-
Search Results
-
አርባ ምንጭ (አ.ም.ዩ.)– አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ5ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 76 የህክምና ዶክተሮች ኅዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በደማቅ ሥነ ስርዓት አስመርቋል።
የዩኒርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የትምህርት መርሀ ግብሮችን (ፕሮግራሞች)እና የሚካሄዱ ምርምሮች የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱና ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የትምህርት ጥራት፣ አግባብነትና ተደራሽነት ግብ ለማሳካት በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል። ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::
ዩኒቨርሲቲው የጤና ዘርፍ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በመምህራን ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቱ፥ የዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 127 መምህራን እያስተማረ የሚገኝ ሲሆን 69ኙ 2ኛ ዲግሪ፣ 11ዱ 3ኛ ዲግሪ እና 41ዱ የስፔሻሊቲ መ/ራን ደረጃቸውን ሊያሻሽል ትምህርት በመከታተል ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
እንደ ፕሬዝደንቱ ማብራሪያ ዩኒቨርሲቲው ከአርባ ምንጭ ሆስፒታልና አጎራባች የጤና ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር፣ በማኅበረሰቡ ጤና መሻሻል ላይ ትኩረት ያደረጉ ምርምሮችን በማከናወንና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ነው።
◌ Selale University (Fiche, Ethiopia) accepts students for the first time
ፕሬዝደንቱ በህክምና ትምህርት የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ በተመለከተ በ2009 ዓ.ም. ከነበሩት 58 የህክምና ዶክትሬት ምሩቃን መካከል የሴት ምሩቃን ቁጥር 1 (አንድ) ብቻ የነበረ ሲሆን በ2011 ዓ.ም. ከተመረቁት 76 የህክምና ዶክተሮች የሴት ምሩቃን ቁጥር 18 መድረሱ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። በተጨማሪም ምሩቃን በዩኒቨርሲቲው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ከሥራው ዓለም ጋር አዋህደው የማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ለአገራችን ህዳሴ ታላቅ ሚና እንዲጫወቱም አሳስበዋል።
የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ በድሩ ሂሪጎ በበኩላቸው እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባሻገር የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ፣ የወባ በሽታን ለመከላከል እንዲሁም መሰል የጤና መሻሻል ሊያመጡ የሚችሉ አገር አቀፍ ምርምሮችን ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን እየተገነባ ያለው የዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ጥራት ያለው የጤና ትምህርትና የህክምና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለመስጠት ያስችላል።
ዓለም የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር በአገራችን ትምህርትና ሥልጠና አቅርቦት፣ ተገቢነትና ጥራት ላይ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች አሉ ያሉት የኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ያለነው በታዳጊና ኢኮኖሚዋ ባልዳበረ አገር እንደመሆኑ መጠን ምሩቃን ችግሮችን በሰከነ መንፈስ በመጋፈጥ በድል መወጣት፣ ቀና አስቢነትንና ትህትናን መላበስ እንዲሁም በአሸናፊነት እና በ”እችላለሁ!” ስሜት ተነሳሽነት የወገናችውን ህይወት የሚቀይር ሃሳብና አሠራር ሊቀይሱ ይገባል በማለት አሳስበን ንግግራቸውን በመቀጠል፦
‹‹ዛሬ ተንብዩ፤ ለነጋችሁ ያለእረፍት ሥሩ፤ የምትይዙት ጓደኛ፣ የምታዩት ፊልም ሁሉ ከህልማችሁ እና መድረሻችሁ ጋር የተገናኘና ግባችሁ ላይ ለመድረስ የሚያግዛችሁ መሆኑን አረጋግጡ›› ያሉት ሚኒስትሯ ዘረኝነት፣ ሌብነት እና ራስ ወዳድነት ከአገራችን ወግና ባህል የወጡ በመሆኑ ልትታገሏቸው ይገባል ብለዋል ።
የኢትዮጵያ የህክምና ማኅበር ተወካይ እንዲሁም የእለቱ ተጋባዥ እንግዳ ዶ/ር መስከረም አለቃ በበኩላቸው የተመረቃችሁበት ሙያ ትልቁን የሰው ልጅ የማዳን ተግባር በመሆኑ በሥራው ዓለም የሚጠብቋችሁን ተግዳሮቶች በትጋት በመወጣት ለወገናችሁን ጤና መሻሻል ልትሠሩ ይገባል በማለት ለአገሪቱ ጤና መሻሻል በጋራ ለመሥራት ለምሩቃኑ በማኅበሩ ሥም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኑ እንዳስደሰተው የገለፀውና 3.54 አማካኝ ወጤት በማምጣት የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ የሆነው ምሩቅ መሠረት ሙሉ በቀጣይ የማህፀንና ፅንስ ሐኪም መሆን እንደሚፈልግና የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ከመቀነስ አንፃር ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚጠብቀው ተናግሯል።
አማካኝ ወጤት 3.46 የማዕረግ ውጤት በማምጣት ሴቶች በህክምና ትምህርት ዘርፍ የተሻለ ተሳትፎ መኖሩን ጥሩ ማሳያ የሆነችው ምሩቅ ትዕግስት ገረሱ የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ሊቀንሱ የሚችሉ በቂ ምርምሮችን በማከናወን ባለት ዕውቀትና ክህሎት ማኅበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ እንደሆነች ገልፃለች።
ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ወራቤ (ሰሞነኛ)–በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልላዊ መንግስት፣ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የሚገኘው የወራቤ ዩኒቨርሲቲ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ክብርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እና ሌሎች የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት በተገኙበት ኅዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመርቋል።
የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ ክብርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ካስተላለፉት መልዕክት ስለ ክልላዊነትና ዓለም አቀፋዊነት (localization and internationalization) የተናገሩት የሚገኝበት ሲሆን በንጽጽር መልክ ባስቀመጡት በዚህ ንግግራቸው ዓለማቀፋዊነት አጉልተው በማሳየት የሚከተለውን ብለዋል።
ብዝሃነትና ዓለም አቀፋዊነት የዩኒቨርሲቲ መሰረታዊና ልዩ መለያ ባህሪዎች ናቸዉ። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ ማኅበረሰቦች የብዝሃነት ባህሪን የሚገልጹ ሲሆን፤ ይህም በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በአመራሩ እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች አከባቢያዊ እና ህብረብሄራዊ አመጣጥ ይገለጻል።
ስለሆነም ዩኒቨርሲቲዎች የፌደራል ተቋማት እንደመሆናቸዉ መጠን ተማሪዎች በየአካባቢያቸው ባለው ዩኒቨርሲቲ ብቻ እንዲማሩ፣ መምህራንም በአካባቢያቸው ባለው ዩኒቨርሲቲ ብቻ ተቀጥረው እንዲያስተምሩ፣ አመራሩም በተወለዱበት አከባቢ የሚገኘውን ዩኒቨርሲቲ ብቻ እንድያስተዳድሩ የሚለው አስተሳሰብ ከዩኒቨርሲቲ ብዝሃነትና ዓለም አቀፋዊነት የማስተናገድ ባህሪ የወጣ ስለሚሆን የዩኒቨርሲቲዎቻችንን ደረጃ ዝቅ የሚያደርግ ነዉ።
ዓለም አቀፍ ቶሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ ዩኒቨርሲቲዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩበት አንዱና ዋነኛው መስፈርት፣ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍል ለሚመጡ ተማሪዎችና ሠራተኞች አቃፊ በመሆናቸውና ዓለም አቀፋዊነትን በማስተናገዳቸው ነው። ዩኒቨርሲቲዎች አለማቀፋዊነት ባህሪ እንጂ አካባቢያዊ ዉስንነት እንደማይመጥናቸዉ ያሳያል።
ስለዚህ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ እና አሠራር በተቃራኒ አቅጣጫ መሄድ የለብንም! የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ከብሄራዊ አስተሳሰቦች አልፎ ዓለም አቀፋዊነት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎቻችንን በአካባቢያዊነትና በባህል በመከፋፈል፣ ባህላዊና ክልላዊ ማድረግ ወይም መከፋፈል አያስፈልግም።
በሌላ የከፍተኛ ትምህርት እንቅስቃሴ ዜና፥ የጎንደር የኒቨርሲቲ ለሴት መምህራንና ሠራተኞች በወሊድ ወቅት በመደበኛነት የሚፈቀድላቸውን የወሊድ ፈቃድ አጠናቀው ወደ ሥራ በሚመለሱበት ጊዜ ህፃናትን በሥራ ቦታ የማቆያና የመንከባከቢያ ማዕከል ኅዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል።
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ክብርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ባስተላለፉት መልዕክት “የህፃናት ማቆያ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መጀመሩ ትልቅ ሥራ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲ ያሉ ሴቶችን ተሳትፎና ስኬታማነት ከማረጋገጥ አኳያ በጣም ትልቅ ሚና መኖሩን ገልፀው፥ ሴት መምህራን በሥራ ገበታቸው ላይ ቤት ትተው የመጡትን ህፃን በማሰብ በተከፈለ ልብ እንዳይሰማሩና ከወንድ አቻቸው ጋር ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ይህ የህፃት ማቆያ ችግራቸውን እንደሚቀርፍላቸው ተናግረዋል።
የዚህ ዓይነቱ የህፃናት ማቆያ ማዕከል በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቢስፋፋ ሴቶች መምህራን በጥናትና ምርምር ሥራቸው ላይ አትኩረው እንዲሠሩ እገዛ እንደሚያደርግላቸውም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ጨምረው ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2011 በጀት ዓመት በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።
ጂንካ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን ድረስ በ14 የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑንና የኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍሎቹን ወደ 41 ለማሳደግ ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑንም የኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ተናግረዋል።
ጂንካ፣ ደቡብ ኦሞ ዞን (ዋልታ) – ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 1ሺ 500 አዳዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ ለዋልታ እንደገለጹት በዘንድሮ የበጀት ዓመት እና የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ቅበላ የተሳካ ለማድረግ በሁለት ዘርፍ የተከፈሉ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
የኒቨርሲቲው የዘንድሮ ዓመትን የመማርና ማስተማር ሂደቱን ለማስጀመር የመምህራን ዝግጅትን ጨምሮ የተማሪዎች የአገልግሎት መስጪያ ተቋማት የሆኑት ቤተ መጽሐፍትና የመመዝገቢያ ሥፍራዎች በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ የማስቻል ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል ፕሬዚደንቱ።
በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት መስጪያ ህንጻዎች ግንባታ መዘግየታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ገብሬ አዳዲስ ተማሪዎችን በጊዚያዊ የመጠሊያ ህንጻዎች እንዲገቡ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል። የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ ዓመት የተማሪዎች የመግቢያ ቀንም እስካሁን አለመቆረጡን ፕሬዚደንቱ አያይዘው ገልጸዋል።
ጂንካ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን ድረስ በ14 የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑንና የኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍሎቹን ወደ 41 ለማሳደግ ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑንም ፕሬዚደንቱ አብራርተዋል።
አዳዲስ የሚከፈቱት የትምህርት ዘርፎችም በደቡብ ኦሞ ዞን የሚታዩ የሙያ ክፍተቶችን ለመሙላት በሚያስችል መልኩ የሚከፈቱ መሆኑም ተገልጿል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ዓመት 1ሺህ 100 ያህል ተማሪዎችን የተቀበለ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት 1ሺ500 አዳዲስ ተማሪዎችን በመቀበል በአጠቃላይ ተማሪዎችን 2ሺህ 600 ለማድረስ እየሠራ ይገኛል።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል (ደብብሕክ)፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ጂንካ የሚገኘው ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም. በትምህርት ሚኒስቴር ስር ከተከፈቱት 11 አዳዲስ የሕዝብ ዩኒቨርሲቲዎች (public universities) አንዱ ነው።
ምንጭ፦ ዋልታ
ተመሳሳይ ዜናዎች፦
- የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻሉን አሳወቀ
- የወንዶ ገነት ኮሌጅ ከ400ሺ በላይ ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞችን ለኅብረተሰቡ አከፋፈለ
- አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን አስታወቀ
- ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከ37 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ለሠራተኞቹ ያስገነባቸውን ቤቶች አስረከበ
- ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመቀየር እያከናወነ ያለው በምርምር የታገዘ የዘር ማባዛት ተግባር
- የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በትምህርት ጥራትና ለኅብረተሰቡ ንጹህ ውሃ ለማቅረብ እየሠራ ነው
- ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪዎች በርካታ መርሀ ግብሮችን ከፈቱ
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ተዘጋጅቷል፤ የትምህርት ዘመኑን የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፤ በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ማዕከላትን ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ነው።
አርባ ምንጭ (ኢዜአ/AMU)– አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ፕሬዚዳንቱ ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ተወያይቷል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ነባርና አዲስ ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰለጥናል። ከነዚህም ከ6ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች አዲስ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገቡ በማኅበራዊ ሕይወታቸው ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ጉዳዮች ላይ የክህሎት ትምህርት እንደሚሰጥም አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ጥቅምት 11 እና 13 ቀናት የነባር ተማሪዎች ቅበላ የሚያከናውን ሲሆን፣ ጥቅምት 15 ና 16 ቀናት 2011 ዓ.ም ደግሞ አዲስ ገቢዎችን እንደሚቀበል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
ተማሪዎቹ ከአቀባበል ጀምሮ በመማር ማስተማር ሂደት ችግሮች እንዳያጋጥማቸው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ያስረዱት ዶክተር ዳምጠው፣ ከግቢ ውጭ ችግር እንዳያጋጥማቸው የከተማው ነዋሪዎች ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
◌ ተመሳሳይ ዜና፦ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በትምህርት ጥራትና ለኅብረተሰቡ ንጹህ ውሃ ለማቅረብ እየሠራ ነው
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፖለቲካ፣ ኃይማኖትና ከትምሀርት ጋር ግንኙነት በሌላቸው ጉዳዮች የጸዳ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ የሰላም ፎረም አባል አቶ ገረሱ በየነ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ተግባሩን ለማከናወን እንዲያስችለው የሰላም ፎረም እንዲያቋቁም አሳስበዋል።
ሌላኛው የሀይማኖት አባት መጋቢ ካሳዬ በየነ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው አካባቢ እየተስፋፉ የመጡትን የሺሻ፣ የጫትና የመጠጥ ቤቶች ጉዳይ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ኤዞ ኤማቆ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከውሃና ከኤሌክትሪክ መቆራረጥ ጋር የሚያጋጥሙትን ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚታዩ ሕገ ወጥ የሺሻ፣ የመጠጥና ጭፈራ ቤቶችን በመቆጣጠርና በመከታተል እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
በውይይቱ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ የከተማው የሰላም ኮሚቴ አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2011 በጀት ዓመት በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ገልጸዋል። ዳይሬክቶሬቱ ማዕከላቱን በቅርበት እንዲከታተል ኃላፊነት የተሠጠው ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመት የቢሮ መጠሪያውን ወደ ‹‹ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት›› እንደሚቀይርም አስታውቋል።
የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህለ እንደገለፁት በፌዴራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 48(6) መሠረት ሴት የመንግስት ሠራተኞች ከወሊድ በኋላ ወደ ሥራ ገበታቸው ሲመለሱ በሚሠሩበት ተቋም ውስጥ ህጻን ልጆቻቸውን በቅርበት እየተንከባከቡና እየተከታተሉ መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ለማገዝ የህፃናት ማቆያ ማቋቋም አስፈላጊ ነው። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 36(1) መሠረት ህጻናት ከወላጆቻቸው ማግኘት የሚገባቸውን ተገቢውን እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።
የህፃናት ማቆያዎቹ መቋቋም ዓላማዎች ከሆኑት ውስጥ እናቶቻቸው በሥራ ምክንያት በአቅራቢያቸው ባለመኖራቸው ምክንያት በህፃናት ጤንነትና ደህንነት ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ፣ በመንግስት ተቋማት ውስጥ የተሰማሩ እናት ሠራተኞች በህጻን ልጆቻቸው ምክንያት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈጥሩትን ክፍተቶች መሙላት፣ በሴት ሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን መቀነስ እና ውጤታማነታቸውን ማሳደግ ጥቂቶቹ ናቸው።
የህፃናት ማዋያዎቹ ከመደበኛው የሥራ መግቢያ ሰዓት እስከ ሥራ መውጫ ሰዓት ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የመኝታ፣ የማረፊያ፣ የመጫወቻ፣ የምግብ ማብሰያ፣ የመመገቢያ አቅርቦትና አገልግሎት እንዲሁም የእንክብካቤ፣ የቅርብ ክትትል እና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎቶችን አካቷል።
እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ አገልግሎቱን ለማግኘት ወላጆች የማንነት መግለጫ መታወቂያ ማቅረብ የሚኖርባቸው ሲሆን የህፃናቱን ምግብ በተመለከተ ከማቆያ ማዕከሉ ጋር በሚደረግ ስምምነት ወላጆች አዘጋጅተው ማቅረብ አልያም ተመጣጣኝ ክፍያ ፈጽመው የማዕከሉን አቅርቦት መጠቀም ይችላሉ። የማዕከሉን የውስጥ ግብዓት ከማሟላት ጀምሮ ተንከባካቢ ሞግዚት የመቅጠሩ ተግባር የዩኒቨርሲቲው ይሆናል።
ወ/ሪት ሠናይት እንደገለጹት በህፃናት ደህንነት ላይ የወጡትን ህግጋት መሠረት በማድረግ በህፃናት ጤንነት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ኬሚካሎች፣ ብናኞች፣ ድምፅ ያላቸው የማምረቻ ቦታዎችና መሠል ጎጂ ነገሮች የራቀ የህፃናት ማቆያ ለመገንባት ዩኒቨርሲቲው የቦታ መረጣ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። የህፃናት ማቆያ ማዕከላቱ ህንፃዎች የመኝታ፣ የመጫወቻና የንፅህና መጠበቂያ ክፍሎችን የሚያካትቱ ይሆናል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሚሰጠውን ትምህርት ጥራት ለማሻሻልና የአካባቢውን ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው – እንደ ዶ/ር አብደላ ከማል ገለጻ
አርባ ምንጭ – የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መሠረት የሆነው የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ2011 በጀት ዓመት ከመደበኛው የመማር ማስተማር ሥራ ባሻገር የአካባቢውን ማኅበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርጉና የውሃ ሃብት አጠቃቀምን የሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እንደሚሰራ ገለፀ።
የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል ኢንስቲትዩቱ በ2010 ዓ/ም እንደገና መቋቋሙን አስታውሰው እንደ መጀመሪያ ዓመት ከመማር ማስተማር ሥራ ባሻገር የኢንስቲትዩቱን መዋቅር የማደራጀት እና የሰው ኃይልና ግብአት የማሟላት ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ገልፀዋል። ኢንስቲትዩቱ ተቋሙን ከመሰል አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የማስተዋወቅ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን ከመሰል ተቋማት ጋር በመማር ማስተማርና በምርምር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነቶችን መፈራረሙን እንዲሁም በቅርቡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀረበ ጥያቄ መሠረት ቻይና ከሚገኝና በውሃው ዘርፍ አንጋፋ ከሆነ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህ ዓመት ኢንስቲትዩቱ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል እንዲሁም አራት አዲስ የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞችን ከፍቶ ሥራ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አብደላ የተማሪዎችን መማሪያ ክፍሎች፣ ማደሪያ ህንፃዎች፣ የመብራትና የውሃ መስመሮች የመጠገንና የማደስ ሥራዎች በአግባቡ ተሠርተው እየተጠናቀቁ ነው ብለዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በዚህ የዝግጅት ምዕራፍ የኮርሶች ድልድል ተሠርቶና ሁሉም መምህራን ዝግጁ ሆነው የተማሪዎችን መግባት ብቻ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በያዝነው ዓመት ተማሪዎቻችን ለመጀመሪያ ጊዜ የመውጫ ፈተና ይወስዳሉ ያሉት ዶ/ር አብደላ ተማሪዎች ፈተናውን በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል ኢንስቲትዩቱ ስትራቴጂዎችን ቀይሶ እየሠራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል። ዶ/ር አብደላ እንደገሉት ከዚህም በተጨማሪ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንፃር ለተግባር ትምህርት ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት በመስጠት በየፋካልቲው ያሉትን ቤተ- ሙከራዎችና የተግባር መለማመጃ ወርክሾፖች በግብአት የማሟላትና ለተግባር ልምምድ ምቹ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮዎች መካከል ምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ዋነኞቹ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶ/ር አብደላ ኢንስቲትዩቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ይሠራልም ብለዋል። ለአብነትም በዩኒቨርሲቲው ሙሉ ወጪ የሻራ ቀበሌ ማህበረሰብን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት በዚህ ዓመት ለመሥራት ታቅዶ ሥራውን ለማስጀመር ኢንስቲትዩቱ እንቀስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል። ዳይሬክተሩ አክለው እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ የሀገርና ውስጥ የውጭ ሀገር ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመሆን ኅብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት በዕቅድ ይዟል።
ከምርምር ጋር ተያይዞ በኢንስቲትዩቱ ስር የሚገኘውን የውሃ ሃብት ምርምር ማዕከል ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑንና በቅርቡ የምርምር ማዕከሉ የራሱን ህንፃ መረከቡን እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ የማዕከሉን ቤተ-ሙከራ በማደራጀት ከንፁህ መጠጥ ውሃ፣ ከመስኖ ውሃ አጠቃቀም እና በአካባቢው የሚገኙ የውሃ ሃብቶች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ትልልቅ የምርምር ሥራዎችና ፕሮጀክቶች እንደሚሰሩ ዶ/ር አብደላ ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም በውሃው ዘርፍ በሀገር አቀፍም ሆነ በአህጉር ደረጃ ታዋቂና አንጋፋ እንደነበር የተናገሩት ዶ/ር አብደላ አሁን ላይ ይህ እውቅና በተወሰነ ደረጃ መደብዘዙን ገልፀዋል። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሥር እንዲሆን መደረጉ አንዱ ምክንያት መሆኑን ተናግረው በአሁኑ ሰዓት ኢንስቲትዩቱ ራሱን ችሎ እንደገና በመቋቋሙ የቀድሞ ስምና ዝናውን ለመመለስ ይሥራል ብለዋል።
የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ1979 ዓ.ም በቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት 4 የመጀመሪያ ፣ 9 የሁለተኛ እና 5 የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞች አሉት።
ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ዶ/ር አብደላ ከማል ገለጻ (ፎቶ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ)