-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ከ12 ቀናት በፊት የተከሰከሰው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው የቦይንግ 737 ማክስ 8 (Boeing 737 MAX 8) አውሮፕን አብራሪ ተገቢዉን የምሰለ በረራ (simulator) ስልጠና አልወሰደም በሚል መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ (The New York Times) ሰላም ገብረኪዳን በተባለች ትውልደ ኢትዮጵያዊት ጋዜጠኛ ፀሐፊነት ያወጣው ዘገባ ከእውነት የራቀ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።
“ምንም እንኳን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማክስ ምስለ በረራ ቢኖረውም የተከሰከሰውን አውሮፕላን ያበር የነበረው ፓይለት የዚህ ምስለ በረራ ስልጠና አልተሰጠውም” (Ethiopian Airlines had a Max 8 simulator, but pilot on doomed flight didn’t receive training on it) በሚል ርዕስ ኒው ዮርክ ታይምስ ያወጣው ዘገባው ከእውነት የራቀና ኃላፊነት የጎደለው መሆኑንም አየር መንገዱ አመለክቷል።
የአደጋው መንስዔ እየተጣራ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ሁሉም አካላት እንዲህ መሰል አሳሳች መረጃ ከማሰራጨት እንዲታቀቡም አየር በሚገባ መንገዱ በአጽንዖት አሳስቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ፥ የተከሰከሰው አውሮፕላን አብራሪ ሁሉንም አግባብነት ያላቸው የበረራ ስልጠናዎችን መውሰዱን አስታውቋል።
● SEMONEGNA on Social Media: Facebook | Twitter | Instagram | Pinterest
አውሮፕላን አብራሪው በቦይንግ የአውሮፕን አምራች ኩባንያ (The Boeing Company) እና በአሜሪካ አቪዬሽን አስተዳደር (US Federal Aviation Administration) የተቀመጡ ሁሉንም የበረራ ስልጠናዎችን መውሰዱንም ነው በመግለጫው የገለጸው።
ዋና አብራሪው ከወራት በፊት በኢንዶኔዥያው ላየን ኤየር (Lion Air) በደረሰው ተመሳሳይ የአውሮፕላን አደጋ ጋር በተያያዘ አስፈላጊዉን የአደጋ ጊዜ የበረራ መመሪያ በቂ ግንዛቤ እንደተሰጠዉም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎቹን ለማሰልጠን የሚያስችሉ የተሟሉ 7 ምስለ በረራዎች ወይም የበረራ ማሰልጠኛዎች እንዳሉት አስታውቋል። በአሁን ወቅት ብቁና የተሟሉ ኪው 400፣ ቢ737 ኤን ጂ፣ ቢ 737 ማክስ፣ ቢ 767 ፣ ቢ 787 ፣ ቢ 777 እና ኤ 350 የተሰኙ ሰባት ምስለ በረራዎች እንዳሉት ይፋ አድርጓል።
በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተሟላ የስልጠና መሣሪያ ጋር በቂ ስልጠና ከሚሰጡት ጥቂት ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑንም ነው ያስታወቀው – የኢትዮጵያ አየር መንገድ። ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ባልተለመደ ሁኔታ ከስልጠና ጋር ተያይዞ ለመሠረተ ልማት ግንባታ ከግማሽ ቢሊየን ዶላር በላይ ወጭ እንዳደረገ ተነግሯል።
የዓለም አቀፍ ሕግን በመከተል የአደጋው መንስዔ ተጣርቶ ይፋ እስከሚደረግ ድረስ በትዕግስት መጠበቅ ተገቢ መሆኑንም አየር መንገዱ አስታውቋል።
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የዓለም የውሃ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ መጋቢት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. “ማንንም ባለመተው” (“Leaving no one behind”) በሚል መሪ ቃል ተከብሯል። የዓለም የውሃ ቀን በዓለም አቀፍ ለ27ኛ ጊዜ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን፥ በሥነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር፣ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት ተዎካዮችና የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በበዓሉ መርሀግብር ላይ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሚተገበር የሁለተኛው ዋን ዋሽ ብሔራዊ መርሃ ግብር (One WASH National Program) ይፋ መደረጉን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሁለተኛው ዋን ዋሽ ብሔራዊ መርሃ የገጠር፣ የከተማና የተቋማት ንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ንጽሕና እና የጤና ንጽሕና አጠባበቅ (water, sanitation and hygiene) የሚያካትትና በሀገር አቀፍ (ብሔራዊ) ደረጃ የሚተገበር፣ የመጠጥ ውሃ፣ሳኒቴሽንና ሃይጅንን በገጠር፣ በከተማ፣ በት/ቤቶችና በጤና ጣቢያዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የሚረዳ እንደሆነ ተገልጿል።
● SEMONEGNA on Social Media: Facebook | Twitter | Instagram | Pinterest
ይህ መርሀግብር (ፕሮግራም) በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በጤና ሚኒስቴር፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ በልማት አጋር አካላትና በህብረተሰቡ ቅንጅት የሚተገበር ነው።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ዋን ዋሽ መርሀግብር (One WASH Program) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለየት ያለ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እየተተገበረ ያለ ፕሮግራም መሆኑን ጠቁመው፥ መንግሥት፣ የልማት አጋሮችና ሕብረተሰቡ አንድ ላይ ሀብት በማሰባሰብና ወደ አንድ ቋት በማስገባት፣ አንድ ላይ በማቀድ፣ አንድ ላይ አፈጻጸሙን በመከታተልና በመገምገም፣ አንድ ላይ ሪፖርትም በማድረግ የሚፈጸም ፕሮግራም መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
የመጀመሪያው የዋን ዋሽ ፕሮግራም ባለፉት አራት ዓመታት ከስድስት ወራት ሲተገበር መቆየቱን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ሁለተኛው የዋን ዋሽ ፕሮግራም ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ትግበራ እንደሚገባና የአምስት ዓመታት ፕሮግራም መሆኑን ተናግረዋል። በመጀመሪያው ፕሮግራም 3ነጥብ6 ሚሊየን ሰዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፥ 90 በመቶ ያህል ተግባራዊ መደረጉ ነው የተገለጸው። በሚቀጥሉት ወራትም እቅዱን በመቶ በመቶ ለማካናዎን እንደሚሰራ ተጠቁሟል።
ሁተለኛው ዋሽ በመጀመሪያው የዋን ዋሽ ፕሮግራም ይተገበር ከነበረው በገጠርና በከተማ፣ በጤና ተቋማትና በት/ቤቶች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽንን ለህብረተሰቡ ከማቅረብ በተጨማሪ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚተገበረውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የመጠጥ ውሃ ፕሮግራም (Climate Resilient WASH) የተካተተበት እንደሆነ ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ተናግረዋል።
በሁለተኛው የዋን ዋሽ ፕሮግራም ከመንግሥት፣ ከልማት አጋሮች፣ ከህብረተሰቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ፣ በአነስተኛ ወለድና በረጅም ጊዜ ክፍያ የሚከፈል ብድር ከአበዳሪ ተቋማት በጠቅላላው 6.5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሀብት ተሰባስቦ ለፕሮግራሙ ማስተግበሪያ ይውላል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው።
ዓመታዊው የትምህርት ጉባዔ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት ተጠናቆ ለመንግስት ውሳኔ በሚቀርብበት፣ 5ኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር የሦስት ዓመት አፈጻጸም የሚዳሰስበት፣ ለቀጣይ ሥራ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነበር።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የሚያዘጋጀው 28ኛው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በትግራይ ብሔራዊ ክልል መቐለ ከተማ ተካሔደ። በየዓመቱ ሚካሄደው እና ከመጋቢት 12 እስከ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በቆየው 28ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በመድረኩ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ከሁሉም ክልሎችና ከተለያዩ ከተማዎች አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች የተውጣጡ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለ ድርሻ አካላት እንዲሁም የትምህርት ልማት አጋር አካላት በሀገር አቀፉ የትምህርት ጉባዔ ተሳታፊ ሆነዋል።
● SEMONEGNA on Social Media: Facebook | Twitter | Instagram | Pinterest
ዓመታዊ ጉባዔው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት ተጠናቆ ለመንግስት ውሳኔ በሚቀርብበት፣ 5ኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር የሦስት ዓመት አፈጻጸም የሚዳሰስበት፣ ለቀጣይ ሥራ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው አቅጣጫ የሚቀመጥበት ሁነኛ ጉባዔ እንደነበር የትምህርት ሚኒስቴር ዘግቧል።
በተጨማሪም በአፈፃጸም ሂደት የተገኙ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ለአብነት የትምህርት ጥራትና የትምህርት ቤቶች ደረጃ ምደባ ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት እንደተደረገባቸው ታውቋል።
የዘንድሮውን ትምህርት ጉባዔን ለየት የሚያደርገው ሀገር አቀፍ የተማሪዎች ስፓርት ጨዋታ ጋር አቀናጅቶ እንዲካሄድ መደረጉ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።
The 28th National Education conference is being held in Mekelle. Major agendas are; the new Education Road Map strategic issues, ESDP V performance evaluation and 2018 National Learning Assessment study findings and future actions to be taken in the remaining two years. pic.twitter.com/h6XTlcTWTv
— Tilaye Gete Ambaye (PhD) (@DrGete) March 22, 2019
ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የዓለም የውሃ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ተከበረ።
- በኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን አገራዊ የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅድ ይፋ ሆነ
- ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች መሠረታዊ ችግሮች በጥናት ሊለዩ ይገባል ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ
- ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
- ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ፤ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ይጀመራል
ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
የተከበራችሁ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች !!
አገራችን ኢትዮጵያ 76 ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩባት ታላቅ አገር ነች። የሕዝባችን አብሮ የመኖር እሴት የሰው ልጆች መደበኛ ማኅበራዊ ግንኙነት ተሻግሮ በደም ዝምድና ተጋምዶ በባህል ተሳስሮ ላይለያይ ተቆራኝቷል። ይህ ህብረት የብሄር ማንነት እና የእምነት ልዩነት ሳይለያየው ለሺህ ዓመታት፣ ሺህ ችግሮችን ተጋፍጦ ይሄው ዛሬም ድረስ በጋራ ዘልቋል።
የዚህ አኩሪ ታሪክ ጉዞ አልጋ ባልጋ ያልነበረ ከመሆኑ ባሻገር፣ ሕዝባችን የሚያነሳቸው የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች በተለያዩ ጊዜያት የነበሩትን መንግሥታት በመታገል ለመብቱ የተከራከረበት ወቅትም በርካታ እንደነበር የሚታወቅ ነው። በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የተነሱት የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰብዓዊ መብትና ሌሎች መሠረታዊ ጥያቄዎች ምክንያት በአገሪቱ ለውጥ አንዲመጣ አድርጓል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያዊንን እና ሌላውን ዓለም ያስደመሙ በርካታ የለውጥ እርምጃዎች ተወስደዋል። ከተማችንም ዘመን ተሻጋሪና ተጨባጭ ውጤቶች እየተከናወኑና ቀደም ሲል ሕዝባችን ያነሳቸው የነበሩ የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የእኩልነት፣ የልማትና መሰል አጀንዳዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል።
በመሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ የሚመራው የከተማችን አስተዳደር ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ መርሆዎችን ተከትሎ የአዲስ አበባ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማካሄድ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸው የከተማው ነዋሪ የሚመሰክረው ሃቅ ነው።
በሌላ በኩል የከተማችን ነዋሪዎች ሕገ-መንግሥቱ በሰጣቸው ሥልጣን መሠረት በከተማው ሕዝብ ተሳትፎ ወኪሎችን በመምረጥ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛሉ። ይህ ሲባል ሕዝቡ ከአስፈፃሚው አካል ጐን ሆኖ ባያግዝና ባይሳተፍ ኖሮ አሁን የተገኘውን ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም ነበር።
ስለሆነም የከተማችን ነዋሪዎች በሁሉም የሥራ መስኮች ያልተቋረጠ ድጋፍ ያደረገና እያደረገ ያለ ሲሆን በተለይም የአዲስ አበባ ሰላም ተጠብቆ እንዲቀጥል በማድረግ ለሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ትልቅ ትልቅ ተምሳሌት ሆኖ ይገኛል። በመሆኑም ሕዝቡ ላበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋናና ዕውቅና ሊቸረው ይገባል።
ይሁንና አሁንም በከተማችን የሚስተዋሉና በልዩ ትኩረት ሊፈቱ የሚገባቸው ችግሮች እንዳሉ በመገንዘብ ችግሮችን ለመፍታት የከተማው አስተዳደር ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሆነ እና ምከር ቤቶችም የክትትል ድጋፍና ቁጥጥር ሥራችን አጠናክረን የተጠያቂነት አሠራር በጥብቅ ዲስፒሊን እየተመራ ተግባራዊ አየተደረገ ይገኛል።
ከምክርቤቱ የምርጫ ዘመንጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መካሄድ የነበረበትን የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ እንዲራዘም በወሰነው መሠረት እና እንዲሁም ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የከተማውን አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995ን ለማሻሻል ባወጣው አዋጅ ቁጥር 1094/2010 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ጊዜ እንዲራዘም የወሰነ እና “ምርጫ ተደርጐ በምርጫው መሠረት አዲስ አስተዳደር እስኪደራጅ ድረስ በሥራ ላይ ያለው ምክር ቤቱ እና አጠቃላይ የከተማው የአስተዳደሩ በነበረበት ሁኔታ ይቀጥላል” በሚል በደነገገውና በወሰነው ውሳኔ መሠረት ህጋዋ ዕውቅና አግኝቶ የቀጠለ አስተዳደር እንደሆነ ሊታወቅ የሚገባው ሲሆን በዚሁ አዋጅ ቁጥር 1094/2010 አንቀጽ 3 ስር “ምክትል ከንቲባው ከምክር ቤት አባላት ውስጥ ወይም ከምክር ቤት አባላት ውጭ የሚሾም ሆኖ የሥራ ዘመኑ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ይሆናል”ተብሎ በግልጽ በተደነገገው መሠረት የከተማው ምክር ቤት ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመት በወቅቱ በተገኙት ምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
ስለሆነም “የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመት የነዋሪው ውክልና የለውም” ህጋዊ አይደለም በሚል የሚነሱ የተሳሳቱ አስተሰሰቦች ምንም ዓይነት ህጋዊ መሠረት የሌላቸው እና በስሜት ብቻ የሚንጸባረቁ እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1094/2010 የሚፃረር እና ህገወጥ እንደሆነ ሁሉም የከተማችን ነዋሪ ሊረዳው ይገባል።
ይሁንና አስተዳደሩ በከተማችን ነዋሪ ተሳትፎ ጭምር በአገር ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ሌት ተቀን ደፋ ቀና በሚልበትና በዕቅድ ተይዘው እየተተገበሩ ያሉ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማሳካት እየተረባረበ እና ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ባለበት በዚህ ወቅት አንዳንድ ወገኖች በሕግ የተቋቋመውን የአስተዳደሩን ተግባራት በማደናቀፍ የሕዝብ ያልሆኑ ጥያቄዎችን የሕዝብ በማስመሰል ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።
ስለሆነም በአገራችን ብሎም በከተማችን የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ በቅርቡ በከተማችን ሰላምን ለማደፍረስ እየታዩ ያሉ ኢ-ሕገመንግሥታዊ እንቅስቃሴዎችን በትኩረት በመከታተልና ሕገወጥ እንቅስቃሴ አድራጊዎችን በሰላማዊ መንገድ በመታገል የከተማችን ነዋሪዎች እንደወትሮው ሁሉ የከተማችንን ሰላም በማስከበር የተጀመረውን ልማት በማስቀጠል የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ከከተማው አስተዳደር ጐን እንደሚቆም ያለንን ጽኑ እምነት እየገለጽን፡-
1ኛ. ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚያራግቡ፣ በህጋዊ መንገድ በተመረጠው አስተዳደር ላይ አመጽ የሚያነሳሱ ማናቸውም ድርጊቶች ለማንም የማይጠቅም ህገወጥ ድርጊት እና ፀረ-ህገመንግሥትም ስለሆነ ባስቸኳይ እንዲቆም፤
2ኛ. አሁን ያለው የከተማው አስተዳደር ህጋዊ መሠረት ያለው እና በም/ቤቱ ፀድቆ የተሾሙ በመሆኑ መላው የከተማው ነዋሪዎች ከከተማው አስተዳደር ጐን በመቆም በከተማችን ነዋሪዎች ድምፅ ውክልና የተሰጠውን ም/ቤት ሥልጣን ወደጐን በመተው እየተነሱ ያሉ የማደናገሪያ አስተሳሰቦችን አምርሮ እንዲታገል፤
3ኛ. በከተማችን ውስጥ የላቀ ልማት ለማስመዝገብ፣ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለማድረግ የሁሉም ወገኖች የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ በመሆኑ ለውጡን ባስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል የከተማችን ነዋሪዎች ሁሉን አቀፍ ትብብር እንዲያደርጉ እና ከከተማው አስተዳደር ጐን እንዲቆሙ ጥሪ እያቀረብን፣ የብሄርብሄረሰቦችና ሕዝቦች የቃልኪዳን ሠነድ እና የህጐች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገመንግሥት የማክበር፣ የማስከበርና የመጠበቅ ኃላፊነታችሁን በመወጣት ሕዝቡን በማደናገር የከተማችንን ሰላም ለማደፍረስ ሌት ተቀን የሚጥሩ ኃይሎችን በመታገል ከከተማ አስተዳደሩና ከምክርቤቱ ጐን በመሆን የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ፤
4ኛ. የአዲስ አበባ ጉዳይን በተመለከተ ከተማችን የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በፍቅር፣ በመተሳሰብና በመቻቻል በአብሮነት ለሰላም ልማትና ዴሞክራሲ ዘብ የቆመ ሕዝብ የሚኖርባት የሁላችንም ከተማ የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መኖሪያ መሆንዋ ታውቆ ከከተማው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች የሕጐች ሁሉ የበላይ በሆነው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ-መንግሥት ምላሽ የሚያገኝ ስለሆነ ፍጸም የግጭት መንስኤ መሆን አይገባውም፤
5ኛ. የከተማው አስተዳደር እንደሌላው ጊዜ ሁሉ የከተማውን ሰላምና ፀጥታ ከማስከበር ባሻገር እያከናወነ ያላቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፕሮግራሞችን አጠናክሮ እንዲቀጥል እያሳሰብን፣ እንደወትሮው ሁሉ የከተማችን ነዋሪዎችም ህግና ሥርዓት እንዲከበርከ አስተዳደሩ፣ ከሕግ እና የፀጥታ አስከባሪ አካላት ጐን በመሆን ለሰላም ዘብ በመቆም የተለመደው ትብብሩን እንዲቀጥል እንጠይቃለን።
እናመሰግናለን!
ወ/ሮ አበበች ነጋሽ
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ
አዲስ አበባ
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዎ አገር እንደ እንደ ካልጠነከረች በመርፌ ስለት በቻ ሳይሆን በዶለዶመ ብረትም ትበሳለች። የመርፌ አቅሙ ጨርቅ ወይም እንደ ጨርቅ በሳሳ ነገር ላይ ነው። ኢትዮጵያ አገራችን ደግሞ ከመቼውም በከፋ ሁኔታ ሳስታለች።
ያሬድ ኃይለማርያም
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትላንትናው እለት የማኅበራዊ ሚዲያዎችን አጠቃቀም በተመለከተ ምክር አዘል ተግሳጽ የያዘ ደብዳቤ ከጽሕፈት ቤታቸው ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል። እርግጥ ነው ጠቅላዩ እንዳሉት ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚተላለፉ ጽንፍ የያዙ እሰጣገባዎች፣ በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጸያፍ ንግግሮች፣ ሕዝብን ለግጭት የሚቀሰቅሱ ጥሪዎች፣ የሃሰት መረጃዎች እና ውንጀላዎች ከመቼው ጊዜ በስፋት እየተስተዋሉ መጥቷል። ይህ ዓይነቱ ችግር በጊዜ ካልታረመ የእርስ በርስ ንቁሪያው ከማኅበራዊ ሚዲያ ወደ መሬት ወርዶ በግልም ሆነ በአገር ደረጃ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ደብዳቤያቸው በግልጽ አስቀምጦታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ጽንፍ ይዘው እና የተሳሳቱ መረጃዎችን እያሰራጩ ሕዝብን የሚያደናግሩ እና ለግጭት የሚያነሳሱ ሰዎችን በመርፌ መስለው አስቀምጠዋል። እንዲህም ይላሉ “መርፌ ዓይናማ ናት ባለ ስለት፤ ችግሩ የፊቷን እንጂ የሚከተላትን አታይም። እናም ጨርቅ ላይ እሷ አለፍኩ ብላ የክር እና የገመድ መአት ታስገባበታለች። የእኛ አገር አንዳንድ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ጦማሪዎች ልክ እንደ መርፌ ናቸው። እነሱ አገር በሚወጋ መርፌያቸው እየወጉን ሲጓዙ እንደ ክር አያሌዎች መድረሻቸውን ሳይጠይቁ ይከተሏቸዋል…” አገላለጻቸው ግሩም ነው። ወድጄዋለሁም፤ ነገር ግን እውነቶች ይጎድሉታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁኔታውን አንድ ገጽታ ብቻ ነው እንደ ዋነኛ ምክንያት ወስደው እና አትኩሮት ሰጥተው ስጋታቸውንና ማሳሰቢያቸውን የሰጡት። እኔ ያላዩት ወይም ችላ ብለው ያለፉት ገጽታ አለ እላለሁ። መርፌ ጨርቅ እንጂ አለት አትሰፋም ወይም አይበሳም።
አዎ አገር እንደ እንደ ካልጠነከረች በመርፌ ስለት በቻ ሳይሆን በዶለዶመ ብረትም ትበሳለች። የመርፌ አቅሙ ጨርቅ ወይም እንደ ጨርቅ በሳሳ ነገር ላይ ነው። አገራችን ደግሞ ከመቼውም በከፋ ሁኔታ ሳስታለች።
አገር እንደ አለት የሚጸናው በጥሩ ሕግ፣ የሕግ የበላይነትን በሚያረጋግጡ ጠንካራ ተቋማት፣ ሕግን በሚያከብሩ እና በሚያስከብሩ የመንግስት ተቋማት እና ሕግ አክባሪ በሆነ ማኅበረሰብ ነው።
በሁሉም አለም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ጥሩም፣ መጥፎም ገጽታ አላቸው። የሕግ የበላይነት በሳሳበት እና መንግስት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ባልቻለበት ስፍራ አሉታዊ ጎኑ ይበረታና አገር እሰከ ማተራመስ አልፎም እስከ ማፍረስ ይደርሳል። በሕግ የጸና ጠንካራ አገር እና ሕግ አክባሪ ማብሀረሰብ ባለበት አገር ደግሞ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ጩኸት ሰሚ አልባ ነው። እዛው አየር ላይ ተንሳፎ ይቀራል።
ክቡርነትዎ፥ የእኛ አገር የማኅበራዊ ድረ-ገጾች መረን የለቀቀ የእርስ በርስ ንቁሪያ እኮ መሬት ላይ ያለው እውነታ ነጸብራቅ ነው። እርሶ በተቀመጡባት መዲና አዲስ አበባ ሳይቀር ሰዎች ሜጫ፣ ድንጋይ፣ ሚስማር የተመታበት ዱላ ይዘው አደባባይ ለፍልሚያ በየቀኑ በሚወጡበት እና ዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት የማይችሉበት አደጋ መሬት ላይ እየታየ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው ጦርነት እንብዛም ትኩረት ሊስብ አይገባውም።
አገሪቱን እንደ ጨርቅ ያሳሳት እንደ እኔ እምነት የመርፌው ጥንካሬ ሳይሆን መንግስት የሕግ የበላይነትን በመላ አገሪቱ ማስፈን አለመቻል ነው። እባክዎ ቅድሚያ አየር ላይ ካለው የቃላት ጦርነት በፊት መሬት ላይ ሕግ ያስከብሩ። የእርሶ ጽሕፈት ቤትም አይደል እንዴ በአደባባይ እና በማኅበራዊ ሚዲያ በሕዝብ ላይ የእልቂት እና የግጭት አዋጅ አውጆ ለቄሮ የክተት ጥሪ ያደረገውን ጃዋር መሃመድን በሕግ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ በቅርቡ በኢሲኤ (ECA) አዳራሽ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ በአገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምን አስመልክቶ ትምህርት እንዲሰጥ ዋና ተናጋሪ አድርጎ ያቀረበው።
ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ያሉት ችግሮች እና ስጋትዎን እኔም ሙሉ በሙሉ እጋራዎታለው። ጽንፈኝነት ነግሷል። የሃሰት መረጃዎች ሕዝብን እያደናገሩ ነው። እኔም ሆንኩ ሌሎች ሚዲያውን የሚጠቀሙ አካላት እርሶንም ጨምሮ ለችግሩ አስተዋጽኦ ይኖረን ይሆናል። ይህ ችግር አገር ሳያሳጣን በፊት በአግባቡ እና በአፋጣኝ ሊፈታ ይገባል። ኢትዮጵያን እንደ አለት የጸናች አገር ማደረግ ከቻልን ግን የማኅበራዊ ሚዲያው ጩኸትም ሆነ ትርምስ ንፋስ ይወስደዋል ወይም እየነጠረ ይመለሳል እንጂ አገር አያፈርስም።
አዎ እርሶ እንዳሉት ኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ያላት አገር ስለሆነች በማኅበራዊ ሚዲያ ወሬ አትፈርስም። መሬት ላይ ያለው ሕግ አልባነት፣ የመንጋ እንቅስቃሴ እና በሕግ ያልተገራና ልቅ የሆነ የግለሰቦች እና የፓርቲዎች እንቅስቃሴ ግን የሞት አፋፍ ሊያደርሳት ይችላል።
የሕግ የበላይነት ትኩረት ይሰጠው!
ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በአቶ ነአምን ዘለቀ ― አቶ ነአምን ዘለቀ ራሳቸውን ከአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ አገለሉ
———ለአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ አባላት፣ የሠራዊት አባላት፣ ደጋፊዎችና፣ በልዩ ልዩ መደረኮች ለምታውቁኝ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፦
በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የአርበኞች ግንቦት 7 የዴሞክራሲና የአንድነት ንቅናቄ (አግ7) አመራር አባላት እ.ኤ.አ. በሀምሌ (July) ወር 2018 በአሜሪካን ሀገር ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ ከተደረሱት የስምምነት ነጥቦች መካከል አንዱ የአግ7 ንቅናቄ ሠራዊት ከኤርትራ በርሃና ከሀገር ውስጥም የነበሩት የአግ7 ታጣቂዎች ወደ ሀገር ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለስና ማቋቋምን የሚመለከት ነበር። በዚህም መሠረት በኤርትራ የነበሩ የንቅናቄው ሠራዊት አባላት እንዲሁም በየበረሃው የነበሩ የንቅናቄው ታጣቂዎች ወደ ልዩ ልዩ ካምፖች በየጊዜው እንዲገቡ መደረጉ ይታወቃል። በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የንቅናቄው አባላትም ከልዩ ልዩ እስር ቤቶች ቀደም ሲል በተከታታይም እንደተለቀቁ ይታወቃል። በኃላፊነት ስመራ በቆየሁት በውጪው ዘርፍ ስር የማኅበራዊ ፈንድ ኮሚቴ እንዲቋቋም በማድረግ በውጭው ዓለም በሚገኙ በንቅናቄው አባላት፣ በደጋፊዎች፣ እንዲሁም አገር ወዳዶች ትብብር መጠነ ሰፊ ገንዘብ በማሰባሰብ በየእስር ቤቱ የነበሩት ተጋዮች ለሦስት ተከታታይ ወራት እንዲረዱ እንዲሁም ከኤርትራ በረሃ ለመጡትና በካምፕና ከካምፕ ውጭ ለሚገኙትም በልዩ ልዩ መንገዶች እርዳታዎች እንዲያገኙ ለማድረግ ተችሏል።
ከኤርትራ በረሃ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የተደረጉትን የአርበኞች ግንቦት 7 የቀድሞ ታጣቂዎች እንዲሁም የሌሎች የፓለቲካ ድርጅቶች ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋሚያ ፕሮጄክት ጽ/ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ስር ከ7 ወራት በፊት የተመሠረተ ሲሆን፥ የውጭ መንግስታትም በተለይም የጀርመን መንግስት ለዚሁ የሚውል ገንዘብ ለመስጠት ከበርካታ ወራት በፊት ተስማምተው ነበር። ሆኖም ከተቋቋመው ጽ/ቤት አቅም ማነስ እንዲሁም ጉዳዩ ተገቢውን ውሳኔዎች ሳያገኝ እየተጓተተ በመቆየቱ ሳቢያ የአርበኞች ግንቦት 7 ሠራዊት አባላት (በተለይም ከካምፕ ውጪ እንዲቆዩ ተደርገው መልሶ የማቋቋሚያ ድጋፍ እንዲጠብቁ የተነገራቸው ጭምር) ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸው ለህሊና እረፍት በሚነሳ ሁኔታ ውስጥ እራሴን አግኝቼ ነበር።
የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እንዲሁም ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ በየጊዜው ከጠቅላይ ሚንስትሩና ከሌሎች የመንግስት ኃላፊዎች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነትና ክትትል እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በችግር ላይ የነበሩ የሠራዊት አባላት ሁኔታ አየተደራረበ የጭንቀት ድምጾች እየተበራከቱ በመምጣታቸው፣ ይህ ጉዳይ የንቅናቄውን ሊቀመንበርና ዋና ጸሐፊውን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን አባላትና ሠራዊቱ የመረጡን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን በሙሉ በተናጠልም ሆነ በጋራ የሚያስጠይቅ፣ ለሠራዊቱም ሆነ ለአባላት ኃላፊነት አለብን በሚል መንፈስ ይህ ለውጡን ለሚመራው መንግስትም የጸጥታና የፓለቲካ ችግር የሚፈጥር ሁኔታ፣ ከሞራልም ሆነ ከፓለቲካ እኳያ የንቅናቄውንም ውስጣዊ ጤንነት እየተፈታተነ የነበረ ትልቅ ችግር እየሆነ በመምጣቱ፣ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ እርዳታ ለመስጠት ቃል ከገቡና ለመርዳት ፈቃደኛ ከሁኑ መንግስታት በተለይም ከጀርመን አምባሳደር፣ ከስዊድን መንግስት ኃላፊዎችና የፓርላማ አባላት፣ ከልዩ ልዩ የመንግስት ኃላፊዎችና ከመንግስት መዋቅር ውጭ የሚገኙ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚቀርቡ ግለሰቦች ጋር በመገናኘት ለማስረዳትና መፍትሄ እንዲያገኝ የበኩሌን አስተዋጽዖ ለማድረግ ጥረቶች ሳደርግ ቆይቻለሁ።
ብዙ ዝርዝሮች ያሉትና ወራት ያስቆጠረ ሂደት ቢሆንም፣ በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ችግር መፍትሄ በማፈላለግ ሊያዳምጡን በራቸውን ለከፈቱ የልዩ ልዩ የመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች፣ በተለይም የብሄራዊ አደጋና መከላከል ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ፣ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ፣ እንዲሁም ከመንግስት መዋቅር ውጭ ያሉና ከለውጡ በኋላ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ሊያገኙን እንደሚፈልጉ በላለቤቴ በኩል መልክት የላኩብኝ የጠቅላይ ሚኒስሩ የአርቅ ኮሚቴ አባል አቶ ብርሃን ተድላ፣ በበርካታ የሕዝብና የሀገር ጉዳዮች ያላሰለሰ አስተዋጽኦ የሚያደርጉትና የረጅም ጊዜ ወዳጄ ለሆኑት ዶ/ር አምባሳደር ካሳ ከበደ፣ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው ለመርዳት ለተንቀሳቀሱት፣ በእርዳታና በመልሶ ማቋቋም ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ለሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ፣ እንዲሁም ለመለሶ ማቋቋም የተቋቋመው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ኣፍሪድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ይልማ፣ ሌሎችም ለችግሩ መፍሄ ለማግኘት ያገኘኋቸውን ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሁሉ እስከአሁኑ ቀን ድረስ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው በሚገኙት የሠራዊት አባላት ስም ምስጋና ሳላቀርብ አላልፍም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ትላንት ከለውጡ በፊት እንኳን እነሱን ደጅ ልንጠና ቀርቶ አጠገባቸው ለመድረስ እንኳን የምንጸየፋቸው፣ የተቀመጡበት የኃላፊነትና የአማካሪነት ቦታ የሀገርና የህዝብ ችግሮች ለመፍታት መሆኑ እምብዛም የሚያስጨንቃቸው የማይመስሉ፣ ራሳቸውን የኮፈሱ አድርባዮች፣ ከንቱና ግብዝ የመንግስት ባለሟሎች በዚህ ሂደት ለመታዘብ ችያለሁ።
የሆነ ሆነ ይህ ከፍተኛ ችግር መፍትሄ እንዲያገኝና በውጭ የሚገኙትም ሆኑ በካምፕ ውስጥ የሚገኙት የንቅናቄያችን ሠራዊት አባላት ቢያንስ አቅም ባለው፣ ሠራዊቱ የሚገኝበትን ችግር ለማቃለል ብቃትና ተቋማዊ ቁመና ለዓመታት ባካበተ የመንግስት ኮሚሽን በኩል እንዲሆን የሚያስችል እርምጃ እንዲወሰድ በቅርብ ቀን መወሰኑን አዲስ አበባ በነበሩኩባቸው አራት ሳምንታት ከሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት አረጋግጫለሁ። ይህም እርምጃ ለወራት የቆየን ከባድ የህሊና ሸክም ያቃለለ ቢሆንም፣ አሁንም ከካምፕ ውጭ የሚገኙ የሠራዊቱ አባላት የሚገኙበትን ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ ችግሮች አስመልክቶ በየዕለቱ በርካታ መረጃዎች እየደረሰን በመሆኑ ከካምፕ ውጭም ሆነ ከካምፕ ውስጥ የሠራዊቱ አባላት ቃል የተገባላቸው እርዳታ እንዲደርሳቸው፣ የመልሶ ማቋቋሙ ሂደት በቶሎ እንዲጀመር፣ የንቅናቄው የሥራ አፈጻሚ ኮሜቴ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች የሚያስፈልገው ያልተቋረጠ ትኩረትና ክትትል እንዲያደርጉ በድጋሚ ለማሳሰብ እወዳለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችና ህልውናዋን የሚፈታተኑ ስጋቶች የተጋረጡባት ከመሆኗም በሻገር ከምንጊዜውም በባሰ መልኩ መስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኝ መሆኑን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሁሉ የሚስማሙ ይመሰለኛል። ይህን አደጋ ለመቋቋም ደግሞ በርካታና ዘርፈ ብዙ ሕዝብ አቀፍ እንቅስቃሴዎች ያስፈልጋሉ። ስለዚህም ውስብስብ በሆኑና ስር በሰደዱ መጠነ ሰፊ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊ ችግሮች አውድና ከባቢ ውስጥ ተዘፍቀው ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፣ ፍትህና፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እየተደረገ በሚገኘው የለውጥ ጅማሮ እንዳይቀለበስ የለውጡን አራማጆች፣ ለውጡን ለማስቀጠል በተጨባጭ እርምጃዎች እስከተንቀሳቀሱ ድረስ ማገዝ አማራጭ የሌለው ነው ብዬ አምናለሁ።
ሀገራችንን ቅርጫ ለማድረግ ሲሉ የ100 ሚሊዮን ህዝብ ዕጣ ፈንታ ላይ ቁማር የሚጫወቱ፣ የሕዝብን የተሻለ ህይወት፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የታገሉለትን፣ የሚመኙትን ፍትህ፣ ነጻነትና የነገን ተስፋ እየረጋገጡ የሚገኙ እጅግ ራስ ወዳድ፣ ስግብግብ ህሊና ቢሶች፣ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ማኅበረሶቦች አብሮነት አጥፍተው ለራሳቸው ጠባብ ብሄረተኝነት እጀንዳ ጥቅምና ስልጣን ለማምጣትም ሆነ ለማስቀጠል በየአካባቢው ትርምስ የሚፈጥሩ፣ ክቡር የሆነውን ሰብዓዊነት ረግጠው ወደ አራዊትነት በተጠጋ የለየለት ጽንፈኝነትና አክራሪነት የታወሩ ጥቂቶች፣ ከራሳቸው ግላዊ ፍላጎትና ጥቅም ውጭ ለሕዝብና የሀገር ደህንነት፣ ለሰላም፣ ለፍትህና፡ ለሕግ የበላይነት ምንም ቁብ የማይሰጡ የጥፋት ኃይሎች በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደአሸን በፈሉበት ሁኔታ ከኢትዮጵያዊነት ውጪ፣ ከፍትህ፡ ከእኩልነትና፣ ከሕዝብ አብሮነት የተለየ ሌላ አማራጭ እንደሌለ፣ ሌላ ሀገር፣ ሌላ ምድርም አለመኖሩን በሚገባ የተረዱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሁሉ በየአካባቢያቸው እያፈጠጠ፣ እያገጠጠ ከሚገኘውን የህልውና አደጋ ከእነዚህ አክራሪና ጽንፈኛ የጥፋት ኃይሎች ሊያመጡት ከሚችሉት የሀገራችንን የመኖር አለመኖር ህልውና የሚፈታተን የሲኦል ጎዳና ራሳቸውን፣ ቤተስባቸውንም ለመከላከል፣ ተከላካይ በሆነ መልኩ እርስ በእርስ መደራጀት፣ እንዲሁም ራስን በራስ ማደራጀትና፣ ብሎም ነቅቶ መጠበቅ ሌላው አስፈላጊና ወቅታዊ ተግባር ነው ብዬ አምናለሁ።
ለአገራችን ሕልውና፣ ለሕዝባችን ሰላም፣ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሰፈነባት ኢትዮጵያ እንድትኖር የሚያስችል የፓለቲካ ስርዓት እንዲረጋገጥ የሚጨነቁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እልህ አስጨራሽ ሁኔታ ውስጥ ብንገኝም ከዚህም ከዚያም የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ እየጣሉ የሚገኙ አክራሪና ጽንፈኛ ብሄረተኞችና የለውጥ ቅልበሳ ቡድኖች ወጥመድ ሰላባ ላለመሆን በስልት፣ በሰከነ ጥበብና በሃገራዊ ኃላፊነት መንቀሳቀስ የግድ ነው ብዬ አምናለሁ። ለኢትዮጵያዊነት፣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዜጎች እኩልነትና ሁለንተናዊ መብቶች የቆሙ የፓለቲካ ኃይሎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ እንዲሁም የፕሬስ ድርጅቶችን ማጠናከር እንዲሁ ሌላቅ የወቅቱ ዐቢይ ተግባራት ይመስሉኛል።
በሀገራችን የተጀመረው ለውጥ ከመጣ ከጥቂት ወራት በኋላ ንቅናቄው የፓለቲካ ፓርቲ እንደሚሆን ስምምነት በተደረሰ ጊዜ የፓለቲካ ፓርቲ አመራርም ሆነ አባል ሆኜ ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌለኝ በአመራሩ ላይ ለሚገኙ ሁሉ በተለያዩ ጊዜያት ገልጬ ነበር። እስካሁንም ድረስ የቆየሁት ከመሪዎች አንዱ ሆኜ እንዳገለግል ለመረጡኝ አባላትና የሠራዊት አባላት ባለኝ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ቢያንስ ከኤርትራ በርሃና በኢትዮጵያም ውስጥ ሆነው በጨለማው ዘመን ለኢትዮጵያ አንድነትና ለሕዝብችን ነጻነት ህይወታቸውን ለመገበር ለቆረጡ እነዚህ ዛሬ በካምፕ ውስጥና ከካምፕ ውጭ የሚገኙ የሠራዊት አባላትና ታጋዮች ህይወት ተገቢውን መስመር እስኪይዝ ነበር።
ቀደም ሲል መልቀቂያ አስገብቸ የነበረ ቢሆንም እንኳን የንቅናቄው ዋና ጸሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ የተለያዩ የንቅናቄው አመራሮች በኃላፊነቴ እንድቆይ በነበራቸው ፍላጎት፣ እኔም ከነሱ ጋር ባደረኳቸው ውይይቶች በቦታው መቆየቴ ሠራዊቱን ይጠቅማል ብዬ ስላመንኩ እስካሁን ድረስ በተሰጠኝ የኃላፊነት ቦታ ላይ የምችለውን እያገዝኩ ቆይቻለሁ። ሆኖም ለቆሙለት ዓላማ፣ ለንቅናቄያቸውና ለሀገራቸው ክብር መተኪያ የሌላት ህይወታቸውን ለመክፈል የቆረጡ የትግል ጓዶቸ ላለፉት 7 ወራት በከፍተኛ ችግሮች ውስጥ ወድቀው ማየት ለኔ እንቅልፍ የሚነሳ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም።
ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለዴሞክራሲና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁለንተናዊ መብቶች መረጋገጥ የበኩሌን አስተዋጽኦ ሳደርግ ቆይቻለሁ። ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በላይ በውጭው ዓለም በተደረገው ትግል ልዩ ልዩ የትግል መድረኮችን በመሥራችነት፣ በአባልነት፣ በአስተባባሪነት፣ እንዲሁም በአመራር ኃላፊነቶች የዜግነት ግዴታዬን ከሚጠበቅብኝ በላይ አስተዋጽኦ በማድረግ ለ26 ዓመታት ያልተቋረጠ የትግል አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ። የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥንን(ኢሳት) በማቋቋም፣ በመገንባት ሂደትና እስከ 2015 ድረስም በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ፣ እሰከአሁኑ ድረስም በቦርድ ሥራ አስፈጽሚ አባልነት የበኩሌን አስተዋጽኦ ተወጥቻለሁ።
ባለፉት 8 ዓመታት የአርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ በመሰማራት፣ እ.ኤ.አ ከመስከረም (September) ወር 2017 ከተደረገው የንቅናቄው ጉባኤ ላይ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆኜ ከተመረጥኩኝ በኋላም የንቅናቄው የውጪው ዘርፍ ኃላፊ በመሆን እስካሁን ድረስ በቅንነትና በምችለው እቅም ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ። በአሁኑ ወቅት ከአርበኞች ግንቦት 7 የሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባልነት፣ እንዲሁም ንቅናቄው የውጭ ዘርፍ ኃላፊነት በገዛ ራሴ ፈቃድ መልቀቄን ለአርበኞች ግንቦት 7 አባላት፣ ደጋፊዎች፣ በልዩ ልዩ የትግል መድረኮች ለምታውቁኝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለማሳወቅ እወዳለሁ።
የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በቅርብ ጊዜ ጉባኤ በማድረግ ይከስማል። አዲስ ሀገራዊና በኢትዮጵያዊነት፣ በዜግነትና በማኅበራዊ ፍትህ ላይ የቆመ የፓለቲካ ፓርቲ የምሥረታ ሂደት ወደ ማገባደጃው በመድረሱ በአዲሱ ፓርቱ ለሚመረጡ አመራሮች እንዲሁም አባላትና ደጋፊዎች ሁሉ ያለኝን ጽኑና መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ። ለወደፊቱ ለኢትዮጵያ ሀገራችን እንዲሁም ለዓዝባችን ፋይዳና ጥቅም በሚያስገኙ ልዩ ልዩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ድርሻዬን እንደምወጣ ለምታከብሩኝ፡ ለምትወዱኝና ለማከብራችሁና ለምወዳችሁ ወገኖቼ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለማረጋገጥ እወዳለሁ። እዚህ ላይ የንቅናቄው ወዳጆችም ሆናችሁ ሌሎች እንድታውቁት ላሰምርበትም የምፈልገው በንቅናቄው አጠቃላይ የፓለቲካ ራዕይና ተልእኮ፣ በሚመሠረተው የፓለቲካ ፓርቲ ዓላማና ተልዕኮ፣ እንዲሁም ከማንም የንቅናቄው አመራር አባላት ጋር በግል ሆነ በፓለቲካ ምንም ዓይነት ቅራኔ የሌለኝ መሆኑን ለማረጋገጥ እወዳለሁ። ዘለአለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለዓባችን ነጻነትና፣ ለፍትህ ሲሉ አይተኬ የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ነአምን ዘለቀ ቦጋለ
ቨርጂኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ
ማርች 18 ቀን፣ 2019
ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው አቤ ደንጎሮ ሆስፒታል የተመላላሽ፣ የአስተኝቶ ማከም፣ የወሊድ አገልግሎት፣ የቀዶ ሕክምና፣ የድንገተኛ ሕክምና፣ የራጅ፣ የላቦራቶሪና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አሉት።
ነቀምት (ኢዜአ) – ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤ ደንጎሮ ወረዳ ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው አቤ ደንጎሮ ሆስፒታል መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። ሆስፒታሉ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ እንዳስደሰታቸው አንዳንድ የወረዳው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ደረጃ ዱጉማ በምርቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው አቤ ደንጎሮ ሆስፒታል የተመላላሽ፣ የአስተኝቶ ማከም፣ የወሊድ አገልግሎት፣ የቀዶ ሕክምና፣ የድንገተኛ ሕክምና፣ የራጅ፣ የላቦራቶሪና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አሉት።
ሆስፒታሉ በአቤ ደንጎሮ ወረዳና በአካባቢው በሚገኙ ተጎራባች ወረዳዎች ለሚገኙ ከ400 ሺህ ለሚበልጡ ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ የሕክምና መሳሪያዎችና የሰው ኃይል የተሟላለት መሆኑንም አመልክተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትና የማኅበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው ሆስፒታሉ የህዝቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የመለሰና የሕዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል። ህብረተሰቡ ሆስፒታሉ የራሱ ሀብትና ንብረት መሆኑን ተረድቶ እንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠብቀው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች በበኩላቸው ሆስፒታሉ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል የቱሉ ዋዩ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ እቴነሽ ደገፉ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው ለበርካታ ዓመታት የጤና ተቋማት ባለመኖሩ በተለይ በእናቶችና ህጻናት ህይወት ላይ አደጋ ይደርስ እንደነበር አስታውሰዋል። የወረዳው ህዝብ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ሻምቡና ነቀምቴ ሆስፒታሎች በመጓዝ ለወጪና እንግሊት ሲጋለጥ መቆየቱንም ጠቁመዋል። በአካባቢያችን ደረጃውን የተጠበቀ ሆስፒታል መገንባቱ ወጪና እንግልትን ከማስቀረቱም በላይ የእናቶችና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ደቻሣ ገለታ ወረዳው ከነቀምቴና ሻምቡ ሆስፒታሎች በብዙ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ስለሚገኝ በተለይ በወሊድ ጊዜ የበርካታ እናቶችና ህፃናት ህይወት ሲያልፍ መቆየቱን አመልክተዋል። የሆስፒታል መገንባት የአካባቢውን ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የመለሰና የህብረተሰቡን የጤና ችግር የሚፈታ በመሆኑ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ባለስልጣናት በተገኙበት በይፋ ተመረቀ
- ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው ዘመናዊ የህክምና ማዕከል ተመረቀ
- የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የግብርና ምርምር ፕሮጀክት ተመረቀ
- የዱባይ ግብረ ሰናይ ድርጅት አዲስ አበባ ውስጥ ያስገነባው ትምህርት ቤት ተመረቀ
- ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው ዘመናዊ የህክምና ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎችች ባለስልጣናት በተገኙበት ተመረቀ
በኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን አገራዊ የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች በተገኙበት ዛሬ ይፋ ሆነ።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅድ አንዲት አገር በዓለም አቀፍ የጤና ህግጋት ላይ የተጠቀሱትን መሠረታዊ የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶችንና አደጋዎችን ለመከላከል፣ አስቀድሞ ለመለየትና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ለማጠናከር የተቀመጡ ግቦችን እንድታሟላ የሚያስችል ዕቅድ ሲሆን በሃገሪቱ ሙሉ ባለቤትነት የሚቀረጽ የትግበራ ዕቅድ ነው።
ማንኛውም የዓለም አቀፍ የጤና ሕግጋት ፈራሚ አገር ይህንን ዕቅድ እንደሚያዘጋጅ ሁሉ ኢትዮጵያም የዚህ ስምምነት ፈራሚ እንደመሆኗ በተደጋጋሚ የሚገጥሟትን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመቋቋም የሚያስፈልጓትን አቅም ለመገንባት ዕቅዱን ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል።
የትግበራ ዕቅዱን በአዲስ አበባ በይፋ መጀመሩን ያበሰሩት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን፥ ስለ አንድ አገር ሰላምና ደህንነት ስንናገር የሕዝቦቻችንን የጤና ደህንነት ጭምር አያይዘን እንደምንናገር መገንዘብ እንደሚገባ ጠቁመው፥ አገራዊ ዕቅዱ ወቅታዊና እንደአገር የሚያጋጥሙንን ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከልና ብዙ ጉዳት ሳያደርሱ ምላሽ ለመስጠት ያስችለናል ብለዋል።
◌ SEMONEGNA on Social Media: Facebook | Twitter | Instagram | Pinterest
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማን በበኩላቸው ሃገሪቱ እ.ኤ.አ በ2016 የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ከአፍሪካ ቢሮ በመጡ ገምጋሚዎች የጤና ደህንነቷ ያለበትን ደረጃ ማስመዘኗን ገልጸው፥ ከግምገማው በተገኙ ግብረ መልሶች እና በሃገሪቱ ከተከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ አሰጣጣችን የተግባር ልምድ በመውሰድ አገራዊ የጤና ትግበራ ዕቅድ አዘጋጅታለች ብለዋል።
የትግበራ ዕቅዱን ለመፈጸም በጀት ስለሚጠይቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያለንን ሃብት አቀናጅተን በመጠቀም ለዕቅዱ መሳካት የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይገባናል ያሉት ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶ/ር ፓሚላ ሙቱሪ ናቸው።
የኢትዮጵይ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ በበኩላቸው፥ እንደ ኩፍኝና ቢጫ ወባን የመሳሰሉ ወረርሽኞችን ለመከላከልና በዓለም ደረጃ ለሚከሰቱ እንደ ኢቦላ እና ዚካ ቫይረስ ያሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል አገራዊ የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ለዕቅዱ ትግበራ 368 ሚሊዮን 764 ሺህ 777 ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 77 በመቶ የሚሆነው የክትባት ሽፋንን ለማሳደግ የሚውል ይሆናል።
አገራዊ የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅዱ ለአምስት ዓመት ማለትም ከ2011/12 እስከ 2016/17 ዓ.ም ድረስ የሚተገበር ይሆናል።
ምንጭ፦ የጤና ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የዘንድሮው የዓለም ቲቢ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ “ጊዜው አሁን ነው…” (It’s Time…) በሚል መሪ ቃል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ “በተጠናከረ አመራር ከቲቢ ነፃ የሆነች ሀገር” መሪ ቃል ይከበራል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር በየዓመቱ የሚከበረውን የዓለም ቲቢ ቀን በዓል ከዓመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባዔ ጋር በማቀናጀት የክልል ጤና ቢሮዎችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችንና አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር ያከብራል።
በዚህም መሠረት ዘንድሮ በዓለም ደረጃ ለ37ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ22ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም ቲቢ ቀን በዓል እና ለ14ኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባዔ “በተጠናከረ አመራር ከቲቢ ነፃ የሆነች ሀገር” በሚል መሪ ቃል በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰመራ ከተማ መጋቢት 14-15 ቀን 2011 ዓ.ም. ይከበራል።
በኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር አገልግሎት እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ መጀመሪያ ከተጀመረ አንስቶ በሁሉም ክልሎች፣ በመንግሥታዊና በተፈቀደላቸው የግል ጤና ተቋማት በነጻ በመሰጠቱ በርካታ የቲቢ ሕሙማን ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ የብዙ ዜጎችን ሕይወት ታድጓል።
እ.ኤ.አ. በ2018 የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት በኢትዮጵያ አጠቃላይ የቲቢ በሽታ ስርጭት ምጣኔ እ.ኤ.አ. በ1990 ከ100,000 ሰዎች ውስጥ 369 የቲቢ ተጠቂዎች የነበሩ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ አሽቆልቁሎ እ.ኤ.አ. በ2017 ከ100,000 ሰዎች ውስጥ 164 የቲቢ ተጠቂዎች አንደሆኑ አሳውቋል። በቲቢ በሽታ ምክንያት የሚከሰት የሞት መጠንም እ.ኤ.አ. በ1990 ከ100,000 ሰዎች ውስጥ 89 ከነበረው ወደ 24 መቀነስ ተችሏል።
አገልግሎቱን በተመለከተ ዛሬም ቢሆን ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉ በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ህይወት ሰለሞን ገልፀዋል። ወ/ሮ ህይወት በመግለጫቸው እንደተናገሩት በአገሪቱ የቲቢ በሽታ ይገኝባቸዋል ተብለው ከሚገመቱት ሰዎች 35 ከመቶ ያህሉ ወደ ሕክምና ተቋማት አለመሄድ እና የቲቢ በሽታ ታካሚዎች መድኃኒትን በሐኪም ትዕዛዝ መሠረት አለመጠቀም፣ ማቋረጥ፣ በባለሙያዎች የሚሰጥ ትዕዛዝና ክትትል ጉድለት ለመጀመሪያው ደረጃ ቲቢ በሽታ ሕክምና በጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ መድኃኒቶች የቲቢ በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን የመግደል አቅማቸውን እያሳጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
- ቲቢ በዓለም ላይ ሰዎች ከሚሞቱባቸው መንስዔዎች ዘጠነኛው ሲሆን፥ በአንድ ተሕዋስ ብቻ ከሚተላለፉ በሽታዎ ከ ኤች አይ ቪ/ኤድስ (HIV/AIDS) ቀጥሎ ሁለተኛው ገዳይ በሽታ ነው፤
- እ.ኤ.አ. በ2016 አፍሪካ ውስጥ ብቻ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች በቲቢ በሽታ ተጠቅተዋል፤ ይህም በመላው ዓለም በበሽታው ከተጠቁ ሰዎች ሩቡን ያህል ነው፤
- እ.ኤ.አ. በ2016 አፍሪካ ውስጥ ብቻ 417,000 ሰዎች፣ በመላው ዓለም ደግሞ 1.7 ሚሊዮን ሰዎች በቲቢ በሽታ ለሞት ተዳርገዋል፤
- ሰባት አገራት፥ ማለትም ህንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቻይና፣ ፊሊፒንስ፣ ፓኪስታን፣ ናይጄርያ እና ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ከሚከሰተው ቲቢ 64 በመቶው ያህሉ ይከሰትባቸዋል፤
- በኤች አይ ቪ (HIV) ለተጠቁ ሰዎች ዋነኛ ገዳይ በሽታ ቲቢ ሲሆን፥ እ.ኤ.አ. በ2016 መሠረት 40 በመቶ የሚሆኑት በኤች አይ ቪ የተጠቁ ሰዎች የሞቱት በቲቢ በሽታ ነው፤
- በየዓመቱ የቲቢ በሽታ በሁለት በመቶ እየቀነሰ ቢሆንም፥ እ.ኤ.አ. በ2020 ቲቢን ከዓለም ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ይህ በሽታ ከአራት እሰከ አምስት በመቶ ያህል በየዓመቱ መቀነስ አለበት፤
- እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2015 ድረስ በአጠቃላይ 53 ሚሊዮን ሰዎችን በሕክምና ከቲቢ በሽታ ማዳን ተችሏል፤ ከዚህ ውስጥም አፍርካ ውስጥ ብቻ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2014 ድረስ 10 ሚሊዮን ሰዎችን በሕክምና ከቲቢ በሽታ ማዳን ተችሏል፤
- እስከ 2030 ድረስ (እ.ኤ.አ.) ከዓለም ላይ የቲቢ በሽታን ማጥፋት ከዘላቂ የዕድገት አጀንዳዎች (Sustainable Development Goals) አንዱ ነው።
ምንጮች፦ የጤና ሚኒስቴር፣ የዓለም ጤና ድርጅት / ሰምነኛ ኢትዮጵያ
እ.ኤ.አ ከ2019 እስከ 2023 ለሚተገበረው አገራዊ የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅድ 10 ቢሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን፥ ወጪው ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት እንደሚሰባሰብ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን አገራዊ የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች በተገኙበት ዛሬ ይፋ ሆነ።
በዚህ ወቅት እንደተገለጸው፥ አገሪቷ መከላከልን መሠረት ያደረገ ስልት ቀይሳ የምታደርገውን ጥረት በጉልህ ይደግፋል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ አለመረጋጋት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎች እንዳይጋለጡ አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ነው።
እ.ኤ.አ ከ2019 እስከ 2023 ለሚተገበረው አገራዊ የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅድ 10 ቢሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን፥ ወጪው ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት እንደሚሰባሰብ ለማወቅ ተችሏል።
የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን እንደተናገሩት፥ በዕቅድ ዝግጅቱ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ተሳትፎ አድርገዋል።
አገራዊ የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅድ ችገሮች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ በመለየት መከላከል፣ ችግሮች ሲከሰቱ ፈጣን ምላሽ መስጠት በኅብረተሰቡ ላይ በህመምና በሞት የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ስትራቴጂ ነው።
◌ SEMONEGNA on Social Media: Facebook | Twitter | Instagram | Pinterest
ባለፉት ሁለት ዓመታት የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵይ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) ጋር በመሆን ዕቅዱን ዝግጅት ሲደረግ እንደነበረ ዶ/ር አሚር ገልጸው፥ አገሪቷ በዘርፉ ምን ክፍተት አለባት? የሚለውን በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፥ ዕቅዱ ከመዘጋጀቱ በፊት አገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል።
ዶ/ር አሚር እንደሚሉት፥ በጥናቱ መሠረት ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየበት አደጋ ሲከሰት ፈጣን ምላሽ መስጠት መሆኑ የተለየ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት በሁለቱ ከተማ መስተዳደሮችና በዘጠኙ ክልሎች ማዕከላት ተቋቁሟል።
ከኬሚካልና ጨረር ጋር በተያያዘ አደጋ ቢያጋጥም ምላሽ ለመስጠት በቂ ዝግጅት እንደሌለ በጥናት የተለየ ሌላው ችግር መሆኑን ጠቁመው በዚህም ላይ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል።
በዕቅዱ ላይ እንደ ክፍተት የተቀመጡ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት 25 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵይ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ በበኩላቸው፥ አገራዊ የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅዱ በአገሪቷ ተላላፊ በሽታዎችና ወረርሽኝን አስቀድሞ ለመግታት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንደገለጹትዕ አገራዊ የጤና ደህንነት የትግበራ ዕቅዱ ወቅታዊና አስፈላጊ ነው። አደጋዎችን ቀድሞ የመከላከል፣ ብዙ ጉዳት ሳያደርሱ የመቆጣጠርና መልሶ የማገገምና እንዳይደገም የማድረግን አቅምን መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ልዑካን ቡድን አባላት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በሙያቸው እንዲያግዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ተክተሎ የመጡ ናቸው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲካሄድ የቆየው መንግስት ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያለውን ዝግጁነት የሚለይና ለችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ አውደ-ጥናት ተጠናቀቀ።
በአውደ ጥናቱ የመንግስት አግልግሎት አሰጣጥ፣ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያለው ዝግጁነት፣ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ክፍተት ተለይተውበታል – ሚኒስቴሩ እንደዘገበው።
የጤና አስተዳደር፣ የታክስ አሰባሰብ ስርዓት፣ የመረጃ ግንኙነት (ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን) ቴክኖሎጂ ደኅንነት፣ በባንክ አገልግሎት፣ በኢንሹራንስ አገልግሎት፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኦዲት አገልግሎት፣ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት፣ የውሃ አወጋገድ ላይ ክፍተቶች ተለይተዋል።
አሜሪካ ውስጥ ቨርጂንያ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ (Virginia International University; Fairfax, VA) መምህር በሆኑት ዶ/ር ተፈራ በየነ የተመራው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ልዑክ ክፍተቶቹን ከለዩ በኋላ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
◌ ከ7ሺህ 800 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በመላው አገሪቱ ሊቋቋሙ ነው
ባለሙያዎቹ በኢንሹራንስ፣ በህክምና ቴክኖሎጂ፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኑኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአሜሪካን ሀገር በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የፋይናንስ ዳይሬክተሮች እና ሌሎችም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ከቡድኑ ጋር ለ1 ሳምንት ክፍተቶችን እና ጉድለቶችን የመለየት ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል።
የሚመለከታቸው አካላት በየዘርፉ የሚደረጉ ማስተካከያዎችን በኃላፊነት ወስደው ወደ ተግባር የመቀየር ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። በማጠቃለያው ላይ፥ ልዑካኑ የኢትዮጵያ መንግስት ወይም የሚመለከተው መንግስታዊ ተቋም ዕድሉን ከሰጠን የሀገራችንን ችግር ለመፍታት በቂ አቅም አለን ብለዋል። ወደፊትም በማንኛውም መልኩ ሀገራቸውን ለማገዝ ቃል ገብተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታዎች ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) እና ጀማል በከር ልዑካኑ ሀገራቸውን ለመረዳት ያላቸውን ቁርጠኝነት በማድነቅ ምስጋና አቅርበዋል።
የልዑካን ቡድኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በሙያቸው እንዲያግዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ተክተሎ የመጡ ናቸው።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
- በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እስካሁን ድረስ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቧል
- ኢትዮጵያ በአሜሪካ ሁለተኛ ቆንስላ አጠቃላይ ጽህፈት ቤት በሚኒሶታ ግዛት ከፈተች
- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ መቋቋሙን ተከትሎ ወደ ተግባር ለመግባት የመዋቅርና የሕግ ማዕቀፍ ሥራን አጠናቀቀ
- ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
- ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ፤ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ይጀመራል
ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ በሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጀ። የአድዋ ከተማ አስተዳደር ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት ሰጠ።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ እያዘጋጀ መሆኑን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩት ጥናትና ምርምሮች ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ በአገሪቷ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡት የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከሚጠበቀው በታች ናቸው፤ ለዚህ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለጥናትና ምርምር የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆኑም እንደ ዋነኛ ምክንያት አስቀምጠውታል። እንዲያውም ለዘርፉ የሚመደበው አጠቃላይ ዓመታዊ በጀት ከሁለት በመቶ በታች መሆኑን በመጠቆም።
በተጓዳኝም የምርምር መሠረተ-ልማቶች አለመኖር፣ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው መምህራን ቁጥር አነስተኛ መሆንና መምህራን ለምርምር ትኩረት አለመስጠታቸውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩት ጥናታ ምርምሮች ቁጥር አነስተኛ መሆነ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው። ይሁንና ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ባሏቸው አቅም በአስገዳጅ መልኩ የጥናትና ምርምር ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ገልጸዋል።
ምንም እንኳን በትምህርት ተቋማቱ ዝቅተኛ ቢሆኑም በሥመ-ጥር ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ምርምሮቻቸውን የሚያወጡ ጉምቱ ምሁራን መኖራቸውንም ዶ/ር ሳሙኤል አልሸሸጉም።
ለጥናትና ምርምር የሚበጀተውን በጀት በተመለከተም ከአገሪቷ እድገትና ከመምህራኑ አቅም ጋር ባገናዘበ መልኩ እያደገ የሚመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ያሏቸውን ጆርናሎች ጥራታቸውን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጥናት እየተደረገበት መሆኑንም አስረድተዋል። መመሪያውንም በቅርቡ ወደ ሕግ በመቀየር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ጆርናሎች የሚመሩበት ወጥ ሥርዓት በመዘርጋት የእውቅና ደረጃም እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ መውሰድ (ረቂቅ አዋጁን ማውጣትም ሆነ ለጆርናሎች መመሪያ መዘጋጀት) የሚካሄዱትን ምርምሮች ጥራታቸውን ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ገልጸው፥ በቀጣይም ጥናትና ምርምር ላይ የግሉ ዘርፍ የድርሻውን ድጋፍ እንዲያደርግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ቁጥር 33 ሺህ ደርሷል፤ ከእነዚህ ውስጥ 5 ሺህ 500 የሚሆኑት ናቸው ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው – የኢትዮጵይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው።
ከከፍተኛ ትምህርት ጋር በተያያዘ፥ ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 114 ሄክታር መሬት መስጠቱን በትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ የአድዋ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል። የዩኒቨርስቲውን ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የአድዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘስላሴ ዘብራአብሩክ ለኢዜአ እንደገለጹት አስተዳደሩ ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ እንዲውል መሬቱ ተሰጥቷል። በዚህም 131 የአካባቢው አርሶ አደሮች ከይዞታቸው ላይ ተነስተዋል። ከይዞታቸው ለተነሱ አርሶ አደሮችም ካሳ ክፍያ ለመፈፀም 15 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ቢተው በላይ በበኩላቸው ግንባታውን ለማስጀመር ከፌዴራልና ከትግራይ ክልል መንግሥታት 450 ሚሊዮን ብር ተመድቧል። ከዚህም የትግራይ ክልል መንግሥት 250 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል መግባቱ ይታወሳል። የአዲስ አበባ አስተዳደርም በቅርቡ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ