Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Viewing 15 results - 601 through 615 (of 730 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    ባህር ዳር (ኢዜአ)–ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በመውጣት በባህር ዳር ከተማ የተጠለሉ የአማራ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ለቀረቡላቸው አማራጮች ከመስማማት ይልቅ የጸጥታ ችግር እየፈጠሩ በመሆኑ ከተማውን ለቀው እንዲወጡ የከተማው ከንቲባ አሳሰቡ።

    የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተማሪዎች የከተማው ህዝብ ባደረገላቸው ድጋፍና እንክብካቤ ከታህሳስ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

    የከተማው ህዝብና ወጣቶች የመኝታ ፍራሽ፣ የምግብ አቅርቦትና አልባሳትን በመደገፍ ያልተቆጠበ ወገናዊ ድጋፍ ቢያደርግም ከጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ጀምሮ ከተጠለሉበት በመውጣት የከተማውን ጸጥታ እያወኩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    “በዛሬው ዕለትም ተመሳሳይ ሁከት በመፍጠር የቱሪዝም ከተማ የሆነችውንና በሰላማዊነቷ የምትታወቀውን የባህር ዳር ከተማ ሲረብሹና ጉዳት ሲያደርሱ ውለዋል” በማለት ጥር 7 ቀን ተናግረዋል።

    “ድንጋይ በመወርወር ጉዳት ማድረስ፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎችና ሌሎች የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲዘጉና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲስተጓጎልም አድርገዋል” ብለዋል።

    ችግሩ በመባባሱ የከተማው ሰላም እየታወከ በነዋሪዎችና በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት መቀጠል ስለሌለበት ከተማውን ለቀው ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረው የከተማው ወጣቶች ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር ላደረጉት የማረጋጋት ጥረትም ምስጋና አቅርበዋል።

    የከተማ አስተዳደሩ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘውዱ ዘለቀ በበኩላቸው “ተማሪዎቹ ከከተማው አልፈው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ፣ ፖሊና ሰላም ካምፓሶች በመግባት ረብሻ እንዲፈጠር አድርገዋል” ብለዋል።

    ከባህር ዳር ከተማ የሚወጣም ሆነ የሚገባ ስምንት በመኪና የተጫነ እህል በማራገፍ፣ ተሽከርካሪዎችን በመስበር፣ ቤቶችን በመደብደብ ከተማረ ሰው የማይጠበቅ ተግባር መፈጸማቸውንም አመልክተዋል።

    ተማሪዎቹ ጩቤ፣ የጭስ ቦንብ፣ የአደጋ መከላከያ ሄልሜትና ዱላ ጭምር በመያዝ አደጋ መፍጠራቸውን ጠቅሰው፤ የፀጥታ መዋቅሩ ከከተማው ሰላም ፈላጊ ወጣቶች ጋር በመተባበር ያለምንም ሰብዓዊ ጉዳት እንዲረጋጋ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን አስረድተዋል።

    “አሁን ላይ ለከተማዋ የሰላም መደፍረስ ምክንያት በመሆናቸው ከህዝቡ ጋር በመሆን የክልሉ መንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ ለመሸኘት ሥራ እየተሠራ ነው” ብለዋል።

    ተማሪዎችን ለማግባባትና መፍትሄ ለመስጠት በከፍተኛ አመራሩ ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም የቀረበላቸውን አማራጭ ባለመቀበል መግባባት ላይ መድረስ አለመቻሉን የገለፁት ደግሞ የክልሉ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ ናቸው።

    ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰው መደበኛ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ አለበለዚያ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም ባለመስማማት ጥር 7 ቀን በኃይል በመጠቀም በአካባቢው የከፋ ችግር ለመፍጠር መሞከራቸውን ጠቁመዋል።

    በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል በተፈጠረ ግጭት የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ችግራቸው እስኪፈታ በጊዜያዊነት በባህር ዳር ከተማ መጠለላቸው ይታወሳል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች


    Semonegna
    Keymaster

    የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ካስመረቃቸው መካከል 86ቱ የህክምና ዶክተሮች መሆናቸውንና፣ ቀሪዎቹ በጤና መኮንን፣ ክሊኒካል ነርሲንግ፣ ሚድዋይፈሪና በሜዲካል ላቦራቶሪ ሳይንስ መስክ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መሰልጠናቸው ተጠቁሟል።

    አሰላ (ሰሞነኛ) – የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በህክምና ዶክትሬት፣ በጤና መኮንንና ሌሎች የጤና ትምህርት መስኮች ለ4ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 388 የህክምና እና የጤና ተማሪዎች አስመረቀ።

    የህክምና ሙያ ምሩቃን መከላከል በሚቻል በሽታ (preventable diseases) መሞት እንዲበቃ ጠንክረው በመሥራት ጤንነቱ የተጠበቀ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሊረባረቡ እንደሚገባ የሣይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት አሳስበዋል።

    በጤና አገልግሎትና አጠባበቅ ረገድ በሚታየው ውስንነት መዳን በሚቻልባቸው በሽታዎች ሰዎች እንደሚሞቱና ታክሞ መከላከል በሚቻል ሁኔታም የአልጋ ቁራኛ እንደሚሆኑ ያብራሩት ዶ/ር ሂሩት፥ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥራው ዓለም የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ከማፍራት አንፃር ትኩረት የሚሹ ቀሪ ሥራዎችን ለመፈጸም መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በህክምና እና በነርስነት ይስተማራቸውን 220 ተማሪዎች አስመረቀ

    የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ኑዋማ ቢፋ ኮሌጁ ካስመረቃቸው መካከል 86ቱ የህክምና ዶክተሮች መሆናቸውንና፣ ቀሪዎቹ በጤና መኮንን፣ ክሊኒካል ነርሲንግ፣ ሚድዋይፈሪና በሜዲካል ላቦራቶሪ ሳይንስ መስክ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መሰልጠናቸውን ጠቁመዋል። በጤናው መስክ ሀገሪቱ ያለባትን የባለሙያ እጥረት ለማቃለል ዩኒቨርሲቲው ድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም ዶ/ር ኑዋማ አመልክተዋል።

    የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዱጉማ አዱኛ ተመራቂዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ከህይወት ተሞክሯቸው ጋር በማዋሃድ በተሰማሩበት መስክ ኃላፊነታውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

    ከተመራቂዎች መካከል በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ዶ/ር አዲሱ ነዲ በሰጠው አስተያየት፥ በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ መሠረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

    ከሴቶች ተማሪዎች በከፍተኛ ውጤት በማምጣት የተመረቀችው ዶ/ር አያንቱ ሆርዶፋ በበኩሏ በዩኒቨርሲቲው የቀሰመችውን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ለውጥ ለማምጣት እንደምትጥር ተናግራለች።

    የህክምና ትምህርት የተግባር ትምህርት እንደመሆኑ እርስ በእርስ የነበረ የመማማር ሂደት አሁን ለደረሰችበት ስኬት እንደረዳት ገልጻለች።

    ምንጭ፦ የሣይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    የአርሲ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ


    Semonegna
    Keymaster

    የጊዳቦ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት በ258 ሚሊዮን ብር በጀት የተጀመረ ቢሆንም ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ እና የዲዛይን ለውጥ በመደረጉ አጠቃላይ የግንባታ ወጭው 1.66 ቢሊዮን ብር መድረሱን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አስታውቀዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢ.ኮ.ሥ.ኮ) በውሃ መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ እየተገነባ የሚገኘው የጊዳቦ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት መቶ በመቶ መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

    የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልፈታህ ታጁ በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም. ፕሮጀክቱን ለጎበኙ በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ባለሙያዎች እንደገለጹት የጊዳቦ ዋና ግድብ ሥራ መቶ በመቶ ተጠናቆ በጥር ወር 2011 ዓ.ም እንደሚመረቅ ገልጸዋል።

    የጊዳቦ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት በ258 ሚሊዮን ብር በጀት የተጀመረ ቢሆንም ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ እና የዲዛይን ለውጥ በመደረጉ አጠቃላይ የግንባታ ወጭው 1.66 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል።

    በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በብዛት አክሲዮን በመግዛት እየተሳተፉበት ያለውና ግንባታው እይተፋጠነ ያለው ግዙፉ የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ማዕከል

    የግድቡን ዲዛይንና የቁጥጥር ሥራውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ ግንባታውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አከናውኖታል።

    የኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎችን በመስኖ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው የጊዳቦ ግድብ በአጠቃላይ 63.5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እና 13,425 ሔክታር መሬት ማልማት ያስችላል የተባለው ይህ የጊዳቦ መስኖ ልማት ግድብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ የዘገየው እና የፕሮጀክቱ የገንዘብ መጠኑ የጨመረው ውሉ ከተፈረመ ከሁለት ዓመታት በኋላ ግንባታው መጀመሩ፣ የዲዛይን ለውጥ መደረጉ፣ በአካባቢው የካሳ ክፍያ የሚጠይቁ ሥራዎች መኖራቸው፣ የባለድርሻ አካላት ችግር፣ በግንባታ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት ምክንያት ነው። ግድቡ የተጀመረው በ2002 ዓ.ም. ሲሆን፥ ሲጀመር ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው በ2004 ዓም ነብር።

    ግድቡ ሲጀመር ተይዞ የነበረው 16 ሜትር ከፍታ ሲሆን አሁን ላይ ወደ 22.5 ሜትር ከፍታ፣ 315 ሜትር ርዝመትና፣ 7.16 ኪ.ሎ ሜትር ርዝመት ያለው በግድቡ ግራ እና ቀኝ የዋና ቦይ ግንባታ ሥራዎችን መሠራቱ እና በአንድ ሺህ አምሳ ሄክታር መሬት ላይ ውሃ እንዳጠራቀመ (ሰው ሠራሽ ሀይቅ እንደሚኖረው) ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

    በአሁኑ ወቅት ግንባታው ሙሉ በሙሉ በመጠናቀቁ በሚቀጥለው በያዝነው ወር የፌዴራል፣ የደቡብ እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ይመረቃል ተብሎ መርሐ ግብር ተይዟል።

    ምንጭ፦ ኢ.ኮ.ሥ.ኮ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    የጊዳቦ ግድብ


    Semonegna
    Keymaster

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ከኢትዮጵያም አልፈው በአፍሪካ አህጉር ለረዥም ዓመታት በዲፕሎማትነት ያገለገሉ ግለሰብ ሲሆኑ፥ ለዚህም አገልግሎታቸው እ.ኤ.አ በኅዳር ወር 2015 የአፍሪካ ህብረት የክብር ሽልማት ሸልሟቸዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ለ52 ዓመታት በተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ኢትዮጵያን በመወከል በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ላባረከቱት አገልግሎት ከኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዕውቅና ተሰጣቸው።

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ የአገልግሎት የክብር እውቅናው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የተሰጣቸው ጥር 07 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው።

    ይህ ሽልማት አምባሳደሯ ለረጅም ዓመታት በተለያዩ የዓለም ሀገራት፣ በአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ ተወካይና ዲፕሎማት በመሆን ላበረከቱት ስኬታማ አገልግሎት እንደተበረከተላቸው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ዘግቧል።

    አምባሳደር ቆንጂት በግብፅ ፣ በእስራኤል፣ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ሀገራቸውን በዲፕሎማትነት በመወከል ውጤታማ ስራ ማስመዝገባቸው ተገልጿል።

    አምባሳደሯ ከምንም በላይ ሀገራቸውን በማስቀደም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያበረከቱት አስተዋጽዖም ለሌሎቸ ዲፕሎማቶች አርዓያ የሚሆን ነው ተብሏል።

    ለአምባሳደሯ የተሰጣቸውን የክብር እውቅና ተገቢ እንደሆነ በመደገፍ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዲህ ብለው ጽፈዋል

    እህቴ፣ ባልንጀራዬ ክብርት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ረዥሙን የአገልግሎት ዘመን የያዙ ዲፕሎማት በዛሬው ዕለት ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የሚገባቸውን ሽልማትና እውቅና በማግኘታቸው እንኳን ደስ አላቸው! ደስ አለን! አገርን በጨዋነት፣ በታማኝነት፣ በታታሪነት የማገልገል ዋጋ ነው። ለሁሉም በተለይ በዛሬ ጊዜ ትልቅ ትምህርት ልንወስድበት ይገባል።

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ለተደረገላቸው እውቅና ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፥ በቅርቡ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በሀገሪቱ ትልልቅ ቦታዎች ላይ ሴቶች ሹመት እንዲያገኙ መደረጉንም አድንቀዋል።

    በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን በመወከል የሚሠሩ ዲፕሎምቶችና አምባሳደሮችም ለሀገራቸው ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ የተወለዱት በሐረር ከተማ እ.ኤ.አ. በ1940 ሲሆን፥ በእንግሊዝ ሀገር ለንደን ከተማ ከሚገኘው ለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እ.ኤ.አ በ1954 ዓለም አቀፍ ግንኙነት (International Relations) በዲግሪ ተመርቀዋል። እ.ኤ.አ በ1963 ኒው ዮርክ ከተማ፣ አሜሪካ ከሚገኘው የኮለምብያ ዩኒቨርሲቲ የካርኒጌ ፌሎውሺፕ (Carnegie Fellowship) አግኝተዋል። ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀጥረው መሥራት የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1962፥ ይህም የአፍሪካ አንድነ ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) ከመቋቋሙ ከአንድ ዓመት በፊት ነው።

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ከኢትዮጵያም አልፈው በአፍሪካ አህጉር ለረዥም ዓመታት በዲፕሎማትነት ያገለገሉ ግለሰብ ሲሆኑ፥ ለዚህም አገልግሎታቸው እ.ኤ.አ በኅዳር ወር 2015 የአፍሪካ ህብረት የክብር እውቅና ሰጥቷቸዋል

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአምባሳደር ቆንጂት በተጨማሪም በተለያዩ ሀገራት በአምባሳደርነት ሲሠሩ ቆይተው በጡረታ ለተሰናበቱ ቀደምት ዲፕሎማቶች የዕውቅና ምስክር ወረቀት ሰጥቷል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ


    Semonegna
    Keymaster

    ኬር ኢትዮጵያ ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያስረከበው ይህ የምርምርና የስልጠና ማዕከል በምሥራቅ ኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማጎጎልበት ከአርሶና አርብቶ አደሮች ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥረት ተጨማሪ አቅም ይፈጥርለታል ተብሎ ይጠበቃል።

    ሐረር (ኢዜአ) – ኬር ኢትዮጵያ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ኩርፋ ጨሌ ወረዳ በ7 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጭ ያስገነባውንና የእንስሳት ምርምርና የአርሶ አደሮች ማስልጠኛ ማዕከል ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ።

    በኬር ኢትዮጵያ የምሥራቅ ሐረርጌ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቶ ሆሳዕና ኃይለማርያም በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ማዕከሉ ለእንስሳት እርባታ፣ ድለባና የዝናብ እጥረት ተቋቁመው ምርት የሚሰጡ የአዝዕርት ሰብሎች ላይ ምርምር ያካሂድበታል።

    ማዕከሉ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ አካባቢዎች የሚያከናውናቸውን የምርምር ሥራዎች እንደሚያጠናከርለትም አመልክተዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጣቢያዎች ዳይሬክተር አቶ አድምቀው ኃይሉ በበኩላቸው ማዕከሉ በምሥራቅ ኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማጎጎልበት ከአርሶና አርብቶ አደሮች ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥረት ተጨማሪ አቅም ይፈጥርለታል ብለዋል። በዚህም የሚገኙ የገበሬዎች ማሰልጠኛ ተቋማትን በመጠቀም ለአርብቶና አርሶ አደሮች በእንስሳት አመጋገብ፣ አያያዝ፣ ርባታና ድለባ ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል። የእንስሳት ጤና ተማሪዎችንና ባለሙያዎችን በመጠቀም የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

    በአማራ ክልል ለገበሬዎች እፎይታን የሰጠ የስንዴ ምርትን መሰብሰቢያ ማሽን (ኮንባይነር)

    የኩርፋጨሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አልዪ ጠለሀ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማኅበረሰብና አርሶ አደሩን በምርጥ ዘር ስርጭትና በሌሎች የማህበረሰብ አገልግሎት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

    ማዕከሉ ኩርፋ ጨሌን ጨምሮ የሦስት ወረዳዎች አርሶና አርብቶ አደሮች በምርምር የሚያገኟቸውን የእንስሳትም ሆነ የሰብል ዝርያዎችን እንዲጠቀምና የቴክኖሎጂ ተጋሪ እንዲሆን ያደርጉታል ብለዋል።

    የኩርፋ ጨሌ ወረዳ ሁላጀነታ ቀበሌ ነዋሪዋ ከፊል አርሶ አደር መፍቱሃ አብዱላሂ ዩኒቨርሲቲው ምርጥ የድንችና የሰብል ዝርያዎችን በማሰራጨት ምርታቸውን እንዳሳደገላቸው ተናግረዋል።

    “በአሁኑ ወቅት የድለባ ከብት ተሰጥቶኝ የማድለብ ሥራ ጀምሬያለሁ” ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፣በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የሰብል በሽታን ለመከላከል ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

    የዚሁ ቀበሌ ሌላዋ ነዋሪ ወይዘሮ ፋጡማ አህመድ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ማዕከሉን መረከቡ ሥራቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማከናውንና ስልጠና ለማግኘት ያስችለኛል ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ኬር ኢትዮጵያ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ


    Semonegna
    Keymaster

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥር 6 ቀን ለኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በሰጡት ገለጻ አስካሁን ባለው ሂደት ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች በቀረበላቸው ሀገራዊ ጥሪ አማካኝነት በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በኩል 1 ነጥበ 9 ሚሊዮን ዶላር አዋጥተዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. አስታወቁ። እስካሁን ባለው ሂደት በትረስት ፈንዱ አማካኝነት 12 ሺህ 9 መቶ ዳያስፖራዎች መዋጮ አድርገዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የ2011 ዓ.ም. አገራዊ በጀትን በአስጸደቁበት ወቅት ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ ሁሉ በአገሩ ልማት ላይ እንዲሳተፍ በቀን የ1 ዶላር መዋጮ መጠየቃቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዳያስፖራው ለጠቅላይ ሚነስትሩ የሰጠው ምላሽ አጥጋቢ እንዳልሆነ ሲነገር ቆይቷል።

    Commercial Bank of Ethiopia to start diaspora mortgage loan to ease Ethiopians’ home ownership

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥር 6 ቀን ለኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በሰጡት ገለጻ አስካሁን ባለው ሂደት ዳያስፖራው በቀረበለት ፈንድ አማካኝነት 1 ነጥበ 9 ሚሊዮን ዶላር አዋጥቷል።

    በመዋጮውም 12 ሺህ 900 ዳያስፖራዎች እንደተሳተፉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከዚህም ውስጥ 10 ሺህ 300 የሚሆኑት በአሜሪካ የሚኖሩ ናቸው። 1ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላሩ ከእነዚህ በአሜሪካ ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች መሰብሰቡን አክለዋል።

    በአሜሪካ ካሉ ግዛቶች መካከል ሜሪላንድና ካሊፎርኒያ እንደቅደም ተከተል ከፍተኛ መዋጮ የተገኘባቸው አካባቢዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

    በዓለም ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎች ቢኖሩም መዋጮው እምብዛም ያልሆነበት ምክንያት መተማመኑ ባለመፈጠሩ መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትሩ አስገንዝበዋል።

    The case of Ethiopian diaspora, their interest to invest in Ethiopia and bureaucratic bottlenecks

    የሚዋጣውን ነገር በሚታይ ነገር ላይ በማዋል መተማመንን ለመፍጠር እንደሚሠራ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፈንዱ የተሰበሰበው ገንዘብ ግን 10 ሚሊዮን ዶላር አስኪደርስ ጥቅም ላይ እንደማይውል ገልጸዋል።

    ይህ የሚሆነውም በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መካካል ፍትሃዊ ክፍፍልን ለመፍጠር መሆኑንም ጠቁመዋል።

    የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ትርስት ፈንድ የተቋቋመው በነሀሴ ወር 2011 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና ሰብሳቢነት ሲሆን፥ በዋነኝነት በተለያዩ የአርሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ 15 ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በአማካሪ ካንስል አባልነት ያቀፈ ቡድን በበላይነት ይከታተለዋል።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ድረ-ገጽ: EDTF

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ዳያስፖራ ትርስት ፈንድ


    Semonegna
    Keymaster

    ቤልካሽ ኢትዮጵያ የሚያስጀምራቸው ሄሎማርኬት እና ሄሎሾፕ የተሰኙ ሁለት የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ገፆች በኢትዮጵያ ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚገኙ ተገልጋዮች ኢንተርኔት አማካኝነት ግብይት መፈም የሚችሉባቸው ናቸው።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ቤልካሽ ኢትዮጵያ ተጠቃሚዎች በበይነመረብ (ኢንተርኔት) አማካኝነት ግብይት መፈም የሚችሉባቸው ሁለት የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ገፆችን በቅርቡ እንደሚያስጀምር አስታወቀ።

    ሄሎማርኬት (Hellomarket) የተሰኘው ገፅ በዋነኛነት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ተገልጋዮቹ ብቻ ካሉበት ቦታ ሆነው ቁሳቁሶችን የሚሸምቱበት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በበይነመረብ አማካኝነት የግዥ ትዕዛዝ እና ክፍያ የተፈፀመባቸው ቁሳቁሶቹን ወደ ደምበኞች ለማጓጓዝም ከ ዓለምአቀፉ ዲኤችኤል (DHL) ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

    The dispute between RIDE Taxi, Ethiopian-kind of Uber, and Addis Ababa Transport Authority continues

    ተቋሙ በመጀመርያው ምዕራፍ ወደ 2,500 የሚጠጉ ሴት ኢትዮጵያውያን በባለቤትነት በሚያስተዳድሩዋቸው የተለያዩ ድርጅቶች የተመረቱ ምርቶችን ለማሻሻጥ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል።

    በተመሳሰይ ቤልካሽ ከኢትዮጵያ ውጭ ሆነው የኤሌክትሮኒክ ግብይት መፈፀም ለሚፈልጉ ደንበኞቹ አገልግሎት የሚሰጥ ሄሎሾፕ (Helloshop) የተሰኘ ሌላ ገፅ ያዘጋጀ ሲሆን የክፍያ ስርዓቱም በማስተር ካርድ አማካኝነት አንደሚከወን ለማወቅ ተችሏል።

    Ethiopia – blueMoon Incubator and Addis Garage co-working space for startups in Ethiopia

    ቤልካሽ ኢትዮጵያ መቀመጫውን ኔዘርላንድ ባደረገው እና ቤልካሽ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን (Belcash Technology Solutions) የተሰኘ በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ የተሰማራ ድርጅት እህት ኩባንያ ሲሆን እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ በኢትዮጵያ በተለይም በሞባይል ክፍያ እና የገንዘብ ማስተላለፍ ዘርፎች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ከኩባንያው ድረገፅ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

    የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓት በተገቢው አለመስፋፋት እና በዚህ ዘርፍ ላይ ግልፅ የሆኑ ፖሊሲዎችን አለመኖራቸው በኢትዮጵያ መሰል የኤሌክተሮኒክ ግብይት ተቋማት እንዳይስፋፉ እንቅፋት መሆኑን ባለሞያተኞች ይገልፃሉ።

    ከዚህ ዜና ጋር በተመሳሳይ የቻይናው ግዙፉ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ (e-commerce) አሊባባ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለውና ከኢትዮጵያ ባላስልጣናት ጋር (የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ) መወያየቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቦ ነበር

    ምንጭ፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ / አዲስ ፎርቹን
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ቤልካሽ ኢትዮጵያ


    Semonegna
    Keymaster

    እንደ ፕሮፈሰር ጣሰው ወልደሃና ገለጻ፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ስድስት ወራት በተጽዕኖ የሚካሄዱ የፖለቲካ አሠራሮችን በማጽዳትና የፖለቲካ ሃሳቦችን በነጻ የሚያራምዱበት የጋራ መድረክ በማዘጋጀት የተሻለ ሰላም ማምጣት ችሏል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከፖለቲካ ተጽዕኖ በማላቀቅ በሰላም አብሮ የመኖር ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፈሰር ጣሰው ወልደሃና ተናገሩ።

    ዩኒቨርሲቲው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ”ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሰላም” በሚል ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. መክረዋል።

    ፕሮፌሰር ጣሰው በዚሁ ወቅት፥ የሰላማዊ አብሮ የመኖር ባህልን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማሳደግ ተማሪዎችን ከፖለቲካ እንቅስቃሴና ፉክክር ነጻ ማድረግ ይገባል። ባለፉት ዓመታት ሰላም ላይ ትኩረት ተደርጎ ባለመሠራቱ ተማሪዎች በዘር የመከፋፈልና እርስ በእርስ ያለመታማመን ችግሮች አጋጥሟቸዋል። ይህም በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭትና ሁከትን በመቀስቀስ የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ያመጣው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

    ተማሪዎችና መምህራን በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያደርጉት ፉክክርና አንዳንድ ድርጅቶችም የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን ያለገደብ በተቋማቱ ማራመዳቸው የተማሪዎችን አብሮነት እንደሸረሸረውም ነው ፕሮፌሰሩ ያብራሩት። የዩኒቨርሲቲዎች ዋነኛ ተግባር ማስተማርና መመራመር መሆኑን አጽንዖት ሊሰጡት እንደሚገባም አመልክተዋል።

    ትውልድን በመቅረጽ፣ አገርን በመገንባት በኩል መምህራን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ― ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

    እንደ ፕሮፈሰሩ ገለጻ፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ስድስት ወራት በተጽዕኖ የሚካሄዱ የፖለቲካ አሠራሮችን በማጽዳትና የፖለቲካ ሃሳቦችን በነጻ የሚያራምዱበት የጋራ መድረክ በማዘጋጀት የተሻለ ሰላም ማምጣት ችሏል።

    ዩኒቨርሲቲው በሰላም ዙሪያ የሚመራመርና ሃሰቦችን የሚያፈልቅ አስር አባላት ያሉት ቡድን አዋቅሮ በተቋሙ ቀጣይነተ ያለው ሰላም ለማምጣት እየሠራ ነውም ብለዋል – ፕሮፌሰር ጣሰው። ለቡድኑም አንድ ሚሊዮን ብር ዩኒቨርሲቲው መመደቡን አስታውቀዋል።
    ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ይህንን ተሞክሮ በማስፋት ለአገር ሰላምና ለአብሮነት የሚያደርጉትን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸውም ተመላክቷል።

    በመድረኩ “ሰላምና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት” በሚል ጽሁፍ ያቀረቡት በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ በበኩላቸው ሰላምን ለማስፈን ተቋማቱን ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል።

    በተለይ በተቋማቱ የሰላም እጦት መንግስትና ምሁራን በሰላም ላይ ያልተገበሯቸው በርካታ ተግባራት ለመኖራቸው ዋቢ ነው ብለዋል – ፕሮፈሰሩ።

    በቀጣይም ኢትዮጵያዊ አብሮነትን ያካተተ መርሃ ግብር በመቅረጽ፤ በጎሳና በዘር የተከፋፈለውን የምደባ ስርዓት በመከለስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፌዴራል ተቋማት መሆናቸውን ማጉላትና የተማሪዎች ህብረትን ከፖለቲካ የጸዱ ማድረግ ይገባል ብለዋል። አክለውም ምሁራን የግጭት አራጋቢዎች ከመሆንና የሥራ መርሃ ግብራቸውን በአግባቡ ካለመወጣት ተቆጥበው ትውልድ የመቅረጽ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

    የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን እንዳሉት ምሁራን ለሀገሩ ቀና የሆነ ዜጋንና ስለአገሩ ሰላምና ዲሞክራሲ የሚተጋ ዜጋን የማፍራት ኃላፊነት እንዳለባቸው በመጥቀስ፥ በተለይ ምሁራን አገሪቷ አሁን ከገጠማት የሰላም እጦት ለመውጣት ሙያዊና የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

    ለአንድ ቀን ብቻ በተደረገው የምከክር መድረኩ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወከሉ መምህራን፣ የተማሪዎች መማክርት፣ የሰላም መልዕክተኞችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ጣሰው ወልደሃና


    Semonegna
    Keymaster

    አል ማክቱም ፋውንዴሽን በየካ ክፍለ ከተማ ካስገነባው ትምህርት ቤት በተጨማሪ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማም በተመሳሳይ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ የሆኑ ተማሪዎች የሚማሩበት ትምህርት ቤት አስገንብቷል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ተቀማጭነቱን በዱባይ ከተማ ያደረገው አል ማክቱም ፋውንዴሽን የተባለ የተባበሩት አረብ ኤምሬት ግብረ ሰናይ ድርጅት በአርባ ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው ትምህርት ቤት ታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመርቋል። ግብረ ሰናይ ድርጅቱ እስከ አሁን በኢትዮጵያ አራት ትምህርት ቤቶችን ማስገንባቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።

    ትምህርት ቤቱ በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አያት አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ ሲሆን የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ የሆኑ ተማሪዎች የሚማሩበት ነው።

    የትምህር ቤቱ የግንባታና የቁሳቁስ ወጪ በግብረ ሰናይ ድርጅቱ የተሸፈነ ሲሆን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የአስተማሪዎችን ሙሉ የደመወዝ ክፍያም በድርጅቱ የሚሸፈን ይሆናል።

    ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ለሚያመጡ ተማሪዎችም ሱዳን በሚገኘው ‘ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አፍሪካ’ በተሰኘው ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት የነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ታቦር ገብረመድህን በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል።

    በተጨማሪም ለመምህራን የትምህርት ዕድል ለመስጠትና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር የመምህራን የልምድ ልውውጥ ለማድረግ መታቀዱንም ጠቁመዋል። የትምህርት ቤቱን የቅበላ አቅም ለማሳደግ የማስፋፊያ ሥራ ለመሥራት ዝግጅት መጠናቀቁንም ዶ/ር ታቦር ተናገረዋል።

    የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ከድር ጃርሶ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ የአፍ መፍቻቸው አፋን ኦሮሞ ለሆኑ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆች የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል። እንዲሁም ትምህርት ቤቱ በአካባቢው መከፈቱ ለበርካታ ሥራ አጥ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።

    የአል ማክቱም ፋውንዴሽን የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ አብዱልሸኩር መንዛ እንዳሉት ግብረ ሰናይ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በማጠናከር በሌሎች ዘርፎች ለመሥራትም ዕቅድ አለው።

    ግብረ ሰናይ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ መጠናከር የአገሪቱ መንግስት ላደረገው ቀና ትብብርም አቶ አብዱልሸኩር አመስግነዋል።

    አል ማክቱም ፋውንዴሽን በየካ ክፍለ ከተማ ካስገነባው ትምህርት ቤት በተጨማሪ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማም በተመሳሳይ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ የሆኑ ተማሪዎች የሚማሩበት ትምህርት ቤት አስገንብቷል።

    በሁለቱም ክፍለ ከተሞች የተገነቡት ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ስር እንዲተዳደሩ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አስረክቧል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አል ማክቱም ፋውንዴሽን


    Semonegna
    Keymaster

    በአስር ሺህ ካሬ ሜትር ላይ በ58 ሚሊዮን ብር ወጪ በአዳማ ከተማ የተገነባዉ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል 10 ሺህ ኪሎ ግራም በሰዓት የማቃጠል አቅም ያለው ሲሆን፥ በሌሎች 7 ከተሞችም 500 ኪሎ ግራም በሰዓት ማቃጠል የሚችሉ ማዕከላትም በመገንባት ላይ ይገኛሉ።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በ100 ቀናት ዕቅድ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን እና የህክምና ግብአቶችን ማስወገጃ ማዕከል ገንብቶ አስመረቀ።

    በአስር ሺህ ካሬ ሜትር ላይ በ58 ሚሊዮን ብር ወጪ በአዳማ ከተማ የተገነባዉ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል (incinerator) ምረቃ ሥነ ስርዓትላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን እንደተናገሩት፥ ማዕከሉ 10 ሺህ ኪሎ ግራም በሰዓት የማቃጠል አቅም ያለው ሲሆን፥ በሌሎች 7 ከተሞችም 500 ኪሎ ግራም በሰዓት ማቃጠል የሚችሉ ማዕከላትም በመገንባት ላይ ይገኛሉ ብለዋል። በቅርቡም ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምሩ ዶ/ር አሚር አክለው ተናግረዋል።

    ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች እና ግብዓቶች ማስወገጃ ማዕከሉ ለሀገራችን የመጀመሪያ ሲሆን ከዚሀ ቀደም በየተቋሟቱ በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ የማይውሉ ወይም የተበላሹ መድኃኒቶችን በማስወገድ ረገድ ይገጥሙ የነበሩ ችግሮችን ከመሠረቱ እንደሚፈታ የገለጹት ሚኒስትሩ፥ የምለሳ ሎጂስቲክ (recycle logistic) ስርዓትን በመተግበር የማያገለግሉ የህክምና ግብአቶች እና በባኅሪያቸው ጎጂ የሆኑ ኬሚካሎችን በዘመናዊ መንገድ አካባቢን በማይበክል ሁኔታ በማስወገድ ከዚህ ቀደም አካባቢ የሚበከልበትን ሁኔታ እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

    የኢትዮ-አሜሪካውያን ዶክተሮች ቡድን እያስገነባ ያለው ዓለም አቀፍ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው ሆስፒታል

    ለዚህ ሥራ መሳካት ተባባሪ የሆኑ ያካባቢው ማኅበረሰብ አባላትና የአዳማ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤትን ያመሰገኑት ሚኒስትሩ፥ ማዕከሉ ለአካባቢ ነዋሪዎች ቅድሚያ ተጠቃሚ የሚያደረግ ስልጠናና የሥራ ዕድል በኤጀንሲው እንዲመቻችላቸውም ተናግረዋል።

    የኢትዮጵያ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬከተር ዶ/ር ሎኮ አብርሀም በበኩላቸው የአዳማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በሌላው ዓለም የሚተገበሩ ዘመናዊ አሠራሮችን በመቀመር የመድኃኒት እና የህክምና መገልገያ አቅርቦት እና ስርጭት የልህቀት ማዕከል ሆኖ ለሌሎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መማማሪያ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ተናግረው ለአካባቢው፥ ማኅበረሰብም የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሆነ እና በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    መድኃኒቶችን ማስወገጃ


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲው የበላይ ኃላፊ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይና ከጣልያን የባህል ማዕከላትና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው ልዩ ልዩ እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል።

    በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ረዳት ዳይሬክተር መ/ር ተመስገን ዮሐንስ ሙሉ ፕሮግራሙን የመሩት ሲሆን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ካፈራቸው ምሁራን አንዱ ናቸው።

    በመርሐ ግብሩ መሠረት የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በይፋ መጀመሩን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው የበላይ ኃላፊ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሲሆኑ በመግቢያ ንግግራቸው ላይ ኮሌጁ በመማር ማስተማሩ ሂደት ዛሬ ላይ ለመድረስ የነበሩትን ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለዩኒቨርሲቲ ደረጃ መድረሱ እግዚአብሔርን ካመሰገኑ በኋላ ዩኒቨርሲቲው አሁን የደረሰበትን ደረጃ እንዲደርስ ሌት ተቀን የሠሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን፣ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳት፣ የቦርድ የሥራ አመራር አባላትና የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

    ከብፁዕነታቸው በመቀጠል ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር ኃይሉ ሀብቱ ናቸው።ተባባሪ ፕሮፌሰ ርኃይሉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚገኙ አምስት ኮሌጆችና ት/ቤቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ገልፀው፥ ትምህርት ቤቱ ከጥቅምት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በማስተርስ ኦፍ አርትስ (M.A.) ዲግሪ ደረጃ የድኅረ ምረቃ ትምህርት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል። ፕሮግራሙን ለማጠናቀቅ የሚወስደው ጊዜ ሁለት ዓመት መሆኑንና የአንደኛው ዓመት መርሐ ግብር ለተማሪዎች፦ (1) በኢትዮጵያ ታሪክ፣ (2) በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ (3) በብሔረሰቦች ወግና ሥርዓት ሰፊጥናትና ጥልቅ ግንዛቤ የሚሰጥ ሲሆን በሁለተኛው መርሃ ግብርም፦ (1) በትውፊታዊ ሥነ መድኃኒት/ ሥነ ፈውስ፣ (2) በትውፊታዊ ሥርዓተ ሕግ፣ (3) በኢትዮጵያ ጥናት አውራ ርዕሰ ጉዳዮች የሚያተኩሩ እንደሆኑ አብራርተዋል። የማስተማሪያ መደበኛ ቋንቋ እንግሊዝኛ ቢሆንም አገርኛ ቋንቋዎች ግዕዝን ጨምሮ እንደ አማራጭ ማስተማሪያ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

    የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ነፃነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ለአብነት ያህል በ17ኛው እና 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ እንደነ ወለተ ጴጥሮስ፣ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ማካኤልን የመሳሰሉ አባቶችና እናቶች ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ሰማዕት ሆነዋል ብለዋል።

    ከዚህ በመቀጠል የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባል የሆኑት ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ ንግግር አድርገዋል። ከተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊያ ልሆኑ የትምህርት ተቅዋማትና ድርጅቶች የመጡትን እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ከልብ አመስግነዋል። በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

    በመቀጠልም በፕሮግራሙ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የተገኙ እንግዶች ለዩኒቨርሲቲው ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳቦችና አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን ከቅድስት በዓታ ለማርያም ቤተክርስቲያን የመጡ መምህር በዓሉን የሚገልጽ ቅኔ አቅርበዋል።

    በመጨረሻም በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት በብራና መጻሕፍት ዝግጅት ክፍል የሚዘጋጁትን የተለያዩ የብራና መጻሕፍት፣ ቀለምና የብራና መሣሪያዎችን በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ እንግዶች ጐብኝተዋል።

    የቀድሞ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በ1935 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ካህናትንና የቤተክርስቲያን ሊቃውንትን ዘመናዊውንና የአብነት ትምህርታቸውን አስተባብረው እንዲይዙ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ እንደተጀመረ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ኮሌጁ በዚህ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፥ በመቀጠልም በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማዕረግ በማስተማር ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ዕጩዎችን ሲያበቃ ቆይቷል። የኮሌጅን ደረጃ በ1960 ዓ.ም. ካገኘ በኋላ ከሦስት ዓመት በኋላ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቲኦሎጂ ፋኩልቲ አካል ሆኖ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ዘልቋል። የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ፋኩልቲው ሲዘጋ በወቅቱ በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩት በሚፈልጉት የትምህርት መስክ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተዛውረው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ መደረጉ ይታወሳል። መንፈሳዊ ኮሌጁ ተወርሶ አራት ኪሎ ከጎኑ የሚገኘው የሳይንስ ፋኩልቲ ለራሱ የትምህርት መርሐ ግብር እንዲጠቀምበት ተደረገ። በ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ኮሌጁ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተመልሶ በነበረው ዕውቅናና ደረጃ የመማር ማስተማሩን ሒደት ሲያከናውን ቆይቷል። ኮሌጁ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ከፍተኛ የሆኑ የልማት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።

    መንፈሳዊ ኮሌጁ እስከ አሁን ድረስ ከ3,500 በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን ከዚሁ በበለጠ መልኩ እንዲጠናከርና የቤተክርስቲያኒቱ የጥናትና የምርምር ተቅዋም እንዲሆን መሉ ዝግጁቱን አጠናቅቆ በመጨረሱ በአሁኑ ሰዓት በቲዮሎጂ (ስነ መለኮት) የትምህርት ዘርፍ በዶክትሬት፣ በማስተርስ ዲግሪ፤ በመደበኛ የመጀመሪያ ዲግሪ፤ በማታው ተከታታይ እና በርቀት ትምህርት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዲግሪ፤ ዲፕሎማ፤ በግእዝቋንቋ (extension) ዲግሪና ዲፕሎማ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።

    ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ፈቃድ ወደ ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ እንዲያድግ ተደርጓል። በዚሁም መሠረት ከኅዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ እንዲጠራ መወሰኑ ይታወሳል።

    ምንጭ፦ ዩኒቨርሲቲው / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ


    Semonegna
    Keymaster

    ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ አዲስ ያወጣው “ሲያምሽ ያመኛል” የተሰኘው የሙዚቃ አልበም አስራ አንድ ዓመታትን እንደፈጀ፤ በግጥም፣ በዜማ እና በቅንብር ከአስራ ሦስት ባለሙያዎች በላይ እንደተሣተፉበት እና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ፈሰስ እንደተደረገበት ተዘግቧል።

    አዲሰ አበባ (ሰሞነኛ) – በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የተወዳጁ ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ አምስተኛ ሙሉ የአልበም ሥራው የሆነውና “ሲያምሽ ያመኛል” የተሰኘው የሙዚቃ አልበም ታህሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በመላው ዓለም በገበያ ላይ ውሏል።

    አራተኛ አልበሙን “ሳታመሃኝ ብላ” በሚል ርዕስ ካወጣ ከ11 ዓመታት በኋላ ለአድናቂዎቹ ያቀረበው ይህ አዲስ አልበም፥ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት አከፋፋዩ “ሪቮ ኮሚዩኒኬሽንና ኢቨንት” መግለጹን ሳምንታዊ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል።

    በኢትዮጵያ ሙዚቃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉትትና የላቀ እውቅናን ከተጎናጸፉት ድምፃዊያን አንዱ የሆነው የድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ አዲስ አልበም፣ ለረጅም ጊዜ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየ ሲሆን፥ ደረጃውን የጠበቀና የተዋጣለት አልበም ለማድረግ ሲባል 11 ዓመታትን መፍጀቱንና ግጥምና ዜማቸው ተሠርተው ከተጠናቀቁ ከ40 በላይ ሥራዎች ውስጥ 15ቱ ተመርጠው በዚህ አልበም መካተታቸውን አከፋፋዩ ጨምሮ ገልጿል።

    አማርኛ ሙዚቃ፦ ድምጻዊ እሱባለው ይታየው — ዘፈን ማሞቂያ አይደለም

    በዚህ አዲስ አልበም ላይ ከተሳተፉ እውቅ የሙዚቃ አቀናባሪዎች መካከል አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ፣ ካሙዙ ካሳአቤል ጳውሎስ፣ መኮንን ለማ (ዶክተሬ)፣ ሚካኤል ኃይሉ (ሚኪ ጃኖ) እና ሱልጣን ኑሪ (ሶፊ) እንደሚገኙበት የገለፀው አከፋፋዩ፥ በግጥምና ዜማውም ከዚህ ቀደም በሠሩት ሥራ አንቱታን ያተረፉት አለምፀሐይ ወዳጆ፣ ይልማ ገ/አብ፣ ሀብታሙ ቦጋለ፣ ቢኒያም መስፍን (ቢኒባና)፣ አለማየሁ ደመቀ፣ መሰለ ጌታሁን እና ራሱ ጎሳዬ ተስፋዬ ተሳትፈውበታል ተብሏል።

    በአገራዊ፣ በማኅበራዊ እና በፍቅር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 15 ሙዚቃዎችን ያካተተው “ሲያምሽ ያመኛል” አልበም ሪከርድ የተደረገው በአሜሪካ ኒው ዮርክ ሲቲ ሲሆን ጥራትና ደረጃውን የጠበቀና ዘመኑ ያፈራው የሪከርዲንግ ቴክኖሎጂ አሻራ ያረፈበት መሆኑም ታውቋል።

    ጎሳዬ ተስፋዬ ከዚህ ቀደም “ሶፊ”፣ ከሌሎች ድምፃዊያን ጋር “ቴክ ፋይቭ”፣ ከአለማየሁ ሂርጶ ጋር “ኢቫንጋዲ” እና በ1999 ዓ.ም ለብቻው የሠራውን “ሳታመሃኝ ብላ” የተሰኙ የሙዚቃ አልበሞችን ለአድናቂዎቹ ማቅረቡ ይታወሳል።

    ◌ ሲያምሽ ያመኛል አልበምን በዲጂታል ለመግዛት: CD Baby Siyamish Yamegnal by Gossaye Tesfaye

    ምንጭ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ጎሳዬ ተስፋዬ

    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በቅርቡ ሥራውን በይፋ የሚጀምርበት በዳያስፖራው ማህበረሰብ እና በባለድርሻ አካላት ዘንድ ተልዕኮው በግልፅ ታዉቆ በጋራ እና በቅንጅት ሥራው እንደሚሰራ መገለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመልክታል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አገራዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥና መብታቸውን ለማስከበር በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ሥራ ለመጀመር የመዋቅርና የሕግ ማዕቀፍ ሥራን ማጠናቀቁን አስታወቀ።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት እና ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ ታህሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ለአገር ውስጥ እና ለዉጭ አገር መገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የመዋቅርና የሕግ ማዕቀፍ ሥራን ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ የኤጀንሲው ወደ ሥራ መግባት ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ብርቱ ተዋናይ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

    በዉጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የዳያስፖራ ምዝገባ እና መረጃ አያያዝ ስርዓት መዘርጋት፣ ዳያስፖራው በዕውቀትና በተክኖሎጂ ሽግግር አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ማስቻል እንዲሁም በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በቱሪዝም ተሳትፎውን ማጎልበት የኤጀንሲው ዋና ዓላማዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

    ተጨማሪ፦ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ እና ለመሥርት ያላቸው ፍላጎትና የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች (ቪዲዮ)

    ኤጀንሲው በቅርቡ ሥራውን በይፋ የሚጀምርበት በዳያስፖራው ማህበረሰብ እና በባለድርሻ አካላት ዘንድ ተልዕኮው በግልፅ ታዉቆ በጋራ እና በቅንጅት ሥራው እንደሚሰራ መገለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመልክታል።

    የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ኤጀንሲ ለማቋቋም የወሰነው በጳጉሜን ወር 2010 ዓ.ም. ሲሆን፥ በዚያን ጊዜ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በትውልድ ሀገራቸው እድገት ላይ የራሳቸውን አስተዋጽዖ ለማድረግ ከምን ጊዜውም በበለጠ እንደተነሳሱ ገልጸው ነበር።

    በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሦስት እስከ አምስት ሚሊዮን እንደሚገመትና ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ በሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ እንደሚኖሩ ዘገባዎች ያመለክታሉ። እ.ኤ.አ ከ2009 በፊት ኢትዮጵያ ከእነዚህ የዳያስፖራ አባላት የምታገኘው ገቢ (remittance) ከ400 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በታች እንደነበረና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ አሀዝ እየጨመረ መምጣቱ ተጠቁሟል።

    በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ወደ ትውልድ ሀገራቸው የሚልኩት የገንዘብ መጠን ከአራት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሆነና ይህም ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ከምታገኘው ገቢ ጋር ሲነጻጸር በአንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ብልጫ አለው።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ


    Semonegna
    Keymaster

    ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አስተማማኝ ሠላም በዘለቄታ እንዲረጋገጥ ከተለያዩ ማኅበረሰብ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን፣ የሀገሪቱ አቅም በሚፈቅደው ደረጃ የተለያዩ ግብዓቶችን ማሟላትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ ችግር በአሁኑ ሰዓት እየተስተካከለ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሒሩት ወልደማርያም ገለጹ።

    ዶ/ር ሒሩት ባለፈው ሳምንት ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መደበኛው የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሪያ አከባቢ በሰላማዊ ሁኔታ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን በሂደት ግን የአገራችን ለውጥ ያልተዋጠላቸው አካላት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ማዕከል በማድረግ ግጭቶችን በማስፋፋት ሠላም እንዳይኖር ታስቦ እንደ ነበር ተደርሶበታል ብለዋል።

    ተመሳሳይ ዜና፦ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በቂ ዝግጅት በማድረግ አዳዲስ ተማሪዎችን መቀበሉን አስታወቀ

    ግጭቶቹ በግል ደረጃ በተማሪዎች ጠብ ተጀምሮ ወደ ብሔር እንዲያድግም ታስቦ እንደነበርና፥ አሁን ግን ከተለያዩ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባላት፣ ከዩኒቨርሲቲው አመራር፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከጸጥታ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ፥ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ መደበኛ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ለዚህም በዩኒቨርሲቲ ቦርድ እንዲሳተፉ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ብቁ ምዑራን መመልመላቸውን፣ ሴቶችም በጉዳዩ እንዲሳተፉ ሀምሳ በመቶ (50%) ያህሉ ሴቶች በቦርድ እንዲመረጡ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ረዘም ላለ ጊዜ ትምህርት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፥ አሁን ግን ከተለያዩ አካላት እና ከተማሪዎች ጋር በተደረገ ውይይት ከጥር 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተማሪዎቹ በመደበኛ የትምህርት ገበታቸው እንደሚገኙ ከስምምነት መደረሱን ሚኒስትሯ አክለው ገልጸዋል።

    የዩኒቨርሲቲዎች አስተማማኝ ሠላም በዘለቄታ እንዲረጋገጥ ከተለያዩ ማኅበረሰብ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን፣ የሀገሪቱ አቅም በሚፈቅደው ደረጃ የተለያዩ ግብዓቶችን ከማሟላት በተጨማሪ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ምሁራንን በመጋበዝ የተማሪ ሥነ-ልቦና ላይ በመሥራት በተማሪዎች ዘንድ የተወዳዳሪነት ስሜት እንዲፈጠር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ክብርት ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ


    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፈረንሳዩ ጂ ኢ ሪኒዌብልስ አካል ከሆነ ጂ ኢ ኃይድሮ ፍራንስ ጋር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማፋጠን የሚያስችል የ61 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርሟል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራዎችን በአዲስ ኃይል ወደቀድሞ ፍጥነት ለመመለስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ በዶ/ር ኢንጂነር አብርሃም በላይ የተመራ የልዑካን ቡድን የግድቡን የሲቪልና የብረታብረት ሥራዎች ጎብኝቷል።

    የግንባታው አማካሪዎች ትራክትቤል ኢንጂነሪንግና ኤልክ ኤሌክትሮ ኮንሰልት ተወካዮች እንደገለፁት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ለታዩት ችግሮች ቴክኒካዊ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ቀደም ሲል የተጀመሩና የተከናወኑ ከብረታብረት ጋር የተያያዙ ሥራዎች ከ90 በመቶ በላይ ፍተሻ ተደርጎ ችግሮቹን ለማረም የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውም ተገልጿል።

    ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ እንደተናገሩት የግድቡ የግንባታ ሥራዎች መነቃቃት እየታየባቸው ነው። በመሆኑም የተለያዩ ሂደቶችን ማለፍ የማይጠይቁ የግንባታ ሥራዎች በፍጥነት እንዲከናወኑ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኢ/ር አብርሃም በላይ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ለማረምና ጉድለቱን ለማካካስ ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የግድቡን ግንባታ ለማፋጠን ቀደም ሲል ከብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በንዑስ ተቋራጭነት ለመሥራት ውል የነበራቸው ተቋራጮች መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከጂ ኢ ኃይድሮ ፍራንስ ጋር ውል ተፈራርሟል።

    የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስምምነቱን ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በተቋሙ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ነው ጂ ኢ ሃይድሮ ፍራንስ ከተባለው ተቋራጭ ጋር ተፈራርሟል። ጂኢ ሃይድሮ ፍራንስ በቅድሚያ እንዲያመነጩ ታስበው ዲዛይን የተደረጉትን ሁለት ተረባይኖችን ጨምሮ አምስት ኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ኮሚሌክስ ከተባለ ድርጅት ጋር በጥምረት ለማምረት፣ ለመግጠምና ለመፈተሽ የ53 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተፈርሟል።

    ጂ ኢ ሃይድሮ ፍራንስ ቀደም ሲል ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ተርባይን ጄኔሬተሮችን ለማቅረብ ብቻ የንዑስ ተቋራጭነት ስምምነት እንደነበረው ዶ/ር አብርሃም ገልጸዋል። አዲሱ ስምምነት ደግሞ የማምረት፣ የተጓደሉ አቅርቦቶችን የማሟላት፣ የተከላና የፍተሻ ሥራዎችን ያከተተ ነው ተብሏል።

    በተመሳሳይ ተቋሙ ሲኖ ሃይድሮ ከተባለው የቻይና ኩባንያ ጋር የብረታ ብረት ሥራዎች ጋር በተያያዘ ስምምነት ለመፈራረም ድርድሮች መጠናቀቃቸውም ተገልጿል። ኩባንያው የኃይል ማመንጫ የውሃ ማስተላፊያ ቱቦዎችን፣ የመቆጣሪያ እና የጎርፍ ማስተንፈሻ በሮችን የመገንባትና የማስተካከል ሥራ እንደሚያከናውን ተጠቁሟል። ሲኖ ሃይድሮ የሚሠራው ሥራ የሲቪል ሥራዎች በማፋጠን ከአጠቃላይ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ሁለቱ አስቀድመው ኃይል እንዲያመነጩ ያግዛል ተብሏል።

    ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ኤፍቢሲ እና ሮይተርስ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ


Viewing 15 results - 601 through 615 (of 730 total)