Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Viewing 15 results - 646 through 660 (of 730 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–የአፍሪካን እና የቻይናን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎ የሚጠበቀው የአፍሪካ-ቻይና የንግድ ትርዒት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ (አዲስ አበባ) ይካሄዳል።

    የአፍሪካ-ቻይና የንግድ ትርዒት በመጪው ሳምንት ከኅዳር 24 እስከ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አግዚቢሽን ማዕከል “የቻይና-ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አቅም ትብብር ትርዒት” በሚል ርዕስ እንደሚደረግ ተገልጿል።

    የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት (ECCSA)፣ የኢፌዴሪ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የቻይና ዓለም አቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክር ቤት (China International Exhibition Center – CIEC) በኅብረት በመሆን ያዘጋጁትን የአፍሪካ-ቻይና የንግድ ትርዒት በተመለከተ በጋራ ጋዜጣዊ መግለቻ የሰጡ ሲሆን፥ ትርዒቱ (Expo) የቻይና የንግድ ኩባንያዎችና በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሠማሩ አካላት በአፍሪካ ካሉ አቻዎቻቸው ጋር የሚኖራቸውን ትስስር ይበልጥ ያጠናክራል ተብሎ ይገመታል ብለዋል። የቻይናው ሲጂቲኤን አፍሪካ (CGTN Africa) እንደዘገበው በቁጥር 29 በሚሆኑ የተለያዩ ዓይነት የኢንዱስትሪ ዘርፎች (sectors) ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ትርዒቱ ላይ ይሳተፋሉ።

    በመግለጫው ላይ እንደተጠቀሰው በቻይና በመሠረተ ልማት፣ በትራንስፖርት ሎጂስቲክስ፣ በጠቅላላ ንግድ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የመረጃ ግንኙነት (information communication) ቁሳቁስ፣ ከከባድ እስከ ቀላል የሆኑ የማሽነሪ መሣርያዎች፣ እንዲሁም በኃይል እና አካባቢ ጥበቃ ላይ ያታኮሩ ምርቶችን የሚያመርቱና የሚያቀርቡ ከአርባ በላይ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።

    The 1st China–Africa Expo at Addis Ababa Exhibition Center, Ethiopia

    የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል ዓይናለም ዓባይነህ (ዶ/ር) እንደገለጹት ትርዒቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሔድ ቢሆንም ከአሁን በኋላ በየዓመቱ እንደሚከናወንና የተሳታፊዎችን ቁጥር በመጨመርና በዓይነት በማስፋት እያደገ እንደሚሔድ ገልጸዋል።

    የቻይና ዓለም አቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክር ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሊኡ ዢያን (Liu Jian) በመግለጫቸው እንደተናገሩት፥ ትርዒቱን ስፖንሰር ያደረጉት የቻይና ዓለም አቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክር ቤት (China Council for the Promotion of International Trade)፣ ከቻይና አፍሪካ ልማት ፈንድ (China-Africa Development Fund) እና ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር ሲሆን፥ የትርዒቱ ዋነኛ ዓላማም በአፍሪካውያን እና በቻይናውያን የንግድ ማኅበረሰብና ግለሰቦች መካከል ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ነው ብለዋል።

    ይህንን የአፍሪካ-ቻይና የንግድ ትርዒት በየዓመቱ በቋሚነት ለማከናወን የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የቻይና ዓለም አቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክር ቤት የመስማሚያ ሰነድ መፈራረምቸውም ተጠቁሟል። ሁለቱ ተቋማት በሁለቱ ሀገራት የሚገኙ የንግድና ኢንቨስትመንት ተቋማትን ለማገናኘት በሚረዳ መልኩ ከዚህ በፊት የቢዝነስ ፎረሞችን፣ ጉባዔያትን፣ ቢዝነስ-ቱ-ቢዝንስ ቁርኝቶችን (B2Bs) ማድረጋቸውንም የኢትዮጵያው ምክር ቤት አስታውቋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የአፍሪካ-ቻይና የንግድ ትርዒት

    Semonegna
    Keymaster

    ሰዎች የእርሻና የግጦሽ ቦታዎችን ለማስፋት በጥብቅ ቦታዎች እና በፓርኮች ዙሪያ በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነቶች የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮዎች የመኖርያ ቦታ ስጋት ላይ ከመውደቁ ባሻገር የዱር አራዊቱ በበሽታው እየተለከፉ መሆኑ ተጠቁሟል።

    (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት) – የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮዎች ውሻን በሚያሳብድ በሽታ እየሞቱ መሆናቸው ተረጋግጧል።

    ብርቅዬ እንስሳቱን ውሻን ከሚያሳብድ በሽታ ለመከላከል ክትባት እየተሰጠ መሆኑን ደግሞ የአማራ ክልል አካባቢ ደን እና የዱር እንሰሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።

    በኢትዮጵያ ከሚገኙ ብርቅየ የዱር እንስሳት መካከል የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮዎች ይጠቀሳሉ። የኢትዮጵ ቀይ ቀበሮዎች በአማራ ክልል በሚገኙ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፣ በቦረና ሳይንት “ወረ ሂመኑ ብሄራዊ ፓርክ፣” በመንዝ ጓሳ እና በአቡነ ዮሴፍ የማኅበረሰብ ጥብቅ ቦታዎች ይገኛሉ። በደላንታ ዳውንት አንዳንድ አካባቢዎችም አልፎ አልፎ እንደሚገኙ ከአማራ ክልል አካባቢ ደን እና የዱር እንሰሳት ጥበቃ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

    በባለሥልጣኑ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለስልጣን አቶ አብርሃም ማርየ እንደተናገሩት በነዚህ አካባቢዎች ከ2 መቶ በላይ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የቀይ ቀበሮ ዝርያዎች አሉ።

    እንደ ባለስልጣኑ ገለፃ ብርቅየ የዱር እንስሳቱን ውሻን ከሚያሳብድ በሽታ ለመከላከል የሚያስችል ክትባት እየተሰጠ ነው።

    የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን የተጋረጠባቸው አደጋ (ቪዲዮ)

    ሰዎች የእርሻና የግጦሽ ቦታዎችን ለማስፋት በጥብቅ ቦታዎች እና በፓርኮች ዙሪያ በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነቶች የዱር አራዊቱ የመኖርያ ቦታ ስጋት ላይ ከመውደቁ ባሻገር ቀይ ቀበሮዎቹ በበሽታው እየተለከፉ መሆኑ ተጠቁሟል።*

    ባሳለፍነው ጥቅምት ወር በአቡነ ዮሴፍ የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ በሽታው የሞቱ የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮዎች መገኘታቸውም ተገልጧል። የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስም ባለሥልጣኑ የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ ፕሮጀክት ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር በሁሉም የቀይ ቀበሮ መገኛ ቦታዎች ክትባት እየሰጠ ነው።

    አብዛኛዎቹ ቀይ ቀበሮዎች ክትባቱን እንዲያገኙ ለማድረግ ውሻን በሚያሳብድ በሽታ መድኃኒት የበለፀገ ስጋ በማቅረብ እንዲመገቡ የማድረግ ሥራ የክትባቱ አንድ አካል ነው።

    በተመሳሳይ መልኩ በመንዝ ጓሳ ማኅበረሰብ ጥብቅ ደን አራት የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮዎች ሞተው ተገኝተዋል። ለህልፈት የዳረጋቸው ናሙና ወደ እንግሊዝ ተልኮ “ካናዲስ ዲስትምፕተር” የተባለ በሽታ መሆኑ መረጋገጡን አቶ አብርሃም አስረድተዋል።

    የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት (አብመድ) እንደዘገበው ክትባቱ እስከያዝነው ኅዳር ወር መጨረሻ ይቆያል።

    * አፍሪካን ዋይልድላይፍ ፋውንዴሽን (African Wildlife Foundation – AWF) የተባለ ድርጅት ስለ አትዮጵያ ቀይ ቀበሮዎች ባወጣው ዘገባ እነዚህ የዱር አራዊት በቁጥራቸው እጅግ ለመምናመን እና ለህልውናቸው አስጊ የሆኑት ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች፥ በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኙ ሰዎች የሚዘወተር እርሻ እና የውሻ ዘርን የሚያጠቁ በሽታዎች ቢሆኑም የእርሻ ሥራ (እና ቦታውን ለከብቶች ግጦሽ ማዋል) ግን ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና AWF

    ቀይ ቀበሮዎች

    Semonegna
    Keymaster

    ድሬ ዳዋ (ሰሞነኛ)– የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በአንድነት ለመሥራት ቃል ገቡ። ከሰሞኑ ግጭት ውስጥ የገቡ ተማሪዎች የሀይማኖት አባቶችና ከፍተኛ የመንግስት አካላት በተገኙበት ዕርቅ አውርደዋል።

    ሰሞኑን ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ባልተከሰተና በሀሰት በተሰራጨ መረጃ ምክንያት በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ዳግመኛ እንዳይከሰት ተማሪዎቹ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉና በተማሪዎች መካከል የሚፈጠሩ የግለሰብ ግጭቶችንም ወደ ቡድንና የብሄር ግጭትነት ለመቀየር የሚፈልጉ አካላትን ጥረት እንደሚያወግዙ ተናግረዋል።

    ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ማዕከል ውስጥ በተካሄደው የእርቅ ዝግጅት ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት፥ ተማሪዎችን በብሄር እንዲጋጩ ሁኔታዎችን በሚፈጥሩና በሚያነሳሱ ተማሪዎችና አገልግሎት ሰጪ አካላት ላይ ዩኒቨርሲቲው ክትትል አድርጎ አስተማሪ እርምጃዎችን በመውሰድ የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር ጠይቀዋል።

    ከየትኛውም ብሄር ጥሩ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ መጥፎዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉና እነዚህ ሰዎች በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ የእኩይ ተግባራቸውን ለማስፈፀም ብሄራቸውን ሽፋን በማድረግ ለመጠቀም ስለሚሞክሩ ተማሪዎች ተሳስተው የወንጀለኞች ተባባሪና የእኩይ ተግባራት ማስፈፀሚያ እንዳይሆኑ መረጃዎችንና ሁኔታዎችን ከስሜት በጸዳና በምክንያታዊነት እንዲመለከቱ የመድረኩ ተሳታፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

    These two Ethiopian students are working to launch their own rocket – the future Eng. Kitaw Ejigu

    የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባለፉት ዓመታት በአንድነት ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ እንደነበርና በመካከላቸውም አለመስማማቶች ሲፈጠሩ በራሳቸው መንገድ ተወያይተው ችግሮችን ሲፈቱ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮም ይህን አንድነታችንን በማስጠበቅ በመካከላችን ልዩነቶችን በመፍጠርና ግጭት እንዲቀሰቀስ በማነሳሳት የድብቅ ሴራቸው ማስፈፀሚያ ሊያደርጉን የሚፈልጉ አካላትን ሴራ እናከሽፋለን ብለዋል። ባለፉት ጥቂት ቀናት መለስተኛ ግጭት በመፈጠሩ ይቅርታ የተጠያየቁት ተማሪዎች አጋጣሚውን ለቀጣይ በመማሪያነት በመውስድ ችግሮችን በጋራ ለመከላከል እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።

    የአማራ ክልልንና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (አዴፓ) ወክለው የተገኙት አቶ ባዘዘው ጫኔ እንደተናገሩት ችግሩ በመፈጠሩ የአማራ ክልልና የክልሉ ገዢ ፓርቲ አዴፓ ማዘኑን ገልፀው ግጭቱ ሳይሰፋና የከፋ ችግር ሳያስከትል በቁጥጥር ስር እንዲውል የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ተማሪዎች እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ አካላት ላደረጉት ጥረት ደግሞ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    ሰዎች በብዛት ተሰባስበው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ግጭት ሊከሰት እንደሚችል አቶ ባዘዘው አስታውሰው በግለሰቦች የሚጀመር ግጭትን ወደብሄር ማዞሩ አደገኛና ሊወገዝ የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል። በሐረማያ ዩኒቨርሲቲም ሰሞኑን በተከሰተው ግጭት በርካታ ተማሪዎች ጉዳዩን በማውገዝ ወደ ግጭት ባለመግባታቸው ቶሎ በቁጥጥር ስር እንዲውል እንዳስቻለ የተናገሩት አቶ ባዘዘው ተማሪዎች በአንድነት ተሳስቦ በፍቅር የመኖር ልማዳቸውን በማጎልበት የዩኒቨርሲቲያቸውንና የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።

    የኦሮሚያ ክልልንና የክልሉ ገዢ ፓርቲ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ኦዲፓ) ወክለው የተገኙት አቶ አብዱላዚዝ መሀመድ ባደረጉት ንግግር ተማሪዎቹ እርቅ ለማውረድ ያሳዩትን ፍላጎት አድንቀዋል። አቶ አብዱላዚዝ አያይዘውም ባለፉት ሰባት ወራት መንግስት ለዓመታት የተከማቹ የሕዝብ ጥያቄዎችን በመፍታት ላይ እንደሚገኝና በዚህም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ በመሆኑ ይህን ለውጥ የማይፈልጉ አካላት የመንግስትን የለውጥ ጉዞን ለማደናቀፍ በየቦታው ግጭቶች እንዲነሱ በማድረግ መንግስትን ግጭቶችን በመከላከል ላይ እንዲጠመድ በማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ጉዞዎችን ለማደናቀፍ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

    ስለዚህ የነገዋ ባለተስፋና የዜጎቿ መኩሪያ የሆነች ኢትዮጵያን ተረካቢ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ይህን ተረድተው ራሳቸውን ከስሜታዊነት አርቀው፣ መረጃዎችን በጥንቃቄ በመመርመር ምክንያታዊ በመሆን ግጭቶች እንዳይከሰቱ ጥረት እንዲያደርጉና ከግጭቶች በመራቅ የእኩይ ተግባር ማስፈፀሚያ ከመሆን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አቶ አብዱላዚዝ ለተማሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።

    በሀገራችን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸው ወጣቶች የሚገኙበት እንደሆነ እንደሚታመን የተናገሩት የሳይንስና የከፍተኛ ትምህር ጉዳዮች ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ጌታቸው ነጋሽ በአስተሳሰባችሁ መላቃችሁንና ማኅበረሰባችን የሰጣችሁን ይህን ግምት ትክክለኛነት ለማሳየት ምክንያታዊ በመሆን ለነገሮች መፍትሄ በመስጠት ልታስመሰክሩ እንጂ እንደዘይትና ውሃ የተፈጠራችሁበት ነገር ሳይለያይ በብሄር ልትከፋፈሉና ልትጋጩ አይገባም ብለዋል።

    የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዝዳንት ጀማል ዩሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተማሪዎች በብሄር ከማሰብ ወጥተው አንድነት ላይ በማተኮር የዩኒቨርሲቲውን ሰላም በጋራ በማስጠበቅ በቂ ዕውቀት ጨብጠው በሀገራችን የእድገት ጉዞ ላይ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉና ራሳቸውን የጥፋት ኃይሎች ድብቅ ዓላማ አስፈፃሚ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

    በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይኖር እንቅፋት ይፈጥራሉ በማለት በተማሪዎች በቀረቡ ጥቆማዎች ላይም አስፈላጊውን ክትትል ግምገማ በማድረግ የእርምት እርምጃዎችና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራዎች እንደሚከናወኑ ዶ/ር ጀማል አረጋግጠዋል።

    በእርቅ መድረኩ ላይ የተሳተፉ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም በተማሪዎች መካከል ሰላም፣ ፍቅርና ይቅር ባይነት እንዲጎለብት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።

    ምንጭ፦ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ (HU FM 91.5 RADIO)

    የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    በደቡብ ክልል የሚገኘው ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ 3ኛ ትውልድ ከሚባሉት 11 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን፥ ከ1 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው በ2010 ዓ.ም. ነው።

    ሚዛን (ኢዜአ) – የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተቋሙ የሚስተዋሉ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የውሃና የምግብ አገልግሎት ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ።

    የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በበኩሉ ተማሪዎቹ ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች አግባብ መሆናቸውንና ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

    በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል (ዋና ካምፓሱ ቦንጋ ከተማ ውስጥ) የሚገኘው ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ 3ኛ ትውልድ ከሚባሉት 11 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን፥ ከ1 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው በ2010 ዓ.ም. ነው።

    የተቋሙ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት ዘንድሮ በዩኒቨርሲቲው መሻሻል ቢኖርም አምና የነበሩባቸው ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

    በተለይ ከምግብ አገልግሎትና ከውስጥ ለውስጥ መንገድ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።

    በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት የእንስሳት ሳይንስ ተማሪ ብርሌው አገኝ በበኩሉ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ባለመሠራቱ በተለይ በዝናብ ወቅት በጭቃ ምክንያት ለመንቀሳቀስ እየተቸገሩ መሆናቸውን ገልጿል። አካባቢው ዝናባማ መሆኑ ችግሩን እያባባሰው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ችግሩን ፈጥኖ እንዲፈታላቸው ጠይቋል፤ ከዚህ ባለፈም ዩኒቨርሲቲው ካለበት የውሃ ችግር በተጨማሪ ለተማሪዎች የሚሰጠው የምግብ አገልግሎት ሊስተካከል እንደሚገባ ጠቁሟል። በተለይ በምግብ አቅርቦት በኩል በተለያዩ ቀናት ተመሳሳይ ምግብ ተደጋግሞ የሚቀርብበት ሁኔታ ስላለ እንዲስተካከል ጠይቋል።

    የሁለተኛ ዓመት የአስተዳደር ተማሪ የሆነው ሙላቱ በቀለ በበኩሉ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ካለፈው ዓመት ብዙም መሻሻል እንዳላየበት ተናግሯል። አምና የመንገድ፣ የውሃ አቅርቦትና የቤተ መጻሕፍት አገልግሎቶች ላይ እጠረቶች እንደነበሩ አስታውሶ እነዚህ ችግሮች ዘንድሮም ባለመሻሻላቸው እየተቸገሩ በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው ትኩረት እንዲሰጠው ተናግሯል።

    የዩኒቨርሲቲው የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መምህር ያሬድ አያሌው በበኩላቸው ችግሮቹን ለመፍታትና ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢ ለመፍጠር ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የመንገድ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በአሁኑ ወቅት የ5 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራ መጀመሩን ገልጸው፥ መንገዱ የዩኒቨርሲቲውን ዋና ዋና መስመሮች እንደሚያገናኝም አመልክተዋል። አካባባቢው ዓመታዊ የዝናብ ሽፋኑ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ይህም በተለይ በዝናብ ወቅት በሚፈጠር ጭቃ እንደልብ ለመንቀሳቀስ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

    ለተማሪዎች ከሚሰጠው የምግበ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የጎላ ችግር እንደሌለ የገለጹት ኃላፊው፣ የምግብ አቅርቦት መርሀ ገብሩም ዩኒቨርሲቲው ከተማሪዎች ማኅበራት ጋር ተስማምቶ እንዳወጣውና በእዚያ መሠረት ምግብ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ዋና ቤተ መጻህፍት ግንባታ ሥራ በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቁም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለው ችግር በቅርቡ ሙሉ በሙሉ እንደሚፈታ አመልክተዋል።

    ከተማሪዎቹ የተነሳው የውሃ ችግር ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን የገለጹት መምህር ያሬድ ችግሩን ለመፍታት ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የራሱን የውሃ ጉድጓድ በመገንባት ላይ መሆኑንና ግንባታው ሲጠናቀቅ ችግሩ ይቀረፋል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል።

    የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በሕግ፣ በምህንድስናና በማኅበረሰብ ጥናት አዳዲስ የትምህርት ክፍሎችን የሚጀምር ሲሆን አጠቃላይ የትምህርት ክፍሎቹንም ወደ 26 እንደሚያሳድግ ከዩኒቨሲቲው የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ

    ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ሑመራ (ኢዜአ)– በትግራይ ክልል የሰቲት ሑመራ ከተማ ነዋሪዎች የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክተው በቅርቡ ላደረጉት ንግግር ድጋፋቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ።

    ነዋሪዎቹ ለዶ/ር ደብረጽዮን ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ትናንት በተሽከርካሪዎች የጀመሩት ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ወጣቶችን ጨምሮ በሰቲት ሑመራ ከተማ ነዋሪዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል።

    በሰልፉ ላይ የተሳተፉት ወጣቶች፣ ማኅበራትና ነዋሪዎች “የትግራይ ሕዝብ ታሪክ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር ታሪክ የለውም! የሕግ በላይነት ይከበር! በሙስና የተጠረጠሩ በቁጥጥር መዋላቸውን ብንደግፍም በሙስናና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ሽፋን ብሔር ተኮር ጥቃት ይቁም! የውጭ ጣልቃ ገብነት ይቁም!” የሚሉና ሌሎች የተለያዩ መፈክሮች ይዘው ሰልፉ ላይ ታይተዋል። የትግራይ ሕዝብ ለሰላም፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ የቆመ ነው ሲሉም ድምጻቸውን አሰምተዋል።

    መንግስት የሕግ በላይነት ለማስከበር የጀመረው እንቅስቃሴ እንደሚደግፉት የገለጹት ሰላማዊ ሰልፈኞቹ፣ ሕግን የማስከበር ሥራው በሁሉም አካላትና የመሥሪያ ቤት ዘርፎች እንዲተገበር ጠይቀዋል።

    በሰልፉ ላይ የተሳተፉ የቃፍታ ሑመራ ወረዳ ነዋሪ አቶ ተመስገን ካሕሳይ “የትግራይሕዝብ በእኩልነትና በፍትህ ያምናል፤ ለዓመታት የታገለውም የሕግ በላይነት እንዲረጋገጥ ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር መስዋዕትነት የከፈለው ለህግ ልዕልና መረጋገጥ ነው – የክልሉ መንግስት

    ወጣት የዕብዮ ኃይሉ የተባለ ሌላው የወረዳው ነዋሪ በበኩሉ “እኛ ሕግ የጣሰና በሙስና የተዘፈቀ መደበቂያ አንሆንም፤ መጠየቅ ያለባቸው በትግራይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች ያሉ በመሆኑ ሕግ የማስከበር ሥራ በሁሉም ሊተገበር ይገባል” ብሏል። የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር ሆኖ መታገሉን ገልጾ አሁንም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረጉ ጥረቶች ማንኛውም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አመልክቷል።

    የሰቲት ሑሞራ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰለሞን አረጋይ በበኩላቸው “ዶ/ር ደብረጽዮን ያደረጉት ንግግር ሰላምና ልማትን የሚፈልግ ማንኛውንም ብሔር የሚመለከት በመሆኑ ድጋፌን ለመግለጽ ወጥቻለሁ” ሲሉ ገልጿል።

    The recent action to impose the rule of law in Ethiopia is getting political agenda – Dr. Debretsion

    ወጣት መሰለ ዕቁባይ በበኩሉ ስለ ሰላም እየዘመሩ የትግራይ ሕዝብን ሰላም ለማወክ መሞከር አግባብ ያልሆነና ተቀባይነት እንደሌለው ተናግሯል። የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ሆኖ የታገለው ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በመሆኑ ማንኛውንም ጭቆና እንደማይሸከም አመልክቷል።

    በሰልፉ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ርስቁ አለማው እንዳሉት ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲከበር የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወገኖቹ ጋር በመሆን መስዋዕት ከፍሏል። በአሁኑ ወቅትም ከሌሎች ሰላም ወዳድ የአገሪቱ ሕዝቦች ጋር በመሆን ሕግ ለማስከበር ድምጹን በሰላማዊ መንገድ እያሰማ መሆኑን ተናግረዋል።

    “በዞናችን የማንነት ጥያቄ ባይኖርም አንዳንድ ሰላም የማይፈልጉ አካላት ሰላሙን ለመንሳት ሌት ተቀን ቢሠሩም ሕዝቡ በትዕግስት እና በሰላም ድምጹን እያሰማ ነው” ብለዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ሰቲት ሑመራ

    Semonegna
    Keymaster

    ወልድያ (ኢዜአ)– የወልድያ ዩኒቨርሲቲ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ከሁለት ወር በኋላ መደበኛ ስርጭቱን እንደሚጀምር አስታወቀ።

    የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ኪዳነ ማርያም ጌታሁን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው የአካባቢውን ሕዝብ የመረጃ ተደራሽነት ለማስፋፋት ያቋቋመው ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ (FM Radio) በጥር ወር መደበኛ ስርጭቱን ይጀምራል።

    ጣቢያው በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርናና ሌሎች ዘርፎች ያተኮሩ ፕሮግራሞች ይኖሩታል ብለዋል አቶ ኪዳነ ማርያም። እንዲሁም ወቅታዊ መረጃና የመዝናኛ ፕሮግራሞች እንደሚኖሩትም ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

    የሙከራ ስርጭቱን በአምስት ባለሙያዎች እየተመራ ካለፈው ወር ጀምሮ በሙከራ ስርጭት እያስተናገደ ያለውን ጣቢያ ሙሉ በሙሉ ሥራ ለማስጀመር የ25 ባለሙያዎች ቅጥር እንደሚከናወን አክለው አሳውቀዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኛነትና ኮሙኒኬሽን የትምህርት ክፍል ተጠሪ አቶ ብርሃኑ ደጀኔ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ሬዲዮ ጣቢያውን መክፈቱ ለአካባቢው ኅብረተሰብ መረጃ ለማድረስና ከማስተማር ባለፈ ወቅቱን ያገናዘበ ተግባር መሆኑን ይናገራሉ።

    ጣቢያው የትምህርት ክፍሉ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበላቸውን 100 ተማሪዎቹን በተግባር የተፈተነ ሙያ ይዘው ለመውጣት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፤ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተቀራርቦ ለመሥራት እገዛ ያደርጋል በማለት አቶ ብርሃኑ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
    የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስርጭቱን የሚያደርገው በኤፍ ኤም 89 ነጥብ 2 መሆኑ ታውቋል።

    ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተያያዘ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ በወልድያ ከተማና በዩኒቨርሲቲው ግቢ የሚፈጠረውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት የሚያግዝ “NE Global Chain” ከተባለ ኩባንያ ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ። ስምምነቱ ከፀሐይ ብርሀን የሚገኝ 50 ሜጋ ዋት ለማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት እንደሆነ ኅዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው ግቢ ሰነዱን በተፈራረሙበት ወቅት ተገልጿል። በስምምነቱ ቤሩትና ሊባኖስ የሚገኘውን ድርጅታቸውን በመወከል የተፈራረሙት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳቢስ ናሃስ ሲሆኑ በዩኒቨርሲቲው በኩል የተቋሙ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ጨምሮ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳዊት መለሰ ተገኝተዋል።

    በሌላ ዜና የዩኒቨርሲቲው ዜና ደግሞ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት በራያ ቆቦ ወረዳ እየተከናወነ ያለውን የአገዳ ቆርቁርና የአቀንጭራ አረሞችን የክስተት መጠንን እንዲሁም የተቀናጀ የእንስሳት መኖ ምርት ያለበትን ደረጃ ለመለየት ባለሞያዎቹ በአርሶ አደሮች ማሳላይ መረጃ በመሠብሰብ ሂደት ላይ ናቸው።

    ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ዜናዎች

    ምንጮች፦ ኢዜአ እና ዩኒቨርሲቲው

    የወልድያ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ ተደርጋ መሾም የሀገሪቱን የምርጫ ሂደት ለማሻሻል የተገባውን ቃል ለማጠናክር እና ለ2012 ዓ.ም. ምርጫ ዝግጅት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድን ለማጠናከር ያለውን የፓለቲካ ቁርጠኝነት ምስክር ነው ብለዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ስብሰባው ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ በአራት ተቃውሞ፣ ሦስት ድምፅ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ ሾሟል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የዕጩዋን ሹመት ባቀረቡበት ወቅት መንግስት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን በአዲስ መልክ ለመተካት የወሰነው የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ዳር እንዲደርስ ለማድረግ የተጀመረው የጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል።

    በተለይም የዲሞክራሲ መገለጫ የሆነው ምርጫ ቦርድ ተዓማኒና ገለልተኛ ለማድረግ ተቋሙን የማዘመንና ማሻሻል ከማድረግ በተጨማሪ ብቁ የሆነ መሪ እንደሚያስፈልገው በማመን ወ/ሪት ብርቱካን ለዕጩነት ቀርበዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

    ዶ/ር ዐብይ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርዶ ሰብሳቢ ተደርጋ መሾም የሀገሪቱን የምርጫ ሂደት ለማሻሻል የተገባውን ቃል ለማጠናክር እና ለ2012 ዓ.ም. ምርጫ ዝግጅት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድን ለማጠናከር ያለውን የፓለቲካ ቁርጠኝነት ምስክር ነው ብለዋል።

    በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቅራቢነት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት የተከናወነው የቀድሞዋ ሰብሳቢ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው።

    ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ማን ናቸው ?

    በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው፣
    ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ስኩል ኦፍ ገቨርንመንት የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው፣
    – በፌደራል ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ያገለገሉ፣
    – የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ፣
    – በውጪ ሀገር በናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዲሚክራሲ በተባለ ድርጅት ተመራማሪ ሆነው የሠሩ፣
    – የፓርቲ አመራርና ተወዳዳሪ (ቅንጅት) ሆነው የሠሩ፣
    – በምርጫ ሂደት ሰፊ ልምድ ያላቸው ናቸው።

    Interview: Birtukan Mideksa, who shook Ethiopian court system, is back to Ethiopia from exile

    ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በአሁኑ ሰዐት የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑና ገለልተኛ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ይታወቃል።

    ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከቀድሞ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) ጋር በተያያዘ ለእስራትና ለእንግልት ከተዳረጉ በኋላ ከሀገር ወጥተው በሀገረ አሜሪካ ለሰባት ዓመታት በስደት የኖሩ ሲሆን፥ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ሁለንተናዊ ለውጥ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባቀረቡላቸው ጥሪ መሠረት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ይታወሳል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ብርቱካን ሚደቅሳ PHOTO: Abebe Abebayehu


    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበርን ላለፉት ስድስት አመታት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲመራ የቆየውና በአሁኑ ሰዓት የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ሆኖ በማገልገል ላይ እሚገኘው አርቲስት ደሳለኝ ሃሉ የአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር የቦርድ አባል ሆኖ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የሹመት ደብዳቤ ተሰጥቶታል።

    ደሳለኝ ሃይሉ ከዘጠኝ ወራት በፊት የፀደቀው የኢትዮጵያ ፊልም ፖሊሲ እውን እንዲሆን ከታገሉ ፊልም ባለሞያዎች መሃል አንዱ ነው።

    የአርቲስቱ ሹመት በተለይም በሲኒማ ቤቶች አካባቢ በስፋት ሚታየውን ግልፅ ሌብነት ና የተጋነነ የአዳራሽ ኪራይ ያስቀረዋል ተብሎ ይታሰባል።

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ኤግል ሒልስ)–በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የበላይ ጠባቂነት በአዲስ አበባ ለገሀር አከባቢ ሥራዉን ለመጀመር ዝግጅቱን ያጠናቀቀዉ የዱባይ አቡዳቢው ኤግል ሒልስ (Eagle Hills) በአዲስ አበባ ለገሀር የተቀናጀ የመኖሪያ፣ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ልማት ሥራውን በይፋ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ በተገኙበት ኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀመረ።

    ይህ በ360,000 ሜትርካሬ መሬት ላይ የሚያርፈዉ የለገሀር የተቀናጀ የልማት ኘሮጀክት የአዲስአበባን መሀል ከተማ ወካይ ሆኖ በዉስጡ ከ4000 በላይ መኖሪያ ቤቶች፣ የመዝናኛ ስፋራዎች፣ ግዙፍ የንግድ ማዕከላት፣ መጋቢና ዋና መንገዶች እና ሌሎች ዘመናዊ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ይኖሩታል ።

    ከቦሌ ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ በቅርብ ርቀት የሚሠራው ይህ ሁለገብ መንደር እንዲሁም ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች፣ አረንጓዴ መዝናኛ ስፍራዎች፣ ምቹና ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች እና የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች በበቂ ሁኔታ በዉስጡ እንዳካተተም ማስተር ኘላኑ ያመለክታል።

    ኘሮጀክቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በዱባዩ ኤግል ሒልስ ትብብር የሚሠራ ሲሆን ነዋሪዎች አሁን ባሉበት ቦታ መኖርያ ቤት ተገንብቶላቸዉ በዘላቂነት በሚያዉቁት ቀዬ እንዲኖሩም ይደረጋል።

    ስለ ኘሮጀክቱ ፋይዳ ሲናገሩ የኤግል ሒልስ ሊቀ መንበረ ሞሀመድ አልባረ፥ “እንደ አንዷ የአፍሪካ ዕንቁዎች ኢትዮጵያ በባህል፣ ታሪክ እና የተፈጥሮ ዉበት የበለፀገች ነች፤ ስለዚህ የእኛ ፍላጎት እንዲህ ዉብ ከሆኑት የሀገሪቱ ትሩፋቶች አንዱ የሆነውን በአዲስ አበባ የለገሀር አካባቢን አልምቶ ዓለም እንዲያውቀው እና ሰዎች ከተለያየ የዓለም ክፍል ኢትዮጵያን መዳረሻቸው አድርገው ሁሉ ነገር የተሟላለት መንደር መኖር፣ መዝናናት እና መገብየት እንዲችሉ ማድረግም ጭምር ነው። ከዚህ በተጨማሪም ይህ ኘሮጀክት ለአከባቢዉ ነዋሪዎችም ሆነ ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የበለጠ የማነቃቃት ሰፊ ሚና ይኖረዋል።” ብለው የዚህን ዘመናዊ ኘሮጀክት ሰፊ ጥቅም አስረድተዋል።

    Addis Ababa City Administration to transfer more than 17 thousand 40/60 condominiums houses

    ለገሀር ከፈረንሳይኛ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜዉም የባቡር ጣቢያ ማለት ነው ይኸውም የባቡር ጣቢያ በአዲስ አበባ ዋነኛ ጣቢያ በመሆን ለዘመናት አገልግሏል። በአዉሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1917 የተጠናቀቀው ጣብያዉ ለከተማዋ ብሎም ለኢትዮጵያ ዋነኛው የባቡር ትራንስፖርት ማዕከልም ነበር።

    አዲሱ የለገሀር ፕሮጀክትም በዉስጡ በጥልቅ የኪነ ህንፃ ጥበብ የሚሠሩ ለቢሮ አገልግሎት የሚዉሉ ህንፃዎች ሲኖሩት በቅርብ ርቀትም ባለ አራት እና አምስት ኮከብ ሆቴሎች ይገኛሉ።

    የአቡዳቢዉ ኤግል ሒልስ ትልልቅ የተቀናጀ የመኖሪያ መንደሮች ግንባታ ድርጅት ሲሆን በተለያዩ ሀገሮች ብዙ ቁጥር ያላቸው መንደሮችን ገንብቷል። ይህ ኩባንያ ተመሳሳይ መንደሮችን በዓለም ዙሪያ ለመገንባት አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

    ኤግል ሒልስ በኢትዮጵያ (በአዲስ አበባ ለገሀር የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት)

    ኤግል ሒልስ በኢትዮጵያ የግል የመኖሪያ ቤቶች አልሚ ድርጅት ሲሆን ትልልቅ እሴት ያላቸው ግንባታዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ የሃገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት በማፋጠን ረገድ የግሉን ድርሻ አበርክቶ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ያበረክታል።

    ይህ በዉበቱ እና ዘመናዊነቱ የላቀ እንደሚሆን የተነገረለት መንደር በዘርፉ ከፍተኛ እውቀት አና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የሚሠራ ከመሆኑም ባሻገር የአካባቢዉን አረንገጓዴነትና እና ለመኖሪያ ምቹነት ባገናዘበ መልኩ ይገነባል።

    በ360,000 ሜትር ካሬ ቦታ ላይ የሚያርፈው ፕሮጀክቱ የአነስተኛ ንግድ ስፍራዎችንም በዉስጡ የያዘ ሲሆን ዙሪያውም በመናፈሻ ፓርክ የተከለለ ነው ።

    ፕሮጀክቱ ሰፋፊ የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠሩም ባሻገር በሀገሪቱ ያሉትን የንግድ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ ይደግፋል። የለገሀር የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት ድረ ገጽ

    ምንጭ፦ ኤግል ሒልስ

    ለገሀር የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት

    Semonegna
    Keymaster

    ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት አውስቷል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር ያለው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ-ጥበባት ማዕከል 40ኛ የጥበብ ውሎ መድረኩን ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ አካሒዷል።

    በዝግጅቱ ላይ የዕውቁ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ሰው የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ተደርጓል። ሥራዎቹን እና ሕይወቱን አስመልክቶ የሙዚቃ ባለሙያ እና በቅርቡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ሆኖ የተሾመው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት የውይይት መነሻ ጥናት አቅርቦ በታዳሚዎች ውይይት ተካሂዶ ነበር።

    “ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ <ባለዋሽንቱ እረኛ>(The Shepherd Flutist)  በተሰኘ ታላቂ ሥራ የኢትዮጵያን መልክ በረቂቅ ሙዚቃ ያሳዩ ናቸው” በማለት አቶ ሠርፀ የገለጿቸው የሙዚቃውን ረቂቅነት በመጥቀስ ሲሆን፤ ፕሮፌሰር አሸናፊ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አውስቷል።

    በሙዚቃ ላይ ከሠሯቸው ከበርካታ የምርምር ሥራዎቻቸው ውስጥ “Roots of Black Music” የተሰኘው መጽሐፋቸው በብዙ የዓለማችን የሙዚቃ አጥኚዎች የተዘነጉ (የተዘለሉ) የአፍሪካ/የምሥራቁ ዓለምን የሙዚቃ ስልትና ፍልስፍናን አጉልተው ለተቀረው ዓለም ያሳዩበት እንደሆነም አቅራቢው አብራርተዋል።

    በውይይቱም ከተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዘመናት መካከል የመድመቅና መልሶ የመደብዘዝ ችግር ከምን የመነጨ እንደሆነ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፥ “ዋናው ችግር በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተቋም ፈርሷል፤ እሱን መልሶ መገንባት የቤት ሥራችን ነው” ብለዋል አቶ ሠርፀ። አክለውም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ትምህርት ሥርዓት ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከምዕራባውያን የሙዚቃ ሥርዓተ-ትምህርት ነፃ መውጣት ያለመቻሉም ሌላ ምክንያት እንደሆነ አቅራቢው ጠቅሰዋል።

    ውይቱን የመሩት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ እንዳለጌታ ከበደ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ማደግ ብርቱ ጥረት ያደረጉ የጥበብ ሰዎችን ፈለግ እና ሥራዎቻቸውን ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ በሁሉም አካላት ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።

    ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ አዲስ አበባ ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። አባታቸው ግራዝማች ከበደ አድነው፣ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ፋንታዬ ነከሬ ያባሉ ነበር። የሙዚቃ ፍቅርን ገና በልጅነታቸው ያሳደሩባቸው እናታቸው ቢሆኑም ታዳጊው አሸናፊ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳሉ እናታቸውን በሞት አጥተዋል።

    ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ መሠረታዊ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (አሁን ኮከበ ጽባሕ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚባለው) ካጠናቀቁ በኋላ ከሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ተመርቀዋል። ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት ኒው ዮርክ ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሮቸስተር፣ ኢስትማን የሙዚቃ ትምህርት ቤት (University of Rochester’s Eastman School of Music) በ1954 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሰ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን መሥርተዋል። የትምህርት ቤቱም የመጀመሪያው ዳይሬክተር ከመሆናቸውም ባሻገር በመሆን ሙዚቃን ከማስተማሩ ባሻገር አገልግለዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ.ወ.ክ.ማ.)፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት መርሓ-ዕውራን ትምህርት ቤት እና በመሳሰሉ የወጣቶች ማኅበራት እየተገኙ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጡ ነበር።

    በድጋሚ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ተመልሰው፣ ኮነቲከት ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዌስልያን ዩኒቨርሲቲ (Wesleyan University) በ1961 ዓ.ም የማስትሬት፣ እንዲሁም በ1963 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ምዕራባዊ ባልሆኑ ሙዚቃዎች ምርምር (ethnomusicology) አግኝተዋል።

    ከሙዚቃው መምህርነትና ተመራማሪነት ባሻገር ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ደራሲም ነበሩ። እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም ኮንፌሽን (Confession)፣ እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም ሩትስ ኦፍ ብላክ ሙዚክ (Roots of Black Music) የሚሉ መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲሆን፣ በሙዚቃ ላይ ያተኮሩ በርካታ ጽሁፎችን፥ በተለይም ደግሞ በአፍሪካ-አሜሪካውያን ባህልና አኗኗር ላይ ለሚያተኩረው “The Chronicler” ለተሰኘው መጽሔት ጽፈዋል።

    በአሜሪካ ፕሮፌሰር አሸናፊ ኑሯቸው ፍሎሪዳ ክፍለ ሀገር በሚገኘው ፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርሲቲ (Florida State University) የሙዚቃ ኮሌጅ ውስጥ በመምህርነት የሠራ ሲሆን፣ ተቀማጭነቱን እዚያው አሜሪካ ያደረገውናታዋቂውን የኢትዮጵያ ምርምር ካውንስልን (Ethiopian Research Council) በዳይረክተርነት መርቷል።

    ፕሮፌሰር አሸናፊ ከመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ባለቤታቸው (ወ/ሮ እሌኒ ገብረመስቀል) እና ሁለተኛ ባለቤታቸው (አሜሪካዊ) አራት ልጆችን (ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ) ልጆችን አፍርተዋል። ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የ60ኛ የልደት በዓላቸው ዕለት በመኖሪያ ቤታቸው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሞተው የተገኙ ሲሆን፤ ምናልባትም የራሳቸውን ሕይወት ሳያጠፉ እንዳልቀሩ ብዙዎች ይገምታሉ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ
    PHOTO: Ethiopian Academy of Sciences

    Semonegna
    Keymaster

    ደብረ ብርሃን (ኢዜአ)–በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በአንጎለላና ጠራ ወረዳ ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከመንግሥት ካዝና ከ466 ሺህ ብር በላይ ለግል ጥቅሟ ያዋለችው ግለሰብ በ18 ዓመት ጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተጣለባት።

    በሰሜን ሸዋ ዞን ፍርድ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወ/ሪት ዘርትሁን ያዘው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት ፍርድ ቤቱ በግለሰቧ ላይ ቅጣቱን የወሰነው በወረዳው ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ጽህፈት ቤት ገንዘብ ያዥ ሆና ስትሠራ የመንግሥትን ገንዘብ ለግል ጥቅሟ ማዋሏ በመረጋገጡ ነው።

    ተከሳሿ ወ/ሮ አበበች ጽጌ ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ በጽህፈት ቤቱ ስትሠራ ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀትና መንግሥታዊ ሰነድ በመደበቅ የሙስና ወንጀል መፈፀሟ በሰውና በሰነድ ማስረጃ እንደተረጋገጠባትም አስረድተዋል።

    ግለሰቧ በአገር አቀፍ ደረጃ በውሃና በአካባቢ ንጽህና ፕሮጀክት (WASH) ግዢ ከአቅራቢዎች ላይ የተሰበሰበ ሁለት በመቶ ገንዘብ 171 ሺህ 417ብር ለግል ጥቅም ማዋሏ ተረጋግጦባታል ነው የተባለው።

    እንዲሁም በ56 ደረሰኞች ላይ በበራሪው ትክክለኛዉን የገንዘብ መጠን በመመዝገብና የከፋዮችን ስም በመቀያየር የገቢ መጠኑን በመቀነስ ለመንግሥት መግባት የነበረበት 94 ሺህ 90 ብር ሰነድ በማበላለጥ መጠቀሟም ነው የተገለፀው። በተጨማሪም በራሪ ደረሰኞችን ለከፋይ በትክክል ቆርጣ ከሰጠች በኋላ በሁለተኛና ሦስተኛ ካርኒዎች ላይ አቀናንሳ 181ሺህ 16 ብር ለግል ጥቅሟ ማዋሏን መረጋገጡን ባለሙያዋ ገልጸዋል።

    ግለሰቧ ወንጀሉን ከፈጸሟ በኋላ ከአካባቢው በመሰወሯ ፖሊስ ወንጀለኛዋን አድኖ በመያዝ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብም ትዕዛዝ ተሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪ ለአምስት ዓመታት ከማንኛውም የእንቅስቃሴ መብቷ እንደታገደችም ተወስኖባታል።

    በሌላ ዜና፥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለረጅም ጊዜ ታጥረው በቆዩ ቦታዎች ንብረታቸውን በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ባላነሱት ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ።

    የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት የደንብ ማስከበር ፅህፈት ቤት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል።

    በዚህም ያለ ልማት ለረጅም ጊዜ ታጥረው የቆዩ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የአጥር ቆርቆሮዎችን ማንሳት መጀመሩን ገልጿል።

    አስተዳደሩ ባልለሙ ቦታዎች ላይ ንብረቶቻቸውን ያስቀመጡ አካላት ንብረታቸውን እንዲያነሱ ከሳምንት በፊት መግለጫ መስጠቱ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጅ እነዚህ አካላት ንብረቶቻቸውን ማንሳት ባለመጀመራቸው ምክንያት አስተዳደሩ በዛሬው ዕለት ወደ እርምጃ መግባቱን ነው የገለጸው።

    አስተዳደሩ የሕዝብን ሃብት ለተገቢው ልማትና ለነዋሪዎች ተጠቃሚነት እንዲውል በጀመረው ተግባር ህገ ወጥነትን እንደማይታገስና፥ ህግ የማስከበር ሃላፊነቱን እንደሚወጣ መግለጹን ከከተማዋ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

    ምንጮች፦ ኢዜአ እና ኤፍቢሲ

    ለግል ጥቅሟ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ኢ.ፕ.ድ) በአዲስ አበባ በ2010 ዓ.ም የትምህርት ጥራት ደረጃን ያላሟሉ 52 የቅድመ መደበኛ፣ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን የአዲስ አበባ አጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን አስታወቀ።

    የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ብሩክነሽ አርጋው ኅዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም ለብዙኃን መገናኛ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በ2010 ዓ.ም በአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን አማካኝነት ቁጥጥር ከተደረገባቸው 1 ሺህ 407 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በቅድመ መደበኛ 26፣ በመጀመሪያ ደረጃ 22፣ በሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ አራት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች በመሆናቸው ተዘግተዋል።

    እንደ ወ/ሮ ብሩክነሽ ገለጻ፥ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ከደረጃ በታች ሆነው የተዘጉ ትምህርት ቤቶች የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተቋም ሊኖሩት የሚገባ የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች ማሟላት አልቻሉም፤ ተመጣጣኝ የሆነ የመምህራንና የሠራተኞች የትምህርት ደረጃም የላቸውም፤ የመምህራንና ሠራተኞች ብዛት አነስተኛ ነው፤ የሕፃናት ማሸለቢያ ክፍልና የመምህራን ማረፊያ ክፍል ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ቁሳቁሶች አልተሟሉም፤ ቋሚ የውጭ መጫወቻ መሳሪያዎች የሏቸውም። የትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከል እጥረት፣ በቂ የሰው ኃይልና ለሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት የሚያስፈልጉ የትምህርት መሳሪያዎችና የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አለመኖርም ለትምህር ቤቶቹ መዘጋት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።

    ወ/ሮ ብሩክነሽ፥ የተዘጉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 3በ1 የሆነ ቤተ ሙከራና የማዕከል ቁሳቁስ ግብአት በተገቢው ያልተሟላላቸው፣ 3በ1 የሆነ የስፖርት ሜዳ ያላሟሉና የሰለጠነ መምህር የሌላቸው እንዲሁም የመምህራን ማረፊያ ክፍል ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ቁሳቁሶችን እንዳላሟሉ ገልጸዋል። የሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶችም በተመሳሳይ ለትምህርት ጥራት የተሰጠውን የመመዘኛ መስፈርት ባለማሟላታቸው እንደተዘጉ ተናግረዋል።

    These two Ethiopian students are working to launch their own rocket – the future Eng. Kitaw Ejigu

    በቅድመ መደበኛ ከተዘጉ ትምህርት ቤቶች መካከል ቦሌ ቡልቡላ፣ ሳሊተ ምህረት፣ ቶምናጄሪ፣ ገነተ ኢየሱስ፣ አዲስ ሰው፣ ኤሎን፣ ሀመር፣ ሙሴ፣ ሜሲ ሚዶ፣ ብራስ ዩዝ፣ ንጋት፣ አሀዱ ቤተሰብ፣ ደብል፣ አፍሪካስ ድሪም፣ ባቤጅ፣ ብሪሊያንት፣ አልአፊያ ቁጥር 1፣ ጂ. ኤች፣ ኢስት አፍሪካ፣ ቅዱስ ዮሃንስ፣ አጼ ተክለጊዮርጊስ፣ ሳም ፋሚሊ፣ ኒው ዩኒክ፣ ብራይት የሚጠቀሱ ሲሆን፥ ማራናታ፣ ቦሌ ካውንት፣ ማይ ፊውቸር፣ ሰብለ መታሰቢያ፣ ጎል፣ አካዳሚ ፎር ኤክሰለንስ፣ ፎንት፣ ሰለሞን፣ አፍሪካስ ድሪም፣ ቤተሰብ፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ብሪሊያንት፣ እየሩሳሌም፣ ስሪ ኤስ ሜርሲ ከተዘጉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ናቸው።

    ከዚህ በተጨማሪ እንጦጦ ወንጌላዊት፣ ማርክ፣ አዲስ አበባ ሉተራንና መካነ ኢየሱስ የሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ መሆናቸውንም ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል። ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በከተማዋ በ2011 ዓ.ም ፈቃድ ያገኙ 101 አዲስ ት/ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን ጀምረዋል።

    የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ጥራትና አግባብነት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን (ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ) የሰጠው መግለጫ

    የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ የ2010 ዓ.ም የትምህርት ተቋማት የኢንስፔክሽን እና የእውቅና ፍቃድ እድሳት ሪፖርትን በተመለከተ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ

    • የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ወ/ሪት ብሩክነሽ አረጋው በ2010 ዓ.ም ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ ድረስ ባሉ የመንግስትና የግል ትምህርት ተቋማት በተካሄደ የኢንስፔክሽን መረጃ መሠረት ተቋማቱ ያሉበትን ደረጃ በዝርዝር አቅርበዋል። በዚሁ መሠረት በቅድመ መደበኛ ትምህርት አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት መካከል 41 ተቋማቱ ደረጃ 1፣ 560 ደረጃ 2 እንዲሁም 108 ተቋማት ደረጃ 3 እና 1 ተቋም ደረጃ 4 ላይ መሆናቸው ገልፀዋል።
    • በመጀመሪያ ደረጃ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት በተደረገ ኢንስፔክሽን 10 ተቋማት በደረጃ 1፣ 409 ተቋማት ደረጃ 2፣ 125 ደረጃ 3፣ እና 1 ተቋም ብቻ ደረጃ 4 ላይ እንደሚገኝ የተጠቆመ ሲሆን በሁለተኛና መሰናዶ ተቋማት ላይ በተካሄደ ኢንስፔክሽን ደግሞ 6 ተቋማት ደረጃ 1፣ 80 ተቋማት ደረጃ 2፣ 66 ተቋማት ደረጃ 3 ላይ ሲገኙ አንድም ተቋም ደረጃ 4 ላይ አለመገኘቱን ነው ዳይሬክተሯ ገልፀዋል።
    • በሌላ በኩል ባለስልጣኑ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን በአዲስ አበባ ደረጃ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ የሚሆንበትን ምክንያት በተለመከተ ጥናት ማድረጉ በመግለጫው ከመገለፁ ባሻገር የጥናቱን ውጤትም የኮተቤ ሜትፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ኤላዛር ታደሰ ያቀረቡ ሲሆን ለ8ኛ ክፍል ውጤት ማሽቆልቆል በዋናነት ከተለዩ ምክንያቶች መካከል ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው አሉታዊ አመለካከት፣ የመምህራን ለደረጃው ብቁ አለመሆን እንዲሁም በየትምህርት ተቋማቱ የሚደረገው (የማስተባበርና መቆጣጠር (የሱፐርቪዥንና ኢንስፔክሽን) አሠራር በቂ አለመሆን እንደምክንያት ተጠቁሟል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ
    ትምህርት ቤቶች

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አባባ (ብርሃን ባንክ)–የብርሃን ባንክ ባለአክስዮኖች ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ ቅዳሜ ኅዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጉማቸው ኩሴ ይፋ ባደረጉት ሪፖርት እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባንኩ በዋና ዋና የአፈፃፀም መለኪያዎች የላቀ የሥራ አፈጻጸም በማስመዝገብ እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ ጠንካራ እና ተፎካካሪ ባንክ መሆኑን በድጋሚ አስመስክሯል ሲሉ ገልፀዋል።

    በተገባደደው የበጀት ዓመት ብርሃን ባንክ ከግብር በፊት ብር 410.9 ሚሊዮን ትርፍ ማስመዘገብ መቻሉን ገልፀዋል። በዚሁ በጀት ዓመት ባንኩ ተጨማሪ አክስዮኖችን በመሸጥ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ ብር 1.7 ቢሊዮን ያሳደገ ሲሆን ከአለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ20 በመቶ የሆነ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ገልፀዋል። በተመሳሳይ መልኩም ባንኩ በበጀት ዓመቱ የባለአሲዮኖቹን ቁጥር ወደ 14,879 አድርሷል። ይህም ባንኩን በኢትዮጵያ ባንክ ኢዱስትሪ ውስጥ ከግል ባኮች በባለአክስዮኞ ቁጥር ቀዳሚ ባንክ አድርጎታል። በመሆኑም ባንኩ ሠፊ የሕዝብ መሠረት /Public Base/ ያለው የሕዝብ ባንክ መሆኑን ያረጋግጣል ብለዋል። በሌላ በኩል ሊቀመንበሩ በበጀት ዓመቱ ባንኩ አጠቃላይ ሀብቱ አምና ከነበረው 10 ቢሊዮን ወደ ብር 14 ቢሊዮን ብር በማድረስ የሀብት መሠረቱን እያሰፋ እና ራሱን ለቀጣይ እድገት ይልጥ በተሻለ ሁኔታ እያደራጀ መሆኑን ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ባንኩ የነበረውን የደንበኞች አገልግሎት በላቀ መልኩ የተቀላጠፈ ለማድረግ እንዲሁም አዳዲስ የባንክ አገልግሎት አማራጮችን በመቅረፅ ደንበኞችን ይበልጥ ለማገልገል የሚረዳ ደረጃውን የጠበቀ የመረጃ ማዕከል ገንብቶ እ.ኤ.አ 2018/19 የበጀት ዓመት ለአገልግሎት ዝግጁ አድርጓል።

    ብርሃን ባንክ በበጀት ዓመቱ ካስመዘገበው የላቀ የሥራ አፈፃፀም ውጤት ባሻገር ከእሴቶቹ መካከል አንዱ የሆነውን ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያ ቀዬዎቻቸው ለተፈናቀሉ የህብተሰብ አካላት ድጋፍ እንዲደረግ ከሚመለከታቸው የክልል መንግስታት በቀረበለት ጥያቄ መሠረት የብር ሁለት ሚሊዮን ድጋፍ አድርጓል።

    Berhan Bank, one of the private banks in Ethiopia, registers more than 410 million birr before tax

    የብርሃን ባንክ ፕሬዘዳንት የሆኑት አቶ አብርሃም አላሮ በበኩላቸው የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከፍተኛ የገበያ ውድድር እና በባንኩ ክፍለ ኢኮኖሚ በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩበት ዓመት መሆኑን ጠቅሰው በበጀት ዓመቱ ባንኩ በሁሉም የሥራ ዘርፍ ያስመዘገበው የሥራ አፈጻጸም ውጤት እጅግ አመርቂ መሆኑን ገልጸዋል። ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጠቅላላ ተቀማጭ ሂሳቡን ወደ ብር 11 ቢሊዮን ሲያሳድግ ይህም ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ42 በመቶ የሆነ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱን አስታወቀው፥ በተመሳሳይ መልኩም ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር ክምችት በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ እድገት አስመዝግቦ ብር 7 ቢሊዮን መድረሱን ይህም ከዓምናው ጋር ሲነጻጸር የ33 በመቶ የሆነ ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል። ባንኩ በኢኮኖሚው በተለያዩ ዘርፎች እያፈሰሰ ያለው የብድር መጠን በየጊዜው እየጨመረ የመጣ መሆኑን ያስረዱት ፕሬዝዳንቱ ባንኩ በአገር ልማት እና እድገት ላይ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ተናረግዋል።

    ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም ብርሃን ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 21 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት በመላ አገሪቱ ያሉትን የቅርንጫፎች ቁጥር ወደ 182 የደረሰ ሲሆን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባንኩ ደንበኞች ቁጥርም ከአለፈው ዓመት ከነበረው የ43 በመቶ የሆነ ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ 523,705 መድረሱን ገልጸዋል።

    ብርሃን ባንክ እያስመዘገበ የመጣውን ከፍተኛ የሆነ ሁለንተናዊ ዕድገት ተከትሎ 372 ተጨማሪ ሠራተኞችን በበጀት ዓመቱ የቀጠረ ሲሆን ይህም ባንኩ ያለውን አጠቃላይ የሰው ሃብት ቁጥር ወደ 3,237 ማሳደጉን ፕሬዘዳንቱ ጠቁመዋል። አያይዘውም ባንኩ ለሰው ሃብት ከሚሰጠው ልዩ ትኩረት የተነሳ በበጀት ዓመቱ የባንኩን የተቀላጠፈ የደንበኞች አገልግሎት የሚያሳልጥ እንዲሁም የባንኩን ግልፅነት እና ተዓማኒነት የተሞላበት እሴቶቹን ሊያስጠብቁ እና ደንበኞችን በልሕቀት ማገልግል ይቻል ዘንድ የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲወስዱ ተደርጓል ብለዋል። አቶ አብርሃም በቀጣዩ የበጀት ዓመት ባንኩ እሰካሁን የመጣበትን የስኬት ጉዞ ሊያስቀጠል የሚችል ስትራቴጂ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ባንኩ የበለጠ ውጤት እንደሚያመጣ ጽኑ እምነት እንዳላቸው ገልጸው፥ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ፣ የበላይ አመራሩ እና መላው ሠራተኛ እንዲሁም በዋናነት ደግሞ የባንኩ ደንበኞች እና ባለድርሻ አካላት እስካሁን ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅዖ ምስጋናቸውን አቅርበው ባንኩ ከዚህም በኋላ በላቀ እና በተቀላጠፈ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ ደንበኞቹን በትጋት እና በታማኝነት እንደሚያገለግል ያላቸውን ፅኑ እምነት ገልፀዋል።

    ምንጭ፦ ብርሃን ባንክ (berhanbanksc.com)

    ብርሃን ባንክ

    Semonegna
    Keymaster

    የትግራይ ሕዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት የህግ የበላይነት እንዲከበርና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሰጠው መግለጫ፥ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲያተኩር ጠቁሟል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የትግራይ ሕዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት በሃገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበርና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር መሆኑን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

    የክልሉ መንግስት ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው መንግስት አሁን የጀመረው የህግ የበላይነትን የማስከበር ሂደት በተገቢው ጥንቃቄ ሊከናወን የሚገባው ነው በማለት አስታውቋል።

    ሰብዓዊ ጥሰትና ሙስና በፈጸሙ ሰዎች ላይ በመንግስት ሰሞኑን እየተወሰደ ያለው እርምጃ የህግ ልዕልና ሳይሸራረፍ ከተጽዕኖ በጸዳ መልኩ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት መግለጫው አመልክቷል።

    የትግራይ ሕዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት የህግ የበላይነት እንዲከበርና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲያተኩር ጠቁሟል።

    በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የሙስና ችግርና ህገ-መንግስታዊ ጥሰት ውስጥ እጃቸው ያለ አመራሮችና ተቋማት ስለመኖራቸው ቀደም ሲል በተካሔዱ የኢህአዴግ መድረኮች ውይይት መደረጉንም አመልክቷል።

    ችግሩ በእኩል እንዲስተናገድ ከማድረግ ባለፈ እርቅና ይቅር ባይነትን መሠረት አድርጎ የተጀመረው ሂደት ወደ ኋላ እንዳይመለስ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሷል።

    “የህግ የበላይነትም ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥናት የሚጠይቅ መሆኑንም የክልሉ መንግስት ያምናል” ብሏል መግለጫው።

    የትግራይ ክልል ሕዝብ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በመሆን የከፈለው መስዋዕትነት የዜጎች እኩልነትና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር እንጂ በማንም አካል እንዲጣስ እንዳልሆነ መግለጫው አመልክቷል።

    ባለፉት ዓመታት ይታዩ የነበሩት የፍትህና የዲሞክራሲ መጓደሎች እንዲስተካከሉ ሕዝቡ በጽናት እየታገለ መምጣቱንም መግለጫው አስታውሶ በጥልቅ ተሀድሶ ወቅት ህዝቡ ያሳየው ተሳትፎ አንዱ ማሳያ መሆኑን አስረድቷል።

    ከሰብአዊ መብት አያያዝና ከሙስና ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እየታየ ላለው ሁኔታ ተጠያቂዎቹ እጃቸው ያለበት አመራሮችና ተቋማት መሆናቸውንም መግለጫው አመልክቷል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)ሰሞነኛ ኢትዮጵያ |
    የትግራይ ሕዝብ

    Semonegna
    Keymaster

    የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ብቃት ያላቸው ዜጎች ሆነው እንዲወጡና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየሠራ መሆኑን፤ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ለተማሪዎቹ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱንም የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ አስታውቀዋል።

    ጋምቤላ (ኢዜአ) – የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለዘንድሮው የትምህርት ዘመን ወደ ካምፓሳቸው ሲገቡ የጋምቤላ ከተማና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ያደረገላቸው አቀባበል አብሮነታቸውን በማጠናከርም ሊቀጥል እንደሚገባ ወላጆችና ተማሪዎቹ ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው በተያዘው የትምህርት ዘመን የተመደቡለትን ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሏል።

    አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የሰጡት ወላጆችና ተማሪዎች እንደተናገሩት ማኅብረሰቡ ያደረገላቸውን አቀባበል በመማር ማስተማሩ ሂደትና በዩኒቨርሲቲ በሚኖራቸው ቆይታ ድጋፍ በመስጠት ሊጠናከር ይገባዋል።

    ልጃቸውን ለማድረስ ወደ ዩኒቨርሲቲው ከመጡት ወላጆች መካከል አቶ ተሾመ ደሳሳ በሰጡት አስተያየት ለተማሪዎቹ የተደረገው አቀባበል ከጠበቅኩት በላይ አግኝቼዋለሁ ብለዋል። በአቀባበሉ ላይ የታየው አብሮነት በቀጣይም ተማሪዎቹ የመጡበትን ዓላማ እንዲያሳኩ ከጎናቸው እንዲሆን ጠይቀዋል።

    ማንኛውም ወላጅ ልጆቹን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚልከው ከተቋሙ በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ አደራ በመስጠት ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ወላጅ አቶ ሂርጳ ደጉ ናቸው። በመሆኑም ኅብረተሰቡ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ድርሻቸውን እንደሚወጡ እምነት አለኝ ብለዋል።

    ተማሪ ጫላ ቶላ በሰጠው አስተያየት በዩኒቨርሲቲው በተደረገለት አቀባበል መደሰቱን ገልጾ፣ በቀጣይም የመጣበትን ዓላማ ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት ማኅበረሰቡ ከጎኑ እንዲሆን ጠይቋል።

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምርጥ የአዝዕርት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል ምርትን በማሳደግ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል

    ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ኒያል ኮት በሰጡት አስተያየት ወላጆች ልጆቻቸውን ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር ለአካባቢው ኅብረተሰብ መስጠታቸው ተገቢ መሆኑን አመልክተው፣ አደራውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ይህንንም ለማሳካት በተለይም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ተማሪዎች ከመምጣታቸው በፊት ከዩኒቨርሲቲው ማህብረሰብ ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

    የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶ/ር ከተማ ጥላሁን እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የትምህርትና የምርምር ሥራዎቹን ሰላማዊና ስኬታማ ለማድረግ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

    በተለይም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ብቃት ያላቸው ዜጎች ሆነው እንዲወጡና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ለተማሪዎቹ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

    የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የተቀበላቸውን አንድ ሺህ አምስት መቶ ተማሪዎችን ጨምሮ ከሦስት ሺህ አምስት መቶ በላይ ተማሪዎች በመደበኛ መርሐ ግብር ተቀብሎ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች እያስተማረ ነው። የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በሆነችው ጋምቤላ ከተማ ውስጥ የተቋቋመው በ2007 በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት ነበር።

    ምንጭ፦ ኢዜአ | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ

Viewing 15 results - 646 through 660 (of 730 total)