-
Search Results
-
ጅማ (ኢ.መ.ባ.)– የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በተገኙበት በይፋ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን (ኢ.መ.ባ) አስታወቀ።
የአንድን ሀገር ልማት በማፋጠን ረገድ ጉልህ ሚና ካላቸው የመሠረተ ልማት ዘርፎች አንዱ መንገድ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እና በነደፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት የዘርፉ ዋነኛ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለተግባራዊ እንቅሰቃሴው ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የመንገድ ፕሮጀክት ነባሩ መንገድ ገፅታ
- በጠባብ የአስፋልት መንገድ ደረጃ የነበረ፣
- የ50 ዓመት አገልግሎት የሰጠ፣
- በ5 ሜትር ስፋት እጅግ አስቸጋሪ የነበረው፣ እና
- ለትራፊክ እንቅስቃሴዎች ምቹ ባለመሆኑ ለአደጋ ሲያጋለጥ የነበረ መንገድ ነው።
የጅማ – አጋሮ – ዲዴሣ ወንዝ ድልድይ የመንገድ ፕሮጀክት አዲሱ መንገድ ገፅታ
- የ2ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመንገድ ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር አንድ አካል ነው፤
- የአገሪቱን ደቡብ አና ሰሜን ምዕራብ ክፍሎች ደረጃውን በጠበቀ የመንገድ መሠረተ ልማት ያስተሳስራል።
መገኛ፦ ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት – ጅማ ዞን ጅማ ከአዲስ አበባ ምዕራባዊ – ደቡብ አቅጣጫ ወሊሶን አቋርጦ በሚያልፈው አስፋልት ኮንክሪት መንገድ 360 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት።
መነሻ እና መድረሻ ፕሮጀክቱ የሚጀመረው ጅማ ከተማ ከሚገኘው “ሃኒላንድ ሆቴል” በመነሳት በዋናነት በጅማ ሰሜን – ምዕራብ አቅጣጫ አድርጐ ወደ አጋሮ እና ዴዴሣ ወንዝ ድልድይ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ከዚያም ከወንዙ እስከ መቱ ከተማ በሚዘልቀው በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኘው መንገድ ጋር ያገናኛል።
የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ኮንትራት እና ውል
የሥራ ተቋራጭ፦ ቻይና ሬል ዌይ 21ኛ ቢሮ ግሩፕ የተባለ አለም አቀፍ ድርጅት
አማካሪ ድርጅት፦ ኦሜጋ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነሪንግ እና ፕሮሜ ኮንሰልታንትስ በጋራ
የግንባታ ወጪ፦ ከ1.3 ቢሊዩን ብር በላይ
የግንባታ ጊዜ፦ 41 ወራት
የግንባታ ወጪ ሽፋን፦ የኢትዮጵያ መንግስትየጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ሁለንተናዊ ፋይዳ
ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤
የተሽከርካሪ የጉዞ ወጪና ጊዜ ይቀንሳል፤
የምርት እና የሸቀጥ ልውውጥን ያቀላጥፋል፤
የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ በማውጣት የገበያ ተደራሽነትን ያቀላጥፋል፤
የከተሞች የእርስ በርስ ትስስር ይፈጥራል፤
የጤና ፣ የትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን ተደራሽነት ያጠናክራል፤
የማኅበረሰቡን ኑሮና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል፤
ቡናን ጨምሮ በግብርና ምርቶችና በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገውን አካባቢ ተጠቃሚ ያደርጋል።ምንጭ፦ ኢ.መ.ባ. | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ዩኒሴፍ ባወጣው መግለጫ መሠረት በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለስደተኞች ህጻናት የሚሆኑ ሦስት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ፣ ባለ 41 ክፍሎች ስምንት ሁለተኛ ደረጃ እና ባለ 84 ክፍሎች አራት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ።
አዲስ አበባ (ኢዜአ)– በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እና ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ሊገነቡ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) አስታወቀ።
ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ኅዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ የሚከናወነው ”ትምህርት ቆሞ አይጠብቅም” በሚል መርህ ለትምህርት በተያዘው እና በመላው ዓለም በስደት ለሚገኙ እና ለአደጋ የተጋለጡ 12,000 የሚደርሱ ህጻናትን በትምህርት ለመደገፍ ከተያዘው የ15 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት ውስጥ እንደሆነ ታውቋል።
ሦስት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ፣ ባለ 41 ክፍሎች ስምንት ሁለተኛ ደረጃ እና ባለ 84 ክፍሎች አራት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ የሚከናወን መሆኑን መግለጫው አትቷል።
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ጊሊያን ሜልሶፕ ”ይህ ፕሮጀክት በስደተኞች መጠለያ ጣቢያና የስደተኞች ተቀባይ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ የምናደርገው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
ማንኛውም ታዳጊ በምንም አይነት ሁኔታ ቢገኝ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን ብሩህ ከሚያደርገው ትምህርት መራቅ የሌለበት መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 3600 ታዳጊዎችን በሁለተኛ ደረጃ፣ 8400 ታዳጊዎችን በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተቀብሎ የሚያስተናግድ ይሆናል። ትምህርት ቤቶቹ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2019 እና 2020 ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚገመት ተገልጿል። ትምህርት ቤቶቹ በቁሳቁስ፣ በላቦራቶሪ፣ በቤተመጽሐፍት፣ በመምህራን ቢሮዎችና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች የተሟላ እንደሚሆኑም ተነግሯል።
ዩኒሴፍ ያውጣውን መግለጫ ሙሉውን (በእንግሊዝኛ ቋንቋ) ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- ውጤታማ የማኅበረሰብ-አቀፍ የአኩሪ አተር የመነሻ ዘር ብዜት ሥራዎች በፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል
- የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስላለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ የሰጠው መግለጫ
- የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በአንድነት ለመሥራት ቃል ገቡ
- ሐረር የሚኖሩ የጉራጌ ህብረተሰብ አባላት በመስቃንና ማረቆ ወረዳ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ100,000 ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
- በአገሪቱ ውስጥ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኤች አይ ቪ/ኤድስ፥ አዲስ አበባ ውስጥ በአፍላ ወጣቶች ላይ ግን ችግሩ ይከፋል
ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሽከርካሪ ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን በአዲስ አበባ እና በሌሎች የክልል ከተሞች የተመረጡ መንገዶችን ለሰዓታት ለተሽከርካሪዎች ዝግ በማድረግ እና በመንገዶቹም ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን የማድረግ መርሃ ግብር ተካሄደ።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን (non-communicable diseases/ NCD) በተመለከተ ግንዛቤ ለማስጨበጥና የእግር ጉዞ ልምድን ለማበረታታትና ባህል ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ በማድረግ (car free day) የጤናና አካል ብቃት ስፖርቶች ተካሄዱ።
ህዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በመዲናዋ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ በማድረግ በተከናወነው የጤና የአካል ብቃት ስፖርቶች መርሃ ግብር የጤና ሚኒስትሩ አሚር አማን (ዶ/ር) እና የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ታዋቂ ግለሰቦች ተሳታፊ ሆነዋል።
መርሃ ግብሩ በየወሩ የሚከናወንና በሌሎች የክልል ከተሞች የሚስፋፋ እንደሆነም ተጠቁሟል። በአዲስ አበባ የተጀመረውን መርሃ ግብር ተከትለው በዚሁ ዕለት ባህር ዳር፣ ጅማ፣ መቐለ፣ ሀዋሳ እና ጅግጅጋ “ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን” በሚል ተመሳሳይ ዝግጅቶችን ማዘጋጀታቸውን ዶ/ር አሚር አማን በማኅበራዊ ገጻቸው አስታውቀዋል።
በመዲናዋ መርሃ ግብሩ ሲከናወን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አደባባዮችና ጎዳናዎች ዝግ ተደርገው ህብረተሰቡ በእግሩ እንዲጓዝ ተደርጓል።
መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ የአዲስ አበባ መንገዶችን በወር አንድ ጊዜ የእግር ጉዞ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲደረግባቸው ለማስቻል እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል። በሚቀጥለው ዓመት 15 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ለእግረኛ እና ለብስክሌት መንቀሳቀሻ ምቹ መንገዶችን ለመስራት መታሰቡን ጠቁመዋል።
በየወሩ መጨረሻ እሁድ በመላው አገሪቱ በእግር የመጓዝ ልምድን ለማበረታታትና ባህል ለማድረግ “ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን” በሚል መሪ ሀረግ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ እንደሚደረጉ ለማወቅ ተችሏል።
ህዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በተደረገው መርሃ ግብር በርካታ ቁጥር ያላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ የእግር ጉዞና የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና አጋላጭ መንስዔዎቻቸውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ህብረተሰቡ የመመርመር ልምዱን እንዲያሳድግም ጥሪ ቀርቧል። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እ.ኤ.አ የ2016 ዓ.ም. መረጃን/ውሂብን ተገን አድርጎ በ2018 ዓ.ም. ባወጣው የሀገራት ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ከሚሞተው ሰው 39 በመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት እንደሆነ ያሳያል። ይህ አሀዝ በበሽታዎች ሲከፋፈልም፥ ከልብ ጋር የተያያዙ በሽታዎች (16 በመቶ)፣ የተለያዩ የካንሰር በሽታዎች (7 በመቶ)፣ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ በሽታዎች (2 በመቶ) እና የስኳር በሽታ (2 በመቶ) ሲይዙ የተቀረው 12 በመቶ ደግሞ በሌሎች የተለያዩ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንደሆነ ሪፖርቱ ያትታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ የደረሱበት ስምምነት በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የፎረንሲክ ምርመራ ተከትሎ በህክምናና በሕግ ጉዳዮች ላይ መረጃን በወቅቱ ለማግኘት የሚያስችል ፈጣን አሠራር ለመዘርጋት ያለመ ነው።
አዲስ አበባ (ኢዜአ)– የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ህክምና ኮሌጅ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር የፎረንሲክ ምርመራን በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ኅዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የፎረንሲክ ምርመራ ተከትሎ በህክምናና በሕግ ጉዳዮች ላይ መረጃን በወቅቱ ለማግኘት የሚያስችል ፈጣን አሠራር ለመዘርጋት ያለመ ነው ተብሏል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ዋና ፕሮቮስት ዶ/ር ወንድማገኝ ገዛኸኝ ስምምነቱ በተፈረመበት ጊዜ እንደገለጹት፥ ከምረዛና ከአደጋዎች ጋር የተያያዙ የሞት መንስዔዎችና የጤና ጉዳቶች በመለየት ለሕግ አካላት መረጃን በወቅቱ በማቅረብ ረገድ በአገሪቱ ውስጥ ክፍተቶች አሉ። በዚህም ሆስፒታሉ በቅርቡ በጀመረው አጠቃላይ የፎረንሲክ ምርመራ ማዕከል ለሕግ አካላትም ሆነ ለመረጃ የሚጠቅሙ መንስዔዎችን የማጣራት ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ይህንን የፎረንሲክ ምርመራ በማጠናከር የወንጀል ምርመራን በፍጥነት በመለየት ከፌዴራል ፖሊስ በመተባበር ለመሥራት የሚያስችለውን ቅንጅታዊ አሠራር ማጎልበት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህን ሰነድ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል ዶ/ር ወንድማገኝ።
በስምምነቱ መሠረትም የአስክሬን ምርመራን ጨምሮ፣ የአስገድዶ መደፈር ጥቃት፣ የእድሜ ምርመራና የመኪና አደጋ በስምምነቱ የተካተቱ እንደሆኑ ተጠቁሟል። በዋናነትም ለፖሊስና ለሕግ ባለሙያዎች የፎረንሲክ ህክምናና ፎረንሲክ ሳይንስ ከተግባር ትምህርት ጋር ስልጠና የመስጠት ሥራ በሆስፒታሉ የሚከናወን እንደሆነና ምርመራውን የሚያግዙ መሣሪያዎችን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ሁኔታም በስምምነቱ ተካቷል።
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ተኮላ አይፎክሩ በበኩላቸው ወንጀልን መርምሮ ተጠያቂውን አካል ለፍርድ በማቅረብ ረገድ የፎረንሲክ ምርመራን ዘመናዊና ፈጣን በሆነ መልኩ ማከናወን አስፈላጊ ነው። ”ይህም ደግሞ በአገሪቱ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥና የዜጎችን ሰላም ለማስፈን ሚናው የጎላ ከመሆኑም ባሻገር ዜጎች በፍትህ አካላት ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ ይረዳል” ብለዋል።
ወንጀሎች በተፈጸሙባቸው አካባቢዎች ከሁለቱም ተቋማት የተውጣጣ የሙያተኞች ቡድን በስፍራው በመገኘት የማጣራት ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት የሚያስችል አሠራር መስምምነቱ መካተቱን ጀኔራል ተኮላ ጠቅሰዋል። ሌላው አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች ውስጥም ብሔራዊ የፎረንሲክ ተቋማትን ለመመስረት የሚያስችል አሠራር የሚዘረጋ እንደሆነና የጋራ የሆነ የስልጠናና የምርምር ፕሮግራሞች የሚካሄድ ይሆናልም ሲሉ አክለዋል።
በአሁኑ ወቅት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፎረንሲክ ማዕከል በቀን ከ25 እስከ 30 የሚሆኑ ምርመራዎችን እንደሚያከናውን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
5ኛውን አዲስ ፎቶ ፌስት የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ያዘጋጁት ደስታ ለአፍሪካ [የፈጠራ አማካሪ] ከስዊዘርላንድ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ሲሆን፥ አውደ ርዕዩ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ይቆያል።
አዲስ አበባ (ቢቢሲ አማርኛ) – በአፍሪካ ውስጥ ስመጥር ከሆኑት የፎቶ ፌስቲቫሎች ከፍተኛ ቦታ ያለው አዲስ ፎቶ ፌስት ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል ተከፍቷል።
ለአምስተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከ61 ሃገራት የተወጣጡ 152 የፎቶ ግራፍ ባለሙያዎች የተለያዩ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ። ይህ አውደ ርዕይ በየዓመቱ አሳታፊነቱ እየጨመረ የመጣ እንደሆነ የምትናገረው ‘ደስታለ አፍሪካ የፈጠራ አማካሪ’ (Desta for Africa Creative Consulting) የተባለ ድርጅት መሥራችና የአዲስ ፎቶ ፌስት ዋና አዘጋጅ የሆነችው የፎቶ ባለሙያዋ አይዳ ሙሉነህ ዋና ትኩረቱም የውክልና ጉዳይ ነው ትላለች።
አፍሪካ በተለያዩ ምስሎችም ሆነ በውጭው ዓለማት የምትታወቀው ሁሌም ከችግር፣ ድርቅና ረሀብ ጋር ብቻ ከመሆኑ አንፃር አዲስ ፎቶ ፌስት በጎ ጎኗንም ለማሳየት እንዳለመ አይዳ ታስረዳለች።
“ይህንን የፎቶ አውደ ርዕይ የምናየው እንደ አቅም ግንባታ ነው፤ እነዚህን ሁሉ ወጣት የፎቶ ባለሙያዎች ስናሰባስብ ወይም ስልጠና ስንሰጥ የኢትዮጵያን እውነታ በምን መንገድ ሊያሳዩ ይችላሉ የሚለውን ለማሳየት ነው” በማለት ታስረዳለች አይዳ።
በተለይም አፍሪካ እንደ ጨለምተኛ ብቻ አህጉር ተደርጋ መታየቷ ትክክለኛ እይታ እንዳልሆነ የምትናገረው አይዳ “ሁሉም ነገር በጎ አይደለም፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር ደግሞ መጥፎ አይደለም። በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጎልቶና ገኖ የሚታየው መጥፎ ነገር ነው” በማለት ይህንንም ለመቀየር ኢትዮጵያዊ ወይም አፍሪካዊ ፎቶ ባለሙያዎችን ማፍራትና እይታዎችንም መፍጠር እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ትሰጣለች።
በዚህ ዓመት አዲስ ፎቶ ፌስት ዓውደ ርዕይ ላይ 1200 ፎቶዎች የሚቀርቡ ሲሆን ከዓመት ወደ ዓመት የተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ አይዳ ሙሉነህ ተናገራለች።
በባለፈው አመት ለመሳተፍ የጠየቁ የፎቶ ባለሙያዎች ቁጥር 500 የነበረ ሲሆን በዚህ አመት ወደ 832 ደርሷል። ከነሱም ውስጥ 152 ባለሙያዎች ተመርጠው ተሳታፊ ሆነዋል። ለአይዳ ሙሉነህ የተሳታፊዎች ቁጥር መብዛት የሚያሳየው አዲስ ፎቶ ፌስት በዓለም ላይ ያለው ስፍራ እየጨመረ መሆኑን ነው።
በተጀመረበት ወቅት አምስትዓ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ያሳተፉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም 35 እንደደረሱ አይዳ ትናገራለች። ምንም እንኳን በፈተናዎች የተሞላ መሆኑን አይዳ ባትክድም “ይሄን ሁሉ ሥራ የምንሰራው ሃገሪቷን ለማሳወቅ ነው” ትላለች።
5ኛውን አዲስ ፎቶ ፌስት የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ያዘጋጁት ደስታ ለአፍሪካ የፈጠራ አማካሪ ከስዊዘርላንድ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ሲሆን፥ አውደ ርዕዩ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ይቆያል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ አማርኛ | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያዊያን አያሌ የሚያስተሳስሯቸው ነገሮች ያሏቸው በመሆኑ የሚያለያዩዋቸውን ጥቂት ነገሮች በመቻቻል አንድነታቸውን የሚያጎለብቱ ጉዳዮችን ጎልቶ እንዲወጣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል።
አዲስ አበባ (ኢ.ፕ.ድ) – የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ከልዩነት በላይ ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ የፊዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ።
የፊታችን ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀን በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ዝግጅት መጠናቀቁንም ምክር ቤቱ አስታውቋል።
ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረውን በዓል ከልዩነት በላይ ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ በምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረሥላሴ በተለይ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢ.ቢ.ሲ) ተናግረዋል። በዚህም ብሔረሰቦች የራሳቸውን ባህል ከማስተዋወቅ በዘለለ የባህል ልውውጥ የሚያደርጉበት መድረክ እንደሚፈጠር ገልፀዋል።
በዚህም አንዱ ብሔር የሌላውን ባህል እንዲያንፀባርቅ በማድረግ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጎለብት ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል ዳይሬክተሩ አቶ ገብሩ።
ኢትዮጵያዊያን አያሌ የሚያስተሳስሯቸው ነገሮች ያሏቸው በመሆኑ የሚያለያዩዋቸውን ጥቂት ነገሮች በመቻቻል አንድነታቸውን የሚያጎለብቱ ጉዳዮችን ጎልቶ እንዲወጣ በዓሉ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
አቶ ገብሩ አክለውም ዘንድሮ በአዲስ አበባ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው የበዓሉ ተሳታፊዎች እየተጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል። በበዓሉ ዕለትም በክልሎች ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲምፖዚየሞች፣ የተለያዩ ውይይቶችና ዝግጅቶች እንደሚካሄዱም ይጠበቃል ብለዋል።
በበዓሉ በሚካሄዱ ውይይቶች ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በግጭቶች መንስዔ ዙሪያ ምክክር ተደርጎ የመፍትሄ ሀሳቦች እንዲቀመጡም እንደሚደረግ አቶ ገብሩ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገ-መንግስት የፀደቀበት ቀን የሆነው ህዳር 29 ቀን‹‹በብዝሃነት የደቀመ ኢትዮጵያዊ አንድነት›› በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ይከበራል።
በበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ወቅትም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ የሰላም ጉባኤዎች በተለያዩ ክልሎች ሲካሄዱ መቆየታቸውንም ምክር ቤት አስታውቋል። ባለፈው ዓመት 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በሆነችው ሰመራ መከበሩ ይታወሳል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢ.ፕ.ድ) | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዳማ ከተማ ውስጥ የሚገነባው የኮንፈረንስና ኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታው ከ3 እስክ 5 ዓመት ጊዜ የሚፈጅ ሲሆን፥ የዘንድሮውን ዓመት ለዝግጅት በመያዝ በቀጣይ ወደ ግንባታ ለመግባት በትኩረት እንደሚሠራ የከተማዋ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ ገልጸዋል።
አዳማ (ኢ.ፕ.ድ./ኤፍ.ቢ.ሲ.) – አዳማ ከተማን የኮንፈረንስና እና ኮንቬንሽን ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ሠራ ገለጸ። የከተማ አስተዳደሩ የአዳማ ከተማ ሀገሪቱ ውስጥ ካላት መዕከላዊ አቀማመጥ እና ለዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ያላትን ቅርበት መሠረት በማድረግ ከተማዋን የኮንፈረንስ እና ኮንቬንሽን ማዕከል ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ነው የተገለፀው።
የማዕከሉ ዲዛይን ተሠርቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ዲዛይኑም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ባህል እና እሴት በጠበቀ መልኩ የተሠራ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም ማዕከሉ መንግስትን እና የአካባቢውን ባለሀብቶች በማሳተፍ የሚሠራ መሆኑ ነው የተገለፀው።
ዲዛይኑ ተሠርቶ እንደተጠናቀቀም ከባለሀብቱ ጋር ወይይት ተደርጓል ያሉት ከንቲባው፥ የማዕከሉ ግንባታ ለከተማዋም ሆነ ለሀገሪቱ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ መስፍን አንስተዋል።
ግንባታው ከ3 እስክ 5 ዓመት ጊዜ የሚፈጅ ሲሆን፥ የዘንድሮውን ዓመት ለዝግጅት በመያዝ በቀጣይ ወደ ግንባታ ለመግባት በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት ከንቲባው። ግንባታውን አጠናቆ ለመጨረስም 2 ቢሊየን ብር ስፈልጋል ያሉት ከንቲባው፥ ለግንባታው የሚያስፈልገው የ10 ሄክታር መሬት የማዘጋጀት ሂደቱም ተጀምሯል ብለዋል።
◌ Addis-Africa International Convention and Exhibition Center (AAICEC) Share Company
በሌላ በኩል በከተማዋ ከኢንቨስትመንት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ቅሬታ መቅረፍም፥ በዚህ ዓመት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ያለ ጉዳይ መሆኑን ነው ከንቲባው የተናገሩት።
ፋና (ኤፍ.ቢ.ሲ.) እንደዘገበው ብዙ ጊዜ የከተማዋ አቅም እና የኢንቨስትመንት አማራጭ ላይ በቂ ዝግጅት ስለማይደረግ ባለሀብቱ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ጠይቆ ምላሽ ሳያገኝ ለበርካታ ዓመታት ወደሥራ ሳይገባ መቆየቱ እና ይህም የተለያየ ቅሬታ መፍጠሩንም ከንቲባው አንስተዋል ።
የተጠራቀሙ ጥያቄዎችን ለመመለስ እና የዘርፉን ውስንነቶች ለመቅረፍም የከተማዋን አቅም እና የኢንቨስትመንት አማራጮች የመለየት ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ለመሥራት ከታሰበው የኮንፈረንስና የኮንቬንሽን ማዕከል አጋዥ የሆኑ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሎች ለመስራት ፍቃድ የሚጠይቁ ባለሀብቶች በቅድሚያ የሚስተናገዱ መሆኑን ከንቲባው ጠቁመዋል።
በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የአዲስ-አዳማ የፈጣን መንገድ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀመሮ ከከተማዋ ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን ጉዞ በእጅጉን እንዳቃለለውና በሁለቱ ከተሞች የነበረውን የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ሁነኛ በሚባል መልኩ እንዳሻሻለው ይታወቃል። ይህ 85 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለውና ወደጎን ስድስት መኪናዎችን ማስተናገድ የሚችለው መንገድ ከተገነባ በእላ አዳማ ከተማ ውስጥ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መጨመሩን ብዙዎች ይመሰክራሉ።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ፋና ብሮድካስቲንግ፣ ሰሞነኛ
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለም ከዚህ በኋላ በልማት ሰበብ የሚፈናቀልና የአርሻ መሬቱ የሚነጠቅ አርሶ አደር እንደማይኖር አረጋግጠውላቸዋል። በእስካሁኑ ሂደት የተጎዱ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እና ሕይወታቸውን ለመቀየር አስተዳደሩ ከምንም በላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራልም ብለዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚገኙ አርሶ አደሮችን አወያዩ። ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አባላት እንዲሁም የክፍለ ከተማ አመራሮች አርሶ አደሮችን ያወያዩ ሲሆን በውይይታቸው መጀመርያም ኢንጂነር ታከለ ኡማ “የአርሶ አደሮችን ሕይወት መቀየር ታሪካዊ ኃላፊነት የጣለብን ግዴታ ነው፣ ይህንን ታሪክ የጣለብንን ኃላፊነት እንወጣዋለን” ብለዋል።
አርሶ አደሮችም አላግባብ ከቀያቸው ስለመፈናቀላቸው፣ ከካሳ ክፍያና በማቋቋሚያ ድጎማ፣ በመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ በካርታ አሰጣጥና የአርሶ አደር ልጆች ካሳ ክፍያ ዙሪያ እንዲሁም በክፍለ ከተሞች ስላለው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጥያቄ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለም ከዚህ በኋላ በልማት ሰበብ የሚፈናቀልና የአርሻ መሬቱ የሚነጠቅ አርሶ አደር እንደማይኖር አረጋግጠውላቸዋል። በእስካሁኑ ሂደት የተጎዱ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እና ሕይወታቸውን ለመቀየር አስተዳደሩ ከምንም በላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራልም ብለዋል።
ምንጭ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት
——
ሌሎች ዜናዎች:- በአዲስ አበባ የትምህርት ጥራት ደረጃን ያላሟሉ 52 ትምህርት ቤቶች ተዘጉ
- የደንበኞቹን ፍላጎት ያልቻለው የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ (ኢትፍሩት)
- ራይድ የተባለዉ የታክሲ አገልግሎት ድርጅት የስም ማጥፋት ዘመቻ እና ጥቃት ደርሶብኛል በማለት ወቀሰ
- የዱባይ አቡዳቢው ኤግል ሒልስ በአዲስ አበባ ለገሀር የተቀናጀ የመኖሪያ፣ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ሥራውን ጀመረ
- በአገሪቱ ውስጥ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኤች አይ ቪ/ኤድስ፥ አዲስ አበባ ውስጥ በአፍላ ወጣቶች ላይ ግን ችግሩ ይከፋል
አዲስ አበባ (ኢዜአ)– በኢትዮጵያ ንብን በዘመናዊ መንገድ በማነብ የአገሪቱን የማር ምርት ለማሳደግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። በአገሪቱ ማርን በብዛትና በጥራት ለማምረት የንብ እርባታ ኢንዱስትሪ መቋቋም ይኖርበታል ተብሏል።
በኢትዮጵያ ከመቶ ዓመት በላይ የንብ ማነብ ልምድ ቢኖርም አሠራሩ ዘመናዊ የንብ አነባብ ግብአቶችን መሠረት ያላደረገ፣ ይልቁንም ባህላዊ መንገድ የተከተለ በመሆኑ የሚፈለገውን ያህል የማር ምርት ማምረትና ለገበያ ማቅረብ አልቻለችም።
በአገሪቱ ከ2 ሚሊየን በላይ ንብ አናቢዎች ያሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በዓመት እስከ 50 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማር በመመረት ላይ ይገኛል። ያም ሆኖ ግን የአመራረት ስርዓቱ እንዲዘምን ቢደረግ በአገሪቱ ከዚህ የበለጠ መጠን ማር ማምረት እንደሚቻል ነው ህዳር 21 ቀን 2011 ዓ.ም. አዲስ አበባ በተጀመረውና በዓለም አቀፉ አናቢዎች ፌዴሬሽን (Apimondia) በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የተመለከተው።
◌ Ahadu Beekeeping and Honey Processing Factory inaugurated in Tigray Region, Ethiopia
“በምግብ ምርት ላይ የንቦች አስተዋጽኦ” በሚል ርዕስ እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን የንብ እርባታ ለዜጎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ከመሆን ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም ገልፀዋል። ሆኖም በኢትዮጵያ በርካታ የንብ ዝርያዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አናቢዎች ቢኖሩም በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን እያገኘች እንዳልሆነ ነው የተናገሩት። በመሆኑም መንግስት ገበያ-ተኮር የማር ምርት ለማምረት በዘርፉ ከተሰማሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም የንቦች ቁጥር እየተመናመነ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ችግሩን ለመከላከል ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብረ መሥራት የግድ መሆኑን አስረድተዋል።
የአየር ንብረት መዛባት፣ በሽታና የተክሎች መጠን መመናመን ለንቦች ቁጥር እንዲቀንስ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የችግሩ መንስዔ በመሆኑ የጋራ መፍትሄ መፈለግ ይኖርብናል ብለዋል።
ለንቦች ቁጥር መመናመን አንዱ ምክንያት የሆነው በአርሶ አደሩ ዘንድ በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ ላለው የጸረ-አረም ርጭት ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል። በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ እድገት እያሳየ ያለውን የግብርና ዘርፍ ዘመናዊ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አነስተኛ እንደሆነም ሚኒስትሩ አክለዋል።
◌ Ethiopia’s apiculture and huge honey production potential need to look for modern techniques
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ዓለም አቀፍ ጉባኤም መንግስትን፣ በዘርፉ የተሰማሩ አናቢዎችን፣ ማኅበራትና ተቋማትን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሊድ ቦምባ በኢትዮጵያ የማር ምርትን ለማሳደግ አሠራሩን ዘመናዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በአገሪቱ ማርን በብዛትና በጥራት ለማምረት የንብ እርባታ ኢንዱስትሪ መቋቋም አንዳለበትም አሳስበዋል። ዘርፉን ማሳደግ አንዲቻል አዳዲስ ቴክኖሎጂ ማላመድ፣ ዛፎችን በብዛት መትከል፣ የገበያ ትሰስር መፍጠር፣ አመራረቱን ዘመናዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ አናቢዎች ፌዴሬሽን (Apimondia) ምክትል ፕሬዚዳንት ፒተር ኮዝሙስ ኢትዮጵያ ካላት የማምረት አቅም አኳያ አሁን ያለው ምርት ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ ገልጸዋል። የአየር ንብረት ለወጥ፣ የንቦች በሽታ እና የዓለም ገበያ መለዋወጥ የዘርፉ ችግር በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ውይይት ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል። “ንቦች ከሌሉ ህይወት የለም” የሚሉት ምክትል ፕሬዘዳንቱ ተመራማሪዎች፣ እውቀት ያላቸው ሰዎች ልምዳቸውን ማካፈል አለባቸው ብለዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
አዲስ አበባ – አዋሽ ባንክ 23ኛውን የባለአክሲዮኖች ዓመታዊ መደበኛና 15ኛውን የባለአክሲዮኖች ድንገተኛ ጉባዔ ኅዳር 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሂልተን ተካሂዷል።
በጉባዔው ላይ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እና ባለአክሲዮኖች የተገኙ ሲሆን፥ በስብሰባው ላይ የባንኩ የዳሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታቦር ዋሚ የባንኩን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በዝርዝር አቅርበዋል።
የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው በሪፖርታቸው እንደጠቀሱት ያሳለፍነው በጀት ዓመት ለአገራችንም ሆነ ለግል ባንኮች እጅግ ፈታኝ ጊዜ የነበረ ቢሆንም ባንኩ እነዚህን ፈታኝ ተግዳሮቶችን በመቋቋምና ወደ መልካም አጋጣሚ በመለወጥ በሁሉም የሥራ ዘርፎች አመርቂ ውጤት ማስመዘገቡን ገልጸዋል። የተመዘገበው ውጤት እ.ኤ.አ ለ2017/18 ሒሳብ ዓመት በአስር ዓመት ስትራቴጂ ውስጥ ከተቀመጠው ግብ አኳያም ሲታይ እጅግ የላቀ ውጤት መሆኑን የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አብራርተዋል።
አዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ በ2017/18 የሒሳብ ዓመት ባንኩን ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የብድር ጣሪያ መኖር እና ከሚገኘው የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲያደርጉ መደረጉ በጉልህ ይጠቀሳሉ።
አዋሽ ባንክ ይህንን ሁሉ ፈተናዎች ተቋቁሞ በሁሉም የሥራ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶችን በማስመዘገብ ከሀገርቷ የግል ባንኮች መካከል የቀዳሚነት ሥፍራውን እንደያዘ መቀጠሉን ገልፀዋል።
◌ Wegagen Bank grosses more than 1 billion birr, which is 49% up from previous fiscal year
እ.ኤ.አ በ2017/18 የሒሳብ ዓመት የባንኩ ያልተጣራ ትርፍ ብር 1.96 ቢሊዮን ሲሆን ይህም ትርፍ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የብር 650 ሚሊዮን ወይም የ49 በመቶ ዕድገት አሷይቷል። ይህም ትርፍ ለአዋሽ ባንክም ሆነ በግል ባንኮች ታሪክ ውስጥ ከፍተኛው ትርፍ እንደሆነ ታውቋል።
ለባንክ ሥራ እንደ ደም ስር የሚታየውን የተቀማጭ ሒሳብን በማሰባሰብ ረገድም ጠቅላላ የባንኩ ተቀማጭ ሒሳብ ኤልሲ ማርጅንን ጨምሮ የብር 13 ቢሊዮን ወይም የ40 በመቶ ዕድገት በማሳየት እ.ኤ.አ ሰኔ 2018 መጨረሻ ላይ ብር 45.9 ቢሊዮን ደርሷል።
አዋሽ ባንክ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠን ብር 31.3 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ብድር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ሲተያይ የብር 8.7 ቢሊዮን ወይም የ38 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል።
እ.ኤ.አ በ2017/18 የሒሳብ ዓመት የባንኩ ጠቅላላ ገቢ አምና ከነበረበት ብር 3.76 ቢሊዮን የብር 1.7 ቢሊዮን ወይም የ44 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ብር 5.4 ቢሊዮን ሆኗል።
◌ Berhan Bank, one of the private banks in Ethiopia, registers more than 410 million birr before tax
በሌላ መልኩ የባንኩ ጠቅላላ ወጪም የብር 1 ቢሊዮን ወይም የ41 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ብር 3.4 ቢሊዮን ሁኗል። ለወጪዎቹ ማደግ ዓብይት ምክንያቶች የወለድ ምጣኔ መጨመር፣ የሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ዕድገት፣ የዕቃዎች ዋጋ መናር እና የባንኩ የሥራ ዘርፎች መስፋፋት እንደሆነ ታውቋል።
ባንኩ ለደንበኞቹ የተቀላጠፈና ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ከመስጠት አኳያም የተለያዩ ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን አገልግሎቶቹንም በዘመናዊ የክፍያ ማሽኖች ማለትም በኤቲኤም እና ፖስ ማሽኖች እንዲሁም በሞባይል ባንኪንግ እና በኢንቴርኔት ባንኪንግ አገልግሎቶች በመታገዝ ለደንበኞቹ በቀን የ24 ሰዓት እና በሳምንት የ7 ቀናት የባንክ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ነው። ለወደፊቱም ዘመናዊ የሆነ የግንኙነት ማዕከል (Contact Center) እና የደንበኞች ግንኙነት አመራር (Customer Relationship Management – CRM) አገልግሎቶችን በሥራ ላይ ለማዋል በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ደንበኞች ሳይጉላሉ በአቅራቢያቸው የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻልም እ.ኤ.አ በ2017/18 ሒሳብ ዓመት ሃምሳ አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፎቹን ብዛት 366 አድርሷል።
ባንኩ ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው አመርቂ ውጤቶች የተነሳም የባንኩ ጠቅላላ ሀብት የዛሬ 3 ዓመት ከነበረበት ብር 25 ቢሊዮን ከእጥፍ በላይ ጭማሪ በማሳየት ብር 55 ቢሊዮን ሁኗል። እንደዚሁም የባንኩ ጠቅላላ ካፒታል መጠባበቂያዎችን ጨምሮ ብር 6.5 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ደግሞ ብር 2.9 ቢሊዮን ሆኖ ተመዝግቧል።
የባንኩ ባለአክሲዮኖች በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ የባንኩን የተከፈለ ካፒታል ብር 6 ቢሊዮን ለማድረስ በተሰማሙት መሠረት በሚቀጥሉ ዓመታት የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከፍተኛ ጭማሪ እንደሚያሳይ ይጠበቃል።
አዋሽ ባንክ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በዘንድሮ ዓመትም በተመሳሳይ መልኩ ለበጐ ሥራዎች የሚውል የብር 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን) እርዳታ እንዲሰጥ የዳይሬክተሮች ቦርድ ወስኗል።
ምንጭ፦ አዋሽ ባንክ
ኢትፍሩት የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች ሸቀጦችን ጨምሮ በመዲናችን አዲስ አበባ ከ60 በላይ ኮንቴነሮችን ይዞ የደንበኞችን ፍላጎት የማርካትና ገበያዉን የማረጋጋት ዓለማ ሰንቆ እየ ሠራ ቢሆንም የተፈለገውን ውጤት አያመጣሁ አይደለም ብሏል።
አዲስ አበባ (ኢቢሲ)– የቀድሞው የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ (ኢትፍሩት) ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እየሰጠ ያለው አገልግሎት የደንበኞቹን ፍላጎት እያረካ አለመሆኑን ተጠቃሚዎች ገለጹ።
የከተማዋ ሸማቾች ምርትና ሸቀጦችን በግል ከሚያቀርቡ የንግድ ተቋማት ይልቅ ኢትፍሩት በዋጋ የተሻለ መሆኑን የሚገልፁት አስተያየት ሰጪዎቹ ፥ ዘይትና ስኳርን ፍለጋ ከጠዋት ተነስቶ እስከ እኩለ ቀን ድረስ በኢትፍሩትና ሸማቾች ሱቆች በራፍ መሰለፍ የተለመደ ተግባር መሆኑን ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ገልፀዋል።
ኢትፍሩት የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች ሸቀጦችን ጨምሮ በመዲናችን አዲስ አበባ ከ60 በላይ ኮንቴነሮችን ይዞ የደንበኞችን ፍላጎት የማርካትና ገበያዉን የማረጋጋት ዓለማ ሰንቆ እየ ሠራ ቢሆንም የተፈለገውን ውጤት አያመጣሁ አይደለም ብሏል።
ድርጅቱ የፍራፍሬና አትክልት ምሮቶችን ጨምሮ ከሌሎች አምራቾች እየገዛ ስለሚሸጥ በሚፈለገዉ ልክ የአቅርቦት መጠኑን ማሻሻል አለመቻሉን ለኢቢሲ አመልክቷል።
◌ Business Cooperation: Meki Batu Vegetable & Fruit Growers and Ethiopian Airlines
ኢትፍሩት ለከተማዋ ነዋሪ በተመጣጣኝ ዋጋ ሸቀጥና ምርትን በማቅረብ የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ለሟሟላት ከአዲስ አበባ ዉጭ በአንዳንድ ክልሎች ቅርንጫፎችን ከፍቶ ህብረተሰቡን በማገልገል ላይ መሆኑን በኮሮፕሬሽኑ የንግድ ሥራ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መህዲ አስፋው ተናግረዋል።
ከመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦትና ቁጥጥር ጋር በተያያዘ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ዘመናዊ አሠራር በመዘርጋት ሂደት ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አመልክቷል።
በቢሮው የግብይት ተሳታፊዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን በቀለ እንደሚሉት እያንዳንዱን ተጠቃሚ ጋር ለመድረስ እንዲያስችል ከኢትፍሩት ሱቆች ባሻገር በግለሰብ ሱቆች መገልገል የሚያስችሉ ከ1 ሚሊየን በላይ ካርዶች ተዘጋጅተዉ ለህብረተሰቡ በመሰረጨት ላይ ናቸዉ።
ኃላፊው እንደሚሉት ካርዶቹን በመያዝ ህብረተሰቡ ትስስር ከተፈጠረባቸዉ ሱቆች የፍጆታ ሸቀጦችን በመሸመት ካለአስፈላጊ መጉላላትና ሰልፍ ራስን ማዳን ይቻላል።
ከ8 በላይ የአትክልትና ፍራፍሬና የፋብርካ ምርቶችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ ላይ የሚገኘዉ ኢትፍሩት ከ5 መቶ በላይ ሠራተኞችን ይዞ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በ60 ኮንቴኔር ሱቆች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
በቅርቡም በንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ስር ተደራጅቶ ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እይተንቀሳቀሰ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢትፍሩት የተመሠረተው በቀድሞ የኢትዮጵያ መንግስት (ደርግ)የመንግስት እርሻ ልማድ ድርጅት ስር እ.ኤ..አ በ1980 ዓ.ም. ሲሆን የተመሠረተበትም ዓላማ በመንግስት እርሻ ልማቶች የተመረቱ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ለገበያ ለማቅረብ ነበር። ከመንግስት ስርዓት ለውጥ (እ.ኤ..አ 1991 ዓም) በኋላ የሽግግሩ መንግስት በመንግስት የተያዙ ንብረቶችን ለግልና ለሕዝብ ለማስተላለፍ በወጣው አዋጅ መሠረት እ.ኤ.አ በ1993 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 131/1993 ኢትፍሩት የሕዝብ ድርጅት (public enterprise) ሆኖ ዕውቅናን አግኝቷል።
ምንጭ፦ ኢቢሲ እና ኢትፍሩት
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አፍሪካዊ የአመራር መጽሔት (African Leadership Magazine) በሚያዘጋጀው የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ምርጫ ላይ ለ2018 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ) የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ መሪ ለመባል ዕጩ ሆነው ተመርጠዋል።
መጽሔቱ የዓመቱ ምርጥ ሰው ብሎ የሚመርጠው በተለያዩ ዘርፎች ለአፍሪካ እና አፍሪካውያን የላቀ አስተዋጽዖ ያበረከቱ እና እጅግ ጉልህ የሆነ ተጽዕኖ የፈጠሩ አፍሪካውያንን በማወዳደር ሲሆን፥ መጽሔቱ መታተም ከጀመረበት እ.ኤ.አ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሽልማቱ ይሰጣል።
ዘንድሮ በእጩነት ከቀረቡት መካከል በወንድ መሪዎች ዘርፍ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በ97.25% ድምጽ በማግኘት ቀዳሚውን ቦታ ሲይዙ፣ የቀድሞው የቦትስዋና ፕሬዝደንት የሆኑት ሰረትሴ ካማ ኢያን ካማ (Serêtsê Khama Ian Khama) በ2.00% የምርጫ ድምጽ ሁለተኛ፣ የነዳጅ ላኪ ሀገራት ህብረት (Organization of the Petroleum Exporting Countries – OPEC) ጠቅላይ ሰብሳቢ የሆኑት ናይጀርያዊው መሐመድ ሳኑሲ ባርኪንዶ (Mohammed Sanusi Barkindo) በ0.75% የምርጫ ድምጽ በሦስተኝነት ይከተላሉ።
የአፍሪካዊ የአመራር መጽሔት ዋና አዘጋጅ ዶ/ር ኬን ጊያሚ (Dr. Ken Giami) እንደገለጸው የዘንድሮው ምርጫ ከሌሎች ጊዘያት በተለየ መልኩ ብዙ ሰዎች፣ ከሁሉም የ አፍሪካ አቅጣቻዎች ድምጽ የሰጡበት ሁሉም ዕጩዎች ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች አሸንፍው በተሠማሩባቸው መስኮች ሁሉ የሚጠበቅባቸውን በመወጣት ልቀው ሊታዩ ችለዋል ብሏል።
በሰባት የዕጩነት ቦታዎች (ስድስት ዘርፎች) በአጠቃላይ ሰላሳ (30) አፍሪካውያን ለዕጩኘት የቀረቡ ሲሆን፥ በሀገር ደረጃ በአጠቃላይ ናይጄርያ አስር (10) ዕጩዎችን በማስመረጠ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች። የሰላሳዎች ዕጩዎች ሀገራዊ ስብጥር፥ ቦትስዋና (2)፣ ኬፕ ቨርዴ (1)፣ ግብጽ (1)፣ ኢትዮጵያ (1)፣ ጋና (4)፣ ኬንያ (1)፣ ሞሮኮ (2)፣ ናይጄርያ (10)፣ ሴኔጋል (1)፣ ደቡብ አፍሪካ (5)፣ እስዋቲኒ/ስዋዚላንድ (1)፣ እና ታንዛንያ (1) መሆናቸው ታውቋል።
ከዕጩዎቹ መካከል አሸናፊዎቹን ለመለየት ማንኛውም ግለሰበ የመጽሔቱ ድረ-ገጽ ላይ ሄዶ መምረጥ (ድምጽ መስጠት) ይችላል። (ድረ-ገጹን እዚህ ጋር ያገኙታል)። በድረ-ገጽ ድምጽ የመስጠት ተግባር እ.ኤ.አ ታህሳስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በመካከለኛው አፍሪካ ሰዓት እኩለ ሌሊት (10th December 2018, at midnight Central African Time.) ላይ ይጠናቀቃል ይዘጋል።
አምና እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም. በተደረገው ተመሳሳይ ምርጫ የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ (Paul Kagame) የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ መሪ ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።
አፍሪካዊ የአመራር መጽሔት (African Leadership Magazine) መቀመጫነቱን በእንግሊዝ ሀገር፣ ፖርትስማውዝ ከተማ አድርጎ አፍሪካንና አፍሪካውያንን ከተቀረው ዓለም ጋር ለማገናኘት፣ ለማቀራረብ የሚሠራ የህትመት ድርጅት ነው። በየዓመቱም በተለያዩ ዘርፎች አፍሪካና አፍሪካውያን ላይ በተለያየ መልኩ ጉልህ ሚና የተጫወቱ አፍሪካውያንን “የዓመቱ ምርጥ አፍሪካውያን” ብሉ ይመርጣል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–የአፍሪካን እና የቻይናን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎ የሚጠበቀው የአፍሪካ-ቻይና የንግድ ትርዒት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ (አዲስ አበባ) ይካሄዳል።
የአፍሪካ-ቻይና የንግድ ትርዒት በመጪው ሳምንት ከኅዳር 24 እስከ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አግዚቢሽን ማዕከል “የቻይና-ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አቅም ትብብር ትርዒት” በሚል ርዕስ እንደሚደረግ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት (ECCSA)፣ የኢፌዴሪ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የቻይና ዓለም አቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክር ቤት (China International Exhibition Center – CIEC) በኅብረት በመሆን ያዘጋጁትን የአፍሪካ-ቻይና የንግድ ትርዒት በተመለከተ በጋራ ጋዜጣዊ መግለቻ የሰጡ ሲሆን፥ ትርዒቱ (Expo) የቻይና የንግድ ኩባንያዎችና በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሠማሩ አካላት በአፍሪካ ካሉ አቻዎቻቸው ጋር የሚኖራቸውን ትስስር ይበልጥ ያጠናክራል ተብሎ ይገመታል ብለዋል። የቻይናው ሲጂቲኤን አፍሪካ (CGTN Africa) እንደዘገበው በቁጥር 29 በሚሆኑ የተለያዩ ዓይነት የኢንዱስትሪ ዘርፎች (sectors) ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ትርዒቱ ላይ ይሳተፋሉ።
በመግለጫው ላይ እንደተጠቀሰው በቻይና በመሠረተ ልማት፣ በትራንስፖርት ሎጂስቲክስ፣ በጠቅላላ ንግድ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የመረጃ ግንኙነት (information communication) ቁሳቁስ፣ ከከባድ እስከ ቀላል የሆኑ የማሽነሪ መሣርያዎች፣ እንዲሁም በኃይል እና አካባቢ ጥበቃ ላይ ያታኮሩ ምርቶችን የሚያመርቱና የሚያቀርቡ ከአርባ በላይ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
◌ The 1st China–Africa Expo at Addis Ababa Exhibition Center, Ethiopia
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል ዓይናለም ዓባይነህ (ዶ/ር) እንደገለጹት ትርዒቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሔድ ቢሆንም ከአሁን በኋላ በየዓመቱ እንደሚከናወንና የተሳታፊዎችን ቁጥር በመጨመርና በዓይነት በማስፋት እያደገ እንደሚሔድ ገልጸዋል።
የቻይና ዓለም አቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክር ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሊኡ ዢያን (Liu Jian) በመግለጫቸው እንደተናገሩት፥ ትርዒቱን ስፖንሰር ያደረጉት የቻይና ዓለም አቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክር ቤት (China Council for the Promotion of International Trade)፣ ከቻይና አፍሪካ ልማት ፈንድ (China-Africa Development Fund) እና ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር ሲሆን፥ የትርዒቱ ዋነኛ ዓላማም በአፍሪካውያን እና በቻይናውያን የንግድ ማኅበረሰብና ግለሰቦች መካከል ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ነው ብለዋል።
ይህንን የአፍሪካ-ቻይና የንግድ ትርዒት በየዓመቱ በቋሚነት ለማከናወን የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የቻይና ዓለም አቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክር ቤት የመስማሚያ ሰነድ መፈራረምቸውም ተጠቁሟል። ሁለቱ ተቋማት በሁለቱ ሀገራት የሚገኙ የንግድና ኢንቨስትመንት ተቋማትን ለማገናኘት በሚረዳ መልኩ ከዚህ በፊት የቢዝነስ ፎረሞችን፣ ጉባዔያትን፣ ቢዝነስ-ቱ-ቢዝንስ ቁርኝቶችን (B2Bs) ማድረጋቸውንም የኢትዮጵያው ምክር ቤት አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ ተደርጋ መሾም የሀገሪቱን የምርጫ ሂደት ለማሻሻል የተገባውን ቃል ለማጠናክር እና ለ2012 ዓ.ም. ምርጫ ዝግጅት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድን ለማጠናከር ያለውን የፓለቲካ ቁርጠኝነት ምስክር ነው ብለዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ስብሰባው ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ በአራት ተቃውሞ፣ ሦስት ድምፅ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ ሾሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የዕጩዋን ሹመት ባቀረቡበት ወቅት መንግስት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን በአዲስ መልክ ለመተካት የወሰነው የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ዳር እንዲደርስ ለማድረግ የተጀመረው የጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የዲሞክራሲ መገለጫ የሆነው ምርጫ ቦርድ ተዓማኒና ገለልተኛ ለማድረግ ተቋሙን የማዘመንና ማሻሻል ከማድረግ በተጨማሪ ብቁ የሆነ መሪ እንደሚያስፈልገው በማመን ወ/ሪት ብርቱካን ለዕጩነት ቀርበዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።
ዶ/ር ዐብይ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርዶ ሰብሳቢ ተደርጋ መሾም የሀገሪቱን የምርጫ ሂደት ለማሻሻል የተገባውን ቃል ለማጠናክር እና ለ2012 ዓ.ም. ምርጫ ዝግጅት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድን ለማጠናከር ያለውን የፓለቲካ ቁርጠኝነት ምስክር ነው ብለዋል።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቅራቢነት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት የተከናወነው የቀድሞዋ ሰብሳቢ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ማን ናቸው ?
– በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው፣
– ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ስኩል ኦፍ ገቨርንመንት የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው፣
– በፌደራል ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ያገለገሉ፣
– የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ፣
– በውጪ ሀገር በናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዲሚክራሲ በተባለ ድርጅት ተመራማሪ ሆነው የሠሩ፣
– የፓርቲ አመራርና ተወዳዳሪ (ቅንጅት) ሆነው የሠሩ፣
– በምርጫ ሂደት ሰፊ ልምድ ያላቸው ናቸው።◌ Interview: Birtukan Mideksa, who shook Ethiopian court system, is back to Ethiopia from exile
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በአሁኑ ሰዐት የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑና ገለልተኛ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ይታወቃል።
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከቀድሞ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) ጋር በተያያዘ ለእስራትና ለእንግልት ከተዳረጉ በኋላ ከሀገር ወጥተው በሀገረ አሜሪካ ለሰባት ዓመታት በስደት የኖሩ ሲሆን፥ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ሁለንተናዊ ለውጥ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባቀረቡላቸው ጥሪ መሠረት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ይታወሳል።
PHOTO: Abebe Abebayehu