ወይዘሮ ፋጡማ አህመድ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ማዕከሉን መረከቡ ሥራቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማከናውንና ስልጠና ለማግኘት ያስችለኛል ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ኬር ኢትዮጵያ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ


Viewing 15 results - 91 through 105 (of 120 total)