-
Search Results
-
ተከሳሽ ዓለም ታምራት ከተለያዩ ዓለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ጥሪዎችን በማስተላለፍ ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን መሠረተ ልማት ወደ ጎን በመተው ዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት ጥፋተኛ ተብላለች።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ዓለም ታምራት የተባለችው ተከሳሽ የቴሌኮም መሣሪያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት፣ ለመጠቀም እና የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራት ወደ ሕገወጥ ተግባሩ መግባቷ ተጠቁሟል። ወንጀሉ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ስሙ ገርጅ አካባቢ መፈጸሙ ታውቋል።
የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 761/2004 አንቀጽ1/ለ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሳሽ ከቀድሞው ኢፌዲሪ መገናኛ እና ኢንስፎርሜሽን ሚኒስቴር በተሰጠ ፍቃድ ብቻ ወደ ሀገር ውስጥ ለመጠቀም የሚቻሉትን የኮል ተርሚኔሽን (call termination)፣ ኮል ባክ (call back)፣ ጥሪ የመቀበል እና ጥሪ የመላክ አገልግሎት መስጠት እንደነበር ተነግሯል።
ሆኖም ግለሰቧ ከሕግ አግባብ ውጪ ኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርዶችን በውስጣቸው በማስገባት በአንድ ጊዜ ብዛት ያላቸውን እቃዎች በቅናሽ በመግዛት እና ጥሪዎችን ማስተላለፍ የሚችሉ ብዛታቸው 4 የሆኑ ጌትዌይ (gateway) የቴሌኮም መሣሪያዎችን በድብቅ በማስገባት ወንጀል ፈጽመዋል።
በድብቅ የገቡ መሣሪያዎችን ከበይነመረብ (internet) የግንኙነት አውታር ጋር በማገናኘት የሚያገኙትን ኔትወርክ (network) በማብዛት ወደ ዋየርለስ ኔትወርክ (wireless network) እንዲቀየር በማድረግ የራሳቸውን ኔትወርክ መፍጠር የሚችሉ 15 ቶፒ ሊንክ የተባሉ መሣሪያዎችን ከሌሎች አጋዥ መሣሪያዎች ጋር መጠቀማቸው በክሱ ቀርቧል።
ግለሰቧ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን ኢትዮ ቴሌኮም በዘረጋው ኔትወርክ በኩል እንዲያልፉ በማድረግ ኢትዮ ቴሌኮምን 6,379,342.19 ብር ማሳጣቷ ተጠቅሷል።
ተከሳሽ ዓለም ታምራት ከተለያዩ ዓለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ጥሪዎችን በማስተላለፍ ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን መሠረተ ልማት ወደ ጎን በመተው ዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት ጥፋተኛ ተብላለች።
ጉዳዩን ተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14 ወንጀል ችሎትም አቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በመመልከት በሚያዝያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ63 ሚሊዮን የገንዘብ መቀጮ አሳልፎባታል።
ምንጭ፡- የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ / የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ሌሎች ዜናዎች፦- በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 59 ባለስልጣናትና ባለሃብቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ
- ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከኔዘርላንድ ኤንባሲ ጋር በመተባበር ለሕግ ባለሙያዎች የትምህርት ዕድል ሰጠ
- አጣየ፣ ካራቆሬ፣ ማጀቴ እና አካባው በሚኖሩ ዜጎች ላይ የታጠቁ ኃይሎች እያደረሱት ያለው ኢ-ሰብአዊ በደል
- ሕገ-ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል ተጨማሪ 36 አዳዲስ ኬላዎች ተቋቁመዋል – የገቢዎች ሚኒስቴር
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ አሠራሩን ለማዘመን ከእንግሊዝ ሀገር አቻው ጋር ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ አሠራሩን ለማዘመን የሚያግዙ ሀሳቦች ላይ ከእንግሊዝ ቤተ መዛግብት ኃላፊዎች ጋር ምክክር አደረገ።
በምክክሩ የቤተመዛግብት እና ቤተ መፃሕፍት አያይዝን ለማዘመን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የእንግሊዙ አቻ ተቋም ልምድ ምን እንደሆነ ያወያየ ምክክር ሚያዚያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በኤጀንሲዉ የቪዲዮ ኮንፈረንስ አዳራሽ ተካሄደ። ለውይይቱ መክፈቻ የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ የኩኖአምላክ መዝገቡ ለእንግዶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ኢትዮጵያ የብዙ መዛግብቶች መገኛና ባለቤት ብትሆንም እንኳን ያላትን ሀብት ለራሷም ለዓለምም ለማበርከት የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እጥረት እንዳለባት በማንሳት ይህንን ክፍተት የእንግሊዝ ቤተ መዛግብት የቴክኖሎጂ ሽግግር እገዛ አንዲያደርግላቸዉ ጠይቀዋል።
በመቀጠል በእንግሊዝ ቤተ መዛግብት የኤሲያና የአፍሪካ የመዛግብት ስብስብ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሊዊሳ ኤሌና ሜንጎሊ (Luisa Elena Mengoni, Head of Asian and African Collections at the British Library) እንዳሉት በሁለቱ ሀገራት ዉስጥ ያሉ ተመራማሪዎች፣ ደራሲያን፣ እንዲሁም ሌሎች ፀሐፍት የእርስ በእርስ የልምድ ልዉዉጥ እንዲያደርጉ መንገዱን ማመቻቸት ለስነ-ፅሑፍ እድገት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
አቶ ክርስቲያን ጄንሰን (Kristian Jensen) የእንግሊዝ ቤተ መዛግብት ኃላፊ እንዲህ አይነት የምክክር መድረኮች ክፍተቶችን ለመለየትና መፍትሔ ለማበጀት እንደሚጠቅሙና ቀጣይነት እዲኖራቸዉ በተለይም የሥነ-ፅሑፍ ታሪኳ ከአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሀገር ቤተ መፅሐፍቷና ቤተ መዛግብቷን በማዘመን ረገድ የእንግሊዝ ቤተመዛግብት እንደሚያግዝ ተናግረዉ፥ ኃላፊዉ የማይክሮ ፊልም (የመፅሐፍት ላይ ፅሑፎችን ወደ ሶፍት ኮፒ የሚቀይር መሣሪያ) በእርዳታ መስጠቷ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር በዶ/ር ሂሩት ካሳዉ በኩል ለኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ለአቶ የኩኖአምላክ መዝገቡ ርክክብ ከተደረገ በኋላ ባህላዊ የቡና ጠጡ ሥነ-ስርዓት ተከናዉኖ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
ምንጭ፦ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ሌሎች ዜናዎች፦- የልዑል አለማየሁ አፅም ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ ተጠየቀ
- የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንፃ (አርክቴክቸር) ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን አስመረቀ
- ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በደብረ ብርሃን ከተማ ሃውልት ሊቆምላቸው ነው
- ጉዞ ዓድዋ ― ታላቁ የዓድዋ ድልን የሚገባው የታሪክ ማማ ላይ ለመስቀል የሚጥር ኢትዮጵያዊ ማኅበር
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
- ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች መሠረታዊ ችግሮች በጥናት ሊለዩ ይገባል ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ
መንግስት በሀገር ውስጥ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን በማስፋፋት ለሥራ ፈላጊ ዜጎች አስፈላጊውን ጥቅም ለማዳረስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። መሥራት ለሚችሉ ዜጎች ሁሉ በሀገር ውስጥ ላሉ የሥራ ዕድሎች ቅድሚያ በመስጠት ሠርተው የሚለወጡበትን ሁኔታዎች በማመቻቸት ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሠርቶ ለመኖር በርካታ መልካም አጋጣሚዎች አሉ። ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑ በሀገራቸው ሠርተው የተለወጡ በርካታ ወጣቶችን መጥቀስ ይቻላል።
ከዚህ ባለፈ ወደ ውጭ ሀገራት ለሥራ መሄድ የሚያስቡ ዜጎች እራሳቸውን ከአቻ ግፊትና ከሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሊጠብቁ ይገባል። ዜጎች ስለሚሄዱበት ሀገር ስላለው እውነታ ያላቸው ግንዛቤና መረጃ ውስንና የተዛባ በመሆኑ ከመሄዳቸው በፊት ስለሚሄዱበት ሀገር ባህል፣ ወግና ልማድ መረዳትና እና የዜጎችን መብት ደህንነትና ክብር ለማስጠበቅ ሲባል በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 923/2008 ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል።
ለጉዞ ከመነሳታችን በፊት ምን ማወቅ ይጠበቅብናል?
ወደ ውጭ ሀገር ሄደን ለመሥራት በምናስብበት ወቅት ጊዜ ሰጥቶ ማሰብ ይገባል። ለምን እንደምንሄድ፣ ከሄድን በኋላ የሚያጋጥሙንን መልካምና መጥፎ አጋጣሚዎች እንዴት መቋቋምና ማለፍ እንደሚገባን፣ የምንሄድበትን ሀገር ባህል፣ ወግ፣ ልማድና ስርዓት እንዴት ተላምደን መኖር እንደምንችል፣ የሠራንበትን ገንዘብ ወደ ሀገራች እንዴት መላክና መቆጠብ እንደምንችል፣ ኮንትራታችንን ጨርሰን መቼ ወደ ሀገራችን መመለስ እንዳለብን አስቀድመን ማቀድ ያስፈልጋል።
በአዋጅ ቁጥር 923/2008 መሠረት በውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ፣ 8ኛ ክፍል ያጠናቀቁ (ወደ 9ኛ ክፍል የተዛወሩ)፣ በሚሄዱበት የሥራ መስክ ስልጠና ወስደው የብቃት ማረጋገጫ ያገኙ፣ የቅድመ ጉዞ ስልጠና ወስደው ሰርተፊኬት የያዙ፣ የጤና ኢንሹራንስ የተገባላቸው፣ ሙሉ የጤና ምርምራ ያደረጉና ከወንጀል ነጻ ሊሆኑ ይገባል።
ይህን ያሟሉ ዜጎች በአስቀጣሪ ኤጀንሲ በኩል ወይም በራሳቸው አማካኝነት ሥራውን በማፈላለግ ማለትም በቀጥታ ቅጥር አስፈላጊውን የቅጥር ፎርማሊቲ በማሟላት ቪዛውን አግኝተው መሄድ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ በቀጥታ ቅጥር የሚጓዙ ሠራተኞች መደበኛ ስልጠና የወሰዱና ከቤት ሠራተኝነት ውጭ በልዩ ልዩ ሙያዎች የሰለጠኑ ሲሆን የሚሠሩትም በካምፓኒና በልዩ ልዩ አነስተኛ የቢዝነስ ተቋማት ውስጥ ነው። ከዚህ በፊት በውጭ ሀገር ሠርተው የተመለሱ ልምድ ይኖራቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ መረጃ ማቅረብ የሚችሉ ከሆነ ስልጠናውን መውሰድ ግዴታ ባይሆንም የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
ለሥራ የት ሀገር ነው መሄድ የሚቻለው?
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቤት ሠራተኝነት የሚሄድ ከሆነ ሊጓዝ የሚችለው በኤጀንሲዎች አማካኝነት ብቻ መሆኑን ሊረዳ ይገባል። የሥራ ስምሪት ማድረግ የሚችለውም አገሪቷ የሁለትዮሽ ስምምነት ወደተፈራረመችባቸው ሀገራት ብቻ ነው። የሁለትዮሽ ስምምነት የተፈፀመባቸው መዳረሻ ሀገራት ለጊዜው ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታርና ጆርዳን ሲሆኑ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚደረገው ስምምነትም በሂደት ይቀጥላል።
ስምምነት በተፈፀመባቸው ሀገሮች የደመወዝ መጠን ስንመለከት ከኳታር መንግስት 1200 ለቤት ሠራተኛና 1300 ለእንክብካቤ (care giver) የኳታር ሪያል፣ ከጆርዳን መንግስት ለጀማሪ 225 ዶላር፣ ልምድ ላላው 250 ዶላር፣ ከሳውዲ አረቢያ መንግሰት ጋር 1000 የሳውዲ ሪያል እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በሠራተኞችና በአሠሪዎች የሚሸፈኑ ወጪዎች
አንድ ሠራተኛ በሥራ ለመሰማራት አስፈላጊውን መስፈርት ካሟላና ብቁ ከሆነ በአዋጁ የተደነገጉ የቅጥርና ምልመላ መንገዶችን በመከተል አስፈላጊውን መፈጸም እና ወጪዎችን መሸፈን ይገባል።
- አሠሪው ወይንም ኤጀንሲው የሚሸፍናቸው ወጪዎች
በአሠሪው የሚሸፈኑ ወጪዎች ሠራተኛውን ወደ ተቀባይ አገር ለማድረስ፣ በተቀባይ አገር ያለችግር እንዲቆይና እንዲሠራ ለማድረግ፣ እንዲሁም በሥራ ላይ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚወጡ ወጪዎች ናቸው።
እነርሱም የተቀባይ አገር የመግቢያ ቪዛ፣ የደርሶ መልስ መጓጓዣ፣ የሥራ ፍቃድ፣ የመኖሪያ ፍቃድ፣ የሥራ ውል ማጽደቂያ ክፍያዎች፣ የመድህን ዋስትና ሽፋን እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኝ የተቀባይ አገር ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ጽህፈት ቤት የሚከፈል ከቪዛና ከሰነድ ማረጋገጥ ጋር የተያያዘ ማናቸውም ወጪዎች ናቸው።
- በሠራተኛው የሚሸፈኑ ወጪዎች
አንድ ሠራተኛ ለሥራ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በሚጓዝበት ወቅት የሚያወጣው ወጪ በአብዛኛው በህይወት ዘመኑና በማህበራዊ ህይወቱ ውስጥ የትኛውም ሰው ስለሚጠቀምባቸው የሚያወጣቸው ወጪዎች ናቸው።
እነርሱም ለልደት ሰርተፊኬት፣ ለፓስፖርት፣ ለክትባት፣ ለህክምና ምርመራ፣ ለሙያ ብቃት ማረጋገጫ፣ ከወንጀል ነፃ ማስረጃ ማረጋገጫ ወጪዎች ናቸው። እነኝህ ክፍያዎች በሙሉ አገልግሎቱን ለሰጡ ሌሎች መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት የሚከፈል እንጂ ምልመላውን ለሚያከናውነው ኤጀንሲ የሚከፈል አይደለም። ኤጀንሲው ምንም አይነት ክፍያ ከሠራተኛው ቢጠይቅ ህገወጥ ያደርገዋል።
ይሁን እንጂ ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ አስፈላጊ ሁኔታዎች ተጠናቀው ያለበቂ ምክንያት ሠራተኛው ወደ ሥራ ባይሰማራ ከቅጥሩ ጋር በተያያዘ አሠሪው ያወጣውን ወጪ ሠራተኛው እንዲከፍለው ሊጠይቅ ይችላል። በተመሳሳይ መንገድ በተራ ቁጥር 2 ላይ የተጠቀሱትን ወጪዎች ሠራተኛው አውጥቶ በራሱ ጉድለት ባልሆነ ምክንያት በሥራ ላይ ካልተሰማራ ኤጀንሲው ወይም አሠሪው የሠራተኛውን ወጪ የመተካት ግዴታ ይኖርበታል።
ለውጭ አገር ለሥራ ስምሪት የሚሰጡ ስልጠናዎችና ማሰልጠኛ ተቋማቱ
ለውጭ አገር ሥራ ስምሪት የሚሰጡ ስልጠናዎች ሶስት ሲሆኑ እነሱም በቤት አያያዝ (Household Service) በቤት ውስጥ ሥራ (Domestic Help) እና በእንክብካቤ ሥራ (Care Giving) ናቸው።
የእነዚህ ሙያዎች የስልጠና መሳሪያዎች፣ የሙያ ደረጃ፤ ሥርዓተ ትምህርት እና የብቃት ማረጋገጫ ምዘና መሳሪያዎች ሲዘጋጁ ለማንኛውም ዜጋ እንዲያገለግል ሲሆን ወንድም ሆነ ሴት በፍላጎቱ ሊሰለጥን ይችላል። ሠልጣኞች ስልጠናውን በግላቸው ሊሠሩበት፣ በአገር ውስጥ ሊቀጠሩበት እንዲሁም ወደውጭ አገር ሊሰማሩበት እንደሚችሉ ሊገነዘቡና በምልመላ ወቅትም ሊነገራቸው ይገባል። በተጨማሪም በስልጠናው የተሳተፈ ሁሉ የብቃት ምዘናውን ያልፋል ማለት አይደለም፣ የብቃት ምዘናውን ያለፈ ሁሉ ቀጣሪ ያገኛል ማለትም አይደለም። በመሆኑም በተጠቀሱት ሙያ እንዲሰለጥኑ የተደረጉ ሁሉ ወደአረብ ሀገር መሄድን እንደመብት ሊያዩት አይገባም።
ይሁን እንጂ ወደአረብ አገር መሄድ የሚፈልጉ ሰልጣኞች ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ሙያዎች ከሰለጠኑ በኋላም የብቃት ምዘና ማረጋገጫ ተፈትነው ማለፍና ሰርተፊኬት መያዝ ይኖርባቸዋል። ስልጠናው በየክልላቸውና በአቅራቢያቸው በሚገኙ በተመረጡ ማሰልጠኛ ተቋማት ይሰጣል። ስልጠናው በየክልላቸውና አቅራቢያቸው የመሰጠቱ ጠቀሜታም የሠራተኞች ምልመላ በየክልላቸው የሚካሄድ በመሆኑ፣ አስፈላጊ መረጃዎችን ለማጣራትና ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን ደህንነትና ክብር በቅርብ ለመከታተል እና ከስልጠና፣ ከምልመላ ጋር ተያይዞ ለአላስፈላጊ ወጪና የመብት ጥሰቶች እንዳይጋለጡ ያግዛል።
ስልጠናን በተመለከተም፣ የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት ትምህርቱን በነፃ የሚሰጡ ሲሆን ማንኛውም ሰልጣኝ በክልሉ በሚገኝ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ወይም በየዞኑና ክፍለ ከተማው ወይም ወረዳዎች በሚገኙ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤቶች በመመዝገብ ለየማሰልጠኛዎቹ በመላክ እንዲሰለጥኑ ይደረጋል።
በተጨማሪም የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት የተደራሽነትና የአቅም ውስንነት ስላለባቸው በፌደራልና በክልል በሚገኙት የቴ/ሙ/ት/ስ/ኤጀንሲ ቢሮዎች ለግል ማሰልጠኛ ተቋማት ፍቃድ በመስጠት በማሰልጠን ሥራው እንዲሳተፉ ተደርጓል። በመሆኑም የግል ማሰልጠኛ ተቋማት የስልጠና ጥራታቸው ላይ ጥንቃቄ በማድረግና አስፈላጊ የስልጠና ቁሳቁሶችን በማሟላት የትምህርቱን ጥራት እንዲጠብቁ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ፍቃድ ሰጪ አካላትም የጀመሩትን ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ በማጠናከር እገዛ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
በየክልሉ የተመረጡ የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት ዝርዝር
በመንግስት የተመረጡ 66 ማሰልጠኛ ተቋማት ሲሆኑ ስልጠናውም በሁሉም ክልል በነፃ ይሰጣል።
የማሰልጠኛ ተቋማት ዝርዝር በየክልሉ፡-
አማራ ክልል
- ባህርዳር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ወልድያ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ደሴ ወ/ሮ ስህን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ከሚሴ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ
- ደ/ብርሃን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ጎንደር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- እንጂባራ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ቡሬ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ
- ደብረታቦር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ደብረ ማርቆስ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ሠቆጣ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ
ደቡብ ክልል
- አዋሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- አርባ ምንጭ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ሶዶ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ዱራሜ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ሆሳዕና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ወራቤ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ቡታጅራ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ሀላባ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ይርጋለም ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ዲላ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
ትግራይ ክልል
- መቀሌ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ዶ/ር ተወልደ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ
- አክሱም ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ዶ/ር አርዕያ ካሳ ኮሌጅ
- ውቅሮ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- (ማይጨው) ጥላሁን ይግዛው ፖሊቴክኒክ
- አላማጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
- እንጦጦ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና (ቴ/ሙ/ት/ስልጠና) ኮሌጅ
- ጄነራል ዊንጌት ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
- ንፋስ ስልክ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
- ምሥራቅ አጠቃላይ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
- የካ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ልደታ ማኒፋክቸሪንግ ኮሌጅ
- አዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ቂርቆስ ማኒፋክቸሪንግ ኮሌጅ
- አቃቂ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር
- መለስ ዜናዊ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
ኦሮሚያ ክልል
- ሀሮማያ ቴክኒክና ሙያ
- አሰላ ቴክኒክና ሙያ
- ሻሸመኔ ቴክኒክና ሙያ
- መርቲ ፖሊ ቴክኒክ
- ቢሾፍቱ ቴክኒክና ሙያ
- ጂማ ቴክኒክና ሙያ
- መቱ ቴክኒክና ሙያ
- መቱ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ
- ነቀምት ቴክኒክና ሙያ
- ነቀምት ጤና ሳይንስ ኮሌጅ
- ባቱ ተራራ ቴክኒክና ሙያ
- ዶና ባርበር ቴክኒክና ሙያ
- ፍቼ ቴክኒክና ሙያ
- መርቲ ፖሊ ቴክኒክ
- አዳማ ፖሊ ቴክኒክ
- አብቦ ፖሊ ቴክኒክ
- ሰበታ ፖሊ ቴክኒክ
- ወሊሶ ፖሊ ቴክኒክ
- አጋሮ ፖሊ ቴክኒከ
- አደላ ፖሊ ቴክኒክ
- ቡሌ ሆራ ፖሊ ቴክኒክ
- ጨርጭር ፖሊ ቴክኒክ
- ደደር ፖሊ ቴክኒክ
- አርሲ ነገሌ ፖሊ ቴክኒክ
- ሀሰሳ ፖሊ ቴክኒክ
- ጊምቢ ፖሊ ቴክኒክ
- ወንጂ ፖሊ ቴክኒክ
ምንጭ፦ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የገቢዎች ሚኒስቴር የተጠናከረ የጉምሩክ ስርዓት እና የተጠናከረ ኬላ ፍተሻ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚያዙ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችና የተለያዩ አገራት ገንዘቦችም (የገንዘብ ኖቶችም) ጨምረዋል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ለሕገ-ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ዝውውር ስጋት ናቸው የተባሉ ቦታዎችን በመለየት ተጨማሪ 36 አዳዲስ የጉምሩክ ኬላዎች መቋቋማቸውን የኢፌዴሪ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
አዳዲስ ኬላዎችን በመክፈት እንዲሁም ቦታቸው ትክክል ያልነበሩ ነባር ኬላዎችን ወደ ትክክለኛ ቦታ በመቀየር ሕገ-ወጥ የገንዘብና የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ይርጋ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ተናግረዋል።
ችግሩን ለመከላከል በተደረው ጥናት በኬላዎች ላይ 1 ሺህ 400 የፖሊስ ኃይል እንደሚያስፈልግ በተጨማሪ ተገልጿል።
ጥናቱን ተከትሎ ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ፣ ስምሪቱ በጉምሩክ ኮሚሽን የሆነ ጥሩ ሥነ ምግባር የተላበሰ፣ ለቦታው የሚመጥን የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ፖሊስ እንዲቋቋምና ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ዳይሬክተሩ አቶ አዲሱ ይርጋ ገልጸዋል።
የተጠናከረ የጉምሩክ ስርዓት እና የተጠናከረ ኬላ ፍተሻ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚያዙ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችና ገንዘቦችም ጨምረዋል ነው የተባለው።
የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጀላል አብዲ በበኩላቸው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ የራሳቸውን ገንዘብ ለማግኘት በሚንቀሳቀሱ ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ከተለያዩ አገራት (በተለይም ከጎረቤት አገራት) ወደ አገር ውስጥ ይገባል ብለዋል።
የጦር መሣሪያዎቹን መዳረሻ ለማወቅ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም ከሁኔታ ግምገማ በመነሳት በአገር ውስጥ ጸጥታና የደህንነት ስጋት ያለ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ራሱን እና ንብረቱን ለመጠበቅ የጦር መሣሪያ ፍላጎት እንደ አንድ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የተለያየ ዓላማና ግብ ያላቸው የታጠቁ ቡድኖችም የጦር መሣሪያ መዳረሻ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል ዳይሬክተሩ።
የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑ ይታዋሳል።
ምንጭ፦ ኢቢሲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት የተሠራው ባለሞተር ማረሻ ተመረቀ
- አለርት ሆስፒታል ውስጥ ዘመናዊ የሕፃናት ሆስፒታል እና የአደጋ ሕክምና ማዕከል ይገነባሉ
- ዩኒቨርሲቲዎች በሦስት መስኮች ተደልድለው እንዲያስተምሩ የሚያስችል ጥናት እየተጠናቀቀ ነው
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
- ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች መሠረታዊ ችግሮች በጥናት ሊለዩ ይገባል ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት የተሠራው ለእርሻ አገልግሎት የሚውል ባለሞተር ማረሻ ተመረቀ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያን (ዶ/ር ኢንጂ.) ጨምሮ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የሮዳ ኢንጂነሪን ሠራተኞች በተገኙበት ተመርቋል።
ከዚህ ቀደም ከውጭ ሀገራት የአርሶ አደሩን ድካም ያቃልላሉ ተብለው የተገዙ ዘመናዊ የማረሻ መሣሪያዎች ከሀገራችን ድንጋያማ መሬት ጋር ባለመስማማታቸው የሚጠበቅባቸውን ጥቅም ሳይሰጡ በ አጭር ጊዜ ውስጥ ከጥቅም ውጭ ይውላሉ። ይህ በኢትዮፕያውያን ዲዛይን ተደርጎ የተሠራው ባለሞተር ማረሻ ግን ለሀገራችን መሬት ተስማሚ እንዲሆን ተደርጎ የተሠራ ነው።
ማረሻው ከተገጠመለት ሞተር ውጪ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሠራ በመሆኑ ለጥገና፣ ማሻሻያ ለማድረግና ተጨማሪ ጥቅሞችን ለመጨመር የተመቸ መሆኑን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በቀጣይ በዚሁ ባለሞተር ማረሻ ላይ አርሶ አደሩ ተቀምጦ የሚያርስበት፣ መሬቱን ለመጎልጎል የሚያስችል፣ ምርቱን ማረሻው ላይ ለመጫን የሚያስችሉ አዳዲስ ግልጋሎቶችን እንዲሰጥ ተደርጎ እንደሚዘምን የሮዳ ኢንጂነሪን ባለቤት አቶ አክሊሉ አባተ ተናግረዋል። ማጨድና መውቃት፣ እንዲሁም ምርት መሰብሰብ የሚችል መጎታችም በቀጣይ እንደሚሠራለት ተጠቁሟል። አርሶ አደሩ በቀላሉ ነዳጅ ማግኘት እንዲችል ከእፀዋት ተረፈ ምርት መሠራት የሚችል ባዮፊዩል (biofuel) እንዲጠቀምም ይደረጋል።
አርሶ አደሮቻንን እስከ ዛሬ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አላደርግናቸውም ያሉት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) በቀጣይ ችግሮቻቸውን የሚያቃልሉ ቴክኖሎጂዎችን ማላመድና መፍጠር ላይ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል። አክለውም፥ ባለሞተር ማረሻውን አርሶ አደሮች የመግዛት አቅም ኖሯቸው እንዲጠቀሙበት ለማድረግም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ይሠራል ነው ያሉት።
ባለሞተር ማረሻውን ከማዘመንና ጠጨማሪ አገልግሎቶችን አንዲያረክት ማሻሻያዎችን ከማድረግ በተጨማሪ ዋጋውም ከጥንድ በሬዎች መግዣ ባነሰ ዋጋ አርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ ጥረት ይደረጋል ተብሏል። ባለሞተር ማረሻው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በሮዳ ኢንጂነሪንግ ትብብር የተሠራ ነው።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- በአዲስ አበባ “ለሁሉ” የክፍያ ማዕከላት ተገልጋዮች መጉላላት እየገጠማቸው ነው
- የሴቶችን ጫና የሚያቃልሉ የተወሰኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባሉ
- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ነው
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
- ቮልስዋገን በኢትዮጵያ የመኪና መገጥጠሚያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፤ የጀርመን የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በስፋት ለመግባት እያመቻቹ ነው
የሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ከሚያዚያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል። ዶ/ር ጀማል ዩኒቨርሲቲው ውስጥ እ.ኤ.አ ከ2003 ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ቦታዎች አገልግለዋል።
ጅማ (ሰሞነኛ) – ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለፕሬዝዳንትነት ቦታ ብቃቱና ፍላጎት ያላቸዉ አመልካቾች እንዲወዳደሩ ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ባወጣዉ ግልጽ ማስታወቂያ መሠረት አመልካቾች መረጃቸዉን በማስገባት በተለያዩ ደረጃዎች ዉድድር ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል::
በምርጫ ሂደቱም ከ250 በላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የዩቨርሲቲዉ ሴኔት እና የሥራ አመራር ቦርድ መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የቃለ-መጠይቅ ፓናል በማካሄድ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩና ማጣሪያዎችን አልፈው የደረሱ 9 ዕጩዎችን በመገምገም 5 ዕጩዎችን ለዩኒቨሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ አስተላልፏል።
የዉድድሩ ሂደት የተመራዉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣዉ መስፈርት ሲሆን፤ ሂደቱን ለመምራት አምስት ሰዎችን የያዘ ኮሚቴ ተቋቁሞ በየደረጃዉ ግምገማ ሲያካሄድ ቆይቷል። ኮሚቴዉ ከቦርድ አባላት፣ ከሴኔት አባላት፣ ከተማሪ፣ ከመምህራን እና ከአስተዳደር ሠራተኞች ተወካይ የተዉጣጣ ሲሆን የዉድድር ማስታወቂያ ከማዉጣት ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ ጉባዔ የሂደቱን ዉጤት እስከ ማሳወቅ ድረስ በትጋት ሲሠራ ቆይቷል።
በዚሁ መሠረት የዩኒቨርሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ ሚያዚያ 02 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሔደው ልዩ ጉባዔ 3 ዕጩዎችን (ዶ/ር ጀማል አባፊጣ፣ ፕሮፌሰር አርጋዉ አምበሉ እና ዶ/ር ናቃቸዉ ባሹን) በዕጩነት ለሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አቅርቧል:: የሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ዶ/ር ጀማል አባፊጣን ከሚያዚያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል።
ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የዩኒቨርሲቲዉ ነባር መምህር እና ተመራማሪ ሲሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች በዩኒቨርሲቲውና ከዩኒቨርሲቲው ውጭ በሃላፊነት ያገለገሉና በአሁኑም ወቅት የማኅበረሰብ አገልግሎት ቢሮ ዳይሬክተር ሆነዉ እያገለገሉ ይገኛሉ። ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስታቲስቲክስ (BSc in Statistics)፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ (MA in Economics)፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በደቡብ ኮርያ ቻንችኦን ከተማ ከሚገኘው ካንግዎን ናሽናል ዩኒቨርሲቲ (Kangwon National University; Chuncheon, South Korea) በግብርና ግብዓቶች ምጣኔ ሀብት (Agricultural Resources Economics) አግኝተዋል።
ስለ ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ይህን ማስፈንጠርያ በመጫን ሙሉ መረጃ ማግኘት ይችላሉ።
ምንጭ፦ ጅማ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና እና ኪነ-ሕንፃ ዘርፍ ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ
- የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንፃ (አርክቴክቸር) ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን አስመረቀ
- አክሱም ዩኒቨርሲቲ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምህንድስና ትምህርት ክፍል ሊከፍት ነው
- ዩኒቨርሲቲዎች በሦስት መስኮች ተደልድለው እንዲያስተምሩ የሚያስችል ጥናት እየተጠናቀቀ ነው
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
አንዳንድ ሰዎች በቅርቡ ሸዋ ዳቦ መጋገሪያ በአንድ ዳቦ ላይ 100 ፐርሰንት ዋጋ ጨምሯል ብለው ኢትዮጵያዊ በዚህ ሳቢያ አብዮት ያነሳል ብለው ሲሰጉ ባየሁ ጊዜ ስቄያለሁ። የኢትዮጵያዊነት ስነልቦና አልገባንም ማለት ነው።
“የዳቦ ፖለቲካ!!”
በጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ – አዲስ አበባአንድ ወቅት ግብጽ ላይ የዳቦ ዋጋ 10 ሳንቲም ጨመረ ተብሎ አብዮት ተነስቶ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ በቅርቡም ሱዳን ላይ እንዲሁ ሆኖ ነበር።
አንዳንድ ‘ፌስቡካውያን’ ሸዋ ዳቦ በቅርቡ በአንድ ዳቦ ላይ 100 ፐርሰንት ዋጋ ጨምሯል ብለው ኢትዮጵያዊ በዚህ ሳቢያ አብዮት ያነሳል ብለው ሲሰጉ ባየሁ ጊዜ ስቄያለሁ። በዳቦ ዋጋ ጭማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ይነሳል ካልን የኢትዮጵያዊነት ስነልቦና አልገባንም ማለት ነው።
ኢትዮጵያዊ ከዳቦ ዋጋ በላይም የየዕለት ኑሮውን የሚፈትን ስንት የዋጋ ንረት ጫንቃው ላይ እያናጠረበት መልካም ቀን በተስፋ የሚጠብቅ ሕዝብ እንደሆነ ለናንተ አልነግራችሁም።
ኢትዮጵያዊ አንድ ሊትር ኬሮሲን (kerosene) ከ400 ፐርሰንት በላይ ዋጋ ጨምሮበት እንኳን ወደከሰል ምድጃው ተመልሶ እሳት እፍ ሲል እንጂ አብዮት ሲቀሰቅስ አታውቁትም።
ኢትዮጵያዊ 5 ብር የሚገዛው ስኳር 20 ብር ሆኖበት እንኳን እንደ ድሮው ቡና በጨው ሲጠጣ እንጂ አብዮት ሲቀሰቅስ አላየነውም።
ኢትዮጵያዊ የግል ትምህርት ቤት ክፍያ በየዓመቱ በ50 በመቶ ሲጨምርበት ልጆቹን ወደመንግስት ትምህርት ቤት ሲያዛውር እንጂ በቁጣ አብዮት ሲያነሳ አይቶት የሚያውቅ የለም።
ኢትዮጵያዊ የትራንስፖርት ዋጋ በዓመት ስንት ጊዜ ሲጨምርበት “እንደውም ጤና ነው” ብሎ በእግሩ ሲገሰግስ እንጂ አብዮት አንስቶ ሲሯሯጥ አልታየም።
ኢትዮጵያዊ የነዳጅ ዋጋ ከኪሱ በላይ ሲሆንበት መኪናውን አቁሞ በእግሩ ሲንከላወስ እናየው ይሆናል እንጂ “ምቾቴ ተጓደለ!” ብሎ አብዮት ሲቀሰቅስ አልታየም።
ኢትዮጵያዊ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ከእሁድ እስከ እሁድ እንዲሠራ ተደርጎ አንድ ሰዓት ቢዘገይ “አረፈድክ” ተብሎ ደሞዙ ሲቆረጥ የመጣውን በጸጋ ሲቀበል እንጂ አመጽ አቀጣጥሎ አብዮት ሲጠራ አላየንም።
ኢትዮጵያዊ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ማግኘት ሰማይ ቤት አንደመግባት ዕድል ሆኖ እንኳን አከራዮች በየወሩ ኪራይ ሲቆልሉበት እንባውን ወደላይ ይረጭ ይሆናል እንጂ መርሮት አብዮት ሲቀሰቅስ አይተነው አናውቅም
ኢትዮጵያዊ አንድ ኩንታል ጤፍ 3 ሺህ ብር ሲገባ “ልመደው ሆዴ” ብሎ ስንዴ ደባልቆ ሲያስፈጭ እንጂ መረረኝ ብሎ አብዮት ሲያነሳ ያየው ማንም የለም።
ኢትዮጵያዊ ማለት ይህ ሁሉ የኑሮ መርግ ተጭኖት እንኳን ደሞዝ ስላልተጨመረለት አደባባይ ወጥቶ አብዮት ሲለኩስ የታየ ሕዝብ አይደለም።
እናም ኢትዮጵያዊ ይህን ሁሉ ሆኖ እንኳን እንደ ቆርቆሮ የሚንኳኳ ሕዝብ ሳይሆን ሲቀጠቅጡት ቢውሉ ድምጹ ጎልቶ የማይሰማ ሕዝብ ነው።
የሚደንቀው ነገር ሰዎች ይህ ሁሉ ፍርሃት፣ ሞኝነት፣ ባርነት የሚመስለው ሰው መብዛቱ ነው። በፍጹም!
ኢትዮጵያዊ ስሜታዊ ሕዝብ አይደለም። “የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል” ባይ ታጋሽ ሕዝብ ነው። “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” ባይ እርጋታን ወዳድ ሕዝብ ነው። የመጣውን መንግስት ሁሉ “እንየው! ጊዜ እንስጠው! እንታገሰው” የሚል ሕዝብ ነው።
ኢትዮጵያዊ ቁጣው እንደግስላ፣ ትዕግስቱ እንደግመል፣ የዋህነቱ እንደርግብ፣ ብልጠቱ እንደእባብ የሆነ ረቂቅ ሕዝብ ነው።
ችግር የሚመጣው ዝምታው እንዳላዋቂነት፣ ታጋሽነቱ እንደጅልነት፣ ታዛዠነቱን እንደባርነት የተቆጠረበት ጊዜ ነው። ልብ በሉ!
ያኔ “ከረጋ ውሃና ዝም ካለ ሰው” ብሎ መውደቂያህን ያፈጥነዋል። “መከበር በከንፈር” ብሎ የአፍህን ዋጋ ይከፍልሃል። ክብር ይፈልጋል። ንቄትን ይጠላል። ካከበርከው ያገንንሃል። ከነገርከው ይ’ረዳሃል። ካሴርክበት ድራሽህን ያጠፋዋል።
እናም ይግባህ! በኢትዮጵያ ውስጥ ቅሬታ አብዮት ወልዶ የማታየው ለዚህ ነው። ህዝቡ ቅሬታውን ነገ ይስተካከላል በሚል ተስፋ መርሳት እና ‘እስኪ የሚሆነውን እንጠብቅ’ በሚል ትዕግስት ማመቻመች የሚችል ባህሪ ያለው ሕዝብ ነው። ዋናው ነገር ቅሬታው ተጠራቅሞ ብሶት እስኪሆን አለመጠበቅ ነው።
በተረፈ የሕዝቡ ዛሬን በትዕግስት ማለፍን ለነገ ሃገር ዋጋ ከመስጠት ጋር እንጂ ጀርባን ለዱላ ከማመቻቸት የባርነት መንፈስ ጋር አዳብለህ አትይበት ! በትንሽ በትልቁ እንደቆርቆሮ እንዲንኳኳም አትጠብቀው። የኛ ፖለቲከኞች ትልቁ ችግር እንመራዋለን የሚሉትን ሕዝብ አለማወቃቸው ነው!
እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው ….
አብዮት የናፈቀው ሰው ‘አብዮት ፍሬ’ የሚባለው ትምህርት ቤት ሄዶ እጁን ይስጥ … (ቦታውን ከፈለጋችሁ እጠቁማችኋለሁ)።
በጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላብራቶሪ ኃላፊ እንደተናገሩት፥ የላብራቶሪ መሣሪያዎቹ በአገሪቱ የመጀመሪያ መሆናቸውን እና በጣም ጠቃሚ የሆኑ የአሚኖ አሲድ መጠኖችን ከምግብና ከደም ናሙና ላይ ለመለየት የሚያግዙ እንደሆኑ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጣሊያን መንግስት ግምታቸው 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሆኑ የላብራቶሪ እቃዎች በእርዳታ አገኘ።
የጣሊያን መንግስት በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) አማካኝነት የለገሰው በተለያዩ ምግቦች ውስጥ የሚገኘውን የአሚኖ አሲድ መጠን የሚለኩ የአሚኖ አሲድ እና የክሩድ ፋት አናላይዘር (amino acid and crude fat analyzer) የተሰኙ የላብራቶሪ መሣሪያዎች ሲሆኑ ግምታቸው 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ይሆናል።
ርክከቡ በኢንስቲትዩቱ ግቢ በተከናወነበት ወቅት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ እንዳሉት፥ በልገሳ የተገኙት የላብራቶሪ እቃዎች ኢንስቲትዩቱ ለሚያከናውናቸው ጥራት ያላቸው የምርምር ሥራዎች ወሳኝ ጥቅም እንዳላቸው ጠቅሰው፤ የኢንስቲትዩቱን ማገዝ አገሪቱ የምግብ እጥረትን ለመቀነስ የምታደርገውን ጥረት ማገዝ ነው ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ከሃያ ዓመት በፊት ጀምሮ በተለያዩ ሥራዎች እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፥ የጣሊያን መንግስት በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት በኩል ላደረገው እርዳታ ምስጋና አቅርበዋል።
● SEMONEGNA on Social Media: Facebook | Twitter | Instagram | Pinterest | Video | Forum
የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተወካይና የቀጣናው ዳይሬክተር ሚስ ኢውሬሊያ ፓትሬዝያ ካላብሮ ካላብሮ (Aurelia Patrizia Calabrò) እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአጋር ድርጅቱ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን (EFDA) ጋር በመተባበር ለሚያከናውነውና በሞሪንጋ የምግብ ጠቀሜታና ይዘት ምርምር ላይ ጠቃሚ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።
የጣሊያን የልማትና ትብብር ኤጀንሲ (Italian Agency for Development Cooperation/ AICS) ተወካይ ፌቨን ጌታቸው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለጣሊያን ቅድሚያ ከሚሰጣቸው አገራት አንዷ መሆ ኗን ገልጸው፥ በግብርና፣ በጤና እና በኢንዱስትሪ መስኮች የተለያዩ የትብብር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አመልክተዋል። የዛሬው እገዛ በሞሪንጋ እየተሠራ ላለው ፕሮጀክት ሁለተኛው ዙር ድጋፍ መሆኑን ገልጸው ወደፊትም ትብብሩ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
ከእቃዎቹ ርክክብ በኋላ የምግብ ሳይንስ እና ሥነ ምግብ ምርምር ላብራቶሪ ጉብኝት ተደርጓል። በጉብኝቱ ወቅት የኢንስቱትዩቱ ላብራቶሪ ኃላፊ አቶ መሰረት ወልደዮሐንስ በሰጡት ገለፃ መሠረት፥ የላብራቶሪ እቃዎቹ በአገሪቱ የመጀመሪያ መሆናቸውን እና በጣም ጠቃሚ የሆኑ የአሚኖ አሲድ መጠኖችን ከምግብና ከደም ናሙና ላይ ለመለየት የሚያግዙ እንደሆኑ ገልጸዋል።
የላራቶሪ እቃዎቹ እንደ አገር በጣም ጠቃሚ መሆናቸውን አውስተው፥ ለግልም ይሁን ለመንግስት ተቋማት እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑን አቶ መሰረት አመልክተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴዎች ዙሪያና በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠረጥረዉ በቁጥጥር ስር እየዋሉ የሚገኙ አካላትን በተመለከተ ሚያዚያ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኃላ በጽሕፈት ቤታቸው ለመገናኛ ብዙኀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመንግስት ተቋማት እና ፕሮጀክቶች ላይ የተፈጸመ ከባድ የሙስና ወንጀልን በተመለከተ በተለይም የመንግስት ግዥ ንብረት አስተዳደርና ማስወገድ አገልግሎት፣ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንና በመድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲ በሦስቱም ተቋማት በበርካታ ሚሊየን የሚቆጠር የመንግስትና የሕዝብ ሀብት የመዘበሩ ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተደራጀዉ የምርመራ ቡድን በቂ ማሰረጃና መረጃ በመሰብሰብ 59 በወንጀሉ የተጠረጠሩ የቀድሞ የሥራ ኃላፊዎችና ግብረ-አበሮች በቁጥጥር ሥር በማዋል ዐቃቤ ሕግ ክስ ለመመሥረት ተጨማሪ የምርመራ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተደራጀ መልኩ በሙስና ወንጀል እጃቸው አለበት ተብሎ ከተጠረጠሩት መካከልም የቀድሞ የመንግስት ግዥ ንብረት አስተዳደርና ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግስቱ ከበደ፣ የመንግስት ግዥ ንብረት አስተዳደርና ማስወገድ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተሮች፣ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ አትክልት ተካ፣ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ፣ የመድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲ (PFSA) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ኃይለስላሴ ቢሆን፣ የመድሃኒት ፈንድ ኤጀንሲ ም/ዋ/ዳይሬክተር እና ሌሎች የነዚህ ተቋማት መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች በተጨማሪም በጥቅም የተሳሰሩ ሌሎች ግበረ-አበሮቻቸው እንደሚገኙ በመግለጫዉ ይፋ ተደርጓል።
በተያያዘም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሀኑ ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፥ ተቋሙ የሕግና የፍትህ ምህዳሩን ለማስፋትና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የቆመላቸው ዋና ዋና ዓላማዎች ማለትም ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማክበርና ማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የወንጀል ሕግን ማስከበርና የፌዴራል መንግስቱን እና የሕዝብን የፍትሀ ብሄር ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ተቋማዊ ለውጦችን ማከናወኑን ተናግረዋል።
በመደበኛ ሥራዎች ላይም ሰፋፊ ለዉጦች ማምጣት ጀምረናል ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ፥ በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎችና አተገባበር በማጥናትና የባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ለማሻሻል የሕጎቹን አተገባበር የሚገመግም ጥናትና በጥናቶቹ ግኝት ተከታታይ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኮች በማካሄድ ከተገኘው ግብዓት በመነሳት ረቂቅ ሕግ የማዘጋጀትና በረቂቅ ሕጎችም ላይ ግብዓት የማሰባሰብ ተግባር መከናወኑን አዉስተዉ አጠቃላይ የተሠሩ የሕግ ማሻሻያዎችን አፈፃፀምን በመግለጫቸዉ አንስተዋል።
በተጨማሪም በልዩ ሁኔታ ምርመራና ክስ እየተደረገባቸው ያሉ ጉዳዩችን በተመለከተ የሰብዓዊ መብት ጥስት ወንጀል ፈጽመዋል በሚል 42 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዉለዉ የወንጀል ምርመራ ሲጣራባቸው የነበረ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ በ10 የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት እንዲሁም በ9 የማረሚያ ቤት አመራሮች ላይ ክስ ተመሥርቶ በክርክር ሂደት ላይ ያለ ሲሆን፣ በ21 የደኅንነት አባላት ምርመራ ተከፍቶ ምስክር እየተሰማ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በተያያዘ መልኩም በተለያዩ ቦታዎች ከተፈጠሩ ሁከትና ብጥብጦች ጋር ተያይዞ በተከናወነ የምርመራ ሥራዎች በወንጀል ተግባራት የተሳተፉ አካላትን ለይቶ ለሕግ በማቅረብ በኩል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ለአብነትም በሐዋሳ ከተማ ከተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ፣ ሱማሌ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈጸመ ወንጀል፣ በኦሮሚያ ክልል ቡራዩና በአዲስ አበባ በተለያዩ በክፍለ ከተሞች ተነሰቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
በመጨረሻም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ አካባቢዎች ዓለማቀፍ ግንኙነት ያላቸዉና የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በዝግጅት ላይ የነበሩ አካላትን ሊያደርሱት የነበሩትን ጉዳት በመቆጣጠርና ቁጥጥር ስር ለማዋል ከብሔራዊ የመረጃ ደኅንነት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንና የምርመራው ሂደት እንደተጠናቀቀ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ካሉ በኋላ ሰላም የሁላችንም ሀብት በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከመንግስት ጎን በመቆም በጋራ ሊሠራ ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ (ኢፌዴሪ) መንግስት ከኔዘርላንድ መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ የሕፃናት ሆስፒታል ለመገንባት የሚውል የ27.44 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ስምምነት ተፈራርሟል። በተጨማሪም የአደጋ (trauma) ሕክምና መስጫ ማዕከል ይገነባል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) የኢትዮጵያ መንግስት ከኔዘርላንድ መንግስት ጋር በመተባበር ከ1.8 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ በአለርቲ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በአይነቱ ልዩ እና የመጀመሪያ የሆነ አዲስ የሕፃናት አጠቃላይ ሆስፒታል ለመገንባት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ በሕፃናት ዙሪያ የሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶችን ማሻሻልና ማዘመን አስፈላጊ ከመሆኑ አንጻር ሆስፒታሉ በሕፃናት ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የልብ፣ የነርቭ፣ የኩላሊት እንዲሁም ከ30 በላይ የሚደርሱ የሕክምና ስፔሻሊቲ አገልግሎት እንደሚኖሩት ተናግረዋል።
በአለርት ሆስፒታል ውስጥ የሚገነባው የሕፃናት አጠቃላይ ሆስፒታል በሁለት አመት እንደሚጠናቀቅና 317 አልጋዎች እንደሚኖሩት ወጪውም በኔዘርላንድ መንግስት፣ በአሜርካን ፋውንደሽን እና በኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፍን በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተገልጧል።
ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የአደጋ (trauma) ሕክምና መስጫ ሆስፒታልን ለመገንባት ከእቴቴ ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር ሚያዝያ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ውል ተፈራርሟል።
ጤና ሚኒስቴር ከእቴቴ የኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር ውል በተፈራረሙበት ወቅት የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን እንደተናገሩት፥ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱና ለህመም፣ ለአካል ጉዳት እና ለሞት የሚያጋልጡ አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመምጣታቸው በዚህ ዙሪያ የሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶችን ማሻሻልና ማዘመን አስፈላጊ በመሆኑ በድንገተኛ አደጋዎችና ተጓዳኝ ሕክምናዎችን የሚሰጥ ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ አለርት ሆስፒታል ውስጥ ይገነባል ብለዋል።
ከ751 ሚሊዮን ብር በላይ የተመደበለት እና ባለ 8 ፎቅ የሚገነባለት ይህ ማዕከል በ3 ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የታሰበ ሲሆን፤ ከ550 በላይ አልጋዎች የሚኖረውና በቀን ከ2000 እስከ 5000 ተገልጋዮችን ማስተናገድ የሚችል እንደሚሆን ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።
የግንባታው በጀት ሙሉ በሙሉ ከመንግስት በመሆኑና ተቋራጩም በተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ሰፊ ልምድ ያለው በመሆኑ በግንባታ ሂደቱ ወቅት ያጋጥማል ተብሎ የሚያሳስብ ችግር የለም ተብሏል።
ምንጭ፦ ጤና ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው ሆስፒታል ተመረቀ
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታ 56 በመቶ ደርሷል
- የአርሲ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ4ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 388 የህክምናና የጤና ተማሪዎች አስመረቀ
- ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች መሠረታዊ ችግሮች በጥናት ሊለዩ ይገባል ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ
- አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገነባው የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ አይጠናቀቅም
በሦስት መስኮች ዩኒቨርሲቲዎቹን መደልደል ያስፈለገው፥ እስካሁን የትምህርት ተቋማቱ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ለማስተማር ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ ስላልነበር እንደሆነ ተነግሯል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር፣ የቲቺንግና የፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ ተብለው ለሦስት ተከፍለው እንዲሠሩ የሚያደርግ ጥናት እያለቀ መሆኑንና በጥናቱ ውጤትም ላይ በቅርቡ ውይይት እንደሚደረግ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ሂሩት ወልደማርያም (ዶ/ር) ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለጹ። ምደባው ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና በትኩረት አቅጣጫ የመደልደል ነገር በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተመልክቷል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ለምርምር የተሻለ የመሠረት ልማትና የሰው ኃይል ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ዩኒቨርሲቲ መደብ ውስጥ እንደሚገቡና በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ፕሮግራሞችንም እንደሚሰጡ አስረድተዋል። የንድፈ ሐሳብና ተግባራዊ ትምህርት አጣምረው የሚሰጡ ፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲዎች መደብ ሥር የሚገቡት ለተግባር ትምህርት የተሻለ የመሠረተ ልማት ዝግጅት ያላቸው ይሆናሉ ተብሏል። ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ሠልጣኞችን እንዲያፈሩና ለቴክኒክና ሙያ ተቋማትም የበቁ መምህራንን እንዲያወጡ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ዶክተር ሂሩት ናቸው። የተቀሩት የማስተማር ተግባር (ቲቺንግ) ላይ የሚያተኩሩ መርሀ ግርብሮች ላይ የሚያተኩሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሆነው እንደሚቀጥሉም ታውቋል።
በሦስት መስኮች ዩኒቨርሲቲዎቹን መደልደል ያስፈለገው፥ እስካሁን የትምህርት ተቋማቱ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ለማስተማር ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ ስላልነበር እንደሆነ ተነግሯል።
◌ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
“ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማሩም፣ በምርምሩም፣ በቴክኖሎጂውም፣ በግብርናውም፣ በሁሉም ዘርፎች ነው የሚያስተምሩት። ይህ ደግሞ ውጤታማ ሊሆኑ በሚችሉበት መስክ እንዳይሠሩና ሀብትም እንዲበታተን አድርጓል” ያሉት ሚኒስትሯ፥ ድልድሉም ዩኒቨርሲቲዎቹ እንዳላቸው የመሠረት ልማት ዝግጅትና ያሉበት አካባቢ ከሚሰጣቸው መልካም አጋጣሚ አንፃር እየታየ ነው ብለዋል።
እንደ ላሊበላና አክሱም ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አርኪዮሎጂ ላይ ያተኮሩ የልህቀት ማዕከላት (center of excellence) ቢሆኑ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኙ፣ በግብርና ላይ ተሞክሮና ታሪክ ያላቸው እንደ ሐሮማያ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በግብርና ውጤታማ የሆነ ባለሙያዎች ማፍራት እንደሚችሉ አስረድተዋል። “ሁሉም ላይ እንሥራ ሲሉ ግን ችግር ነው። በሁሉም ዘመናዊ ማሽኖችን፣ የምርምር ግብዓቶችን፣ ሪፈራል ሆስፒታሎችን መገንባትና ማሟላት አይቻልም፣ የአገርም ሀብት ይባክናል” ብለዋል።
ምንጭ፦ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦ለተከበሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ― ድምጻዊ ዳን አድማሱ
አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያለተከበሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ፥ እኔ እንደ አንድ ኢትዮጽያዊ ወጣት ይህን ማለት እወዳለሁ ተወልጄ ባደኩባት ሀገር ነፍስ ካወኩባት ጊዜ በሀገሬ ጉዳይ በነፍስ በስጋዬ ስሟገት እዚህ ደርሻለሁ።
በተለይም እድሜ ለቅንጅት ፓርቲ ወጣቱ መብቱን እንዲጠይቅ አንቅቶታል ብዬ አምናለሁ፤ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እየተገደለ፣ እየተቀጠቀጠ፣ እየታሰረ እዚህ ወንበር ላይ እርሶን አምጥቷታል።
እኔ የለውጡን ዋጋ የምሰጠው ለእግዚአብሔር ነው። ለውጡ የመጣው ፈጣሪ ለዚህች የቃልኪዳን ምድር ስለራራላት ነው፤ እንዲራራላት ደግሞ ወይባ ለብሰው በገረገራ የፆሙ፣ የፀለዩ፣ በየመስጊዱ ውስባህ ይዘው ዱአ ያደረጉ፣ የትውልድ ወላጆች ፈጣሪ ከሰማይ እንዲወርድ፣ ከመንበሩ እንዲነሳ አድርገውታል። ሲቀጥል የደም ትንሽ ትልቅ የለውም፤ ድፍን ኢትዮጵያዊ ዋጋ ከፍሏል፤ የድሀ እንባ፣ የወጣት ደም፣ የእናት፥ የአባት ለቅሶ ወደ ላይ ጮሆ አምላክ ለኢትዮጵያ ወርዷል፤ በዚች የአኬልዳማ ምድር ግን የአቤል ደም አሁንም ይጮሀል።
በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በሀገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ‘ሆ!’ ብለን ስንወጣ፥ ስለ እርሶ በቂ ዕውቀት እንኳን ኖሮን አይደለም። መጀመሪያ ሰው ኖት፤ ሲቀጥል ‘ኢትዮጽያ’ ብለው መጡ። ያኔ ሁለቴ አላሰብንም! እንደ ምድር አሸዋ በዝተን፣ እንደ ሰማይ ኮከብ ደምቀን መጣን። የኢትዮጵያ አምላክ ቀድሞን ባይወጣ ኖሮ እነዛ ሰማዕትት ከሁለት ሰው ወደ ሀያ ሚሊየን ላለመድረሳቸው ማንም እርግጠኛ አልነበረም። ወጣቱ ሰማዕት ከሞት ጋር ተናንቆ ‘የኔ ችግር የለም፤ አብይን አደራ’ ሲል ምን እንደተሰማዎት ባላቅም ኢትዮጵያን አደራ እያሎትም ጭምር ነበር። ከዛች ቀን ጀምሮ በርካታ መልካም ጅማሮዎትን አይተን እግር በእግር እየተከተልን ምስጋናን እና ማበረታታትን አልተውንም፤ ግን እውነቱን ማወቅ ከፈለጉ ይህን አንድ ዓመት በጥፍር ቆመን አሳልፈናል፤ ጠዋት ስንነቃ ከአዋውፋት መዝሙር ይልቅ የሕዝብ እሮሮ ቅርባችን ነው፤ ማታ የእንቁራሪት ሲርሲርታ ሳይሆን የሕዝቦች ዋይታ ቤታችን ነው።
ለምን ደጋግመው ሲሉት እንደሰማሁት ማሰር እና መግደል ስለማያዋጣ እየታገስን ነው ማለት ምን ማለት ነው? በማን ደም ነው ትዕግስት የምንለማመደው? በማንስ ለቅሶ ነው ትከሻ የምናሰፋው? በጌዲኦ፣ በአጣዬ የሚሞተው ህፃን የእርሶ ልጅ ቢሆን ትንሽ ልታገስ ይሉ ነበር? ቆይ ታግሰው ሁለተኛ ልጆን ቢነጠቁ ‘መግደል መሸነፍ ነው’ ይላሉ? አይመስለኝም።
ስለዚህ እርሶ ኪጋሊ፣ ሩዋንዳ ያስቀመጡትን አበባ የሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ እዚህ መጥተው እንዳያስቀምጡት ትዕግስቱ ገደብ ቢኖረው የተሻለ ነው እላለሁ። ይህን ሁሉ ችግር መፍታት ቀላል እንዳልሆነ ብንረዳም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና የአዲስ አበባ ልጅ ላይ የተሰጠውን ጠንከር ያለ መግለጫ ዓይነት መስጠት ግን ከባድ አይመስለኝም። እዚህ ላይ መጨመር የምፈልገው ከእያንዳንዱ ችግር ጀርባ በሚሊየን የሚቆጠረውን ደግ እና ሀገር ወዳድ የኦሮሞ ህዝብ ለእያንዳንዱ ችግር አብረን ባንወቅጠው ጥሩ ነው፤ ካልሆነ ግን እኛ እርሶን ከልባችን ላለማውጣት የምንታገለውን ያክል እርሶ ከልባችን ለመውጣት እየታገሉ ይመስለኛል።
ዳን አድማሱ (ድምጻዊ)
አንድ ኢትዮጵያ
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከስዊድኑ ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ (The University of Gothenburg) ጋር በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤን የሚመለከት ትምህርት ለመስጠት የሚያስችላቸው የመግባቢያ ሰነድ ይፈርማሉ።
በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ መስክ በሀገራችን ያለውን የባለሙያ እጥረት የሚቀርፍ መነሻ ሀሳብ ከስዊድን ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ የመጡ መምህራን ለክቡራን ሚንስትሮች ገለፃ አድርገዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሀገራችን ኢትዮጵያ ከስዊድን መንግስት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑ በተለይ በኪነ-ሕንፃ ትህምርት ዘርፍ ያላቸው ልምዶች ታሪካዊና ጠናካራ ግንኙነት የተፈጠረበት መሆኑ ብዙ ይወሳል።
በመሆኑም የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስዊድን ውስጥ በትልቅነቱ ሁለተኛ ከሆነው ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ (The University of Gothenburg) ጋር በትብብር ለመክፈት ያሰበው የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ እውን እንዲሆንና የቅርስ ጥገና ተግባራዊ ትምህርት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥ ታስቦ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በኩል ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርኪዮሎጂ (archeology) ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር መንግስቱ ጎበዜ፥ የታሰበው የትምህርት መርሀግብር ለክቡራን ሚኒስትሮች (ለፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና ለወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት፥ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ) የሥልጠናውን ዓላማና ግብ የሚያግባባ ገለፃና ትውውቅ አድርገውላቸዋል።
በመቀጠልም በልዑካኑ በስዊድን ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በኩል የመጡት መምህራን ያላቸውን ዝግጁነትና ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲሁም የገጠሩ ሕዝብ ባህላዊ ሀብቱን እየተወ ወደ ከተማ ከሚኮበልል እዛው በቅርሱ ተጠቃሚ የሚሆንበት መሠረት የጣለ ልምድ መኖሩን የሚያብራራ ገለጻ በ‘Bosse Lagerqvist’ እና ‘Lars Runnquist’ የልዑኩን ቡድ ኑን በመወከል ገለፃ አደርገዋል። ተመራማሪ ፕሮፌሰሮች በነሱ በኩል ተግባራዊ ትምህርቱ ከቁሰቁስ አቅርቦት እንደሚደገፍ ጭምር በትብብር የሚሠራበት ሁኔታ ለመፍጠር በቻርትና ስዕላዊ መግለጫዎች ማብራሪያ አድርገዋል።
◌ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
ለመርሀግሩ ማጠቃለያ ክቡራን ሚኒስትሮችም በበኩላቸው በሁለቱም ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት መልካም በሚባል ደረጃ የደረሰ መሆኑን በማመስገን፥ ያቀረባችሁት ሀሳብ የሚጠቅመንና እንደኢትዮጵያ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ መስክ የሚሰጡ ትምህርቶች በንድፈ-ሀሳብ ብቻ በመሆኑ በትብብር ስለምንሠራው ብዙ ባለሙያዎችን የምናፈራበት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የትምህርት ማስተማሪያ መርሀግብሩ የሁለተኛ ዲግሪ ለመስጠት የሚያበቃ ሲሆን፥ ለዚህ የመግባቢያ ሰነድ በቅርብ ጊዜ እንደሚፈረም እንዲሁም ተግባራዊ ትምህርቱ የሚሰጥበት ቦታ አንድ ካምፓስ በላሊበላ ቅርጫፍ የሚዘጋጅበት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
“ገና በጠዋቱ ሀገሪቱ መሪ እያላት ስርዓት አልበኝነት ነገሰ፣ ሕግ ረከሰ፣ የንፁሃን ደም በከንቱ ፈሰሰ የሚል ጩኸት ብዙዎች ቢያሰሙም የሽግግር ባኅሪው ነው በሚል ሚዛናዊ ምላሽ መስጠት አልተቻለም።”
———–ሚዛናዊነት ከራስ ቢጀምር ― ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)
አለማየሁ ገበየሁ
ፍርድ ቤት የቆመችው የፍትህ ምስል /Lady Justice/ ተጠሪነቷና ምሳሌነቷ ለፍርድ ቤት ሥራ ብቻ አይመስለኝም። አይኗን ሸፍና ያላጋደለ ሚዛን የያዘችው አስተዳዳሪዎች በሞራል ሕግ ተመርተው ለዜጎች ሁሉ ሚዛናዊ አገልግሎትና ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ነው።
ዶ/ር አብይ አህመድ ደጋግመው ስለሚዛናዊነት ይሰብካሉ። ጋዜጠኞች የተመጣጠነ ዜና እንዲያቀርቡ፣ አክቲቪስቶች ከዋልታ-ረገጥ ሀሳብ ወደ መሃል እንዲመጡ፣ ፖለቲከኞች እኔ ብቻ ነኝ አዳኝህ ወይም የማውቅልህ ከሚለው አባዜ ተላቀው ለሌላውም ሥራ እውቅና እንዲሰጡ ወዘተ…
የሚዛን መንሻፈፍ ግለሰብን፣ ማኅበረሰብንና ሀገርን እየቆየ እንደሚጎዳና ለማይጠገን ቀውስ እንደሚዳርግ የሚገነዘብ ሁሉ በዚህ ሀሳብ ይስማማል። ችግሩ ዶ/ር አብይ እንዳሉት ሁሉም ቀድሞ ጣቱን የሚቀስረው ሌሎች ላይ የመሆኑ አባዜ ነው። ይህ የጣት ቅሰራ ራሳቸው ዶ/ር አብይንም ይመለከታል። አንዱን ትልቅ ጥፋት ሸፋፍነህ ሌላው ላይ ጣትህን ስትቀስር ሚዛናዊነት ይንጋደዳል። አንዱን ትልቅ ጥፋት አላየሁም ብለህ አይንህን ከሸፈንክ ሌላኛው ጥፋት ላይ የአይንህን መጋረጃ ቀደህ ለመጣል ሞራል ታጣለህ።
ከብዙ ምሳሌዎች የተወሰኑትን ብቻ እናንሳ። ገና በጠዋቱ ሀገሪቱ መሪ እያላት ስርዓት አልበኝነት ነገሰ፣ ሕግ ረከሰ፣ የንፁሃን ደም በከንቱ ፈሰሰ የሚል ጩኸት ብዙዎች ቢያሰሙም የሽግግር ባኅሪው ነው በሚል ሚዛናዊ ምላሽ መስጠት አልተቻለም። ከዚህ ይልቅ በቅድሚያ ለውጡ ያመጣቸውን ትሩፋቶች ሳትደባብቁ አሞግሱ ማለት መጣ። ትክክል ነው ሚዛናዊ ለመሆን የበርካታ ባኅሪያት/ ጥሩ ተናጋሪ፣ ትዕግስተኛ፣ ይቅር ባይ፣ ትሁትና የሰላም አጋር/ መሆናቸውን መመስከር ይቻላል። በዚህ ጥሩ ባኅሪ በመታገዝም መንግስታቸው አስደሳች ፖለቲካዊ ድሎች አስመዝግቧል። ይህ ማለት ግን ለውጡ መሳ ለመሳ እየተጓዘ ያለው ከነውጥ ጋር ነው ነው ማለት ስህተት አይደለም። ሕገ-ወጥነት ሀገሪቷን የወረረው ይቅርባይነት ስለበዛ ነው የሚል የቄለ ግምገማ የለኝም – በዚህ ረገድ መንግስታቸው ስትራተጂካዊ ብቃት የለውም የሚለው ሀሳብ የበለጠ ቅርብ ነው። አሁን በቅርቡ እንኳን የሀገራችን ስርዓት አልበኝነት ተግባር ከ8 እስከ 10 ወራት ይቀጥላል በማለት እንደ ዓመታዊ ዕቅድ ነግረውናል። ሕገ-ወጥነትን አምርሮ ከመታገል ይልቅ ከሕገ-ወጥነት ጋር ተቻቻሎ ለመኖር ማሰብ ገራሚ አቋም ነው። በተሸፋፈነች ፍትሃዊ አይን ሚዛናዊነትን እንይ ከተባለ ከዚህም በላይ ነው።
መንግስት ባለበት ሀገር አሥራ ምናምን ባንኮች በጠራራ ፀሐይ ሲዘረፉ የሽግግር ሂደት ባኅሪው ነው የምትል ከሆነ ሌላውን ሌባ ወይም ሙሰኛ ለመገሰጥም ሆነ ፍርድቤት ለማቆም ይከብዳል። ምክንያቱም ፍ/ቤት የቆመችው የፍትህ ምስል ስለምትታዘብ። ለተቃውሞ ዱላና ገጀራ አደባባይ ይዞ የወጣ ማኅበረሰብ በቸልታ አልፈህ ያለዱላ ስብሰባ የከተመውን ወጣት በማያሳምን ምክንያት አስረህ የምታሸማቅቅ ከሆነ የሚዛናዊነት መሠረትህ ተናደ ማለት ነው። ይከበር እየተባለ የሚለፈፈው ሕግ ባለመከበሩ ዱላና ገጀራው አድጎ እነሆ ዛሬ የጦር መሣሪያ ይዞ አደባባይ መውጣት ተጀምሯል። በገዛ ፍቃድህ ሚዛናዊ ካልሆንክ ብሎም ቸልተኝነት እንደ ኩይሳ ካሳደግክ ሌሎች አደባባይ የተገተረውን የፍትህ ሚዛን በሌላ ጡንቻ ይሰብሩብሃል። ትርፉና ውጤቱም ይሄው ነው።
የቸገረው የከተማ ህዝብ ከሰውነት ተራ ወጥቶ በሠራው ኮንዶሚኒየም አትገባም ተብሎ ገጀራ ሲወደርበት “የባለገጀራዎች ሀሳብ ይለምልም” ብሎ መግለጫ ማውጣት እንዴት ሚዛናዊ ሊሆን ይችላል? በቡራዩና ለገጣፎ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰው መፈናቀል፣ እንግልትና አግላይ ርምጃዋች ከልብ ሳታወግዝ ሌላ ታፔላ ለጥፎ አደባብሶ ማለፍ የሚዛናዊነትን ጥያቄ ያስነሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር የሚበትኑ ሀሳቦች ይወገዙ ይላሉ። በሀገሪቱ ያለው ሁለት መንግስት የአብይና የቄሮ ይባላል የሚል ትንታኔ የሚሰጠው ጃዋር የበርካታ በታኝ ሀሳቦች ባለቤት ቢሆንም ውግዘት አይመለከተውም። ኦሮሞ ከቋንቋው ውጭ ሌሎችን ማነጋገር የለበትም፤ ከሌሎች ጋር መጋባትም ማቆም አለበት የሚለው የ“ምሁሩ” በቀለ ገርባ አፓርታይዳዊ አስተያየት ለመመርመርም ሆነ ለመተቸት አልተፈለገም። በተቃራኒው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚንቀሳቀሰው እስክንድር ነጋ ላይ ግልጽ ጦርነት እናውጃለን ተብሏል። ሲጠቃለል ዶ/ር አብይ በበቀለ፣ በኦነግ፣ በጃዋር፣ በሕገወጥ ፖለቲከኞችም ሆነ በእስክንድር ሀሳብ ላይ ሚዛናዊ መሆን አልቻሉም።
ለዚህም ነው ማንኛውም ሚዛናዊ ለመሆን የሚጥር ሰው ለምን የሚል ቀጥተኛ ጥያቄና እንዴት የሚል የጀርባ ምፀት ለማንሳት የሚገደደው። ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ እንዲሰብር ብሂሉ ስለሚያስገድድ? ምንም ቢሆን ዘር ከልጓም ስለሚስብ?… ኢትዮጵያዊነትን መርህ አድርጌያለሁ የሚል መሪ ለጃዋርም ሆነ ለእስክንድር ሀሳቦች እኩል የድጋፍም ሆነ የተግሳጽ መስፈርት ማበጀት ካልቻለ መርሁ ሁሉ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ ለራሱ ችግር ይፈጥሩበታል (backfire ያደርግበታል)። ዶ/ር አብይ ከጊዜ ወደጊዜ እየገረጣ የመጣባቸውን ሕዝባዊ እምነት ስር ሳይሰድ ለማከም ከፈለጉ ሚዛናዊነት ከራሳቸው መጀመር ያለባቸው ይመስለኛል። ጥሩ መሪ ደግሞ እንደዛ ነው። መንገዱን የሚያውቅ፣ በመንገዱ የሚሄድ እና መንገዱን የሚያሳይ ስለሚሆን። ባለጊዜ ነን በሚሉ ቡድኖች የሚጊሩ አስከፊና አቀያያሚ ጉዳዮችን አደብ ማስገዛት፣ አቅም ቢያጥር እንኳን በግልጽ ‘አካፋን አካፋ’ በማለት ማውገዝ መጀመር አለባቸው። ከዚህ ከጀመሩ ሌላኛውን ብልሹ ሀሳብና ተግባር ለማረቅ ምቹ መደላድል ይፈጥራል። ይህ አካሄድ ልበ ሙሉነትን በቀላሉ ማትረፍ የሚያስችል ሲሆን፥ ከሁሉም አቅጣጫ በቂ ድጋፍ ያስገኛል። አክባቢዎን በሚያውቋቸው ሰዎች መሙላት ብቻ ሳይሆን ገለልተኛና ሚዛናዊ ሀሳብ የሚሰጡትንም አማካሪዋች ቢያበዙ ጭልጥ ብሎ ከመሳሳትም ያድናል።
አለማየሁ ገበየሁ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል አለማየሁ አፅም ከሀገረ እንግሊዝ ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ ኢትዮጵያ ተጠየቀ። በተጨማሪም ለንደን ከተማ ውስጥ በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም (Victoria and Albert Museum) የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።
በኢፌዴሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድን መጋቢት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በለንደን ጉብኝት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም በለንደን የዊንዶዘር ቤተመንግስት (Windsor Castle) የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን መካነ መቃብር እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አፄ ሃይለስላሴ ይጸልዩበት የነበረውን ወንበር ጎብኝተዋል።
ዶ/ር ሂሩት ካሳው በአጼ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል አለማየሁ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን እንደመረጃ ምንጭነት በመጥቀስ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
በጉብኝቱ ወቅትም “የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ማግኘታችን ደስ ብሎናል፤ ይሁን እንጂ ከትውልድ ቦታው ተለይቶ ህይወቱ ያለፈው ልዑል አለማየሁ አፅም በትውልድ ሀገሩ እንዲያርፍ የኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ስለሆነ በክብር ወደ አገሩ እንዲመለስ” ሲሉ ዶክተር ሂሩት ጠይቀዋል።
አፅሙ ወደኢትዮጵያ ተመልሶ ከአባቱ አጼ ቴዎድሮስና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መቀላቀል እንደሚገባውና የዊንዶዘር ቤተመንግስት ለሚመለከተው አካል ጥያቄውን አቅርቦ በአፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ ልዑካን ቡድኑን በመቀበል ከቡድኑ ጋር የተወያዩት የዊንዶዘር ቤተ-መንግስት ሃላፊ ዶ/ር ማርክ ፓወል በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንነጋገርበታለን ብለዋል። ሂደቱን በተመለከተ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመከታተል እልባት እንዲያገኝ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግም ሚኒስቴሩ ተገልጿል።
በሌላ በኩል የልዑካን ቡድኑ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለንደን የሚገኘውን የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም ጎብኝቷል። በዶ/ር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድኑና በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሙዚየሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ትሪስታራም ኸንት (Tristram Hunt, PhD) ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ ወቅት በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።
እ.አ.አ በ2018 የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ለኢትዮጵያ መመለስ እንደማይችል፤ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ውሰት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚቻል መገለጹ ይታወቃል። የሙዚየሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ትሪስታራም ኸንት ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው ውሰት የሚለው ቃልም ለኢትዮጵያውያን ከባድ መሆኑን እንደተረዱት ተናግረዋል። በመሆኑም “የተቸገሩት ጉዳዩ የሕግ ጉዳይ በመሆኑና ምላሽ ለመስጠት ያለን አማራጭ ይህ ብቻ ስለሆነ ነው ” ብለዋል።
“ያለን አማራጭ ይህን ቀዳዳ በመጠቀም ሊስተካከሉ የሚችሉ አባባሎችን ተጠቅመን የሚመለሱበትን ሁኔታ መፍጠር፤ ይህን ካላደረግን ግን በሕጉ ላይ ጸንተን ወደፊት የሚሆነውን ነገር መመልከት ይኖርብናል” ሲሉም ዶ/ር ኸንት አክለዋል።
የባህል ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ቅርሶቹ የኢትዮጵያ በመሆናቸው በረጅም ጊዜ ውሰት ሳይሆን በቋሚነት ቅርሶቹ ለኢትዮጵያ መመለስ የሚችሉበት አማራጭ መፍትሄ ሙዚየሙ ሊያበጅ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በኤምባሲውና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል በአስቸኳይ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም፣ ካለው ሕግ ጋር በማይጋጭና የኢትዮጵያን ጥያቄ ሊመልስ በሚችልበት ሁኔታ በመንቀሳቀስ ጉዳዩ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት እልባት እንደሚያገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸፀዋል።
በለንደን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ባለው ሙሉ አቅምና ጊዜ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ቅርሶቹ ወደ አገራቸው እንዲገቡ እንደሚያደርጉ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻወል ገብሬ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ